Wednesday, March 30, 2016

“ሊቃናተ ኢታመጕጽ ተአዘዝ ከመ ዘለአቡከ” “ሽማግሌ የሆነውን አትገሥጸው፥ እርሱን ግን እንደ አባት . . . ለምነው።” (፩ጢሞ. ፭፥፩-፪)ከዘሩባቤል
ምሁራንንና አባቶችን የመስደብ አባዜ የተጠናወተው ዳንኤል ክብረት እጅግ ግብዝ እና በትዕቢት የተሞላ መሆኑን ሰሞኑን በፓትርያርኩ፣ በቅዱስ ሲኖዶስና በቤተ ክህነቱ በአጠቃላይም በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ በጻፈው ድፍረትና ጽርፈት የተሞላው ጽሑፉ ግልጽ አድርጓል፡፡ እርሱና አድናቂዎቹ ስድቡን ሕጋዊና የተፈቀደ ለማድረግ ሲሞክሩ ተስተውሏል፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ግን እንዲህ ያለው ስሕተት እንዳይፈጸም “ሽማግሌ የሆነውን አትገሥጸው፥ እርሱን ግን እንደ አባት . . . ለምነው።” ይላል፡፡ የማኅበረ ቅዱሳን" ፍሬ የሆነው ይህ ሰው ግን ይህን ቃል ተላልፎ በዚህ ርካሽና ቃለ ጽርፈትን በተመላ ጽሑፉ እግዚአብሔር የቤተ ክርስቲያኒቱ ርእስ አድርጎ ያስቀመጣቸውን ፓትርያርኩን ተሳድቧል፡፡ ፓትርያርኩን ብቻም አይደለም፤ እርሳቸው ርእስ ሆነው የሚመሩት ቅዱስ ሲኖዶስ አባላት የሆኑትን ሊቃነ ጳጳሳቱን ጭምር ነው፤ ሊቃነ ጳጳሳቱን ብቻም አይደለም፤ እነርሱ በሲኖዶስ የሚመሯትን ቤተ ክርስቲያን በአጠቃላይ ነው የተሳደበው፡፡ ይህን ሁሉ ያደረገው ግን በቤተ ክርስቲያኒቱ ስም እየነገደ ለማኅበሩ ሲል ነው፡፡  

ምናልባት የእኛ ስም በቀጥታ አልተነሣም ወይም እርሳቸውን እንጂ እኛን አልተሳደበም የሚል ጳጳስ ቢኖር ስሕተት ይፈጽማል፡፡ ቀድሞ እጅግ ይከበሩና እንደ ብርቅ ይታዩ የነበሩ ብፁዓን አበው ማኅበረ ቅዱሳን ከተነሣ ወዲህ በየጊዜው ሲሰደቡና ሲዋረዱ ማየት የተለመደ ሆኗል፡፡ በልዩ ልዩ ምክንያት ለማኅበሩ አጎብዳጅና ተገዢ የሆኑትን አንዳንድ ጳጳሳት “ብፁዕ ቅዱስ” እያለ ለእርሱ እኩይ ተግባር ተባባሪ ያልሆኑትን ደግሞ ማዋረዱን በከፍተኛ ሁኔታ ተያይዞታል፡፡ ይኸውና በግልጹም ሆነ በስውሩ አመራር ዘንድ የማይወደደውና በማኅበሩ አባላት ዘንድ ባለው ተሰሚነት ግን እንደ ዋና ሰው የሚታየው ዳንኤል ቅዱስ ፓትርያርኩን አንድ ተራ ሰው እንኳ ሊናገራቸው በማይደፍራቸው ተራ ቃላተ ጽርፈት በመሳደቡ ትልቅ ድፍረትና ቃለ ውግዘት እንዲተላለፍበት የሚያደርግ ጥፋት ነው የፈጸመው፡፡ የእርሱ ጥፋት ብቻ ሳይሆን ብዙዎቹ ተከታዮቹ ጭምር ይህን አሳፋሪ ድርጊቱን ከማውገዝ ይልቅ በማድነቅ “ጀግናችን በርታ” እያሉ አስተያየት መስጠታቸው ማኅበረ ቅዱሳን ያፈራው ትውልድ ለቤተ ክርስቲያን ትልቅ ጠንቅ መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡
ዳንኤል ከአሁኑም ሆነ ቀደም ካለው የማኅበሩ ግልጽ አመራር ጋር እንደማይዋደድና ጠበኛ እንደ ሆነ የሚታወቅ ነው፡፡ በተለይ አሁን ያለው አመራር እርሱን እንደ ትልቅ ሥጋት ያየዋል፡፡ ከስውር አመራሩ ጋርማ ጠብ ውስጥ ከገባ ቆየ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ራሱን በልዩ ልዩ መንገድ በማስተዋወቅ ማኅበረ ቅዱሳን ማለት ዳንኤል ክብረት እስኪመስል ድረስ ማኅበሩን ሸፍኗል የሚል ነው፡፡ ከማኅበሩ ሰዎች ገንኖ የወጣው እርሱ ስለሆነም ነው፡፡ እርሱም አመራሩን ባይወድም ለማኅበሩ ያለውን ፍቅር ግን እንዲህ ባለው ክፉ ቀን በተቆርቋሪነት መንፈስ መግለጹ አልቀረም፡፡ ማኅበሩን በተሳሳተ አቋሙና አካሄዱ ሲተች ይቆይና ማኅበሩ ላይ ክፉ ቀን ሲመጣ ግን ማኅበሩን የመከላከል ሥራ ይሠራል፡፡ ይህም በአንድ ወገን ለእርሱ ሳያውቅ አዋቂ ያሰኘውና ዝናን ያተረፈለት በማኅበሩ ውስጥ ጎልቶ መውጣቱ ስለሆነ ድንገት ማኅበሩ አንድ ነገር ቢሆን የእርሱም ዝና አብሮ ሊከስም እንደሚችል ስለሚያስብ ይመስለኛል፡፡ ስለዚህ እርሱ ለጻፈው ግብዝነትንና ቃላተ ጽርፈትን ለተመላው፣ በሐሰት መረጃ ላይ ለተመሠረተው ጽሑፉ ምላሽ ለመስጠት እሞክራለሁ፡፡ ለዛሬው ለጽሑፉ ከሰጠው ርእስ እጀምራለሁ፡፡

Monday, March 28, 2016

ዘማሪ እንግዳ ወርቅ በቀለ ታቦት ሲሸጥ እጅ ከፍንጅ ተያዘከመጀመሪያዎቹ የባህታዊ ገብረ መስቀል ተከታዮች አንዱ የነበረውና በኋላ ላይ ስለማርያም ዘማሪ ሆኖ የተገለጠው እንግዳ ወርቅ በቀለ ሰሞኑን ታቦት ሲሸጥ እጅ ከፍንጅ ተይዞ መታሰሩ ተሰማ፡፡ እንግዳ ወርቅ ፀረ ወንጌል አቋም ያለው በመሆኑ በሚያወጣቸው የመዝሙር ካሴቶች 8 የማርያም 2 የክርስቶስን ብቻ በመዘመር ይታወቃል፡፡ ከዚህ የተነሣ “ኦንሊ ማርያም” እየተባለ ነው የሚጠራው፡፡ በቀጥታ ለእግዚአብሔር የተነገረውን በድፍረት ለድንግል ማርያም ሰጥቶ በመዘመሩ ነው ይህ ስም የተሰጠው፡፡ 

በተለይ “ቆይቼ እግዚአብሔርን ደጅ ጠናሁት” የሚለውን የመዝሙረ ዳዊት ክፍል “ደጅ ጠናሁ ቆይቼ ኪዳነ ምህረትን” ብሎ መዘመሩ ብዙ የቤተክርስቲያን ሊቃውንትን አሳዝኗል፡፡ በተጨማሪም “በእስራቴ አላፍርም እኔ የማርያም ነኝ ሮማዊ አይደለሁ ፍጹም ክርስቲያን ነኝ” በማለት የክርስትና መሠረት የሆነውን የክርስቶስን ስፍራ በማርያም ተክቶ ዘመሯል፡፡ ሰው ክርስቲያን የሚሆነውና ክርስቲያን ተብሎ የሚጠራው በክርስቶስ እንጂ በማርያም አይደለም፡፡ “በወልድ ውሉድ፣ በክርስቶስ ክርስቲያን” መሰኘታችን የታወቀ የተረዳ የክርስትና ትምህርት ነው፡፡ እንግዳ ወርቅ ግን እውነትን እስከዚህ ድረስ እየለወጠ ሲዘምርና ክሕደትና ኑፋቄን ሲያቀነቅን ቤተክርስቲያን ድምጿ አለመሰማቱ ምን እየሠራች ነው አሰኝቷል፡፡ ለኑፋቄና ለክሕደት ትምህርት በሯ ምን ያህል ክፍት እንደሆነም የሚያሳይ ነው፡፡ 

Sunday, March 27, 2016

ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ ከዳላስ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን እንዲነሡ ተወሰነባቸው፤ እስከ ፋሲካ ሊቆዩ ይችላሉ።በእውነት ተናጋሪነታቸው ተወዳዳሪ የማይገኝላቸው አባት ናቸው አቡነ ዮሐንስ። በዚህ ክፉ ዘመን እንዲህ ዓይነት ለእግዚአብሔር የተሰጠ ሰው ማግኘት ከባድ ነው። እኛ ኢትዮጵያውያን እግዚአብሔርን ለማወቅ ብቻ ሳይሆን የሚጠቅመንን ሰውም ለማወቅ የእግዚአብሔር ምሪት ያስፈልገናል። ለእግዚአብሔር ከተሰጠ ሰው በቀር ማን ሊጠቅመን ይቻላል? አቡነ ዮሐንስ ከልጅነታቸው ጀምሮ ሰይጣን ሲያሳድዳቸው የኖሩ ሰው መሆናቸውን ያገኘነው መረጃ ያሳያል። ሰይጣን ያልተቀባውን አያሳድድም ሰማያዊ መዓዛ ሲሸተው ምንጊዜም ፈተናውን አያቋርጥም አቡነ ዮሐንስ ለእግዚአብሔር መንግሥት ሥራ ከተጠሩ ጀምሮ በስደት ላይ ናቸው። ስደተኞች እናርፋለን ብለው ወደሚሰደዱባት አሜሪካ ሄደው ያላረፉ ቢኖሩ አቡነ ዮሐንስ ናቸው። አቡነ ዮሐንስ እውነትን ማወቅና መናገር ብቻ ሳይሆን እውነትንም ለመኖር የሚታገሉ በመሆናቸው መሰደድ እጣ ፈንታቸው ሆኗል። ከሲያትል ቅዱስ ገብርኤል በስደት ወደ ዳላስ ቢሄዱም አሁንም ስደት ገጥሟቸዋል።
ያሳዳጅነቱን ሚና እየተጫወተ ያለው "እርስዎን ያገኘሁበት ቀን የተረገመ ይሁን” ሲል እግዚአብሔር የሰጠውን መልካም ቀን የረገመው የዳላሱ ዲያቆን አንዱ ዓለም (አሁን ቄስ ሆኗል) ነው። የቤተ ክርስቲያንን ሰዎች በማሳደድ አቻ አይገኝለትም ይላሉ የሚያውቁት ሰዎች። ከናዝሬት ቅድስት ማርያም ከማህበረ ቅዱሳን ጋር በማበር የሰንበት ተማሪዎችን ከቤተ ክርስቲያን እንዲፈልሱ አድርጓል። የጎፋ ገብርኤል ሰንበት ተማሪዎችን ለማሳዳድ ከማህበረ ቅዱሳን ተመድቦ አስፈጻሚ የነበረው ይህ ሰው ነው። ከቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ከ10 የማያንሱ ደቀ መዛሙርትን እንዲሰደዱ አድርጓል።

Friday, March 25, 2016

ቀሲስ የ“ክብረት ልጅ”፥ ምነው በስድብ ቃል በጣም ጮኸ?!ምንጭ፦ የአቤኔዘር ተክሉ ገጽ http://abenezerteklu.blogspot.com/
የክብረት ልጅ እይታዎቹን በሚያቀርብበት ብሎጉ፥ “ፓትርያርኩ፦ ለኢትዮጲያ የደኅንነት ፣ ለምእመናን የድኅነት ሥጋት” በሚል አንድ ጽሁፍ፥ ዛሬ አስነብቦ ድንገት ያየ ሰው ጠቆመኝና ወደጡመራው መድረኩ ገብቼ አነበብኩት፡፡ ዳንኤል በዚህ ጽሁፉ “100% ማኅበረ ቅዱሳን ሊያዘጋጀው ከጫፍ የደረሰውን ዐውደ ርእይ የከለከሉት ፤ ያስከለከሉት ፓትርያርኩ ናቸው”፥ ብሎ ደምድሞ አስቀምጦታል፡፡ የዐውደ ርእዩ ባለቤት ማኅበረ ቅዱሳን ደግሞ፥ በዋናው ጸሐፊው አቶ ተስፋዬ ቢኾነኝ በኩል ትላንት ማምሻውን ለጋዜጠኞች በሰጠው ጋዜጣዊ “መግለጫ”፥ “ለመታገዱ ፓትርያርኩ እንደሌሉበትና በመንግሥት አካላት መመሪያ መታገዱን”ይፋዊ መግለጫ ሰጥቷል፡፡ 

ዳንኤል ፓትርያርኩን ከሰይጣን እኩል ነበር የሳላቸው ፤ “... ፓትርያርክ ማለት በግሪክ “ታላቅ አባት” ማለት ነው፡፡ የታላቅ አባት ተግባር የልጆቹን ሥራ ማፍረስ አይደለም ፤ ለዚህማ አባት አያስፈልግም ሰይጣን እንጂ፤ ...” በማለት፡፡ እንደከዚህ ቀደም ልማዱ ዳንኤል ሌሎች ማስጮኺያዎችንም በዚህ ጽሁፍ ለማካተት ጥሯል፡፡ አዳዲስ ስድቦችንም ለፓትርያርኩ እንደእጅ መንሻ አቅርቦላቸዋል፡፡

Wednesday, March 23, 2016

ሰበር ዜና - ማኅበረ ቅዱሳን በቤተ ክርስቲያን ስም ሊነግድበትና ሊያትርፍበት አስቦ ያዘጋጀው ዐውደ ርእይ በ11ኛው ሰዓት ላይ ታገደበትበሕገ ወጥ መንገድ መጓዙን የቀጠለውና ቤተክርስቲያንንና ዕሴቶቿን ማትረፊያ አድርጎ እየተጠቀመባት ያለው ማኅበረ ቅዱሳን ለቤተክርስቲያን ሳይሆን ለማኅበሩና ለግል ጥቅማቸው በቆሙ አንዳንድ ጥቅመኛ ጳጳሳት በመደገፍ ፈቃድ ጠይቆበት የነበረው ዐውደ ርእይ በ11ኛው ሰዓት ላይ ዛሬ መታገዱ ተሰማ፡፡ ማኅበሩ የቅዱስ ፓትርያርኩን መመሪያ ላለመቀበል ወስኖ በትዕቢትና በማንአለብኝነት እየተንቀሳቀሰ ባለበት በዚህ ወቅት ዓውደ ርእዩ ሊታገድ እንደሚችል የብዙዎች ግምት ነበር፡፡ እንደተጠበቀውም አውደ ርእዩን ማካሄድ እንደማይችል ከኤግዚቢሽን ማእከል የተጻፈለት ደብዳቤ ጠቁሟል፡፡ የደብዳቤው ሙሉ ቃል እነሆ

Tuesday, March 22, 2016

በኦሮሚያ በብዙ ሥፍራ ተከስቶ የነበረው ግጭት ዓላማው ምን ነበር? ምንስ አስተዋልንበት? (የጃዋር መሐመድ ኦሮሞ - እስላማዊ ፍሬዎች)


Read in PDF
ከዲያቆን ሞቲ
  እግዚአብሔር አምላክ ሰውን ሲፈጥረው ከነሙሉ መብቱ ነው፡፡ አምላካችን እሱን እንከተል ዘንድ እንኳ ማንኛችንንም አያስገድደንም፡፡ ማመን ወይም አለማመን ሙሉ በሙሉ ለኛ የተተወ ነገር ነው፡፡ በነጻነት እንኖር ዘንድ ነው ክርስቶስ ኢየሱስ ነጻ ያወጣን፡፡ የሰው ልጅ ነጻ መብቱን ተጠቅሞ ሌላውን እስካልጎደሰበት ድረስ እምነቱን እና አስተሳሰቡን ባልተገደቡ መልኩ ተግባራዊ የማድረግ መብት አለው፡፡ ከዚህ የማይገደብ መብት በመነሳትም ሰሞኑን በአሮሚያ የተነሳውን ተቃውሞ ለመምርምር እንሞክራለን፡፡
በኦሮሚያ የተነሳው ተቃውሞ ዝም ብሎ የልጆች ጨዋታ አድርጎ ማሰብ ተገቢ አይደለም፡፡ የተነሳው ተቃውሞ መሰረት ያለውና በአስተዳደርና በሌሎች ጉዳዩች የሚደርስበትን በደል በአዲስ አበባ የማስፋፊያ ፕላን ጋር አያይዞ የተቃወመበት እንቅስቃሴ ነው፡፡ ህዝብ ተበደልኩ ሲል አልተበደልክም ማለት አይቻልም፡፡ በደሉን መስማትና ትክክለኛ የመፍትሔ እንቅስቃሴ ማድረግ በመንግስት በኩል የሚጠበቅ ነበር፡፡ ነገር ግን የመብት ጥያቄውን በመቃወም የወሰደው የሀይል እርምጃ በምንም መልኩ ተቃባይነት የሌለውና የሚያሳዝን ነው፡፡ በተነሳው ተቃውሞ የሰው ህይወት ጠፍቷል፡፡ በጣም በጣም ያሳዝናል፡፡ ሰዎች ከመኖሪያ ቀዬያቸው ተፈናቅለዋል፡፡ ጉዳዩ የማይመለከታቸው ሰዎች ሀብትና ንብረት ተቃጥሎዋል፡፡ ይህም ያሳዝናል፡፡


ችግሩ በረድ ቢልም ጠፍቷል ግን ማለት አይቻልም፡፡ የሚቀለው ተዳፍኗል ቢባል ነው፡፡ መንግስት አሁንም ነገሩን ቸላ ሳይል ለኦሮሚያ ህዝብ የፍትህ የመልካም አስተዳደርና የመብት ጥያቄ አፋጣኝ ምላሽ መስጠት ይኖርበታል፡፡
በርግጥ የነገሮች አካሄድ ሙሉ በሙሉ ትክክል ናቸው ማለት አይቻልም፡፡ በመንግስት በኩል የተወሰደው እርምጃ አሁንም ከተለመደው ስህተቱ ምንም ያለመማሩን የሚያሳይ ነው፡፡ በህዝቡም በኩል ለምሳሌ በኡመያ አካባቢ የተደረገው የሌላ ብሔር ሰዎችን የማባረር እንቅስቃሴ ባይሆን ጥሩ ነበር፡፡ የአበባ እርሻን እና የችግሩ አካል ያልሆኑትን የትራንስፖርት መኪኖችን ማቃጠልም ተገቢ አይደለም፡፡ ህዝብ በጅምላ ሲወጣ ከሚጫሩ ስሜታዊነቶች በመነሳት ተገቢ ያልሆነ እንቅስቃሴ መደረጉ የሚጠበቅ ነው፡፡ እንኳን በኢትዮጵያ ሥር የሰደደ የዲሞክራሲ ባህል አላቸው በሚባሉት በነ አሜሪካ እንኳን ህዝብ ለተቃውሞ ሲወጣ ከስሜታዊነቶች ጋር ተያይዘው የሚፈጸሙ ስህተቶች አይጠፉም፡፡
ህዝቡ አሁንም ጥያቄ አለው መልስም ይፈልጋል፡፡ መንግስትም በተለይም ከመልካም አስተዳደር ጋር ተያይዞ በመላው ሀገሪቱ እየተነሳበትን ያለውን ተቃውሞ ከግምት በማስገባት በአስቸኳይ የማስተካከል እርምጃ መውሰድ ይኖርበታል፡፡ የኦሮሞ ህዝብም ጥያቆዎቹ ተመልሰውለት ኢትዮጵያዊነቱን አምኖበትና እንዲኖር አስፈላጊው ሁሉ ሊደረግለት ይገባል፡

Monday, March 21, 2016

የአፋን አሮሞ የቅዳሴ መጽሐፍ መመረቅ የቤተክርስቲያን ተሀድሶ አንዱ መገለጫ ነው።ግእዝን የአምልኮዋ ቋንቋ አድርጋ ለብዙ ምእት ዓመታት ስትጠቀምበት የኖረችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በአንዳንዶች ኋላ ቀር አስተሳሰብና ከዘመኑ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር መራመድን በመፍራት ወይም ሃይማኖት የመቀየር ያህል በመቁጠር ከግእዝ ውጪ ሌላውን ቋንቋ ለአምልኮ መፈጸሚያነት መጠቀም የማይቻልባቸው በርካታ ምእት ዓመታት አልፈዋል፡፡ ዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስ ግእዝን ቸል እያሉ አማርኛን ያበረታቱ የነበረ ቢሆንም ቤተክህነቱ ግን በሥርአተ አምልኮት ላይ አማርኛን መጠቀም የጀመረው በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግስት ነው ማለት ይቻላል፡፡ እርሳቸውና በዘመናቸው የነበሩት ታላላቅ የቤተክርስቲያን አባቶች የዘመኑን ተጨባጭ ሁኔታ በማየት የግእዝ መጻሕፍት ወደ አማርኛ እንዲመለሱ በማድረግ ስርአተ አምልኮት ሕዝቡ በሚሰማው ቋንቋም እንዲፈጸም በማድረጉ በኩል ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳበረከቱ ይታወቃል፡፡ እነሆ አሁን ደግሞ መጽሐፈ ቅዳሴ ወደ ኦሮምኛ ተተርጉሞ መቅረቡ በጣም የዘገየ ቢሆንም እንኳን እጅግ አስደሳች ዜና ነው፡፡ 

ከሀገራችን ብሔር ብሔረሰቦች በርካታ የህዝብ ቁጥር ያለው የኦሮሞ ህዝብ የቅዳሴ መጽሐፍን ለመጀመሪያ ጊዜ በቋንቋ ሊጠቀምበት መሆኑ በእርግጥም አስደሳች ዜና ነው። ሰው በአፍ መፍቻ ቋንቋው የወንጌልን እውነት እንዲረዳና አምላኩን እንዲያመልክ መርዳት አንዱና ወሳኙ የወንጌል ተልዕኮን መፈጸሚያ መንገድ መሆኑ ግልጽ ነው።


ቤተክርስቲያኒቱ ላለፉት 10 ዓመታት ስታዘገጀው የነበረው የቅዳሴ መጽሐፍ ባለፈው ቅዳሜ ቅዱስ ፓትርያርኩ በተገኙበት በኢሌሌ ሆቴል ተመርቋል። የቅዳሴው መጽሐፍ በግዕዝና በኦሮምኛ የተዘጋጀ ሲሆን ኦሮምኛው ቁቤንና የሳባን ፊደል ያካተተ ነው። መጽሐፉ ባለ 516 ገጽ ሲሆን በምረቃው ዕለት የነበሩና በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ለተለያየ መንፈሳዊ ትምህርት ሲሄዱ በአማርኛ በትግርኛ ቋንቋ ሲቀደስ መንፈሳዊ ቅናትና ቁጭት ይሰማቸው የነበሩ አንዳንድ የኦሮሞ ተወላጅ የቤተ ክርስቲያኒቱ አገልጋዮች የቅዳሴው መጽሐፍ የኦሮምኛ ትርጉምን በማየታቸው ደስታቸውን በታላቅ ስሜት ሲገልጹ ነበር።

Sunday, March 20, 2016

ደስታ ጌታሁን በቀሰጠው የመዝሙር መጽሐፍ ምክንያት ታሰረየሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ያሳተመውን መጽሐፍ ደግሞ በስሙ ማኅበረ ቅዱሳን ያሳተመለት ደስታ ጌታሁን ተከሰሰ፣ በህግ ቁጥጥር ስርም ውሏል፡፡ ከዚህ ቀደም “የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ … በተለያዩ ደራስያን የተደረሱ ዝማሬዎችን በመሰብሰብ የሰንበት ት/ቤቶች እንዲጠቀሙበት በሚል ያሳተመውን መጽሐፍ ማኅበረ ቅዱሳን ዲ/ን ደስታ ጌታሁን በተባለው ቀሳጤ ድርሰት ስም ማሳተሙ ውዝግብ ማስነሣቱን” ዘግበን ነበር፡፡ ውዝግቡ ቀጥሎ የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ የመዝሙር መጽሐፉን በስሙ ባሳተመው በዲ/ን ደስታ ጌታሁን ላይ ክስ መሥርቶ ደስታ በሕግ ቁጥጥር ሥር መዋሉን፣ መታሰሩንና ፍርድ ቤት መቅረቡን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ደስታ ፍርድ ቤት ቀርቦ የዋስ መብት የጠየቀ ቢሆንም ከእርሱ ጋር ተጨማሪ የሚፈለጉ አካላት በመኖራቸው ቀነ ቀጠሮ ተጠይቆበት በማረፊያ ቤት እንዲቆይ ተደርጎ ጉዳዩ ለመጪው እሮብ ተቀጥሯል፡፡

ደስታ ከዚህ ቀደም የተለያዩ ወንጀሎችን ፈጽሞ ተከሶ የነበረ ሲሆን ከእነዚህ መካከል አንዱ የመጋቤ ሐዲስ በጋሻውን ስም በማጥፋት ባጻፋትና በስሙ ባሳተማት ትንሽ መጽሐፍ ምክንያት ተከሶ በሁለት ዓመት ገደብ መለቀቁ ይታወሳል፡፡ ቤተክህነት ውስጥ ከተቀጠረ ጀምሮ ደስታ የልደት፣ የጋብቻ ሰርተፊኬት በመሸጥ፣ ከመዝገብ ቤት ደግሞ ደብዳቤዎችን ቀድሞ ለደጀ ሰላም አሁን ደግሞ ለሀራ ብሎጎች በመስጠት የሚታወቅ ነው፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን በዚህ ሰው እጅ በርካታ ወንጀሎችን የሰራ ሲሆን አንድም ቀን ግን እንዲማርና እንዲሻሻል ያደረገበት ሁኔታ የለም፡፡ ምክንያቱም ከተማረና ከተሻሻለ ነገሮችን በአእምሮ ማከናወን ይጀምራልና ለማቅ ገንዘብ አይሆንም፡፡ ስለዚህ አሁን ደግሞ ማኅበሩ ተባባሪው ሆኖ እርሱ ሰርቆ በስሙ ባሳተመው የመዝሙር መጽሐፍ ምክንያት ለእስር ተዳረገ፡፡

Friday, March 18, 2016

ማኅበረ ቅዱሳን ዳጎስ ያለ ገቢ ለማሰባሰብ አቅዶ ያዘጋጀው አውደ ርእይ እና አንድምታውከተቋቋመበት ዓላማ ውጪ እየተንቀሳቀሰና የቤተክርስቲያንን መዋቅራዊ አሠራር እየተፈታተነ የሚገኘው ማኅበረ ቅዱሳን ከመቼውም ጊዜ ይልቅ ለቤተክርስቲያን ህልውና አስጊ በሆነበት ወቅት ላይ እንገኛለን፡፡ ለሕገ ወጥ እንቅስቃሴው መገለጫ ከሆኑት የማኅበሩ ተግባራት መካከል አንዱ የቤተክርስቲያንን ሀብቶችና እሴቶች በመጠቀምና እነርሱን ወደቢዝነስ በመለወጥ ያለ ቤተክርስቲያን ፈቃድ በቤተክርስቲያን ስም የተለያዩ ገቢዎችን መሰብሰቡና ለራሱ ድብቅ ዓላማ ማዋሉ የሚጠቀስ ነው፡፡ ከመጋቢት 15-21/2008 ዓ.ም በአዲስ አበባ ኤግዚብሽን ማእከል ለማዘጋጀት ያሰበው አውደ ርእይ የዚህ ሕገወጥ ድርጊት አንዱ ማሳያ ነው፡፡
ማኅበሩ በዚህ ወቅት ይህን አውደ ርእይ ለምን አዘጋጀ? ለሚለው አሁን ካለበት ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር ከታየ ሁለት ትርፎችን አስቦ ነው ማለት ይቻላል፡፡ የመጀመሪያው ጠቀም ያለ ገንዘብ መሰብሰብ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በአውደ ርእዩ ሰበብነት ሰዎችን በቤተክህነቱ ይልቁንም በቅዱስ ፓትርያርኩ ላይ ማነሳሳት ነው፡፡ 

Wednesday, March 16, 2016

ማኅበረ ቅዱሳን ዲላ ላይ ያዘጋጀው የግንዛቤ ማሰጨበጫ እንዳይተላለፍ ታገደበአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በሩ እየተዘጋበት ያለው ማኅበረ ቅዱሳን ዕድሜውን ለማራዘምና ደጋፊዎቹን ለማብዛት እየሰራባት ያለውን ስለተሐድሶ ግንዛቤ አስጨብጣለሁ የሚለውን ስልቱን ወደ ክፍለ ሀገር በማዞር በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ተግባራዊ እያደረገ መሆኑ ሲታወቅ በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ደግሞ ተቃውሞ እየገጠመው መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ሰሞኑን በደቡብ ክልል በዲላ ከተማ በገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተክርስቲያን ከመጋቢት 2-4/2008 ዓ.ም አዘጋጅቶት የነበረው የግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራም በሰንበት ት/ቤቱ ተጋድሎ ሳይካሄድ ቀርቷል፡፡ ለግንዛቤ ማስጨበጫው ወደ ዲላ የሄዱት ፖለቲካና ሃይማኖትን እያጣቀሰ የሚንቀሳቀሰው የማቅ አባል ታደሰ ወርቁ እና ዓባይነህ ካሴ ሲሆኑ ኪነጥበብና ወርቅነሽ ተፈራ መዝሙር ለማቅረብ የተገኙ መሆናቸው ታውቋል፡፡

የግንዛቤ ማስጨባጨውን ያመቻቹት የደብሩ አስተዳዳሪ የሆኑት አባ ታዬ ሲሆኑ እኚህ አለቃ ከማቅ ጋር የተጠበቀ ግንኙነት ያላቸውና ማቅ በአርአያውና በአምሳሉ የቀረጻቸው ስለሆኑ በልማት ስም እየተንቀሳቀሱ ከሚገኝው ትርፍ በአካፋ ለራሳቸው እየዛቁ ለቤተክርስቲያን ግን በማንኪያ የሚያስገቡ አማሳኝ ናቸው፡፡ በማኅበረ ቅዱሳን ዘንድ ማቅን መደገፍ በሙስናም ሆነ በማንኛውም ወንጀል የማያስጠይቅ በጎ ስራ ተደርጎ ስለሚወሰድ አባ ታዬም ማቅን ተጠግተው የቤተክርስቲያንን ገንዘብ የሚበዘብዙ አማሳኝ ሆነዋል፡፡ በተጨማሪም ለማቅ ትልቅ ቦታ በመስጠት ከሰንበት ት/ቤት ጋር የሚጋጩ አለቃ ናቸው፡፡ በቤተ ክርስቲያን መዋቅር ውስጥ ያለን ሰንበት ት/ቤት አሳንሶ ማየትና ለማቅ ቦታ መስጠት በጥቅም ግንኙነት የሚመጣ መሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡ የአለቃውን አማሳኝነት የተገነዘቡት የደብሩ ሰንበት ተማሪዎችም አለቃው አማሳኝነታቸው ሳያንስ ከማቅ ጋር በመሞዳሞድ ከሕገ ቤተክርስቲያን ውጪ የግንዛቤ ማስጨበጫ በሚል የተዘጋጀውን መርሐ ግብር በመቃወም መርሀ ግብሩ አይካሄድም በማለት ከአለቃው ጋር ግጭት ውስጥ የገቡ ሲሆን አለቃውም በመጀመሪያው ቀን ሸሽተው ሄደዋል፡፡

Tuesday, March 15, 2016

ለምን መሬት መሬት ታያለህ?

ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል
March 3, 2016
የተደረገልን እኔና አንተ ከምናደርግለት በላይ ነው! ለምን መሬት መሬት ታያለህ?
የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በአሁን ሰዓት ስለምትገኝበት ገፅታ ለምስክርነት አልበቃም። መልካም - ለጊዜው ብዙ ርቄለሁ። ይህ መልዕክት በቀንና በሌሊት በመንፈሴ ሲመላለስ ግን ቢያንስ ስድስትና ሰባት ወራት ሆኖታል። የዚህ ጽሑፍ ዓላማ እንደሆነም ከመልዕክቱ ይዘት ለመረዳት እንደሚቻለው ግቡ ግልፅ ነው። ይኸውም፥ አንድ ሰው ቢሆንም ለዚያ ከወንጌል የተነሳ በመከራ ውስጥ የሚገኝ/የምትገኝ የእግዚአብሔር ባሪያ የእውነት ቃል ለማካፈል ተጻፈ።
መሪ ጥቅስ፥
እውነት እላችኋለሁ፥ ስለ እኔና ስለ ወንጌል ቤትን ወይም ወንድሞችን ወይም እኅቶችን ወይም አባትን ወይም እናትን ወይም ሚስትን ወይም ልጆችን ወይም እርሻን የተወ፥ አሁን በዚህ ዘመን ከስደት ጋር ቤቶችን ወንድሞችንና እኅቶችንም እናቶችንም ልጆችንም እርሻንም መቶ እጥፍ፥ በሚመጣውም ዓለም የዘላለም ሕይወት የማይቀበል ማንም የለም።” የማርቆስ ወንጌል 10፥ 29, 30
ለምን መሬት መሬት ታያለህ?
ወንድሜ ሆይ! እነሱ የአመፃና የክፋት ሰይጣንዊ አጀንዳቸውን በአማኞችና በቤተ ክርስቲያን ብሎም በሀገር ላይ ለመጫን ተደራጅተውና ቆርጠው ከተነሱ አንተ ደግሞ ከምን ጊዜ በላይ የእምነትን ጋሻ የማዳን ራስ ቁር የመንፈስም ሰይፍ ይዘህና አንስተህ፤ ወገብህን በእውነት ታጥቀህ፥ የጽድቅንም ጥሩር ለብሰህ መልካሙን ውጊያ የምትዋጋበት ሰዓቱ አሁን ነው።

Friday, March 11, 2016

“ቤተ ክርሰቲያናችን በቅኝ ግዛት ... በቅኝ ገዢዎች ተይዛለች፡፡” (ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አባ ማትያስ)

Read in PDF

ክፍል 2
የአለማዊ መሪዎችና የፖለቲካ ጉርብትና ጉዞ ቅን መንገድ ይመስላል እንጂ ለቤተ ክርስቲያን የሞት መንገድ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ዘወትር ሕብረቷ ሙሽሪት እንድትሆን ለሙሽራው ኢየሱስ ካጫትና እንድትሆንለትም ዘወትር ከሚያጠራት ከእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ጋር ብቻ ነው፡፡  በዚህ እውነት የሚስማማ ወገን፣ ሕዝብ፣ ነገድ ፣ ብሄር ሁሉ አካሏ ነው ፤ ይህን እውነት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የሚንድና የማይቀበል ግን በማናቸውም አይነት መልኩ ሊዛመዳት ሊቀራረባት ፈጽሞ አይችልም፡፡ 
    ማህበረ ቅዱሳን የሚባለው ማኅበር ቤተ ክርስቲያንን ለዳግመኛ ባርነት ከሚያጭበት መንገድ አንዱ  እንግዲህ ይህ ነው፡፡ ለዚህ ሃሳብ ማስገበርያነት የወንጌል ልብ የሌላቸውን ፤ ዓለማዊ ዕውቀትና ዝና ያላቸውን ጋዜጠኞች ፣ መሪዎች ፣ ነጋዴዎች ፣ የቤት እመቤቶች ፣ አርቲስቶች ፣ ዘፋኞች ፣ ደራሲዎች ፣ የጤና ባለሙያዎች ፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎችንና መምህራንን ፣ ለሕዝብና ለእውነት ያላደሉ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችንና ሌሎችንም ይጠቀማሉ፡፡

Wednesday, March 9, 2016

ችግርን በትክክል መረዳት የመፍትሔ ጅማሬ ነው
ከመምህር አዲስ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ  ቤተ ክርስቲያን ጥንታዊትና ሐዋርያዊት ቤተክርስቲያን ስትሆን በምድረ ኢትዮጵያ ቀዳሚትና ለአገሪቱ በርካታ ነገሮችን ያበረከተች ታላቅ ቤተክርስቲያን ነች፡፡ ይሁን እንጂ በተለያዩ ምክንያቶች የተመሠረተችበትን ዋናውን የወንጌል ተልእኮ በሚገባና የሚፈለገውን ያህል ስላልተወጣችና አባሎቿን በተገቢው ትምህርተ ወንጌል መያዝ ሳትችል በመቅረቷ ምእመናኖቿ ወደሌሎች እየፈለሱ የእርሷ ምእመናን ቁጥር ደግሞ እየተመናመነ መምጣቱ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በቤተክርስቲያኒቱ አባቶች አንደበት ጭምር እየተነገረ ይገኛል፡፡ እስካሁን ሲነገር የቆየው ግን ለምእመናን ፍልሰት ሌሎቹን የእምነት ተቋማት አሊያም ምእመናኑን ብቻ ተጠያቂ የሚያደርግ ምክንያት ነበር፡፡ አሁን አሁን ግን ለችግሩ ራስንም ተጠያቂ ማድረግ መጀመሩ ቤተክርስቲያኗ ችግሩን በመግለጥ መፍትሔ ለመፈለግ እየተዘጋጀች መሆኗን የሚያመለክት ፍንጭ እየሰጠ ነውና ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡

ከዚህ ቀደም ራስን ንጹሕ አድርጎ ሌሎችን ብቻ ችግር ፈጣሪ አድርጎ መውቀስ ችግሩን ከማባባስ ውጪ መፍትሔ አላመጣም፡፡ ስለዚህ የራስን ጉድለት እንደ አንድ ችግር ማየት መጀመሩ መፍትሔውን ለመፈለግ ወሳኝ መነሻ ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኦርቶዶክስ አማኞች ቁጥር እየቀነሰ መሄዱ ያሳሰባቸው የቤተክርስቲያኒቱ አባቶች ችግሩ የወንጌልን ተልእኮ በተገቢው መንገድና ዘመኑን በዋጀ ሁኔታ መፈጸም አለመቻላችን ነው እያሉ ነው፡፡ ስለዚህ አባቶች ቆም ብለን ማሰብ ካልጀመርንና አሠራራችንን ሳናሻሽል በዚሁ ከቀጠልን ባዶአችንን እንዳንቀር ያሰጋል ሲሉ ስጋታቸውን እስከ መግለጽ የደረሱበት ሁኔታ አለ፡፡ ይኸው የምእመናን ፍልሰት ሊቆም የሚችለው የወንጌልን ተልእኮ በተገቢውና ዘመኑን በዋጀ መንገድ መወጣት ሲቻል መሆኑን ታላላቅ የቤተክርስቲያኒቱ ሃላፊዎች መናገራቸው ለቤተክርስቲያኒቱ ችግር መፍትሔ ለመፈለግ ጅማሬ ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል፡፡

Monday, March 7, 2016

የማቅ የመልስ ደብዳቤ ፓትርያርኩን ሽቅብ የሚመለከት ወይስ ቍልቍል?          ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስ ናት! ክርስቶስ ደግሞ ለቤተ ክርስቲያን መሪዎችን ሾሟል (ኤፌ.4፥11) የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም ከእግዚአብሔር በተሾሙ አባቶችና መሪዎች ትወከላለች፡፡ በተለይ ቅዱስ ፓትርያርኩ ቤተ ክርስቲያኒቱን የመወከል ሥልጣን ከእግዚአብሔርም ከሕገ ቤተ ክርስቲያንም እንዳላቸው ግልጽ ነው፡፡

          በቤተ ክርስቲያናችን የመጨረሻው ውሳኔ ሰጪ አካል ቅዱስ ሲኖዶስ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ፓትርያርኩ የቋሚውም ሆነ የምልዐተ ጉባኤው ሲኖዶስ ሰብሳቢና መሪ በመሆናቸው ትልቁ ሥልጣንና ሚና ያለው በፓትርያርኩ እጅ ነው፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ ከፓትርያርኩ ውጪ በሌላ መሪ የሚመራና የሚሰበሰብ ቢሆን የፓትርያርኩ ሥልጣን ውሱን ይሆን ነበር፡፡

በዚህ ወቅት በቤተ ክርስቲያን ወቅታዊ ከሆኑ ጉዳዮች አንዱ ማኅበረ ቅዱሳን የሚባል ማኅበር በአደረጃጀት፣ በአሠራርና በአካሄዱ ላይ ባለበት ብልሽት ምክንያት በቤተ ክርስቲያን ሥር ባሉ ሌሎች ተቋማት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያመጣ ይህንንም እያጠናከረው በመሄዱ በማኅበሩ ጥቃት ከተከፈተባቸው መካከል አንዳንዶቹ ቅሬታቸውን ለቤተ ክርስቲያኒቱ የመጨረሻ የበላይ አካል ለሆኑት ለቅዱስ ሲኖዶስና ለቤተ ክርስቲያን መሪና ሰብሳቢ ለቅዱስ ፓትርያርኩ ማቅረባቸውን ተከትሎ ቤተ ክርስቲያኒቱ በፓትርያርኩ ፊርማ የተበደሉ የትምህርት ተቋማት ላቀረቡት አቤቱታ ምላሽ መሰጠታቸው ይታወሳል፡፡

Sunday, March 6, 2016

ማኅበረ ቅዱሳን በእጅ አዙር ያስጠራውና “ድንገተኛ” ተብሎ የተገለጸው የሲኖዶስ ስብሰባ የማቅን አጀንዳ ሳያስተናግድ ተበተነ፡፡

Read in PDF


ራሱ በጫረው እሳት ችግር ውስጥ የገባውና ከግንቦት ሲኖዶስ በፊት ሊወሰድበት የሚችል እርምጃን በመፍራት ደጋፊና የጥቅም ተጋሪዎቹን ጳጳሳት ይዞ ባልተለመደ ሁኔታ “ድንገተኛ” የተባለ ስብሰባ እንዲጠራለት ያደረገው ማኅበረ ቅዱሳን ያሰበው ሳይሳካ ድንገተኛ የተባለው ስብሰባ ተበትኗል፡፡ በማቅ መንደር የስብሰባው ሴራ ተጎንጉኖና ተሸርቦ የማቅ ደጋፊ በሆኑና፣ በጥቅምና ባለባቸው የሕይወት ድካም በተያዙ ጳጳሳት በኩል ተጠናክሮ በድንገት ለፓትርያርኩ የቀረበው የእንነጋገር ጉዳይ ድንገቴ ከመሆኑ የተነሣ ቅዱስ ፓትርያርኩ የዐቢይ ጾም መግቢያን አስመልከተው የተለመደውን ጋዜጣዊ መግለጫ ለመስጠት ተገኝተው ሳለ ከመግለጫው ፍጻሜ በኋላ በአባ ማቴዎስ በኩል የቀረበ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡
ማቅ ይህን ጊዜ ለስብሰባ የመረጠው የብፁዕ አቡነ ናትናኤል ዜና እረፍትን አስመልክቶ ጳጳሳት ለቀብራቸው ስለተሰበሰቡ ይህን አጋጣሚ በመጠቀም ጳጳሳቱ ወደየሀገረ ስብከታቸው ከመበተናቸውና ፓትርያርኩ ቀጣይ እርምጃ ከመውሰዳቸው በፊት ፓትርያርኩ ላይ አንዳች ጫና በማሳደር ማኅበረ ቅዱሳንን መሥመር ለማስያዝ የጀመሩትን ሕጋዊ ጉዞ ለማደናቀፍና ክፍፍል ለመፍጠር ነው ተብሏል፡፡ የማኅበሩ ልሳን የሆነው ሐራ ከዚህ ቀደም እንደዘገበው ፓትርያርኩ ማኅበረ ቅዱሳን ላይ በያዙት አቋም የተነሣ ፓትርያርኩን እስከ ግንቦት ሲኖዶስ ስብሰባ ድረስ ከሥልጣን እስከ ማውረድ የደረሰ ዕቅድ ይዞ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ፍንጭ ሰጥታለች፡፡ የአሁኑ በምስጢር ተይዞ በድንገት እንዲጠራ የተደረገው ስብሰባ የዚህ ሴራ አካል እንደ ሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡

Thursday, March 3, 2016

ያገር ያለህ ወይም የዳኛ ያለህ!!! /ለውይይት የቀረበ/


1/ መግቢያ
በድሮ ጊዜ ሰው በሰው ሲበደልና ፍትሕ ሲጓደል ‘ያገር ያለህ’ ወይም ‘የዳኛ ያለህ’ በማለት ይጮህ ነበር፤ ይህ ዓይነቱ የተበዳይ ጮኸትም ለትውልድ መርገም እንዳይሆን ተብሎ በአካባቢው በሚኖሩ እድሜና ልምድ ጠገብ ሺማግሌዎች ገላጋይነት/ዳኝነት የበደለ እንዲክስ የተበደለ ደግሞ እንዲካስ በማድረግ ጉዳዩ እልባት እንዲያገኝ ይደረግ ነበር፤ እኔም ዛሬ በዲሞክራሲ ስም በምድራችን ውስጥ እየሆነ ያለውን አጠቃላይ እንቅስቃሴ /በተለይ ባለውለታ በሆነችው በኦርቶዶክስ ቤ/ክ ውስጥ/ ቀረብ ብየ ስመለከት ይህ እውነተኛ የፍትህ ፈላጊዎች ያገር ያለህ ጩኸት ትዝ ብሎኝ ለኢትዮጵያውን በሙሉ ለውይይትና ለመፍትሄው ፍለጋ ጭምር የሽማግሌ ዳኞች ያለህ በማለት ጮኸቴን ላቀርብ ተገደድኩ።
መቸም ለተወሰኑ ዓመታት ከአገሩ ራቅ ብሎ ለኖረ ኢትዮጵያዊ የአዲስ አባባ ገጽታ ቀየር እንደምትልበት ይታመናል፤ በርካታ ሕንጻዎችና መንገዶች ተሠርተዋል፤ ባቡርም ተጀምሮ ሕዝቡ እየተጠቀመበት መሆኑን በግልጽ ማየት ይቻላል፤ ለራሴ ሕሊና ታማኝ መሆን ስላለብኝ የሚታዩትን መልካም ነገሮች እሰየው በማለት፣ ደስ የማይሉትንና ደካማ የሆኑትን ደግሞ ለእርምት በግልጽነት ብጠቁም ሰውነቱን የሸጠ ካልሆነ በስተቀር ቅር የሚሰኝ እውነተኛ ሰው የሚኖር አይመስለኝም።

Tuesday, March 1, 2016

በዕውቀቱ ሥዩም፡- የንግሥተ ሳባ ጥበብን ፍለጋ ጉዞዋ መነሻውም ኾነ መድረሻው የአልጋ ላይ የፍቅር ጨዋታ/የወሲብ ረኻብ አልነበረም!!በዲ/ን ኒቆዲሞስ  ~nikodimos.wise7@gmail.com
(ምንጭ፡- ከሰደንቅ ሳምንታዊ ጋዜጣ መጠነኛ ማስተካከያ ተደርጎበት የተወሰደ፡፡)

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪ እያለን ነበር በመጀመሪያ ጊዜ ከበዕውቀቱ ሥራዎች ጋር የተዋዋኩት፡፡ በወቅቱ በዕውቀቱ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ዋናው ካምፓስ የሥነ ልቡና/Pyschology ተማሪ እያለ ‹በራረሪ ቅጠሎች› በሚል ርዕስ ከደርዘን የሚልቁ ጣፋጭና አከራካሪ ወጎቹንና ትረካዎቹን በአንድ ላይ ጠርዞ ለአንባብያን ያቀረባቸው መጣጥፎቹ በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅነትንና ተደናቂነትን እንዲያተረፍ አድርጎት እንደነበር አይዘነጋም፡፡
በዚህ መጽሐፉ በዕውቀቱ በተለይ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች መካከል ያለውን የዘር ሽኩቻ፣ የርዕዮተ ዓለም ቅኝት፣ የዘመኑን የብሔር ፖለቲካዊ ቀውስ፣ ተማሪዎች ዶርም ያለውን አስቂኝ፣ አዝናኝና አሳዛኝ ገጠመኞችን- እኛ ተማሪዎችን ራሳችንን በቅጡ እንድናይና ቆም ብለን እንድጠይቅ የሚያደርጉን መረርና ከረር ያሉ እውነቶችን ከቀልድና ከተርብ፣ ከአሽሙርና ከአግቦ ጋር እያዋዛና እያዛነቀ የተረከበት መጣጥፎቹ አሁንም ድረስ በብዙዎች በናፍቆት ተደጋግመው የሚነበቡ ናቸው፡፡