Tuesday, January 26, 2016

ይድረስ ለብፁዕ አቡነ መልከ ጸዴቅ እና ለ‹አሜሪካው ሲኖዶስ› አባቶች!በዲ/ን ተረፈ ወርቁ፡፡
ብፁዕነትዎ፣ ‹‹ቤተ ክርስቲያን በኦርጋን የሙዚቃ መሳሪያ መዘመርን መፍቀድ እንዳለባትና ካህናቶቿም በኦርጋን መዘመርን መማር እንዳለባቸው፡፡›› የሚል ይዘት ያለውን መልእክትዎን ከተለያዩ ድረ ገጾችና ይህን የእርስዎን መልእክት እየተቀባበሉ ክርክርና ሙግት ከገጠሙባቸው፣ የቤተ ክርስቲያናችን የሶሻል ሚዲያው አባላት/ጓደኞቼ ገጾች ላይ አነበብኩ፡፡ እናም ለብፁዕነትዎ፣ በአሜሪካ ለሚገኘው ሲኖዶስና ይህን የእርስዎን አሳብ ለሚያቀነቅኑ በአገር ውስጥና በውጭ አገር ለሚገኙ ወገኖቼ አንዳንድ የግል የኾነ ጥያቄዎችንና የግል አስተያየቴን ለማቅረብ ስል ብዕሬን ለማንሣት ወደድኹ፡፡
ብፁዕነትዎ በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሊቀ ሥልጣናት ከነበሩበት ዘመናት ጀምሮ የጻፏቸውን መጽሐፎችዎን በሚገባ አንብቤያለሁ፡፡ ከሁሉም ከሁሉም ደግሞ ‹የስብከት ዘዴ› የምትለው መጽሐፍዎን አልረሳውም፡፡ መንፈሳዊ አግልግሎትን በጀመርኩበት ወራት መልካም ዕውቀትን፣ ግሩም የኾነ መንፈሳዊ ምክርንና ጥበብን፣ ስንቅና ማስተዋልን የሰጠችኝ መጽሐፍ ነበረች፡፡

ብፁዕነትዎ በኢትዮጵያ ቤ/ን ዶግማና ቀኖና፣ ታሪክና ባህል፣ ትውፊትና ሥርዓት ያለዎትን ጥልቅ ዕውቅትም በሚገባ አውቃለኹ፣ አደንቃለኹም፡፡ ለዚህም ያለኝን አድናቆትና ምስጋና ከገለጽኩ በኋላ ግን ‹‹የቤተ ክርስቲያናችን ዝማሬ አግልግሎት በኦርጋን ሊታጀብ ይገባዋል!›› የሚል ይዘት ባለው በሰሞኑን መልእክትዎ ዙርያ ለብፁዕነትዎ ላነሣኹ ስለወደድኩት አንዳንድ ጥያቄዎቼና የግል አስተያየቴ ልመለስ፡፡
ለመሆኑ ዛሬ ቤተ ክርስቲያናችን- የኢትዮጵያው ሲኖዶስ፣ ‹‹ሕጋዊው/የአሜሪካው ሲኖዶስ››፣ ገለልተኛ በሚል በተከፋፈለችበት፣ ምእመናኖቿ መንፈሳዊ ካባን በደረቡ ፖለቲከኞች ሴራና ደባ በአገር ቤትና በውጭ- ከአፍሪካ እስከ አሜሪካ፣ ከአውሮፓ እስከ አውስትራሊያ፣ መካከለኛው ምሥራቅ- እስራኤልና ካናዳ ድረስ የትግሬ፣ የኦሮሞ፣ የአማራ ቤ/ን በሚል በተከፋፈሉበት በዚህ የቤተ ክርስቲያናችን ‹የጨለማ ዘመን› እንዲህ ዓይነቱን ከቁጥር ሊገባ የማይችል ርዕሰ ጉዳይ ማንሣት ለምን አሰፈለገን?!
በቅዳሴያችን ሥነ-ሥርዓት በእንተ ቅድሳት ላይ ዲያቆኑ፣ ‹‹አንድ በምታደርግ ሥጋውና ደሙ እግዚአብሔር በይቅርታው አንድ ያደርግን ዘንድ ሰላምን እንማልዳለን፤ እስከ ፍጻሜያችን ድረስ እግዚአብሔር በመንፈስ ቅዱስ አንድነት ይጠብቀን ዘንድ ስለ አንድነታችን እንማልዳለን!›› የሚለው የዘወትር ጸሎታችንና ምልጃችን- የግብዝነታችን መገለጫ በኾነበት በዚህ ክፋታችንና ዓመፃችን፣ ዘረኝነታችንና ጎጠኝነታችን፣ መለያየታችንና መከፋፈላችን የተነሣ መሳቂያና መሳለቂያ በኾንበት፣ በዚህ ቤተ ክርስቲያኒቱ እግዚኦ! የመንፈሳዊ አባት ያለህ በምትልበት ፈታኝ ወቅት በእውነት ከምንወድዎ ብፁዕነትዎ ‹‹በኦርጋን ይዘመር ወይስ አይዘመር!›› የሚል ተራ መልእክትን አንጠብቅም፡፡
ረኻብ ሕዝቦቿን በየዐሥር ዓመቱ እያሰለሰ እየመጣ በሚያጭድባት፣ ልጆቿ በስደት በባዕድ አገር እንደ እስራላዊቷ ኖኃሚን ስማቸውን ታሪካቸው ተቀይሮባቸው በሰሰቀቀን በኀዘን ሌት ተቀን በሚያለቅሱባት፣ ከእግዚአብሔርና ከሕዝብ አደራ የተሰጣቸውን ሥልጣን ለግል ጥቅማቸውና ቅጥ ላጣ ምኞታቸው የሚያውሉ ሙሰኞች በበዙባት፣ ከእኛ ወዲያ የፖለቲካ አማራጭ እሳቤ/ፖሊሲ ምን ሲደርግ የሚሉ አምባ ገነኖች የገዛ ሕዝባቸውን በወኅኒ በሚያጉሩባት መከራና ሞት ባጠላባት አገር፡፡
ሰሞኑን ሁላችንም እንደታዘብነው የኦሮሚያው ዘግናኝ እልቂት፣ በገዛ ሕዝባቸው ላይ የመሳሪያ አፈሙዛቸውን በወገኖቻቸው ላይ ለማዞር አንዳንች ልባዊ ርኅራኄና ኀዘኔታ በሌላቸው ታጣቂዎች- ነገ ተምረው ችግረኛ ቤተሰዎቻችን፣ ወገኖቻችንና አገራችንን እንጠቅማለን በሚል ሕልም ወደ ዩኒቨርሲቲ ለትምህርት የመጡ ወጣት ተማሪዎች ደማቸው እንደ ውሻ ደም በከንቱ በሚፈስባት እናት ምድራችን ኢትዮጵያ- ከብፁዕነትዎ የምትጠብቀው የጊዜውን መንፈሳዊ መልእክትና ማጽናናት ነው እንጂ፣ እንዲህ ዓይነቱን በምእመናን መካከል ልዩነትንና መከፋፈልን የሚፈጥር ተራ መልእክትን አይደለም፡፡
ለመሆኑ ይህ ለበርካታ ጊዜያት የተነሣና በተደጋጋሚ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ሊቃውንቶች መልስ የተሰጠበት ‹በኦርጋን የመዘመር› ጉዳይ ዛሬ በምን ሰበብ ነው እንደ አዲስ ጉዳይ ሊነሣ የቻለው፡፡ በእውነቱ ከሆነ በጣሙን አስገርሞኛል፣ አሳዝኖኛልም፡፡ መቼም ብፁዕነትዎ በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሊቀ ሥልጣናት በነበሩበት ዘመን በወቅቱ ለምን በኦርጋን ይዘመር የነበረበትን ዋንኛ ምክንያቱን ይስቱታል ብዬ አላስብም፡፡ በዚህ በኦርጋን የመዘመር ጉዳይ/ክርክር ላይ በወቅቱ በጠቅላይ  ቤተ ክህነት የወጣቶች ጉዳይ ሓላፊ የነበሩትና በአሁን ሰዓት ደግሞ በመንበረ ፓትርያርክ በጠቅላይ ቤተ ክህነት የዕድና ልማት መምሪያ ሓላፊ የኾኑት ሊቀ ትጉሃን ሃ/ጊዮርጊስ ዳኜ በአንድ ወቅት እንዲህ ብለው ነበር፡፡
በ፲፱፻፹ዎቹ መጨረሻ አካባቢ የእምነት ተቋማት ወጣቶችን በመንጠቅ እያደረጉ ያሉትን ፍልሰት ለመቋቋም ሲባል ለእነርሱ የአጸፋ መልስ ለመስጠት ሲባል በኦርጋን መጠቀም ተጀመረ፡፡ እነዚህ ዘመናዊ ሙዚቃ መሳሪያዎች ታዲያ ምን ለውጥ አመጡ ለሚለው ጥያቄ መልስ ሲሰጡም ምንም! ኦርጋኑ በምስባክ ጊዜ ጥቅም ላይ በዋለበት ጊዜ ምስባኩ ምልክቱን ጠብቆ በትክክል ሲዜም ፒያኖው ማጀብ ስለማይችል ዜማው ያለ ምልክቱ ይለጠጥ ነበር፡፡ አንዳንዴም ዜማው በየመኻሉ እንዲቆረጥ ይደረግ ነበር፡፡ ከዚያም ባሻገር እንደተፈራው ሰውን ዘፋኝ አደረገው፡፡ ወደ አንድ የዘፈን ትርኢት/ኮንሰርት ስትሔዱና ወደ አንድ ሰንበት ት/ቤት አዳራሽ ስትሔዱ ምታዩትና የምትሰሙት ተመሳሳይ እየኾነ መጥቶ ነበር፡፡
ሊቀ ትጉሃን ኃ/ጊዮርጊስ ዘመናዊ መሳሪያዎች ከቤተ ክርስቲያን እንዴት ሊወጡ እንደቻሉም እንዲህ በማለት ያብራራሉ፡፡ በመሠረቱ በቤ/ን ትውፊትና ሥርዓት እንኳን ከቀኖና ውጭ ያሉ መሳሪያዎችን አገልግሎት ላይ ለማዋል ቀርቶ ድምፀ መልካም የኾነ አገልጋይ እንኳን ድምፁን ለቆ እንዲጮኽ አይፈቀድም፡፡ ድምፁ/ዜማው ወደ ሥጋዊ ሐሳብ እንዳይወስድና ምስጢሩን እንዳይሸፍን ድምፁን መለስ ቀለስ አድርጎ መጮኽ አለበት፡፡ ዜማው ሥጋዊ ድምቀት እንዳይኖረው እስከዚህ ድረስ ጥንቃቄ መደረግ አለበት፡፡ ስለዚህ ከላይ የጠቀስኳቸው ነገሮች አዝማሚያቸው አሉታዊና ለቤ/ን ሥርዓት አደጋ ያላቸው መኾናቸው ስለታወቀ ቤ/ን ጉዳዩን በቶሎ እንደቀጨችው ያብራራሉ፡፡
 እንደው የሆነስ ሆነና የእኛውን አገሪኛ መሳሪያዎቻችንን መች በቅጡ ተጠቀምንባቸውና አውቀናቸው ነው ወደ ውጩ ዓለም መማተር ያስፈለገን?! ከመቋሚያው እስከ ከበሮውና ጽናጽሉ፣ ከበገናው እስከ እንዚራው ድረስ በመንፈሳዊ ትእምርታቸውና ትርጓሜያቸው ታላቅ መንፈሳዊ ምስጢርን የተሸከሙ መሳሪያዎች እያሉን የውጮቹን የሙዚቃ መሳሪያ መቋመጥ ምን ይሉት ነገር ነው ጎበዝ?!
ታሪካቸውን፣ ማንታቸውን፣ ቅርሳቸውንና ባህላቸውን በአሰቃቂው የባሪያ ንግድና በቅኝ ግዛት ወረራ ወቅት የተዘረፉ የአፍሪካ፣ የደቡብ አሜሪካና የኤዥያ ሕዝቦች ወደ ጥንቱና ትክክለኛ ማንነታችን መመለስ ይገባናል ‹‹Back to the Root›› በሚል ዘመቻ ወደትናንትናው የአባቶቻቸውን ታሪክና ማንነት፣ ቅርስና ባህል ለመመለስ በሚታገሉበት በዚህ ዘመን- እኛ የሰው ልጆች ግዙፍ ታሪክና የገናና ሥልጣኔ መነሻ፣ የጥቁር ሕዝቦች የነጻነት ተጋድሎ ቀንዲል፣ የክርስትና ሃይማኖት ደሴየት፣ ለአፍሪካውያንና ለዓለም ሕዝብ የታሪክ መዝገብ/እምብርት ተብለን የተጠራን ኢትዮጵያውያን የራሳችንን አሸቀንጥረን ጥለን የሌላውን ማማተር ከራስ ታሪክና ማንነት ጋር መጣላት/Identity Crisis እንጂ ሌላ ምን ሊባል ይቻላል?!
እስቲ ለአብነት ያህል በቤተ ክርስቲያናችን ለመንፈሳዊ አገልግሎት ስለሚውለው መንፈሳዊ መሳሪያ በገና ጥቂት ነገሮችን ላንሣ፡፡ እንደ በገና ያሉ የመንፈሳዊ ሙዚቃ መሳሪያዎቻችን ከጥንታዊነታቸውና ታሪካዊነታቸው ባሻገርም መንፈሳዊ ፋይዳቸው ላቅ ያለ እንደሆነ በአንድ ወቅት ላይ ለዶክትሬት ድግሪዋ ማሟያ የሚኾነውን ጥናቷን በበገና ላይ የሠራች አንዲት ቤልጄማዊት ምሁር የጥናት ወረቀቷን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ባደረገችው ገለጻ/ሌክቸር ላይ ገልጻ ነበር፡፡
ይህች ተመራማሪ በጥናቷ እንዳረጋገጠችው በዓለማችን ከሚገኙ የክር መሳሪያዎች መካከል በሚያወጣው ድምጽ በገናን የሚወዳደር እንደሌለ ነበር በጥናቷ ማረጋገጧን የገለጸችው፡፡ በፊዚክስ ሳይንስ ጥበብ የታገዘው የዚህች ምሁር ጥናት እንዳረጋገጠው በገና የሚያወጣው የድምፅ ንዝረት ከፍተኛ የሆነ ፍሪኬዌንሲ/High Frequency ያለው መኾንኑና የበገና ድምፅ ንዝረትም በኼርዝ ሲለካ ከሌሎች የክር መሳሪያዎች ሁሉ የላቀ እንደሆነ ነበር በ‹ፓወር ፖይንት› በተደገፈ ሳይንሳዊ ገለጻዋ ያስረዳችን፡፡
ይህ የበገና ከፍተኛ የኾነ የድምፅ ንዝረትና ፍሪኩዌንሲ ደግሞ ከሰው ልጅ መንፈሳዊ ማንነት ወይም ከነፍሱ ጋር የተቆራኘ፣ ለአምልኮተ እግዚአብሔርና ለተመስጦ ከፍተኛ እገዛ የሚሠጥ መኾኑን ነው በጥናቷ ያረጋገጠችው፡፡ የዚህችን አውሮፓዊት ሴት ጥናት ተመርኩዘውም ኢትዮጵያዊው ሳይንቲስትና የኤሌክትሮኒክስ ፊዚክስ ምሁር የኾኑት ዶ/ር ኢንጂነር ብርሃኑ ግዛው በበገና ላይ ባደረጉት ሰፊ የኾነ ጥናትም በገና ለመንፈሳዊ ምጥቀት፣ ለአምልኮተ-እግዚአብሔር፣ ለአርምሞና ለተመስጦ መንፈሳዊ ሕይወት ያለውን ከፍተኛ የኾነ አስተዋጽኦ በጥናታቸው በስፋት አብራርተውታል፡፡
ከዚህም ባሻገር የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የአምልኮ ሥርዓት፣ ታሪክና ባህል፣ ትውፊትና ሥርዓት እንዲሁም እንደ በገና ያሉ የሚዳሰሱና ሌሎች የማይዳሰሱ የቤተ ክርስቲያኒቱ በርካታ ቅርሶች/Tangible and Intangible Heritages ለአገራችን የቱሪዝም ኢኮኖሚ ዕድገትና ግሥጋሤ እያደረጉት ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ እነዚህ የኢትዮጵያ ቤ/ን ለሺሕ ዘመናት ጠብቃ ያቆየቻቸው የቤተ ክርስቲያኒቱ ሀብታትና ቅርሶች ዘር፣ ጎሳና ሃይማኖት ሣይለዩ ለብዙዎች የሥራ ዕድልንና የገቢ ምንጭ ኾነዋል፡፡ ታዲያ እነዚህን የአገራችን የቱሪዝም ኢኮኖሚ ዋልታ፣ የታሪካችንና የማንነታችን መገለጫ የኾኑ ሀብቶቻችን ምን ባጎደሉና ባጠፉ ነው በሌሎች እንዲተኩ እየፈረድንባቸው ያለው?!
በጀመርኩት ርዕሰ ጉዳይ ጥቂት ሐሳቦችን ልጨመርና ጹሑፌን ላጠናቅ፡፡ መቼም ዛሬ ዛሬ መንፈሳዊ መዝሙር ይኹን ዘፈን መለየት ማይቻሉ መዝሙር መሰል ዳንኪራዎች ለወጣቱ ትውልድ ምን ያህል ፈተና እየኾኑ እንደመጡ በግልጽ እየታዘብን ነው፡፡ መንፈሳዊው መልእክታቸው እጅግ በበዛው የሙዚቃ መሳሪያ አጀብና ግርግር የተሸፈነ፣ ለንስሐና ለጸጸት ከሚያነሳሡ ይልቅ ለሥጋዊ ስሜትና ሞቅታ የሚዳርጉ የአስረሽ ምቺው መዝሙራት ለጫት መቃሚያና ለመዝናኛነት እስኪውሉ ድረስ ወርደውና ዘቅጠው ያሉበትን ደረጃቸውን በቁጭት ምንታዘብበት ጊዜ ላይ ደርሰናል፡፡
ይህን በዘመናዊ መሳሪያ ካልዘመርን ምናች ነው ታዲያ ክርስቲያን?!፣ መፈታት አለብን የምን መታሰር ነው- ታሪክና ባህል፣ ትውፊትና ወግ እያሉ በሰለጠነ ዘመን የምን ኋላ ቀርነት ነው ያሉ፣ የ‹መዝሙር አብዮተኞች› ነን ባዮች ዛሬ ምን ላይ እንዳሉ የምናውቅ እናውቃለን፡፡ መንፈሳዊ ክስረታቸውንና ውርደታቸውን በመሳሪያ ጋጋታና በተዋበ መድረክ ለማካካስ እየተጉ ያሉ የእምነት ተቋማት በዘመናዊነት ስም ውስጣቸው ነትቦ፣ ተራቁተውና ፈራርሰው ወዴት አቅጣጫ እየተጓዙ እንዳለም እያየን፣ እየታዘብን ነው፡፡
እንደው እሰቲ በዚህ ዘመን ‹በኦርጋን ይዘመር ወይስ አይዘመር?!› የሚል ጉንጭ አልፋ መከራከሪያ ማንሣት ምንድን ነው ጠቀሜታው፡፡ በኦርጋን ካልዘመራችሁ ምስጋናችሁም ሆነ ጸሎታችሁ ሰማይ ሰማያት አያርግም፣ በሙዚቃ መሳሪያ ካልዘመራችሁ መንግሥተ ሰማያት አትገቡም የሚል ትእዛዝስ አለ እንዴ?!
ለምን መከራከር መወያየት ካለብን ስንት ጭንቅላት አስይዞ ኡ…ኡ….ኡ…! የሚያሰኙና ጆሮን ጭው የሚያደረጉና ልብን በኀዘን ጦር የሚወጉ ጉዳዮች በምናይበትና በምንሰማበት የቤተ ክርስቲያናችን ኁልቆ መሣፍርት ችግሮች አሉ አይደል እንዴ?! ለምን ከቤት እስከ ውጭ የነገሠብንን መለያየት፣ ዘረኝነት፣ ጎጠኝነትና መከፋፈል እንዴት ማስወገድ እንደምንችል፣ ከአባቶችና ከአገልጋዮች እስከ ምእመናን ድረስ በእጅጉ ስለተንሰራፋው የሞራል ውድቀትና ዝቅጠት፣ ኃጢአትና ዓመፃ አንወያይም፡፡
ወደ ማጠቃለያ ሐሳቤ ስመለስም፣ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ለራሷ ብቻ ሣይሆን ለአገራችን ኢትዮጵያ፣ ለአፍሪካና ለዓለም ሁሉ መደነቂያ የሆነ የዜማ ሀብት፣ ሥርዓትና ትውፊት እንዲሁም ለዘመናት ስትጠቀምባቸው የነበሩ በርካታ መንፈሳዊ የሙዚቃ መሣሪያ ያላት ናት፡፡ ታዲያ በምን ምክንያት ይሆን የሌሎችን የሙዚቃ መሳሪያ መጠቀም ወይም መቀላወጥ ያስፈለገን?!
በመሠረቱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዓለም ገና ስለ ሙዚቃና የዜማ ምሥጢር ማወቅና መነጋገር ከመጀመሩ ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት ጥልቅና ሰማያዊ  የሆነ መንፈሳዊ ዜማ ድርሰትና ምልክቶች/Nota ምን መሆኑን ሳይደርስበት በፊት በታላቁ ሊቅና ማሕሌታይ በቅዱስ ያሬድ አማካይነት የሰማያዊ ድርሰትና ዜማ ባለቤት ለመሆን የበቃች፣ ራሷ የሆነ ታሪክና ቅርስ፣ ባህልና ሥርዓት፣ ትውፊትና ወግ ያላት ጥንታዊትና ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡
እናም እባካችሁ በውጭ አገር-በተለይም በአሜሪካ ያላችሁ አባቶች ‹በኦርጋን ይዘመር አይዘመር› የሚል የማይጠቅምና አንዳንች ረብ የሌለው ጉዳይ እያነሳችሁ ምእመናንን እንዲለያዩ ባታደርጉ መልካም ነው፡፡ እንዴ ክርስትናን በፍቅር፣ በተግባር የኖሩ አባቶቻችን እኮ ‹‹ሥጋን መብላት ወንድሜን የሚያሰናክለው ከኾነ ለዘላለም ሥጋ አልብላ፡፡›› እስከ ማለት በወንጌል ያገኙትን አርነታቸው ለፍቅር ሲሉ ለሌሎች ወንድሞቻቸው አሳልፈው የሰጡ የእምነት አርበኞች በተጋደሉበት ቤ/ን ውስጥ እኮ ነው ያለነው፡፡
ታዲያ እኛ ዛሬ ከየት በተገኘ እውቀትና ጥበብ ነው ሊያውም ቤተ ክርስቲያን በቀኖናዋ የእኔ አይደለም ብላ በከለከለችው መሳሪያ ካልዘመርን በማለት ሌሎችን የሚያሰናክል፣ እንዲህ ያለ መለያየትን የሚያነግሥ ሙግትና ክርክር መፍጠር ምን የሚሉት ነገር ነው?! ምንስ ጥቅም ለማግኘት ተብሎ ነው?! እናም እባካችሁ በአገር ውስጥም ኾነ በውጭ አገር ይህን አሳብ በማቀንቀን በአገልጋዮችና በምእመናን ዘንድ ልዩነት በመፍጠር ላይ ያላችሁ ወገኖችም ቆም ብላችሁ እንድታስቡ፣ እንድናስብ አደራ እላለኹ፡፡
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!
 

7 comments:

 1. Teriye yeliben siletsfkilign egziabher aemirohin yibarkew
  zare tinignin mewat gimelin matrat tsidq behonebet bezih zemen betiqaqin tirki mirki negeroch wanawun yetefetrnibetin endihum yebetekiristiyanachinin guday eyesatin new
  egna sile organ mezemerina alemezemer enikerakeralen leloch...

  ReplyDelete
 2. ፅሁፉ ጥሩ ነው ::ተረፈ ነኝ ብለሃል የትኛው ተረፈ ሽማግሌው ጴንጤ?

  ReplyDelete
  Replies
  1. egziabher yiqir yibelih pentew shimaglew min ametaw tsihufu astemari new aydelem
   Dn Terefe Worku eskawekut dires fitsum orthodosawi memihir new yetihitna na yetselot sew new
   Please dont the judge the book by its cover

   Delete
 3. ስለ ኢየሱስ ሰበኩ

  ReplyDelete
 4. አሜን! ጌታ ጸጋዉን ያብዛልህ.......... እግዜአብሄር ይርዳን እና እኛም በማስተዋል ነገሮችን እንድንመረምር ይፍቀድልን............. ክርስትና ወንድሜ ከሚሰናከል እኔ ...... ብለን የራሳችንን የምንተዉበት የሂዎት ጉዞ እንጂ ብናደርገዉም ባናደርገዉም እርባና ለሌለዉ ነገር የራሳችንን ፍላጎት የምናከናዉንበት አይደለም! ጌታ ማስተዋሉን ያብዛልን!

  ReplyDelete
 5. ጥሩ ነገር አስቀምጠኸል ወቅቱ በሌሎች ቤተክርስቲያን በምትናወጥበት ሰዓት ይህን ጉዳይ ማንሳት ከወደቀችበት እንዳትነሳ ድንጋይ እንደመጫን ነው ለምን አባታችን የድርቁን የረሃቡን ጉዳይ አንስተው ከኛ የሚጠበቀው ይህ ነው ዕርዳታ ማድረግ አለብን ቢሉ ኖሮ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ይከተልዎት ነበር እባክዎ የቤተክርስቲያኗ ችግር ይህ አይደለም በውስጥም በውጪም ያላችሁ አባቶች አለመስማማት ነው የገንዘብ እና የምግብ ዕርዳታችሁ ይቅርብንና እናንተ ታረቁና ከዚህ ረሐብ ይታደጉን ።
  (ከደብረ ታቦር)

  ReplyDelete
 6. egeziagbehire yekere yeblachrhu

  ReplyDelete