Wednesday, February 24, 2016

“ቤተ ክርሰቲያናችን በቅኝ ግዛት ... በቅኝ ገዢዎች ተይዛለች፡፡” (ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አባ ማትያስ)
ከዲያቆን ኢሩባኖን ዘኢየሱስ
    ክፍል 1
 ቤተ ክርስቲያን በነጻነት ዘመን ከምትፈተንባቸው ዋና ነገሮች አንዱ አለማዊነት ነው፡፡ በመከራ ዘመን የነበረችው ቤተ ክርስቲያን ትልቁንና ዘላለማዊውን ተልዕኮዋን መቼም ሳትዘነጋ በጽናት የእውነትንና የመዳንን ወንጌል ሰብካለች፡፡ በሚያስደንቅ ሁኔታ ወንጌልን መስበኳ ብቻ ሳይሆን በሰማዕትነት ዘመኗ በጭካኔያቸውና በፍጹም አሳዳጅነታቸው የታወቁ መሪዎችንና ወታደሮችን ጭምር ፊታቸውን ወደክርስቶስ ዘወር እንዲያደርጉ በተጋድሎ አሳይታለች፡፡
    ታላቁ ቆስጠንጢኖስ ለቤተ ክርስቲያን “ነጻነትን” ሲሰጥ ቤተ ክርስቲያንን “ብቻዋን” ሊተዋት የወደደ አይመስልም፡፡ ከቤተ ክርስቲያን ጳጳሳት እኩል ሊሰማ እንዲችል መንገድን ለራሱ አበጀ፡፡ [i] ስለዚህም የጳጳሳት ጉባኤ በሚደረግበት “በማናቸውም ጊዜ” በሰብሳቢነት ወይም እንደ“የበላይ ጠባቂነት” መገኘትን “አዘወተረ”፡፡ ከፍ ሲልም ውግዘት እንዲሻር እስከማዘዝ ደረሰ፡፡ [ii] ይህ በቤተ ክርስቲያን ላይ የራሱ የሆነ አሉታዊ ተጽዕኖ አሳድሯል፡፡ ኬልቄዶናውያን “ጳጳሳት” በኋላ ዘመን “መለካውያን” [iii] ለመሆን ያበቃቸው ጅማሬው በታላቁ ቆስጠንጢኖስ ያቆጠቆጠው የቤተ ክርስቲያን ንጉሣዊ ጣልቃ ገብነት ሥር ሰዶ ፍሬ በማፍራቱ ምክንያት ነው ለማለት ያስደፍራል፡፡

     በታላቁ ቆስጠንጢኖስ በግልጥ የተጀመረው የቤተ ክርስቲያንና የቤተ መንግሥት “ሽርክና” ከዚያ በኋላ አድጎ የቤተ ክርስቲያንን ሃሳብ ለማስቀየር ይደረጉ የነበሩ ቤተ መንግሥታዊ ትንኮሳዎችና የሌሎችም ተጽዕኖዎች ነበሩበት፡፡ ቤተ መንግሥትና ቤተ ክርስቲያን ሲዋደዱ ካህኑ ፖለቲካ ፖለቲካ ፤ ካድሬው ደግሞ ዕጣን ዕጣን መሽተቱ አይቀሬ ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ጌታ ቶሎ ሳይመጣባት ንስሐ ካልገባች በቀር ቤተ ክርስቲያንን ከክርስቶስ እንደሚለያት ምንም ጥርጣሬ የለውም፡፡
    ለዘመናት ይህ ፈተና የቤተ ክርስቲያን ትልቁ ፈተና ሆኖ ከእኛ ዘመን ተሻግሯል፡፡ በአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ቤተ ክህነት ቤተ መንግሥትን እየመራች ብዙ ሺህ ዓመታትን አዝግማ ብትመጣም እንደቤተ እስራኤል (ሮሜ.10፥3) ቅርስና “ታሪክ” ከማትረፍ በቀር እምብዛም የሚያስመካ የሰዎች ሕይወት ላይ ሠርታለች ለማለት በቂ እማኝ መጥቀስ ያዳግታል፡፡  [iv]
    ቤተ ክርስቲያንን ሁለት መንገዶች እንዳልጠቀሟት ከመጽሐፍ ቅዱስና ከታሪክ ልንማር ይገባናል፡፡ እኒህም፦
1.     ለአንድ አገረ ስብከት አንድ ጳጳስ በመሾም ውጤታማ የሆነ መፍትሔ ይመጣል ማለት መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነትን መዘንጋት ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ለቤተ ክርስቲያን ጳጳስ ማለት በአንድ አገረ ስብከት ለሚፈጠር መንፈሳዊም ሆነ በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ለሚከሰት አስተዳደራዊ ችግር “የመጨረሻውን” ውሳኔ ሰጪ አካል ነው፡፡ በአትዮጲያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መዋቅራዊ አሠራር በጠቅላላ በአገር ቤት  ሃምሳ አህጉረ ስብከትና በውጪው ደግሞ አስር አህጉረ ስብከቶች አሉ፡፡ [v]ነገር ግን የኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጠቅላላ ያላት ጳጳሳት ቁጥር ብቻ ነው፡፡ ይህ በራሱ ሌላ ሁለት አደገኛ ችግሮችን አመንጭቷል፡፡
1.1    አንድ ባለሃብት ወይም ማኅበር ይሁን ቡድን ወይም ጎሳ ይሁን ብሔር ... የአንድን አገረ ስብከት ጳጳስ መግባባት ከቻለ ድቁናና ቅስና በግፍ ማሾም እንደሚችል በዘመናችን መታዘብ ችለናል፡፡ ይህን መንገድ በዋናነት በቤተ ክርስቲያን ዙርያ ስሙ ተደጋግሞ የሚጠራው ማኅበር ማኅበረ ቅዱሳን  የሚከተለው ስልት ነው፡፡
1.2. አህጉረ ስብከቱን ወይም ጳጳሱን የሚቀርቡት አድባራትና ምእመናን እንጂ በርቀት ያሉት እንኳን ችግራቸውን ጳጳሱን ለማየት  የማይታደሉ ሆኑ፡፡ ስለዚህ በብዙ አስተዳደር በደል ምክንያት ብዙ ምዕመናን ቤተ ክርስቲያኒቱን ጥለው ሊሄዱ ግድ ሆነ፡፡
    ወደመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ተመልሰን አንድ የእግዚአብሔር ቃል ክፍል ብናነሳ፦ “በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ።” (ሐዋ.20፥28) ይላል፡፡ በኤፌሶን ቤተ ክርስቲያን ብዙ ጳጳሳት እንደነበሩ ከቅዱስ ጳውሎስ ንግግር እናስተውላለን፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ እኒህን ሁሉ ጳጳሳት በአንድ ቦታ ብቻ ከመንፈስ ቅዱስ የተነሣ መሾሙ የጤና ነውን? ብንል፥ አዎ! እጅግ በጣም የጤና ነው፡፡ የእያንዳንዱን አማኝ መንፈሳዊ ጤንነት ለመጠበቅ መጋቢዎችና እረኞች በቅርብ ሊገኙ ግድ ነው፡፡ አስፍተን ካየን ሥነ ምግባርና መንፈሳዊ የጸጋ ወንጌል እውቀት የሌላቸውን ካህናትና ዲያቆናት ለማስተማርና ለመምከር ቅሩብ መሆኑ ስሜት ይሰጣል፡፡
2.    ቤተ ክርስቲያን በበትረ መስቀሏ የቤተ መንግሥትን በትረ መንግሥት መጨበጧ ደቀ መዛሙርትን በሕይወት ከማፍራት አንጻር አከሰራት እንጂ ምንም አልጠቀማትም፡፡ መኳንንት መሣፍንት “ከጳጳሳትና ከካህናት” ጋር በተጫጩበት በባለፈው ዘመን ታሪክ ከእጅግ በጣም ጥቂቶቹ በቀር እንኳን ወንጌል ሊሰብኩ በቃለ እግዚአብሔር ሲዘበትና ሲሳለቁ እንኳ መልስ ለመስጠት ያልደፈሩ ናቸው፡፡ ከዚህም አልፈው ነገሥታትና መኳንንት አብያተ ክርስቲያናትን እንዲህ አድርጉ ፤ እንዲህ ደግሞ አታድርጉ እያሉ ያዙ ፤ መመርያ ይሰጡ እንደነበር ታሪክ ሳያፍር ሳይፈራ በግልጥ ይነግረናል፡፡     [i]  አቡነ ጎርጎርዮስ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ በዓለም መድረክ በሚለው መጽሐፋቸው ታላቁ ቆስጠንጢኖስ የቤተ ክርስቲያን መብቶች በሕገ መንግሥቱ ላይ ያሰፈረበትን ምክንያት ሲገልጡ “ከልብ በመነጨ እምነትና ፍቅር እንጂ አንዳንድ የኋላ ሰዎች ይልቁንም አርዮሳውያን እንደሚተቹት ላገዛዝ እንዲመቸው አይደለም፡፡ የክርስቲያኖችንም ድጋፍ ለማግኘት አልነበረም፡፡ … ማንን ፈርቶ!”  ብለው፥ ጉባኤ ኒቂያን “ … ቤተ ክርስቲያን ጉባኤ ሠርታ ቀጥተኛውን የሃይማኖት ትምህርት ከሌላው ለይታ እንድታስታውቅ እንጂ እንዳትከፋፈል ጉባኤው እንዲሰበሰብ ጥረት ፤ በጉባኤውም ለተሰበሱት አባቶች ያሳየው ክርስቲያናዊ ጠባይና ትህትና” በማለት እጅግ አድንቀው ገልጠውታል፡፡ (ገጽ.46-47)
        [ii]  በሚገርም ሁኔታ አባ ጎርጎርዮስ “… አርዮስ በተጋዘ በሁለት ዓመቱ የቈስጠንጢኖስ እኅት በአርዮስ ደጋፊዎች በነአውሳብዮስ ዘኒቆዲሚያ ተለምና በሲኖዶስ የተወሰነው የአርዮስ ውግዘት እንዲፈታና ከተጋዘበትም እንዲመለስ ወንድሟን ማለደችው፡፡ በዚህ ጊዜ ቈስጠንጢኖስ አርዮስ ከተሰደደበት እንዲመለስ፥ እስክንድርያ እንዲሄድ፥ ከውግዘት እንዲፈታና ወደቤተ ክርስቲያን እንዲመለስ በቤተ ክርስቲያን የነበረውም የክህነት ሥልጣን እንዲመለስ አዘዘ ፤ …” በማለት አስቀምጠዋል፡፡ (ዝኒ ከማሁ ገጽ.117)  
      [iii] አቡነ ጎርጎርዮስ አሁንም “ጉባኤውን ያዘጋጁትም የቤተ መንግሥት ባለ ሥልጣኖችና የጦር አለቆች ናቸው፡፡ የጉባኤው ሊቃነ መናብርት የነበሩት የልዮን እንደራሴዎች የቁስጥንጥንያው ሊቀ ጳጳስ አናቶሊዮስና ሌሎችም የመንግሥት ሹማምንትና የጦር አለቆችም ነበሩበት፡፡” (ዝኒ ከማሁ ፤ ገጽ.152) በማለት አስቀምጠዋል፡፡
      [iv] ምናልባት ይህ ሁሉ ገዳም ፣ ካቴድራል ፣ አድባርና ደብር ባላት ቤተ ክርስቲያን፥ ይህን ያህል ጳጳሳት ፣ ቀሳውስት ፣ ዲያቆናት ፣ አማኞች ላሏት ቤተ ክርስቲያን ይህን ማለት ምን ማለት ነው? የሚል እንደማይጠፋ አምናለሁ፡፡ ግና ከዚህም አልፎ መጠየቅ ይቻላል፡፡ በቅዳሴው ፣ በየንግሱ ያለደወልና አዋጅ የሚወጣ የኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምዕመን እንደሆነ አውቃለሁ፡፡ ይህ ባሕላዊ ወደመሆን ያደላው የሃይማኖት ትውፊት በአማኙ ፍጹም መንፈሳዊ ሕይወት ላይ ያመጣው ተጽዕኖና የለወጠው ፤ ካለበት ልማዳዊና ድግግሞሻዊ የኃጢአት ሕይወት አጠራው? አነጻውን? ራሱን በእውነተኛ ንስሐ እንዲያይና ዘወትር መስቀሉን ተሸክሞ እንዲኖር ረዳው ወይ? የሚለውንና ሌሎችን ዋናና ዘላለማዊ የሕይወት ጥያቄዎች በተደጋጋሚ ብናነሳ በእግዚአብሔር ፊትና ከሕሊና ወቀሳ እንዲሁም በትውልድ ታሪክ ፊት ከመጠየቅ ያድናል ብዬ አስባለሁ፡፡
[v] አዋጅ ነጋሪ ፤ 7ኛ ዓመት ቁጥር 10 ፤ በሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ የተዘጋጀ ፤ በትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ የታተመ፡፡ ገጽ.31-32

ይቀጥላል

1 comment:

  1. gira yegebachihu......ande tekorkotry ande demo nekafi tihonalachihu yikir yibelachihu yaw yihen tarik mazabatun ketlachihubetal tigermalachihu......wulude Arios!!!

    ReplyDelete