Wednesday, January 6, 2016

“ … ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች …” ሉቃ. 2፥10-11ቤዛ ኩሉ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ መወለዱ ለሚታሰብበት 2008ኛው ዓመት በዓለ ልደት እንኳን አደረሳችሁ፡፡
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን በዓለ ልደት በየዓመቱ ታኅሣሥ 29 በአራት ዓመት አንድ ጊዜ በዘመነ ዮሐንስ ደግሞ ታኅሣሥ 28 ቀን በኢትዮጵያውያን ዘንድ ይከበራል፡፡ በዓሉ በሃይማኖታዊም በባህላዊም ሥነ ሥርዓቶች ነው የሚከበረው፡፡ በዓለ ልደት በኀጢአት የወደቀውን የሰውን ልጅ ለማዳን በነቢያት ትንቢት የተነገረለት፣ ሱባኤ የተቆጠረለት መሲሕ ሰው ሆኖ መወለዱ የሚታሰብበት በዓል ነው፡፡ እነሆ መወለዱን ምክንያት በማድረግ በዓል ስናደርግ ጌታ ሲወለድ በተላለፈው መልእክት ተመርተን ወደ መሲሑና ወደ አዳኝነቱ መድረስ አለብን፡፡
ጌታ በተወለዳበት በዚያች ሌሊት መንጋቸውን ይጠብቁ ለነበሩ እረኞች የተገለጠው የጌታ መልአክ እንዲህ ነበር ያለው “እነሆ፥ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ፤ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና።” (ሉቃ. 2፥10-11)፡፡ የጌታ መወለድ ታላቅ የምሥራች ነው፡፡ ምክንያቱም የተወለደው መድኃኒት፣ በናፍቆት ሲጠበቅ የነበረው መሲሕና ጌታ ነው፡፡ መድኃኒትነቱ ደግሞ ለኀጢአተኛው ዓለም ነው፡፡ ስለዚህ  በዓለ ልደቱን የሚያከብር ሰው ሁሉ የጌታ መወለድ ይዞለት የመጣውን ደስታና የምሥራች ማስተዋል አለበት፡፡ አዎን የተወለደው ሕጻን መድኃኒት ነው፡፡ የምሥራቹም ለኃጢአታችን መድኃኒቱ መጥቷል ደስ ይበላችሁ የሚል ነው፡፡ መድኃኒት ባልተገኘለት በሽታ ሲሰቃይ የነበረና ወደሞት እየቀረበ ያለ ሰው ለበሽታህ መድኃኒቱ ተገኝቷል ቢሉት ምን ያህል ደስታ እንደሚሰማው መገመት አይከብድም፡፡ የጌታ መልአክም ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆነውን የምሥራች የተናገረው ለኃጢአት መድኃኒቱ መጥቷልና ኃጢአተኞች ሁሉ ደስ ይበላችሁ ሲል ነው፡፡

ነገር ግን የልደት በዓሉ የመከበሩን ያህል በክብረ በዓሉ የልደቱ ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምን ያህል ይታሰባል? ምን ያህሉስ ሰው በክርስቶስ የልደት ዜና ላይ ብቻ ቆሞ ስለተወለደው ሕፃን ብቻ ያስባል? ማለት የተወለደው ሕጻን የዓለም ቤዛ ሊሆን እንደተወለደና በኋላም ቤዛ ሆኖ ከዘላለም ሞት እንዳዳነው ምን ያህሉ ሰው ይገነዘብ ይሆን? የዓለሙ ሁሉ ቤዛ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ እንደሆነና ሰው ሆኖ የተወለደበትን ዓላማና የፈጸመውን የማዳን ሥራ አምኖ በመቀበል በእግዚአብሔር ፈቃድና ዘላለማዊ ዕቅድ ውስጥ የገባ ስንቱ ሰው ይሆን? ይህ በሕይወቱ ያልተከናወነለት ሰው በዓለ ልደትን ማክበሩ ለሥጋው ደስታ በበዓል ከሚያገኘው ፌሽታ በቀር ለነፍሱ የሚያተርፈው አንዳች ነገር የለም፡፡
ስለዚህ በዓለ ልደቱን ስናከብር ከቅድስት ድንግል ማርያም በሥጋ ስለተወለደው ሕጻን ብቻና የእርሱን መወለድ በማሰብ በመብል በመጠጥና በመሳሰለው ሥጋዊ ድግስና በጭፈራ ራስን ለማስደሰት ከሆነ የበዓሉን መንፈሳዊ ትርጉም ስተናል፡፡ እንደ ኢትዮጵያውያን ዘመን አቆጣጠር የዛሬ 2008 ዓመት የተወለደው ሕጻን በ34 ዓ.ም ለቤዛ ዓለም እንደሞተና ለኃጢአት የሚበቃውን መሥዋዕት ራሱን እንዳቀረበ በእርሱ ቤዛነት በኩል ወደዘላለም ሕይወት መግባት እንደሚቻል የተገነዘበ ሰው በዓለ ልደትን ቢያከብር ብዙ ትርጉም ይሰጠዋል፡፡ ይኸውም ሰው ሆኖና ራሱን የተወደደ መስዋዕት አድርጎ በማሳረግ ያዳነው አምላክ አስቀድሞ የሰጠውን ተስፋ ለመፈጸም ሰው ሆኖ ከቅድስት ድንግል ማርያም መወለዱን ስለሚያስታውሰው ሁሌም የሚደነቅበትን የእግዚአብሔርን ፍቅርና በውድ ልጁ ሞት ሕይወት ያገኘበት የማዳን ሥራው የተበሠረበት ዕለት ነው፡፡
 
በዓለ ልደቱን የምታከብሩ ሁሉ ይህን እውነት እንድታስተውሉ እግዚአብሔር አእይንተ ልቡናችሁን ያብራ በማለት መልካም በዓለ ልደት እንዲሆንላችሁ እንመኛለን፡፡

5 comments:

 1. Enter your comment...the Protestant world does not give due emphasis about the birth and rise of our lord, savour, and god (Jesus Christ). here in Ethiopia, they seem to respect because of the Ethiopian church unreserved celebration

  ReplyDelete
 2. እጅግ በጣም ጥሩ ጽሁፍ ነዉ
  አስተዋይ ልቡና ይስጠን

  ReplyDelete
 3. አባ ሰላማም ሀራም ወሬ ጠረረባቸው!!

  ReplyDelete