Thursday, December 3, 2015

ውግዘትና የቤተ ክርስቲያን ኃላፊነት - ክፍል ሰባት


Read in PDF 
በዲያቆን ኢሩባኖን ዘኢየሱስ
ካለፈው የቀጠለ
2.   በውግዘት ጊዜ ሊደረግ የሚገባው ጥንቃቄ
     ነገሩ በምስክር ተረጋግጦ፤ ትምህርቱ ወይም ድርጊቱ ብዙዎችን ያሰናከለና እያሰናከለም ያለ እንደሆነ ቀድሞ በሚገባ ተጢኖ፥ ከተደመደመ በኋላ ወደውግዘት መሄድ የሚገባ ነገር ነው፡፡ በዚህ ጊዜ፦
2.1. በንጹህ ህሊና መዳኘት

   የንጹህ ህሊና መገኛ መሠረቱ ዕውቀትና የራስ ጥበብ ሳይሆን ዛሬም ትኩስ ሆኖ በሰማያት ያለው የክርስቶስ ደም ነው፡፡ (ዕብ.9፥10 ፤ 14 ፤ 1ጴጥ.3፥21) በንጹና መልካም ህሊና ለመዳኘት በደሙ ህያውነት ቀድሞ መመላለስ ያሻል፡፡ የክርስቶስ ደሙ ለህይወታችን ምን ያህል እንደሚያስፈልግ በሚገባ ከተረዳን፤ ለእኛ ብቻ ሳይሆን ለተወጋዡም ያስፈልገዋልና በውግዘት ጊዜ ክርስቶስንና ቤተ ክርስቲያንን ብቻ እንድናስብና በእግዚአብሔር ፍርሃት ውስጥ እንድንኖር ያደርገናል፡፡ ስለዚህ ምስክሮችን በቃሉ መሠረትነትና ሚዛንነት ላይ በማስቀመጥ በንጹህ ህሊና መዳኘት ያስችለናል፡፡
    በክርስቶስ ደም የተወቀረ ንጹህ ህሊና ከእግዚአብሔር ውጪ የሚፈራው ምንም ነገር የለውም፡፡  
v አድሎአዊነት ንጹህ ህሊናን ያሳጣል፡፡
v አድሎአዊነት ፍርድን ያዛባል፡፡
v አድሎአዊነት ደምን በእጅ ያስጨብጣል፡፡
v አድሎአዊነት ፍርድን በራስ ያስመልሳል፡፡
     ስለዚህ በማውገዝ ጊዜ በንጹህ ህሊና መሆን ከክፉ ጥፋት ያድናል፡፡ የጌታን ትምህርትና ቀኖናን እንጂ የሰዎችን ስሜት አለመከተል ከብዙ ነገር ይጠብቀናል፡፡ ይህን በተመለከተ በአንድ ወቅት ፓትርያርክ አቡነ ጳወሎስ በጻፉት ደብዳቤ እንዲህ ብለው ነበር፦

      “ከጥንት ጀምሮ ሲሠራበት የነበረ አሠራርም ይህ እንደሆነ በአርዮስ፤ በመቅዶንዮስና በንስጥሮስ ላይ የተላለፈው ሲኖዶሳዊና ቀኖናዊ ውሳኔ ማስረጃችን ነው፤ ይህን መርሕና ቀኖና ቤተ ክርስቲያን ተከትሎ ውሳኔ ባልተሰጠበት ሁኔታ በግል ስሜትና ቀኖናው በማይፈቅደው አካሄድ የግለሰቦችን ስም ማጥፋት በስም አጥፊነት በሕግ ከማስጠየቅ ያለፈ ሌላ ፋይዳ አኖረውም፡፡
      ሕግን፣ ሥርዓትንና የሥልጣን ገደብን ጠብቆ የማይፈጸም ድርጊት የምዕመናንን ኅሊና በማሻከር በቤተ ክርስቲያኒቱ የአስተዳደር ሥርዓትና በሀገሪቱ ሰላም ላይ እንቅፋት ለመፍጠር ሆን ተብሎ የሚደረግ ሙከራ መስሎ ስለሚታ ጎጅነቱ ቀላል አይሆንም፡፡”
  
በእርግጥም ያሉት ሲሆን ታይቷል፡፡

2.2.     ተወጋዥን በንጹህ እይታ ማየት

    ትምህርቱን በሚገባ ሳናጤን፣ ከአንደበቱ ገና ምንም ሳንሰማ፣ ከባድ ነውር ተገኘበት ተብሎ ስለቀረበ ብቻ ከፊታችን የቀረበውን ሰው ንጽዕና (በንጽዕና መታየት) ልንገፈው አይገባም፡፡ እንደአይሁድ ሊቃነ ካህናት “ሲኖዶስ” ቀድሞ ህሊናችን “በክፉ ወሬ ከታጨቀ” ክርስቶስ እንኳ ከፊታችን ቆሞ መልካሙን ገና መናገር ሳንጀምር፤ ሃሳቡን በመሐል ገትተን የራሳችንን ትርጓሜ መስጠት የማንጀምርበት ምክንያት ይኖራል ብዬ ለመገመት እቸገራለሁ፡፡(ሉቃ.22፥71) ከራሱ ሰምተናል፤ ሌላ ምስክር አያሻም” የሚል ጉባኤ መንፈሳዊና በክርስቶስ ደም የተፈወሰ ህሊና ነው ያለው ማለት ፈጽሞ አይቻልም፡፡
   “የፖለቲካ እስረኞች” (እኔ ግን ከበጣም ጥቂቶቹ በቀር የፖለቲካ እስረኞች ለማለት እቸገራለሁ) ብዙ ጊዜ ተይዘው ለፍርድ ሲቀርቡ “መንግስት ዳኞችን በማይታይ እጅ ይዘውራልና ዳኞቹ ንጹሕ ህሊና አይኖራቸውም ፤ የማይታየው እጅ እንደወደደ ያዛቸዋልና” የሚል ስሞታ በየዘመኑ ይነሳል፡፡ ስለዚህም እስረኞቹ በአንድም ይሁን በሌላ ምክንያት ከመቀጣት አይድኑም፡፡ አሁን አሁን ሳይ በተለይ ገቅርብ ዘመን ወዲህ ለእኔ “መናፍቃን” የሚባሉ ወገኖች (ሌላ ኃጢአት የሠሩ ሲኖዶስ ሲቀርቡ ፈጽሞ ስላላየን) ተከሰው ሲቀርቡ እንደ“ፖለቲካ እስረኞች” በንጹህ ህሊና የመታየት ዕድላቸው ጠባብ ይመስለኛል፡፡ የአርዮስን ክህደትና ትምህርት የመረመሩት አባቶች የቆዩበት ጊዜ እጅግ ትዕግስተኞች መሆናቸውን ያሳያል፡፡ ዛሬ ግን አስራ አምስት ቀን ባልሞ፤ ዕድሜና ተከሳሽ ባልቀረበበት “የሲኖዶስ ዝግ ችሎት” ብይንና ፍርድ እየሰማን፤ እያየንም ነውና፡፡ እንኪያስ “ንጹህ ህሊናና በንጹህ የምታይ ህሊና ሆይ ወዴት ነህ?” ያሰኛል፡፡
    መናፍቃን አይወገዙ የሚል አቋም ፈጽሞ የለኝም፡፡ ሊወገዙ ይገባል፤ እጅግ አምናለሁ፡፡ ይሁንና የውግዘት መንገዳችን ሰው ሳይሆን እግዚአብሔር እንደሚያየው ይሁን ግን ሙግቴ ነው፡፡ 


2.3.      አንድ ሐሳብና ልብ መሆን

    የመጀመርያይቱ ቤተ ክርስቲያን ትልቅ ውበት የነበረው “በየቀኑም በአንድ ልብ ሆነው በመቅደስ እየተጉ በቤታቸውም እንጀራ እየቈረሱ፥ በደስታና በጥሩ ልብ ምግባቸውን ይመገቡ ነበር፡፡” የሚለው ቃል ነው፡፡(ሐዋ.1፥14 ፤ 2፥46) ብዙ ልዩነቶች ቢኖሩንም በክርስቶስ ሥራ ግን አንድ ልንሆን ይገባናል፡፡ ቃሉም “እርስ በርሳችሁ በአንድ አሳብ ተስማሙ” ይላልና፡፡(ሮሜ.12፥16)
  አንድ ሰው የበደለው በደልና ኃጢአቱ ብዙዎችን ማሰናከሉን ቤተ ክርስቲያን በአንድ ሐሳብና በአንድ ልብ ልታምንበት ይገባታል፡፡ ፍርድ በልዩነት የሚሰጠው ዓለማዊ የዳኝነት ሥርዓት ላይ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ግን ክህደቱን ክህደት ፤ ኃጢአቱን ኃጢአት፤ መናፍቅነቱን መናፍቅነት ፤ ዝሙቱን ዝሙት  ለማለት በልዩነት ዳኝነትን መስጠት አትችልም፡፡ ኃጢአት ሁለት ስም የለውምና፡፡ በእርግጥ ዛሬ ዝሙት ፍቅር ፣ ሌብነት ሙስና ፣ ሴሰኝነት ከአልጋ መውደቅ … ተብሎ ተንሻፈፎ ወይም ተጣምሞ ተተርጉሟል፡፡ ግን ኃጢአት ኃጢአት ነው፡፡ አዎ! ቅዱስ ሲኖዶስ “ … ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ኃይል ጋር ተሰብስበን፥ … ” (1ቆሮ.5፥5) ብለው በሙሉ እምነት ፥ በአንድ ልብ ደፍረው ተናግረው ሊያወግዙ ይገባቸዋል እንጂ በሁለት ተከፍለው የውግዘት ፍርድን በልዩነት የሚፈርዱ ከሆነ ቤተ ክርስቲያንን አንዳች ጤና ያልሆነ ነገር እንዳገኛት ምንም አይጠረጠርም፡፡

2.4.     አለም አቀፍ የቤተ ክርስቲያን መርሆችን ማሰላሰል


    ቤተ ክርስቲያን የምትቀበላቸው ሦስት አለም አቀፍ ጉባኤያትና ውሳኔዎቻቸውን በሚገባ ማስተዋል ሊዘነጋ የማይገባው ጉዳይ ነው፡፡ በእነዚህ ጉባኤያት ላይ የተወሰኑት ውሳኔዎች የቤተ ክርስቲያን ዋና መሠረተ እምነቶች ናቸው፡፡ አለም አቀፍ ከወሰኑት ውሳኔዎች ባሻገር የሐዋርያት የእምነት መግለጫ፣ የአትናቴዎስ የእምነት መግለጫ፣ የኤጲፋንዮስ የእምነት መግለጫ ቤተ ክርስቲያን የቆመችባቸው መሠረቶች ናቸው፡፡
     በተለይ የሐዋርያት የሃይማኖት መግለጫ የሃይማኖት መግለጫዎች ሁሉ የበላይ ሲሆን እንደሌሎቹ የእምነት መግለጫዎች ሙሉ ለሙሉ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት ያለው፣ የመናፍቃንን ኑፋቄ በመቃወም አጭርና ግልጥ በሆነ መንገድ የቀረቡ ናቸው፡፡ እነዚህ መግለጫዎች እህት አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ የሚቀበሏቸውና የሚያምኗቸው ናቸው፡፡ ነገር ግን ቀኖናዊ በሆኑ ነገሮች ደግሞ በብዙ መልኩ የምንለያይባቸው ነገሮች አሉ፡፡ በሐገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ግን ልንታገሳቸው የሚገቡና ሊያስወግዙ የማይገባቸው ብዙ ሰዎች ሲያስወግዙ እንያለን፡፡ (ለምሳሌ፦ የመብል፣ ዜማና የዜማ መሣርያ፣ በአንድ መርፌ ስንት መላዕክት ይቆማሉ፣ የበዓል አከባበር፣ ጫማ አድርጎ “ቤተ ክርስቲያን” የመግባትና ያለመግባት … ጉዳይና ሌሎችም) ሲያስወግዙ እናያለን፡፡ ነገር ግን የእህት አብያተ ክርስቲያናት ቀኖናና መርህን ብናይ የምንታገሰው ብዙ የምንቆጣበት ጉዳይ አልነበረም፡፡

2.5.      ፈጥኖ ባለመታገስ ማውገዝ አይገባም

 “እንድትድኑ ወደን እንታገሳችኋለን እንጂ በእናንተ ላይ ቸኩለን ሰይፋችንን አንመዝም (ቸኩለን አናወግዛችሁም)” 

(ተግሳጽ ዘቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ አን.4)


    በታሪክ እንደምናነበበው ሦስት መቶ አስራ ስምንቱ ሊቃውንት በ325 ዓ.ም በኒቂያው አለም አቀፍ የቤተ ክርስቲያን ጉባኤ ላይ የአርዮስን ትምህርትና ተከታዮቹን ለማውገዝ ሲሰበሰቡ ከማውገዛቸው በፊት ያሳዩት ትዕግስት እጅግ ሊደነቅ የሚገባ ነው፡፡ ምናልባት ሞኝነት እስኪመስል ትምህርቱን እንኳ እየሰሙ ብዙ ታግሰው፤ አልመለስ ቢል እርሱን ከቤተ ክርስቲያን አንድነት ለይተው ትምህርቱን አውግዘዋል፡፡
  ሠለስቱ ምእት አርዮስን ከማውገዛቸው በፊት ከመስከረም ወር አጋማሽ እስከ ህዳር አጋማሽ ሱባኤ መግባታቸውንና ለመመለስ ብዙ ጥረት እንዳደረጉ መልካም ታሪክ ተመዝግቦላቸዋል፡፡ ይህ ጊዜ የእርሱን ትምህርት ለመስማትና ለመምከር የወሰደውን ጊዜ አያካካትም፡፡ በእርግጥም ከውግዘት በፊት ብርቱና የተጋ ጸሎት ያስፈልገዋል፡፡
    በቤተ ክርስቲያን ትዕግስትና መደማመጥ አለመኖሩ ብዙ አማንያንና የወለደችው ልጆቿን አላስፈላጊ በሆነ መልኩ እንደትሰዋ አድርጓታል፡፡

“ኃጢአተኛውን ብታገኘው ጥቂት በጥቂት ምከረው፡፡ ፈጥነህ አትለየው፡፡ ዲያቆናትም በውጪ አጊኝተው አባብለው እንዲመልሱት ስለእርሱም እንዲጸልዩ እዘዛቸው፡፡ ያን ጊዜም በችሎታው መጠን ጾም ሥራለት፡፡ አንድና ሁለት ሱባኤ ቢሆን ወይም ሦስት ወይም ፬ ወይም ፭ ወይም ፮ ሱባኤ ሥራለት፡፡ ኃጢአቱን ለማሥተሠረይ በሚገባ እንዲገስጽ አስተምረው፤ አክብረው፡፡ በራሱ ትሑት የዋሕ እንዲሆን አስተምረው፡፡

(ፍትሐ ነገስት አን.5 ቁ.125)
                                        ...ይቀጥላል

1 comment: