Saturday, January 30, 2016

የመካነ ሕያዋን ጐፋ ገብርኤል ካቴድራል ታሪክ እያበላሹ ያሉትን ሰባኪዎች በመጋበዙ ማስጠንቀቂያ ተሰጠው

Read in PDF

በማኅበረ ቅዱሳን ተጽዕኖ ሥር ከወደቁት አድባራት መካከል አንዱ ለሆነው የጎፋ መካነ ሕያዋን ቅዱስ ገብርኤል ካቴድራል ከን/ስ/ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ቤተክህነት የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ተጻፈ፡፡ ደብዳቤው የተጻፈው ከአ/አ ሀገረ ስብከት እይታ ውጪ ለመሄድ ብሎም የቤተክርስቲያንን ዶግማና ቀኖና ባልጠበቀ መልኩ ፈቃድ ሳይኖራቸውና የቤተክርስቲያንን መዋቅር ባልጠበቀና የቅዱስ ሲኖዶስን ትእዛዝ በመተላለፍ የማቅን አጀንዳ ለማስፈጸም ሌተቀን የሚተጉትን ያረጋል አበጋዝንና አባይነህ ካሴን ጋብዘው አባቶችን በተለመደው በላፕቶፕና በፕሮጀክተር ሲያሰድቡ በማምሸታቸው ነው፡፡ ደብዳቤው ከዚህ ቀደም መዋቅሩን ባልጠበቀ አሰራር የስብከተ ወንጌል አገልግሎት እንዳይሰጡ በቁጥር 1177/482/08 በቀን 27/3/08 ደብዳቤ ጽፎ የነበረ መሆኑን አስታውሶ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ መመሪያው መጣሱን አመልክቷል፡፡ እነዚህ የማቅ አገልጋዮች በሌላቸው ሥልጣንና የስብከት ፈቃድ በሙስናና በሌላም ነውረኛ ሥራ ያንበረከኳቸውን የደብሩን አስተዳዳሪ መላከ ገነት አባ ገ/ሥላሴ ጠባይን በመጠቀም ነው ህገወጥ ድርጊቱን የፈጸሙት፡፡
ከዚህ ቀደም እንደዘገብነው አባ ገ/ሥላሴ ከፍተኛ ሙስና ከሚፈጽሙ አለቆች አንዱ ቢሆኑም የማቅ ሚዲያ ሐራ ግን አንድም ጊዜ ስማቸውን አንሥቶ አያውቅም፡፡ ምክንያቱም ለማኅበረ ቅዱሳን ጥቅም ሲል የሲኖዶስን ውሳኔ ጭምር እየጣሰ መድረኩን የሚያመቻችና ተገቢውን ድጋፍ ለማኅበሩ የሚያደርግ አለቃና ጸሐፊ ወይም መሰል ባለሥልጣን የቱንም ያህል በሙስና ቢነቅዝ የቱንም ያህል የስነምግባር ችግር ቢኖርበት በማቅ ዓይን እርሱ በሃይማኖቱ የጸና በምግባሩ የቀና ንጹሕ ነውና፡፡

Thursday, January 28, 2016

መንፈሳዊ ኮሌጆች በማኅበረ ቅዱሳን ላይ ላቀረቡት ክስ ፓትርያርኩ አንጀት አርስ መመሪያ ሰጡበሌለው ሥልጣን መንፈሳዊ ኮሌጆችን የመናፍቃን መፈልፈያዎች ናቸው ሲል በጅምላ በወነጀላቸውና ራሱን ከሕግ በላይ በማድረግ በቤተክርስቲያኒቱ ውስጥ እኩይ ሥራውን እየሠራ ባለው ማኅበረ ቅዱሳን ላይ መንፈሳዊ ኮሌጆቹ ላቀረቡት ክስ ቅዱስ ፓትርያርኩ ከፍተኛ አድናቆት የተቸረውንና ተገቢና ጠንካራ አቋማቸው የተንጸባረቀበትን መመሪያ ሰጡ፡፡ ፓትርያርኩ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ይህን ድንቅ መመሪያ የሰጡት ጥር 16 ቀን 2008 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ለሚገኙት ለቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ እና ለሰዋስው ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ እንዲሁም መቀሌ ለሚገኘው ለቅዱስ ፍሬምናጦስ አባ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን መንፈሳዊ ኮሌጅ በአድራሻቸው በጻፉት ደብዳቤ ነው፡፡
ቅዱስነታቸው በደብዳቤያቸው እንደ ገለጹት “ማህበረ ቅዱሳን የቅዱስ ሲኖዶስን ሥልጣን በመጋፋትና ቤተክርስቲያንን በማተራመስ ቀኖና የለሽ ሥርዓት ሲከተል ይስተዋላል” ሲሉ የማኅበሩን የሚታይ ሕገወጥ አካሄድ ገልጸዋል፡፡ የሚያሳዝነው እስካሁን ቅዱስ ሲኖዶስ የሚያወጣው ደንብና መመሪያ በማኅበሩ በኩል በተደጋጋሚ እየተጣሰና እየፈረሰ ሳለ አንዳንድ ጳጳሳት በሲኖዶስ ስብሰባ ላይ ተቀምጠው ለወሰኑት የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔና መመሪያ ሳይሆን ለማኅበሩ መወገናቸው ማኅበሩ የልብ ልብ እንዲሰማው እንዳደረገ የታወቀ ነው፡፡ ስለዚህ በቀጣይ ሊወሰድ የሚገባው እርምጃ የማያዳግምና በተደጋጋሚ ሲጣስና ሲፈርስ የነበረውን የሲኖዶስን ውሳኔ የሚያስከብር መሆን እንዳለበት የብዙዎች ተስፋ ነው፡፡ 

Wednesday, January 27, 2016

ማቅ በስደተኛው ሲኖዶስ ላይ ጦርነት ሊከፍት ነውበዘንድሮው የጥምቀት በዓል በተሰበከው ወንጌል እጅግ የተቆጣው ሰይጣን ሰራዊቱን አሰባስቦ በሲኖዶሱ አባቶች ላይ ሊዘምት መሆኑን ምንጮች አረጋግጠዋል። በዳንኤል ግርማ የሚመራው የሁከት እንቅሥቃሴ ውስጥ ለውስጥ አዋኪዎችን እየመለመለ ሲሆን እነአባይነህ ካሴና እነዳንኤል ክብረት በቀስቃሽነት ተመድበዋል። እንደ ምክንያት የተወሰደው አቡነ መልከ ጼዴቅ በኦርጋን መዘመር ይቻላል ማለታቸውን ተከትሎ ቢሆንም አላማው ግን ቦታ እያየዘ የመጣውን የወንጌል ክብር ለመቃወም መሆኑ ግልጥ ነው።
 ኦርጋን መሣሪያ፣ እስከ አሁን ድረስ በአንዳድ የሲኖዶሱ አብያተ ክርስቲያናት እየተዘመረበት የቆየ ሲሆን በሎስ አንጀለስ ቅድስት ማርያም ግን በማህበሩ የውስጥ እንቅሥቃሴ ታግዶ ቆይቶ እንደነበር ምንጮች ይጠቁማሉ። ማህበሩ በአንድ መነኩሴ አማካኘነት ሰንበት ተማሪዎችን በማሸፈት በቅድስት ማርያም ሰርጎ ለመግባት የሚያደርገውን እንቅሥቃሴ አስቀድመው ያወቁ ካህናትና የቦርድ አባላት ኦርጋኑ እንዲመለስ አድርገዋል። ይህን ያደረጉበት ምክንያት የማህበሩ አባላት የኦርጋን ድምጽ ሲሰሙና የኢየሱስ ስም ሲነሳ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ መቆም ስለማይችሉ ነው ተብሏል። የማህበሩን አባላት ለማባረር የኢየሱስን ስም ደጋግሞ መጥራት እና ኦርጋን ማሰማት ተወዳዳሪ ያልተገኘለት ፍቱን መድኃኒት መሆኑን ካህናቱ ይናገራሉ። የአዲስ አበባው ቤተ ክህነትም ይህን ዘዴ ቢጠቀም ረፍት ሊያገኝ እደሚችል ብዙዎች ይመክራሉ። የማህበሩ አባላት ከኢየሱስ ስምና ከኦርጋን ጋር በተያያዘ በሚማሩት ትምህርት የሥነ ልቦና ችግር እንደገጠማቸው የሚናገሩ አሉ። በዘንድሮው ጥምቀት በዓል ላይ ኦርጋን ሲመታ ጆሯቸውን እየያዙ ሲሮጡ የታዩ የማህበሩ አባላት ነበሩ ተብሏል።

Tuesday, January 26, 2016

ይድረስ ለብፁዕ አቡነ መልከ ጸዴቅ እና ለ‹አሜሪካው ሲኖዶስ› አባቶች!በዲ/ን ተረፈ ወርቁ፡፡
ብፁዕነትዎ፣ ‹‹ቤተ ክርስቲያን በኦርጋን የሙዚቃ መሳሪያ መዘመርን መፍቀድ እንዳለባትና ካህናቶቿም በኦርጋን መዘመርን መማር እንዳለባቸው፡፡›› የሚል ይዘት ያለውን መልእክትዎን ከተለያዩ ድረ ገጾችና ይህን የእርስዎን መልእክት እየተቀባበሉ ክርክርና ሙግት ከገጠሙባቸው፣ የቤተ ክርስቲያናችን የሶሻል ሚዲያው አባላት/ጓደኞቼ ገጾች ላይ አነበብኩ፡፡ እናም ለብፁዕነትዎ፣ በአሜሪካ ለሚገኘው ሲኖዶስና ይህን የእርስዎን አሳብ ለሚያቀነቅኑ በአገር ውስጥና በውጭ አገር ለሚገኙ ወገኖቼ አንዳንድ የግል የኾነ ጥያቄዎችንና የግል አስተያየቴን ለማቅረብ ስል ብዕሬን ለማንሣት ወደድኹ፡፡
ብፁዕነትዎ በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሊቀ ሥልጣናት ከነበሩበት ዘመናት ጀምሮ የጻፏቸውን መጽሐፎችዎን በሚገባ አንብቤያለሁ፡፡ ከሁሉም ከሁሉም ደግሞ ‹የስብከት ዘዴ› የምትለው መጽሐፍዎን አልረሳውም፡፡ መንፈሳዊ አግልግሎትን በጀመርኩበት ወራት መልካም ዕውቀትን፣ ግሩም የኾነ መንፈሳዊ ምክርንና ጥበብን፣ ስንቅና ማስተዋልን የሰጠችኝ መጽሐፍ ነበረች፡፡

Wednesday, January 20, 2016

ማኅበረ ቅዱሳን የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ የዛሬ 15 ዓመት ያሳተመውን የመዝሙር መጽሐፍ ፈቃድ ሳይጠይቅ በደስታ ጌታሁን ስም ማሳተሙ ውዝግብ አስነሣየሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ከዚህ ቀደም በተለያዩ ደራስያን የተደረሱ ዝማሬዎችን በመሰብሰብ የሰንበት ት/ቤቶች እንዲጠቀሙበት በሚል ያሳተመውን መጽሐፍ ማኅበረ ቀዱሳን ዲ/ን ደስታ ጌታሁን በተባለው ቀሳጤ ድርሰት ስም ማሳተሙ ውዝግብ ማስነሣቱ ተሰማ፡፡ ዲ/ን ደስታ ጌታሁን ድርሰቱ የሌሎች መሆኑንና የመሰብሰቡን ስራ ሠርቶ “መዝሙረ ማኅሌት” በሚል ስም በ1993 ዓ.ም ያሳተመው የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ መሆኑን እያወቀ መጽሐፉ በታተመ በ15 ዓመቱ ራሱ እንደሰበሰበው ንቡረ እድ ኤልያስ እና መ/ር ዕንቆባሕርይ ተከሥተ ግጥሙንና ዜማውን እንዳስተማሩት በማስመሰል “ዋይ ዜማ” በሚል ስም በማኅበረ ቅዱሳን አሳታሚነት ሰሞኑን በ2008 ዓ.ም ያንኑ መዝሙር መልሶ አሳትሞታል፡፡ ከደስታ ይልቅ በአሳታሚነት ተሳታፊ የሆነው ማኅበረ ቅዱሳን የመጽሐፉ ባለቤት የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ መሆኑን ጠንቅቆ የሚያውቅ ቢሆንም ማን ምን ያመጣል በሚል ትምክህት የማደራጃ መምሪያውን መጽሐፍ አሳትሞ እየቸበቸበ ይገኛል፡፡ በመጽሐፉ ውስጥ “ይህን የመዝሙር መጽሐፍ ሙሉ በሙሉ ዜማውንና ግጥሙን ላስተማሩኝ ለክቡር ንቡረ እድ ኤልያስ አብርሃ፣ ለመምህር እንቈባሕርይ ተከሥተ ለመሪጌታ ሐዲስ አዱኛ እና በአሁኑ ሰዓት በሕይወት ለሌሉት መሪጌታ ጌራወርቅ ቀለመወርቅ” ምስጋና ያቀረበ መሆኑ ከስርቆቱ በላይ ሌላው አነጋጋሪ ነጥብ ሆኗል፡፡ እነዚህ በስም የተጠቀሱት ሰዎች በተለይም ንቡረ እድ ኤልያስ እና መምህር እንቈባሕርይ መቼ ነው በመዝሙር መጽሐፉ ውስጥ የሚገኙትን የመዝሙሮቹን ግጥምና ዜማ ሙሉ በሙሉ ያስተማሩት? የሚለው ከማነጋገሩም ባሻጋር በግለሰቦቹ በተለይም በመ/ር ዕንቆ ባሕርይ ዘንድ ቅሬታን እንዳሳደረ ምንጮች ገልጸዋል፡፡ ደስታ ይህን ያደረገው ምስጋና ካቀረብኩላቸው ምንም አይሉም ብሎ ይሆናል፡፡ ነገር ግን በተሰረቀ ድርሰት ያላደረጉትን አስተማሩኝ ማለት መብታቸውን እንደመጋፋት የሚቆጠርና በሕግም ሊያስጠይቅ የሚችል ተግባር ነው፡፡ ምክንያቱም የስርቆቱ ተባባሪ እንደማድረግ የሚቆጠር ድርጊት ነውና፡፡ ይልቁንም የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ኃላፊው መ/ር ዕንቈ ባሕርይ በመምሪያው የታተመውን የመዝሙር መጽሐፍ ደስታ እንዲያሳትመው የተባበሩት ያስመስላልና፡፡

Friday, January 15, 2016

የቤተክርስቲያኒቱ ኮሌጆች በማኅበረ ቅዱሳን ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ ጠየቁቤተክርስቲያን በሰጠችው ፈቃድ ውስጥ ከመብቱና ከሥልጣኑ ውጪ በሕገወጥና በአልታዛዝ ባይነት ከእኔ በቀር ለቤተክርስቲያኒቱ ማንም የለም በሚል የትእቢት መንፈስ እየተንቀሳቀሰና ብዙ ጥፋቶችን እያደረሰ ያለውን ሁከት ፈጣሪ ማኅበረ ቅዱሳንን የቤተክርስቲያኒቱ መንፈሳዊ ኮሌጆች ተገቢው እርምጃ እንዲወሰድበት ሲሉ ጠየቁ፡፡ የቅድስት ሥላሴ የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ እና  የከሣቴ ብርሃን ሰላማ ኮሌጆች ተማሪዎችና ኃላፊዎች ለቅዱስ ፓትርያርኩ ባቀረቡት አቤቱታ ማኅበረ ቅዱሳን በቤተክርስቲያኒቱ ላይ ትልቅ አደጋ የጋረጠ በመሆኑ አስፈላጊው እርምጃ እንዲወሰድ ጠይቀዋል፡፡ ፓትርያርኩም በማኅበሩ ሕገወጥ አካሄድ ላይ የጀመሩትን እንቅስቃሴ ከሚመለከታቸው የቤተክርስቲያኒቱ አካላት ጋር በመሆን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ቃል ገብተዋል፡፡
ማኅበሩ ከኮሌጆቹ ጋር ውዝግብ ውስጥ ከገባ የቆየ ቢሆንም ለአሁኑ ክስ መነሻ የሆነው ግን በስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ 23ኛ ዓመት ቁጥር 5 ቅጽ 23 ቁጥር 333 ከኅዳር 16-30 ቀን 2008 ዓ.ም እና በዌብሳይቱ www.eotcmk.org ላይ በሦስቱ ኮሌጆች ላይ ከአንድ ለቤተክስቲያን ድጋፍ እሰጣለሁ ብሎ ከተደራጀ ማኅበር የማይጠበቅ የስም ማጥፋት ዘመቻ በመክፈት በቤተክርስቲያኒቱ ላይ ያለውን ከፍተኛ ንቀትና ኃላፊነት የጎደለው ጽሑፍ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲሠራጭ በማድረጉ ነው፡፡ በዚህ ጽሑፍ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ በቁጥር 532/05/04/08 በቀን 3/5/2008 ዓ.ም ለቅዱስ ፓትርያርኩ ያቀረበውን ደብዳቤ እና ያወጣውን መግለጫ እንዳስሳለን፡፡ በቀጣይም የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስና የከሳቴ ብርሃን ሰላማ ደብዳቤዎችን ይዘት ለማቅረብ እንሞክራለን፡፡

Tuesday, January 12, 2016

ስለ ወንጌል እውነት መሞት እንጂ መግደል የክርስቲያኖች ተግባር አይደለምየማኅበረ ቅዱሳን ብሎግ የሆነችው ሐራ ሰሞኑን አንድ ሊታመን የማይችል ወሬ አስነብባለች፡፡ ይኸውም ሁለት ማሊያ ለብሶ ለፖለቲካም ለሃይማኖትም በሚጫወተው በታደሰ ወርቁ ላይ ተሐድሶዎች የግድያ ሙከራ አደረጉበት የሚል ነው፡፡ በቅድሚያ ታደሰ ወርቁ ላይ ደረሰ የተባለው የግድያ ሙከራ ማንም ያድርሰው ማን እውነት ከሆነ ተገቢ አይደለም፡፡ ሐራ ግን ይህን ያደረጉት ተሐድሶዎች ናቸው ብላ ታደሰን አጽናንታዋለች፡፡ ምክንያቱም በህልሙም ሆነ በእውኑ የታደሰ ወርቁ ቅዠት ይህ ስለሆነ በተሐድሶ ላይ ማላከኳ እርሱ እንዲጽናና ካልሆነ በቀር ውሸት ለመሆኑ ዘገባው መለክታል፡፡ ለምን? ቢባል ታደሰ ወርቁ የግድያ ሙከራ ተቃጣበት ያለችው ቦታ ላይ ግድያን ጨምሮ በርካታ ወንጀሎች የሚፈጸሙበት ስፍራ መሆኑን ያካባቢውን ነዋሪዎች አነጋግሬ ደርሼበታሁ ስትል ገልጻለች፡፡ ታደሰ ላይ የተሰነዘረው ጥቃት በተሐድሶዎች እጅ ነው የተፈጸመው መባሉ በየትኛው መንገድ ነው የተረጋገጠው? የሚለው ግን በቀላሉ የሚታለፍ አይደለም፡፡
ሐራ ራሱን ታደሰን ጠቅሳ እንደጻፈችው ጥቃት አድራሾቹ ተሀድሶዎች ሲሆኑ “የእኛ የፀረ ተሐድሶ ገላጭ አሁን እስኪ ማህበሯ ታድንህ እንደሆነ እናያለን እንገድልሃለን” አሉኝ በማለት ሰዎቹ ተናገሩኝ ያለውን ጠቅሳለች፡፡ ለዚህ ግን ከእርሱ ውጪ ሌላ ምሰክር የለም፡፡ 

Wednesday, January 6, 2016

“ … ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች …” ሉቃ. 2፥10-11ቤዛ ኩሉ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ መወለዱ ለሚታሰብበት 2008ኛው ዓመት በዓለ ልደት እንኳን አደረሳችሁ፡፡
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን በዓለ ልደት በየዓመቱ ታኅሣሥ 29 በአራት ዓመት አንድ ጊዜ በዘመነ ዮሐንስ ደግሞ ታኅሣሥ 28 ቀን በኢትዮጵያውያን ዘንድ ይከበራል፡፡ በዓሉ በሃይማኖታዊም በባህላዊም ሥነ ሥርዓቶች ነው የሚከበረው፡፡ በዓለ ልደት በኀጢአት የወደቀውን የሰውን ልጅ ለማዳን በነቢያት ትንቢት የተነገረለት፣ ሱባኤ የተቆጠረለት መሲሕ ሰው ሆኖ መወለዱ የሚታሰብበት በዓል ነው፡፡ እነሆ መወለዱን ምክንያት በማድረግ በዓል ስናደርግ ጌታ ሲወለድ በተላለፈው መልእክት ተመርተን ወደ መሲሑና ወደ አዳኝነቱ መድረስ አለብን፡፡
ጌታ በተወለዳበት በዚያች ሌሊት መንጋቸውን ይጠብቁ ለነበሩ እረኞች የተገለጠው የጌታ መልአክ እንዲህ ነበር ያለው “እነሆ፥ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ፤ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና።” (ሉቃ. 2፥10-11)፡፡ የጌታ መወለድ ታላቅ የምሥራች ነው፡፡ ምክንያቱም የተወለደው መድኃኒት፣ በናፍቆት ሲጠበቅ የነበረው መሲሕና ጌታ ነው፡፡ መድኃኒትነቱ ደግሞ ለኀጢአተኛው ዓለም ነው፡፡ ስለዚህ  በዓለ ልደቱን የሚያከብር ሰው ሁሉ የጌታ መወለድ ይዞለት የመጣውን ደስታና የምሥራች ማስተዋል አለበት፡፡ አዎን የተወለደው ሕጻን መድኃኒት ነው፡፡ የምሥራቹም ለኃጢአታችን መድኃኒቱ መጥቷል ደስ ይበላችሁ የሚል ነው፡፡ መድኃኒት ባልተገኘለት በሽታ ሲሰቃይ የነበረና ወደሞት እየቀረበ ያለ ሰው ለበሽታህ መድኃኒቱ ተገኝቷል ቢሉት ምን ያህል ደስታ እንደሚሰማው መገመት አይከብድም፡፡ የጌታ መልአክም ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆነውን የምሥራች የተናገረው ለኃጢአት መድኃኒቱ መጥቷልና ኃጢአተኞች ሁሉ ደስ ይበላችሁ ሲል ነው፡፡

Friday, January 1, 2016

በሚኒሶታ ስቴት በጽርሐ አርያም ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ለቅዱስ ፓትርያርኩ ታላቅ አቀባበል ተደረገ!


Read in PDF 
ከሚኒሶታ የፓትርያርኩን የአሜሪካ ጉዞና አቀባበል በዚያም የነበረውን ሁኔታ የተመለከተ ዘገባ ደርሶናል ቀጥሎ እናቀርበዋለን፡፡ ቀጣይ ዘገባዎችንም እንደደረሱን ለማቅረብ ጥረት እናደርጋለን፡፡
  
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓርትርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ባለፈው ታኅሣሥ 11/2008 ቅዳሜ ከሰዓት በኋላ ከዋሽንግተን ዲሲ ወደ ሚኒሶታ የገቡ ሲሆን ታላቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል። ከኤርፖርት ጀምሮ እስከ ቤተ ክርስቲያኑ ድረስ እጅግ በብዙ ሺ የሚቆጠር ሕዝብ ያጀበ ሲሆን በመቶዎች የሚቆጠሩ ሞተረኞችም አጅበው እንደነበረ ለማወቅ ተችሏል። ልብሰ ተክህኖ የለበሱ በርካታ ካህናት የተገኙ ሲሆን ቅዱስ ፓትርያርኩ በሊቃነ ጳጳሳት ታጅበው በሊሜዝን ሆነው የሰንበት ት/ቤት መዘምራንና ሕዝቡ በዝማሬና በይባቤ ኢያሸበሸቡ ነበር ያጀቡአቸው። የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ አቀባበል በአሜሪካ ይህ የመጀመሪያው ባይሆንም በዓይነቱና በይዘቱ ግን እጅግ የተለየ እንደነበረ ተገልጿል። ቅዱስ ፓትርያርኩ ከቤተ ክርስቲያን እንደ ደረሱ ጸሎተ ኪዳን ተደርሷል። የያሬድ ጣዕመ ዜማና ቅኔ ከተበረከተ በኋላ ቅዱስ ፓትርያርኩ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ ሰጥተዋል። የቅዱስ ፓትርያርኩን ቃለ ምዕዳን ከዚህ ጽሑፍ ቀጥለን እናቀርባለን።

ሚኒሶታ ጽርሐ አርያም ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ከመድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ለይቶ የተቋቋመ ሲሆን ከተቋቋመ ሁለት ዓመት ያልሞላው አዲስ ቤተ ክርስቲያን ነው። የመቋቋሙ ምክንያትምበኢትዮጵያው ቅዱስ ሲኖዶስ እንመራ፤ የቤተ ክርስቲያን ቀኖናና ሥርዓት ከበር አለበትሲሉ ሌላው ወገን ደግሞ በገለልተኛነት መቀጠል አለብን በማለት የተፈጠረ ከፍተኛአለመግባባት ነበረ። ጉዳዩ በመጨረሻ ፍርድ ቤት ደርሶ አንደኛው ወገን እንደምንም የሰው ቁጥር በማብዛት በእጅ ብልጫ አስፈርዶ ቤተ ክርስቲያኑን ተረከበ። የቀረው ወገን በቁጭት ወጥቶ የራሱን ቤተ ክርስቲያን ገዝቶ ሚኖሶታ ጽርሐ አርያም ቅድስት ሥላሴ አሰኘ። አንዳንድ ጳጳሳት የገንዘብ ልመናን ተገን በማድረግ በሁለቱም መካከል ግጭቱን ወደተባባሰ ደረጃ ወስደውት የነበረ ሲሆን በዚህም የጽርሐ አርያም ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን ክፉኛ ያዘኑ መሆናቸው ይታወሳል። በዚያ ክፉ የፈተና ጊዜም ቅዱስነታቸው የማጽናናት መልእክታቸውን እንደአስተላለፉላቸው ተወስቷል። ያ ሁሉ የፈተናና የመከራ ጊዜ አልፎ ዛሬ ቅዱስ ፓትርያርኩ በአካል ተገኝተው ሲባርኩአቸው ደስታቸውን ዕፅብ ድርብ አድርጎታል። ስለዚህም አቀባበሉን ልዩ ያደረገው ይህ ሁሉ ተደማምሮ እንደሆነ ተገምቷል።