Thursday, March 3, 2016

ያገር ያለህ ወይም የዳኛ ያለህ!!! /ለውይይት የቀረበ/


1/ መግቢያ
በድሮ ጊዜ ሰው በሰው ሲበደልና ፍትሕ ሲጓደል ‘ያገር ያለህ’ ወይም ‘የዳኛ ያለህ’ በማለት ይጮህ ነበር፤ ይህ ዓይነቱ የተበዳይ ጮኸትም ለትውልድ መርገም እንዳይሆን ተብሎ በአካባቢው በሚኖሩ እድሜና ልምድ ጠገብ ሺማግሌዎች ገላጋይነት/ዳኝነት የበደለ እንዲክስ የተበደለ ደግሞ እንዲካስ በማድረግ ጉዳዩ እልባት እንዲያገኝ ይደረግ ነበር፤ እኔም ዛሬ በዲሞክራሲ ስም በምድራችን ውስጥ እየሆነ ያለውን አጠቃላይ እንቅስቃሴ /በተለይ ባለውለታ በሆነችው በኦርቶዶክስ ቤ/ክ ውስጥ/ ቀረብ ብየ ስመለከት ይህ እውነተኛ የፍትህ ፈላጊዎች ያገር ያለህ ጩኸት ትዝ ብሎኝ ለኢትዮጵያውን በሙሉ ለውይይትና ለመፍትሄው ፍለጋ ጭምር የሽማግሌ ዳኞች ያለህ በማለት ጮኸቴን ላቀርብ ተገደድኩ።
መቸም ለተወሰኑ ዓመታት ከአገሩ ራቅ ብሎ ለኖረ ኢትዮጵያዊ የአዲስ አባባ ገጽታ ቀየር እንደምትልበት ይታመናል፤ በርካታ ሕንጻዎችና መንገዶች ተሠርተዋል፤ ባቡርም ተጀምሮ ሕዝቡ እየተጠቀመበት መሆኑን በግልጽ ማየት ይቻላል፤ ለራሴ ሕሊና ታማኝ መሆን ስላለብኝ የሚታዩትን መልካም ነገሮች እሰየው በማለት፣ ደስ የማይሉትንና ደካማ የሆኑትን ደግሞ ለእርምት በግልጽነት ብጠቁም ሰውነቱን የሸጠ ካልሆነ በስተቀር ቅር የሚሰኝ እውነተኛ ሰው የሚኖር አይመስለኝም።

እዚህ ላይ የሕንጻዎችና የመንገዶች መገንባት መልካም ቢሆንም፤ በራሳቸው ግን ያንድ አገር እድገት ዋና መስፈርቶች ናቸው ብሎ መውሰዱ ተገቢ አይመስለኝም፤ ሕንጻ ያለሰው ከንቱ የድንጋይ ክምር ብቻ ስለሚሆን! በሌላ መልኩ ደግሞ አብዛኛው ሕዝብ በኑሮ ችግር እየተጠበሰና ያገሪቱ ሃብት በጥቂቶች እጅ ውስጥ ሆኖ እያለ ኢኮኖሚስቶች በነፍስ ወከፍ የገቢ ስሌት ተመስርተው አድገናል ማለታቸው በሕዝቡ አጠቃላይ የኑሮ ምጥ ላይ የሚታየውን የህይወት ማቃሰት በግልጽ መካድ ነው የሚሆነው፤ የተመጣጠነ የሃብት ክፍፍል በሌለበት አገር ውስጥ ይህ ዓይነቱ የሂሳብ ቀመር እንዴት ሆኖ እውነተኛ ሚዛን እንደሚሆን ፈጽሞ አይገባኝም።
ማየት ከመስማት የበለጠ ጥሩ መረጃ እንደሆነ ይታመናል፤ በመሆኑም አገራችን ኢትዮጵያ ምን እየሆነችና ወዴት እየተጓዘች እንደሆነ ከዚህ በፊት በጆሮዬ የሰማሁትን ዛሬ በዓይኔ አይቼ ለራሴ ህሊና ያገኘሁትን መረዳት በሚከተሉት ርእሶች ላይ ያለኝን ስጋት በትንሹ ላካፍል፡
1. ፖለቲካውና ኢኮኖሚው በሕዝቡ ኑሮ ላይ ያስከተለው አውንታዊና አሉታዊ ተጽእኖ፣ /በሁለተኛ ደረጃ የሚታይ ይሆናል/
2. በሐይማኖታዊ ተቋማት /በተለይ አብዛኛው ሕዝብ ችግሩን ለፈጣሪው የሚያቀርብባትና ለመጽናናት የሚሞክርባት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን/ ውስጥ እየሆነ ያለው መተራመስ፤

በምድራችን ውስጥ በርካታ የሃይማኖት ተቋማት ይገኛሉ፤ ሆኖም ግን ከአገሪቱ ታሪክ ጋር ከፍተኛ ትስስር ያላትና በበርካታ ጠንካራ ጎኗ ጉሉህ ስፍራውን ይዛ የምትገኘው ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ስለመሆኗ የሚክድ ኢትዮጵያዊ ያለ አይመስለኝም፤ ካለ ግን ልሟገተውና ጣሊያንን በምስክርነት ጠርቸ ላስመሰክርበት እችላለሁ፤ ይህ የሚሆነውም በራሳቸው ሙያ የሚተማመኑ እውነተኛ ዳኞች ከተገኙ ብቻ ነው።
ስለዚች ቤተ ክርስቲያን ታሪካዊ አጀማመር፣ ላገር ስላበረከተችው መልካም አስተዋጽኦ፣ በረጅም የታሪክ ሂደቷ ውስጥ ስለገጠሟት በርካታ ተግዳሮቶችና ስለከፈለችው ከፍተኛ መስዋትነት ማወቅ ለሚፈልግ /የራሱን ታሪክ ማወቅ ለሚፈልግ/ ወደ ኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ጎራ እንዲል እየጠቆምኩ፤ የዛሬውን መልእክቴን ግን በቤተ ክርስቲያኒቷ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ በስፍራው ላይ ተገኝቼ ያየሁትን እውነት ብቻ ጥንቃቄ ባለው መልኩ በዚህ የመጀመሪያ ጽሑፌ ላይ ለማቅረብ እሞክራለሁ።
በዚች ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከላይ ከፓትሪያሪኩ ጀምሮ በተዋረድ ወደታች የሚፈስ ያስተዳደር መዋቅር አለ፤ በተጨማሪ በርካታ መንፈሳዊ የትምህርት ማሰልጠኛዎች እያስመረቁ የሚያወጧቸው ወጣቶች ዐውደ ምህረቱን ሞልተውት የሰንበት ትምህርት የማስተማሩን ሥራ በሰፊው ተያይዘውታል፤ እኔን የገረመኝና የማላውቅበትን ብእር እንዳነሳ ያደረገኝ ግን በዚህ ግራና ቀኙን በማያውቅና እግዚአብሔርን በሚፈራ የዋህ ወገናችን መካከል በተለያየ መንፈሳዊ ስያሜ ተመስርተው የሚያካሂዱት የእርስ በርስ ጦርነት ነው፤ በዘመናት መካከል እኔ ‘አውቅልሃለሁ የሚልለት ተቆርቋሪ አጥቶ የማያውቅ’ አሳዛኝ ሕዝብ፤!
በዚህ መሰረት ለዛሬ ማህበረ ቅዱሳንን እና ኦርቶዶክስ ተሐድሶ የሚባሉትን መንፈሳዊ ማህበራትን ከሥራቸውና ከሚያራምዱት ዓላማ አኳያ በማየት ፍርዱን ለእውነት ፈላጊዎችና ለወገን ተቆርቋሪ ወገኖች ስተወው፤ ለበለጠ መፍትሄ ፍለጋ ግን ቤተ ሰብ ከቤተሰብ፣ ጓደኛ ከጓደኛ፣ ባል ከሚስት፣ ጎረቢት ከጎረቢት፣ አንዳችን ከሌላው ጋር በእውቀትና በቅንነት ግልጽ ውይይት በማድረግ ለአገርና ለሕዝብ የሚጠቅመውን መደገፍ ለሁላችንም ይበጃል።
1/ ማህበረ ቅዱሳን ማነው?
ከማሕበረ ቅዱሳን አጠቃላይ እንቅስቃሴ ሁላችንም ልንማረው የሚገባ ቁምነገር እንዳለ አምናለሁ፤ ዋና ዓላማው ግልጽ ባይሆንልኝም የአባላቱ ስብጥር፣ አባላት ለማህበራቸው የሚከፍሉት ዋጋና የርስ በርስ መደጋገፍ ይበል የሚያሰኝ ነው። እንዲሁም በየደብሩና በየገዳማቱ ለወደቁ ምስኪን ወገኖቻችን ከሚያደርገው መልካም ሥራ ባሻገር /እውተኛው ክርስትና የመስቀሉ ሥራ ውጤት እንጂ የመልካም ሥራ ውጤት አይደለም ወይም በሌላ አባባል የጽድቅ ሥራ ለመሥራት በመጀመሪያ በጸጋው አምኖ መጽደቅ አለበት ይላሉ ተሐድሶዎች/ ለባህልና ለቅርስ ጥበቃው ሥራ የሚከፍለው ዋጋም በቀላሉ የሚታይ ጉዳይ አይደለም።
የዚህ ማህበር ሌላ መገለጫ ባህሪው የተለያየ የጉዞ ፕሮግራም በማዘጋጀት ሕዝቡ ገንዘቡን ከፍሎ በነጭ ልብስና በኢትዮጵያ ባንዲራ ከቦታ ቦታ እንዲንቀሳቀስ በማድረግ የሕዝቡ ማህበራዊ ትስስር እንዲበረታታ ያደርጋል፤ ሌላው አብዛኛው ሕዝብ አዲስና ልዩ ፈዋሽ ጸበል ተገኘ በተባለበት ስፍራና በየገዳማቱ ሁሉ አብዝቶ እንዲንቀሳቀስ ያደርጋል።
ማህበሩ በተጨማሪ ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከል ጥቂቶቹ፡- ሕንጻ መገንባትን፣ ንግድ መነገድን፣ የራሳቸውን አባላት ማሰልጠንን፣ አዳዲስ ታቦታት መትከልንና ስነጽሁፎችን በሰፊው አውጥቶ ማሰራጨት ሲሆኑ በእነዚህ ጽሁፎቻቸውም ላይ በዋናነት ተሐድሶን የሚያጥላላና የሚያወግዝ መልእክት በትኩረት ያወጣል።
የማህበሩን እንቅስቃሴ ለማጠቃለልም፡
የውስጣቸውን/የልባቸውን ባላውቅም አለባበሳቸው በባንዲራ የታጀበ ነጭ ልብስ በመሆኑ የየዋሁን ሕዝባችንን ልብ ለዓላማቸው በቀላሉ ማማለል ይችላሉ፤ ችለዋልም፣
 ለቅርስና ባህላዊ እሴቶቻችን ከፍተኛ ትኩረት በመስጠታቸውም ለአገር ብቸኛ ተቆርቋሪ ከነሱ ሌላ ፈጽሞ የሌለ አስመስሏቸዋል፣
 ባህላዊ የቆሎ ትምህርት ቤቶች የበለጠ እንዲጠናከሩ ድጋፍ ያደርጋል፣
የገዳምና የምንኩስናን ኑሮ በማበረታት ምሁራን ሳይቀሩ ወደገዳም እንዲገቡ ያበረታታል፤ እንዲያውም ከውጭ አገር ኑሯቸው ተመልሰው ገዳም እንዲገቡ የተደረጉ እንዳሉ ይነገራል፣
 ዘርዓ ያዕቆብን የቤተ ክርስቲያኒቱ ባለወለታ በማድረግ ያወድሱታል፤ታሪኩንም ሕዝቡ እንዲያውቀው ለማድረግ የተደጋገመ ወርክሾፕ በስሙ አድርገውለታል/እያደረጉለትም ነው፣
 መጽሐፍ ቅዱስ የማያውቃቸውን አዳዲስ ቅዱሳንን ሳይቀር ሕዝቡ እንዲያውቃቸውና ጽላት/ታቦት እንዲቀረጽላቸው ያደርጋል፤ አድርጓልም /ምሳሌ አርሴማ የምትባልን ነጭ ሴት/፣
 ለአባላቱ ሁለንታዊ ድጋፍና ስልጠና በትጋት ከማድረጉም ባሻገር በምረቃና በሰርግ ላይ ከበሮና ጸናጽን ይዞ በመገኘት በሚያደርገው ሞቅ ያለ የሽብሸባ አምልኮ ከጴንጤዎች ጋር ውድድር የገባ አስመስሎታል፣
ሕንጻ ይገነባል፣ ንግድ ይነግዳል፣ ገንዘብ ይሰበስባል፣ አባላትን ያደራጃል /ከቀን ሰራተኛ እስከ ምሁር ባለስልጣናት ድረስ/፣
በዩኒቨርስቲዎችና ኮሌጆች ውስጥ የሚማሩትን ተማሪዎች በማሰልጠንና በእረፍታቸው ወቅት ወደየቤተ ሰቦቻቸው በመላክ ዓላማቸውን በሰፊው እንዲያስተዋውቁላቸው ያደርጋል //ይህን በተመለከተ አንድ በመንፈሳዊም ሆነ በታሪክ በቂ እውቀት የሌለው /ከስሜታዊነት በስተቀር/ የወንድሜ ልጅ መሳተፉን አጫውቶኛል//፣
 ማህበሩ በሚያደርገው አጠቃላይ እንቅስቃሴ አባላቶቹንና የዋሁን ሕዝብ ፍጹም የጉልበት ሃይማኖተኛ እያደረገው እንደሆነ በአንዳንድ ደብር በስሜታዊ አባላቱ በኩል የሚታዩት የደም መፋሰስ ግጭቶች ይመሰክራሉ፣
 አዳዲስ የቤተ ክርስቲያን ሕንጻ ሥራ ላይ በሙያተኞቹ በኩል በሰፊው ይሳተፋል፣
 ጎልቶ የሚታየው ሌላው ሥራው በቤተ ክርስቲያኒቷ ውስጥ ከሚገኙ አገልጋዮች መካከል አንዳንዶችን በመክሰስና ከሥራ በማሳገድ እስከ ቤተሰባቸው ችግር ላይ እንዲወድቁ ያደርጋል /ይህ በደል የደረሰባቸውን አንድ ሊቅ ይህ ጸሐፊ አናግሯል/፣
 ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ተሃድሶ ያስፈልጋታል የሚሉትን ጳጳሳት፣ ካህናት፣ መሪጌቶች፣ መነኮሳት፣ ዲያቆናትና አባላትን በሙሉ የፕሮቴስታንት ቅጥረኞችና ጸረ ኦርቶዶክስ ናቸው በማለት በመጽሄታቸው፣ በጋዜጣቸውና በአውደ ምህረት ላይ በማውጣት ከፍተኛ ዘመቻ ያደርጋል።

በማህበሩ መንፈሳዊ እንቅስቃሴ ላይ ያስተዋልኩት ድካም፡
የግብጽ ቤተ ክርስቲያን የጫነችብንን ኢመጽሐፍቅዱሳዊ የባእላት አከባበርን ሕዝቡ በበለጠ መልኩ እዲቀጥልበት ለማድረግ ሰምተናቸው ለማናውቃቸው ሰዎች የቅድስና ማእረግ በመስጠት/በማሰጠት ሕዝቡ ከሥራ ይልቅ ባእል አክባሪ እንዲሆን መደረጉ፣
 በሌለ የጉልበትና የገንዘብ አቅም ሕዝቡ ለጽድቅ እየተባለ ወደ ተለያዩ ስፍራዎች በመጓጓዝ እንዲደክም መደረጉ /ፈጣሪ በቦታ የሚወሰን ይመስል/
 በዓለም አብያተ ክርስቲያናት ታሪክ ውስጥ ታይቶና ተሰምቶ የማይታወቅ የጽላት ቀረጻና የታቦት ተከላ ሥራ መሥራት፣
 እግዚአብሔርን ተርቦና ተጠምቶ በአውደ ምህረቱ ዙሪያ ለተሰበሰበው የዋህ ሕዝብ ፍቅር የሚያስተምረውን የወንጌል ቃል ከመስበክ ይልቅ በእለቱ የሚከበረውን የጻድቅ ገድልና ታሪክ ከሃይማኖትህን ጠብቅ የማስፈራሪያ መርገም ጋር በማሰማት ለጦርነት ማዘጋጀት፣
ሕዝቡ በራሱ መረዳት ማን ምን እንደሆነ በእግዚአብሔር ቃል እውቀት እየመዘነ ሃሰቱንና እውነቱን በመለየት የሚጠቅመውን እንዳይዝ መረጃ በሌለው አሉባልታ ተሞልቶ በውስጡ ጥላቻና ቂም አዝሎ የራሱን ወገን እንዲጠላ በልዩ ወንጌል ሰባኪዎች መሰበኩ፣
 የበጉ ሐዋርያትና ሌሎች የቤተ ክርስቲያን ቀደምት የእምነት አባቶች አድርገውት የማያውቁትን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆነ በጸበል ተገኘ ጋጋታ ሕዝቡን ማንገላታታቸው፣
 በአጠቃላይ ሕዝቡን በቃል እውቀት ሳይሆን በቅርስና በባንዲራ ፍቅር የራሱን ወንድም በጭፍን ወግሮ የሚያሳድድ ሃይማኖተኛ እንዲሆን እየተደረገ መሆኑን ይህ ጸሐፊ በራሱ ቤተ ሰብ መካከል ባደረገው አጭርጥናት ሊያረጋግጥ ችሏል።
2/ ኦርቶዶክስ ተሐድሶ ማነው?
በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተወልደው በማደግ ባህሏንና ትምህርቷን ጠንቅቀው የሚያውቁ የቤተ ክርስቲያኒቷ ልጆች ነን ይላሉ፤ የኦርቶዶክስ ተሐድሶ ማህበር በሚል መጠሪያ ስም፡ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያናችን ከውጭና ከውስጥ በደረሱባት ልዩ ልዩ ተጽእኖ ምክንያት ከተመሰረተችበት የክርስቶስ ኢየሱስ ወንጌል ርቃ ልዩ ወንጌል በመስበክ የመስቀሉን የማዳን ሥራ ቸል ብላለች፤ ስለዚህ ወደ ቀደመ የወንንጌል ጅማሬዋ ትመለስ፤ በእግዚአብሔር ቃል /መጽሐፍ ቅዱስ/ መስተዋት ፊቷን በማየት ክፉ ሰዎች ያለበሷት የደብተራዎች፣ ያስማተኞችና የደጋሚዎች ልብስ በንጹሁና እንከን የለሽ በሆነው በእግዚአብሔር ቃል ልብስ /በክርስቶስ/ ይተካ በማለት ይጮሃሉ።
እንዲያውም እነዚህ ሰዎች የቤተ ክርስቲያናችን ወይም ያገራችን ታሪክ ይፈተሽና ይመርመር፤ ይዘነው የተነሳነውንም የተሐድሶ ጥያቄና ሃገራዊ አጀንዳ ያገራችን ሽማግሌዎች፣ ጳጳሳት፣ ምሁራን፣ ተማሪዎች በአጠቃላይ ሕዝቡ ይስማውና ማን የኦርቶዶክስ ጠላትና ወዳጅ እንደሆነ ጠቅላላ ምእመኑ እውነቱን ይረዳ በሚል ግልጽነት በይፋ እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን መረዳት ችያለሁ።
እኔም እነዚህን አንዳንድ የኦርቶዶክ ቤተ ክርስቲያንን የተሀድሶ ሥራ አራማጆችን ጠጋ ብየ በመጠየቅ የሚከተሉትን መረጃዎችን አግኝቻለሁ፡
1. የቤተ ክርስቲያናችን ጅማሬ ከኢየሩሳሌም ቀጥሎ በወንጌል ላይ ብቻ የተመሰረተች መሆኗን፣
2. በመጀመሪያው ጳጳስ በወንጌል ላይ የተጀመረው ክርስትናችን ግን እኒሁ ጳጳስ ከሞቱ በኋላ፡
 በእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያን ቁጥጥር ስር በመውደቅ ለ1600 ዓመታት ከ110 በላይ በሚሆኑ የውጭ ሀገር ጳጳሳት /የግብጽ የፖለቲካ ሠራተኞ/ መንፈሳዊ ቅኝ ተገዢዎች በመሆን አባይን በመገደብ ሥራ ሠርተን እንዳንበላ እስካሁን ድረስ የ30 ቀናት ባእላት ባሪያዎች መደረጋችንና ከእነዚህ መካከል አንዱ የካሊፋው ዋና ወኪል /አቡነ ሳዊሮስ/ እነደነበረ፣
 የዮዲት ጉዲት የ40 ዓመታት ግዛትና የቤተ ክርስቲያኗ መጽሐፍትና ካህናት መቃጠል፣
 የግራኝ ሙሐመድ የ15 ዓመታት ግዛትና የሙስሊም ክርስቲያኑ ሬሽዮ 9፡1 መድረሱና የቤተ ክርስቲያኒቷን ውበት ማበላሸቱ፣
ዘርዓ ያእቆብ በንግስናው ወራት በመጽሐፍ ቅዱስ ያልተመዘኑ የድርሰት ጽሑፎችን በቤተ ክርስቲያኒቷ ውስጥ ያለገደብ ማስገባቱና የተሃድሶን ጥያቄ ያነሱ መነኮሳትን መጨፍጨፉ /የፕ/ር ጌታቸውን ደቂቀ እስጢፋኖስን መጽሐፍ መረጃ ይጠቅሳሉ/፣
የቤተ ክርሰቲያኒቷ ሲሦ መንግሥት ውል መዋዋልና ከዚህ ጋር በተያያዘ መልኩ መንግሥትን ከሰሎሞንና ከዳዊት ጋር በማያያዝ የታቦትና የጽላት መጥቷል አፈታሪክ ጅማሬ /አቡነ ተክለ ሐይማኖትን ተጠያቂ ያደርጋሉ/፣
የደብተራ ቡድን በቤተ ክርስቲያኒቷ ውስጥ ተነስቶ የመናፍስት አሠራር እስካሁን ድረስ በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ በሰፊው መለመዱ ……….. ወዘተ።
የመሳሰሉትን ነጥቦች በድፍረትና በማስረጃ በማቅረብ ቤተ ክርስቲያኒቷ ከተመሰረተችበት የወንጌል መሰረቷ ፈቀቅ ብላለችና ወደ ቀደመ የወንጌል ጅማሬዋ ትመለስ በማለት አጥብቀውና በነፍሳቸው ተወራርደው ለዚህ ሥራ እንደተነሱ ጨክነው ይሟገታሉ። ይህም መንፈሳዊ መታደስ በአገሪቱ ውስጥ ላለው ሁለንተናዊ ችግር /ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ሃይማኖታዊ ችግር/ ዋና መፍትሄ ይሆናል ብለው በማስራጃ ለማሳመን ይሞክራሉ።
ይህን ጉዳይም የኢትዮጵያ ሕዝብ በሙሉ ተረድቶና ማን ምን እንደሆነ ተገንዝቦ ለመንፈሱ፣ ለነፍሱና ለሥጋው የሚበጀውን በመጽሐፍ ቅዱስ/በወንጌል ሚዛን መዝኖ የሚረባውን ይይዝ ዘንድ ራእያቸውንና ዋና ተልእኳቸውን ለሕዝብ በይፋ ያቀርባሉ፡
የተሐድሶ ራእይ፡
‘‘ጥንታዊና ሐዋርያዊት የነበረች ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያናችን በየዘመናቱ ከደረሰባት ውስጣዊና ውጫዊ ተጽዕኖ የተነሳ ከተተከለችበት የእውነት ወንጌል በማፈንገጥ አሁን ላለችበት ውድቀት በመዳረጓ ይህን ሁኔታዋን በከበረው የጌታችንና የመድኃኒታችን ቅዱስ ወንጌል በመመዘንና ወደ ቀደመ የወንጌል ክብር በመመለስ በእጇ የሚገኘውን ተከታይና የተቀረውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ክርስቶስ ኢየሱስን በማወቅና በማመን የሚገኘውን የዘላለም ሕይወት በማግኘት ለጌታችን ቀን ያለነውርና ያለነቀፋ ሆኖ እንዲገኝ በማዘጋጀት ለአፍሪቃና ለተቀረው ዓለም የሚላኩ ቅዱሳን አገልጋዮችን በማፍራት የሚጠበቅባትን የወንጌል አደራ ስትወጣ ማየት ነው’’
የተሐድሶ ተልዕኮ፡
1. የቤተ ክርስቲያኒቷን አንድነትና የሀገራችንን ጥቅም በጠበቀ መልኩ ምዕመናን በጌታችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ትክክለኛና እውነተኛ ተሀድሶ በማድረግ ለዘላለም ሕይወት እንዲዘጋጁ መርዳት፣
2. በየደረጃው የሚገኙ የቤተ ክርስቲያኒቱ አገልጋዮች እንደ የደረጃው በተዘጋጁ የወንጌል ትምህርቶች በማሰልጠንና በማሳወቅ ለስብከተ ወንጌል ሥራ ማዘጋጀትና የአገልግሎት ቦታዎች ሁሉ እውነትን በተረዱ አገልጋዮች እንዲሸፈኑ ማድረግ፣
3. በየዘመናቱ ወደ ቤተ ክርስቲያኗ የገቡትን የስህተት ትምህርቶች ሥርዓቶችና ባሕሎች በቅዱሱ ወንጌል በመዳኘት ከሕዝባችንና ከቤተ መቅደስ ዕቃ ቤቶቻችን እንዲወገዱ ማድረግ፣
4. ለአገራችን ኢትዮጵያ ዕድገትና ለዓለማችን ጥቅም በክርስቲያናዊ አስተሳሰብ ከመልካም ዜጋ ግንባታ ጀምሮ ለልማትና ለመልካም አስተዳደር መስፈን ግዴታቸውን የሚወጡ ትጉህ ሠራተኞችን ማፍራት፣
5. ጸረ ወንጌል ያልሆኑና ለክርስቶስ ወንጌል መስፋፋት ጠቀሜታ ያላቸውን ሥርዓቶች፣ ባህሎችና ልማዶች ለክርስቶስ ወንጌል መሰበክ እንዲያገለግሉ መጠበቅና ማስጠበቅ።
ስለዚህ ተሐድሶ ማለት፡
አሮጌው አዲስ የሚሆንበት፣ የሳተ የሚመለስበት፣ የላላ የሚጠብቅበት፣ የቆሸሸ የሚነጻበትና ቤተ ክርስቲያን በቃሉ መስተዋት እራሷን እያየች መንገዷን በመንፈስ ቅዱስ መሪነት የምታስተካክልበት የተመለሺ የሁልጊዜ ጥሪ /ራእይ 2፡1_3፡22/ እንጂ የጽድቅ/የእውነት ጠላቶች እንደሚሉት ዛሬ ተዘርቶ የበቀለ ወፍ ዘራሽ /መጤ/ ዘር ወይም ወልዳ ያሳደገችንን እናት ቤተ ክርስቲያናችንን የማፍረስ ሥራ አይደለምና ሰሚ ካለ የዳኛ ወይም ያገር ያለህ በማለት አጥብቀው ይጮሃሉ
በመጨረሻም የእኛ የኢትዮጵያውያን ታሪክ፡
1. ወንጌልን ተምረን ክርስቶስን በመቀበል/ከኢየሩሳሌም ቀጥሎ/ አንደኛ፣
2. የተቀበልነውን ወንጌል በመጣልና ልዩ ወንጌል በመስበክ አንደኛ፣
3. የተበላሸውን ለማስተካከል ተሐድሶን በመጀመር /ከካቶሊኩ ሉተር በፊት/ አንደኛ
4. የተሐድሶ/የእንመለስ/ ፋና ወጊ አባቶችን በመውገር፣ በማሰር፣ በማሳደድና በመግደል አንደኛ ስንሆን ማጠቃልያው የዜሮ ብዜት ውጤት ሆኖብናልና ታሪካችን ተፈትሾ ወደ ቀደመ መልካም የወንጌል ጅማሬያችን እንመለስ በማለት አሁንም ደግመው ደጋግመው ያገር ያለህ በማለት ይጮሃሉ::
3/ የጸሐፊው ግንዛቤ፡
እዚህ ላይ ቆም በማለት እናስተውል ሁለቱም ወገኖች ባእድ ወይም የውጪ ዜጎች አይደሉም። ወይም አንዱ ሌላውን እንደሚወነጅለው የገንዘብ ቅጥረኞ ፈጽሞ አይደሉም። እንዲያውም በተፈጠረው ትርምስ ምክንያት በስደትና በችግር ላይ የወደቁት ቤተ ክርስቲያኒቷ ያፈራቻቸውና ደህና ስልጣን ከወፍራም ደሞዝ ጋር የነበራቸው በርካታ ሊቃውንት መሆናቸው ለሚያስተውል ሰው ውንጀላው ከንቱ እንደሆነ እንዲረዳ ያደርገዋል /ጥሩ ደሞዝ ከከፍኛ ክብር ጋር ያገኙ የነበሩ ሊቃውንት ሲራቡ በዓይኔ አይቻለሁ/ ያለመታደል ሆኖ ግን አብዛኛዎቻችን አሉ በሚል በሽታ ተለክፈን በመጨረሻም ነው ወደሚል መደምደሚያ ላይ በመድረስ አብረን ዋና ፈራጅ ሆነን መገኘታችን ነው።
እንግዲህ እነዚህ ሁለት ያንድ እናት ልጆች በየፊናቸው የራሳቸውን ዓላማ ትክክል፣ እውነትና ለሃገር የሚጠቅም ነው እያሉን ነው። ለእያንዳንዳችን ጥያቄ የሚሆነው ግን እውነቱ የትኛው ነው? በመቅደሱ ሚዛን ሁለቱም ሲመዘኑ ምን ይመስላሉ? የሚለው ይሆናል። ሁላችንም እንደ ፊት መስተዋት ሕይወታችንን እለት በእለት እንድናይበት በእጃችን ላይ ያለው መጽሐፍ ቅዱስ ደግሞ ሁሉን ፈትኑ መልካሙንም ያዙ /1ኛ ተሰ 5፡21/ ስለሚለን በዚህ የመለኮት ህያው ቃል ብቻ እየተመራን ሁላችንም የየግልና የምድራችንን ችግሮች እንደሚገባ በመረዳት ለመፍትሔው በጋራ እንድንነሳሳ አንባቢዬን እያሳሰብኩ በዚህ ጉዳይ ላይ ያለኝን መረዳት እንደሚከተለው አቀርባለሁ፡
እውነት በሚባል ሚዛን ሲመዘን እንደ ገለባ የሚቀል ዓይነት ፍቅር እንዳይሆን ያስፈራል እንጂ ሁላችንም አገራችንን እንደምንወድ እንናገራለን፤ አገር ስንል ታዲያ በውስጧ ስለሚኖረው ሕዝብ ማለት እንደሆነ የሚዘነጋ ሰው ያለ አይመስለኝም። እንግዲህ ለብዞዎቻችን ያልተመለሰ ጥያቄ የሚሆንብን በዚች አገር ውስጥ በሚኖሩ ብሔረሰቦች፣ ሃይማኖተኞች፣ ፖለቲከኞችና ቤተሰቦች መካከል ካለው የእርስበርስ ጥላቻና ትርምስ ስንነሳ አገሬን እወዳለሁ የሚለውን ሁሉ እንዴት ማመን ይቻላል እውነተኛ/genuine/ ደጋፊና ተቃዋሚስ ይኖር ይሆንን???
ተሐድሶ የሚለው ቃል በአሁኑ ጊዜ በአሉታዊና በአውንታዊ መልኩ በሕዝባች መካከል እየተነገረ ያለ ቃል ሲሆን፤ ነገር ግን ታሪካችንን እንደሚገባ ለማናውቅ አዲስ፣ ለምናውቅ ግን የቀደሙት አባቶቻችን አሮጌውን በአዲስና ጠቃሚ በሆነ መልካም ነገር ለመተካት ሲሉ ሕይወታቸውን አሳልፈው ለሰጡበት በጎ ዓላማ መጠሪያ የነበረ የግብር /የሥራ መገለጫ/ መጠሪያ ቃል ነው። ለዚህ ጉዳይ መረጃን ለምትፈልጉ እውነተኛ ወገኖቼ:-
1. የፕሮፌሰር ጌታቸውን ደቂቀ እስጢፋኖስ በሕግ አምላክ መጽሐፍ በማንበብ፣
2. አለቃ ታዬ የወንጌል ቃል ብቻ ይብቃ በማለታቸው በቤተ ክህነትና በመንግሥት የጋራ ጡንቻ እስር ቤት ተወርውረው ሲሞቱ በልቅሷቸው ላይ እህታቸው የተቀኙትን የሚከተለውን የአማርኛ ቅኔ ይመልከቱ፡
ከወኅኒ ቤት አስረው የዘጉበት ሳንቃ ብሎ ተናግሮ ነው የወንጌል ቃል ይብቃ የወንጌል ሥርዓት ተማሩ ቢላቸው ትንሹም ትልቁም ሁሉም ከንቱ ናቸው አሉት ጸረ ማርያም መልስ ቢሳናቸው
እውቀትና ትምህርት ጉድጓድ ተከተተ
አርባ አራት ነው እንጂ መች አንድ ሰው ሞተ
ወዝውዘው ወዝውዘው ጣሉት እንደ ዝሆን
ያው ወደቀላቸው ይበሉት እንደሆን
አጥፉት አጥፉት አሉ እንዳይታየን።
ስለዚህ የተሐድሶ ዓላማና እንቅስቃሴ በአሁኑ ትውልድ ብርታትና ትጋት ዛሬ የተጀመረ ሥራ ሳይሆን፣ ወይም ከዘመናት በፊት ጀምሮ የእውነተኛ ሕይወት ጠላት የሆኑ ክፉ ወገኖቻችን አውርተው እንደሚያስወሩት ሳይሆን በመግሥትና በቤተ ክህነት የጋራ ትብብር ተዳፍኖ በርካታ ዘመንን ካለውጤት ያስቆጠረ ያባቶች መልካም የታሪክ አሻራ ነው። ጅማሬ መልካም ቢሆንም ካለግብ/ካለፍጻሜ የሚቀር ከሆነ ደግሞ በራሱ ትልቅ የሕይወት ክስረት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ጉዳይ ላይ፡ ከእናንተ ግንብ ሊሠራ የሚወድ ለመደምደሚያ የሚበቃ ያለው እንደሆነ አስቀድሞ ተቀምጦ ክሳራውን የማይቆጥር ማን ነው? በማለት በሉቃስ 14፡28 ላይ ማስተዋልን የሚፈትሽ ጥያቄ ጌታ እራሱ ይጠይቃል። የእኛን የኢትዮጵያውያንን የሕይወት ክስረት ልዩ የሚያደርገው ደግሞ ይህን የወንጌል ትምህርት አስረግጦ ባስተማረውና የደም ዋጋ በከፈለው በክርስቶስ ኢየስስ ስም ከበርካታ የዓለም አገሮች በፊት ይኸው ወንጌል ተሰብኮልን ክርስቲያን ተብለን ከተጠራን በኋላ መሆኑ ነው::
አጭር የመፍትሔ ሃሳብ፡
በነዚህ በሁለቱ ማህበራት ላይ የተገነዘብኩትን ብርታትና ድካም ከዚህ በላይ ባጭሩ ለመግለጽ ሞክሬያለሁ፤ ሆኖም ግን የእኔ እይታ ፍንጭ ብቻ ሊሰጥ ይችል ይሆናል እንጂ በቂ ግንዛቤ አያስጨብጥም፤ ስለዚህ ነገሩን እንደ ዜጋ እንደሚባ ለማጥናት ሞክረን ማን ምን እንደሆነ በመረጃ በማወቅ እውነትና ለሃገር/ለወገን የሚጠቅመውን ይበል፣ የማይጠቅመንን ደግሞ አይሆንም በማለት ተገቢውን አቋም መያዝ አለብን፤ አገሬን/ወገኔንና ቤተ ክርስቲያኔን እወዳለሁ የሚል ሰው ተመልካች መሆን የለበትምና ዛሬውኑ በማወቅና በማድረግ ጨክነን እንድንነሳ በዚህ ለዘመናት በታረዘና የሕይወት ትርጉም በጠፋበት የዋህ ወገናችን ስምና ፍቅር እየጠየቅሁ ለማህበረ ቅዱሳንና ለተሃድሶ ማህበር ደግሞ የሚከተሉትን ጥያቄዎች አቀርባለሁ፡
1. የጓዳ ሥራችሁንና ዓላማቸሁን ለሕዝባዊ ውይይት ማቅረብ ፈቃደኞች ናችሁን?
2. በአገር ሽማግሌዎችስ ለመዳኘት ፈቃደኞች ናችሁን?
3. እስቲ ሁላችሁም ቆም በማለት የእራሳችሁን መንገድ ለማዬት ብትሞክሩስ?
4. በእውነት በእናንተ ምክንያት ነፍሱ እረፍት አጥታ የሚቅበዘው የወገናችሁ ሕይወት እንቅልፍ ነስቷችሁ ያውቃል??????????

በመጨረሻም ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ አንዲት ጥያቄ ብቻ ላቅርብና ያገር/የወገን ያለህ ጮኸቴን ላቁም፡
 እውነቱንና ሃሰቱን እንዴት እንወቅና የሚጠቅመንን እንያዝ??? መልሱ በመጽሐፍ ቅዱስ ቃል በጥንቃቄ መዝነን መሆን አለበት።

ቸር ይግጠመን
እውነቱ

23 comments:

 1. Amazing!!!! JORO YALEW YISMA

  ReplyDelete
 2. የምን ወዲህ ወዲያ ነው።
  አንድ ያስተዋልኩት ነገር ቢኖር፣ ባለፈው ባቀረባችሁት አንድ መጣጥፍ ላይ የብሎጋችሁ ተልዕኮ እና ግብራችሁ ግራ ያጋባው አንድ አስተያየት ሰጪ በማኅበረ ቅዱሳን ላይ የምታዘንቡትን አድሏዊና የተለመደ የውግዘትና የስድብ ናዳ ተመልክቶ ግራ ቢገባው ራሳችሁን እንድትመረምሩ የሰጣችሁን አስተያየት ተከትሎ ”ለውይይት በር የሚከፍት“ የሚመስል ነገር ማቅረባችሁ መሰለኝ። ግለሰቡ የሰጠውን አስተያየት በበጎ ተመልክታችሁት ከሆነ ይህንን መጣጥፍ ያቀረባችሁት፣ እኔም አመሰግናችኋለሁ። ይበል የሚያሰኝ ነው። ነገር ግን አሁንም በዚህ መጣጥፍ ላይ አድሏዊነታችሁ አፍ አውጥቶ ይጮሃል። እንዲያው እንዲመስል እንኳ ለማድረግ ብትሞክሩ ጥሩ ነበር። ምክንያቱም “የተሃድሶን" ርእይ፣ ተልዕኮ እና የመሳሰሉትን ጉዳዮች በጣም በሚገባና አሰማምራችሁና አብራርታችሁ እንዳቀረባችሁት፣ የማኅበረ ቅዱሳንንም አመሰራረት፣ ርእይ፣ተልዕኮ እንዲሁም በዓይን የሚታይና በእጅ የሚዳሰስ አገልግሎቱን ወዘተ ከራሱ ከማኅበሩ ገጸ-ድር /Web site/ላይ እንዳለ ገልብጣችሁ በመለጠፍ ፍርዱን ለአንባቢ መተው በተገባ ነበር። ነገር ግን ይህ አልሆነም። ስለዚህ ገለልተኛነታችሁ ወዴት አለ ብዬ እሞግታችኋለሁ። ከታረማችሁ አብረን እንዘልቃለን። ካልሆነ ግን ማንነታችሁን ግልጽ እያደረጋችሁልኝ ስለሆነ ሳላመሰግናችሁ አላልፍም።

  ይቆየን።

  ReplyDelete
 3. Yibel yetesegnge hasab new. Egziabher yibarekeh.

  ReplyDelete
 4. “እውነቱ” ጽሑፍህን አንብቤዋለሁ፡፡ ሚዛናዊ ለመሆን ያደረከውን ጥረት ሳላደንቅ ማለፍ አይሆንልኝም፡፡ ነገር ግን ወደ አንድ ያደላና የዐራ ጥቃን/ተሐድሶ/ አዲስ ስልት ያስተዋወቀኝ በመሆኑ አመሰግንሀለሁም አዝኘብሀለሁም፡፡ ይህንንም አንዱን ሐሳቤን ላቅርብልህና ስምህ “እውነቱ” መሆኑንና እውነት ተናግረህ እንደማታቅ ላሳይህ፡፡ ካቀረብካቸው ሐሳቦች መካከል ጎልቶ የወጣብኝ የዘመዶችህን ዐራ ጥቃን/ተሐድሶ/ ርዕይ ደጋግመህ ለማስነረጽ ያደረከው ጥረት በጭራሽ አልተሳካልህም፡፡ ይቅርታና “ከዝንብ ማር አይጠበቅም” እያልኩ የምጽፈው እንዲሁ እንዳልሆነ ብትረዳ መልካም ነው፡፡
  እስቲ አንድ ጥያቄ ልጠይቅህ፡፡ ልክ የዘመዶችህን ዐራ ጥቃን/ተሐድሶ/ ርዕይ እንዳብራራህ የማኅበረ ቅዱሳን ርዕይን ለምን አላብራራህም? የማኅበረ ቅዱሳን ድክመቶች ባብራራው ጽሑፍህ የተሐድሶን ድክመቶች ለምን አላብራራህም?መቼም አይሆንልህ፡፡ ማኅበ ቅዱሳን እኔ እስከማውቀው አንተ ከምትለው በላይ ድክመቶች አሉብኝ የሚል ማኅበር እንደሆነ ነው፡፡ ይህን ለማወቅ ደግሞ የየጊዜውን ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት መመልከት በቂ ይሆናል፡፡ በተጋበዝኩባቸው ጠቅላላ ጉባኤያቶች የምሰማው ያከናወናቸውን ተግባራት ሳይሆኑ ያሉበትን ድክመቶች ነው፡፡ አባላቱም ያልሆነውን ሆነ ብለው ላለማቅረብ ከልባቸው ሲጥሩ አይቻለሁ፡፡ ይህን የምለው ጽሑፍ ማኅበረ ቅዱሳንን ለመውቀስ አንደት የሌለውና እኔን እንኳን ማሳመን አልቻለም ልልህ ነው፡፡
  በርዕይ ደረጃ ዐራ ጥቃን/ተሐድሶ/ ይዘው ከተነሱት ለጌታችን ለመድኃኒታችን ወንጌል ለሕዝብ ሁሉ ይዳረስ ዘንድ የትኛው ሚዛን ይደፋል፡፡ አንባብያን ዐራ ጥቃን/ተሐድሶ/ ርዕይ ከላይ አንብባችኋል ብዬ አስባለሁ፡፡ የማኅበረ ቅዱሳንን ደግሞ ተመልከቱና ፍረዱ፡፡ “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ተጠናክራ፣ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርተ ወንጌል በመላው ዓለም ተስፋፍቶ፣ ጽኑዓን የሆኑ ምዕመናን በዝተው ማየት ነው”
  “እውነቱ” በሌላ ዙር ማኅበረ ቅዱሳንን የምትወቅስበት ነገር ካለ ተመለስ ለዛሬው አልተሳካልህም!

  ReplyDelete
 5. ሌባ ለአመሉ ዳቦ ይልሳል፡፡ ለማያውቅህ መቼም መቼም ቢሆን ለሐራጥቃ ቦታ የለንም፡፡ ሌባ ለአመሉ ዳቦ ይልሳል፡፡ ለማያውቅህ መቼም መቼም ቢሆን ለሐራጥቃ ቦታ የለንም፡፡

  ReplyDelete
 6. ይገርማል ለሚታገስ አካል አግዚአብሔር እውነትን እንዴት በሀሰተኞች አፍ እንደሚያስመሰክር የታየበት ጹሑፍ…… አባ ሰላማዎች እውነት ብትዘገይም መገለጧ ስለማይቀር በው ማኅበረ ቅዱሳንን እከሳለሁ ብላችሁ አምሮው ማመዛዘን የሚችል እውነቱ ማን ጋር እንዳለ ያሳያችሁን፡፡ አምላከ እስራኤል ቅድስት ቤተክርስቲያናችንን እና ማኅበረ ቅዱሳንን ይጠብቅልን እኛንም በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ሃይማኖታችን ያጽናን

  ReplyDelete
 7. የሚገርመው ምን አይነት ውሸተኛ እንደሆናችሁ ከብዙው በጥቂቱ በሁለት መንገድ ተረዳሁ
  - አንደኛው ማኅበረ ቅዱሳንን ለመክሰስ እንዲመቻችሁ እና ሚዛናዊ ለመሆን ማኅበሩ ያከናወናቸውን ጠንካራ ሥራዎች በማለት የተለመደ አላዋቂነታችሁን በሚያስገነዘብ መልኩ ለመዘርዝር ሞከራችሁ
  - ሁለተኛው የአላዋቂነታችን ጥግ እና እንኳን ከቤተክርስቲያን አስተምህሮ ውጭ መሆን የቤተክርስቲያኗን አሠራር ምንም የማታውቁ መሆናችሁን ያስገነዘበኝ ማኅበረ ቅዱሳን የጽላት ቀረጻ እና የታቦት ተከላ በሰፊው እንደሚሠራ መግለፃችሁ ነው፡፡
  አይ ሉተራዉያን በቃ የአባታችሁን ያክል እንኳን የመዋሸት አቅማ አጥታችሁ እያደር በሀሳብ ወደ ታች ቁልቁል ትወርዳላችሁ፡፡ እኔ የምመክረው እንደ ክርስቲያን ምነው ወደ እውነት ብትመለሱ ለክፉ ሥራ ይህን ያክል ከምትደክሙ ለመልካም ብትሠሩ ምን ያክል ባተረፋችሁ፡፡

  ReplyDelete
 8. “አባ ሰላማዎች” የጽሑፋችሁን ርዕስ ገና እንዳየሁት ወደሐሳቤ የመጣው ሌላ ጉዳይ ነበር፤ ውስጥ ካነበብኩት ማለቴ ነው፡፡ ምን ሆናችሁ ብዬም ነበር፡፡ ግን እናንተ ለአንባብያን የአሰላለፍና የአካሄድ ለውጥ ለማድረግ መሆኑን ዘግይቶ ገባኝ፡፡
  ጸሐፊው “እውነት” ደግሞ በእውነት ዛሬ አልተሳካልህም፡፡ ለምን? በለኝ፡፡ ርዕስ ወዲህ፤ ውስጡ ወዲያ ሆነብኝ፡፡ “ያገር ያለህ ወይም የዳኛ ያለህ!!!” ብለህ ስትጀምር ፍርድ አጥተህ የተገፋህ መስሎኝ ነበር፡፡ ነገሩ ወዲህ ነው፡፡ ጹሕፍህን ሳነበው ግን በዐራ ጥቃ/ተሐድሶ/ እና በማኅበረ ቅዱሳን መካከል እርቅ ለማውረድ የሀገር ሽማግሌዎችን ሰብስበህ የመጣህ መሆንህን ተረዳሁ፡፡ ባንድ በኩል ምን ታደርግ አሁን ገዥው ፓርቲንና ተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል ሀገራዊ እርቅ ቢደረግ አሁን በየቦታው ያለው ረብሻ መፍትሄ ያገኛል ብለው እየተንቀሳቀሱ ያሉ አካላት ጋር አብረህ እየሠራህም መሰለኝ፡፡ በዛኛው ያልተሳካልህን በዚህኛው ግብ ለማድረስ፡፡ ሰውኮ ውል ሲልበት አደጋ አለው!፡፡ በሌላ በኩል በማኅበረ ቅዱሳንንና በዐራ ጥቃ/ተሐድሶ/ መካከል የእውነት እርቅ እንዲመጣ ፈልጎ ይሆን ብዬ ደግሞ እራሴን ጠየኩኝ፤ ግን መልሱን ከጽሑፍህ ማግኘት አልቻልኩም፡፡ ደጋግመህ ለማስረጽ እንደሞከርከው የዐራ ጥቃ/ተሐድሶ/ ስትራቴጂን ነው፡፡

  ጸሐፊው አንተ እውነት ግን ስምህ “እውነት” ነው፡፡ በእውነት ይከብድሃል፡፡ አትችለውም፡፡ ሌላ የብዕር ስም አጣህ እንዴ ላውስህ፡፡ ደግሞ ያሰብኩትም አይመጥንህም፡፡ ከዚህ በኋላ ሌላ የብዕር ስም ተጠቀም፡፡

  ላነሳሀው ሐሳብ ብዙ ርቀት መሄድ አይገባህም፡፡ በቀላሉ ራስህን ለምክረ ንስሐ አባትህ ከዚህ በፊት በየአጥቢያው ስትወሰልት የነበረውን ተናዘህ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቀርበህ ንሰሐ ግባ፡፡ የማይረሳ ነገር የለም አምላክ ይቅር ይልሃል፡፡ ዳር ዳር አትበል፡፡ የመዳን ቀን ዛሬ ነው! ለአባ ሰላማ ብሎገሮችም ንገር እርቅ ከማኅበረ ቅዱሳን ጋር ሳይሆን ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጋር ነው፡፡ ስትበደል የነበረች በእንዳንተ ዓይነት በዐራ ጥቃ/ተሐድሶ/ ነውና፡፡ ንሰሐ.....

  ReplyDelete
 9. unknowingly,you are witnessing how your deeds are disgusting and you tried to seem neutral body,but nobody can do more than what is in his mind.I'm decidedly sure you're member of anti Tewahdo.

  ReplyDelete
 10. ማቅ ጋ ድርድር ? ጅብን vegiterian እንዲሆን ማግባባት ነው። ከእውነት እና ከወንጌል ርቀዋል። ማቅን አንድ ፈርጠም ያለ union ፈጥሮ strategy ነድፎ ይህን አረም መንቀል ነው።

  ReplyDelete
  Replies
  1. ha ha ha ha ha ha. Essey tebesacheh. Gena taraleh tidebnaleh. Tewahedo tilemelmelech

   Delete
 11. ፀሐፊ ሆይ አንተ ማነህ?ከወዴት ነህ?

  ፀሐፊው ማህበሩ/ማህበረ ቅዱሳን/ ምንም አይነት የጽድድ ስራ እንደማይሰራ የገለጸበት ቃል /እውተኛው ክርስትና የመስቀሉ ሥራ ውጤት እንጂ የመልካም ሥራ ውጤት አይደለም ወይም በሌላ አባባል የጽድቅ ሥራ ለመሥራት በመጀመሪያ በጸጋው አምኖ መጽደቅ አለበት ይላሉ ተሐድሶዎች/
  ማህበሩ/ማህበረ ቅዱሳን/ እየፈፀመው ያለው አላማ ና ተልእኮ
  《የዲላ ወረዳ ማእከል ትምህርትና ሐዋርያዊ አገልግሎት ክፍል ከሰንበት ትምህርት ቤቶች ጋር በመተባበር በዲላ ማረሚያ ቤት ያስተማሯቸውን 48 ኢ አማንያን የነበሩ የሕግ ታራሚዎች ተጠምቀው የሥላሴ ልጅነትን አገኙ፡፡〉

  ReplyDelete
 12. MAHBERE KIDUSAN BEMALET RASUN YADERAJEW AROGE POLETICA ARAMAJNA AKENKAGN YALETESEDEBE MAN YISEDEB EWNET LEMENAGER NEGADE ENJI MAN NEW YE HAYMANOTE SIBSIB YADEREGEW BETEKRSTIYANS KEMAHBERE MIEMENAN WICH LELA MAHBERE YELATIM YIH YSENEFOCH SIBSIB YEHIZIB GENZEB BE BETEKRSTIYAN SIM EYESEBESEB BALE ACSIYONOCHUN ENA FABRICA HONOWAL ENDIHU KEKETELE ISS YITEKAL TOLO TOLO ENDITEFA METSELEY YASFELGAL

  ReplyDelete
 13. ጥንትም እኮ እባብ አዳምና ሄዋን በመልካም ጠባይ በጥሩ አቀራረብ ቀርባ ነበር ወደ ሞት መንገድ በማስመሰሎ የወደሰደቻቸው። አሁን ማቅ በጥሩ ጠባይ እንደ አባቡዋ ውጭውን አሳምሮ በቤተ ከርስቲያን ወስጥ ሰርጎ በቅዱሳንና በእመቤታችን ስም ሽፋን መቃብር እየቆፈረ ነው። ገንዘብ ማግኛ መንገዱም በዚሁ ከቤተ ክርስትያን ሰዎችን በማደናገር እየሰበሰበ ያለው።እስት ቆም ብለን በጤናማ አእምሮ እናስብ። በማቅ ዘገባ መሰረት በአንድ ወቅት በቀረበው ዘገባ ለይ የቤተ ከርስትያናችን አባላት ከ70% ወደ 40 % ወርዶዋል በማለት ይናገር ነበር። ለመሆኑ ይህ ሁሉ ህዝብ ከእኛ የወጣው በማቅ ጥላቻና እርሱ ያለ ስም ስም እየሰጣቸው እራሱን ከስኖዶስ በላይ በማድረግ አንዳንድ ሊቃነ ጳጳሳትና ካህናት በነዋይ ጥቅም በማጥመድ ቤተ ከርስትያንቷን እየገደለ ነው።ለተሀድሶም መፈጠር ማቅ እጅ እንዳለበት እናውቀዋለን።ማንም ሞኝ የለም። እግዚአብሄር ስራ ድንቅ ነው። በውጭ ያሉትን አባቶች እዚአብሔር አነሳስቶዋቸው ማቅ ህዝቡን በማስተማር እያጋለጡ ናቸው። ተመስገን ተመስገን ተማስገን ማለት ነው።

  ReplyDelete
 14. በዚህ ግራና ቀኙን በማያውቅና እግዚአብሔርን በሚፈራ የዋህ ወገናችን መካከል በተለያየ መንፈሳዊ ስያሜ ተመስርተው የሚያካሂዱት የእርስ በርስ ጦርነት ነው፤ በዘመናት መካከል እኔ ‘አውቅልሃለሁ የሚልለት ተቆርቋሪ አጥቶ የማያውቅ’ አሳዛኝ ሕዝብ፤!

  ReplyDelete
 15. አሮጌው አዲስ የሚሆንበት፣ የሳተ የሚመለስበት፣ የላላ የሚጠብቅበት፣ የቆሸሸ የሚነጻበትና ቤተ ክርስቲያን በቃሉ መስተዋት እራሷን እያየች መንገዷን በመንፈስ ቅዱስ መሪነት የምታስተካክልበት የተመለሺ የሁልጊዜ ጥሪ /ራእይ 2፡1_3፡22/ እንጂ የጽድቅ/የእውነት ጠላቶች እንደሚሉት ዛሬ ተዘርቶ የበቀለ ወፍ ዘራሽ /መጤ/ ዘር ወይም ወልዳ ያሳደገችንን እናት ቤተ ክርስቲያናችንን የማፍረስ ሥራ አይደለምና ሰሚ ካለ የዳኛ ወይም ያገር ያለህ በማለት አጥብቀው ይጮሃሉ

  ReplyDelete
 16. በመጨረሻም የእኛ የኢትዮጵያውያን ታሪክ፡
  1. ወንጌልን ተምረን ክርስቶስን በመቀበል/ከኢየሩሳሌም ቀጥሎ/ አንደኛ፣
  2. የተቀበልነውን ወንጌል በመጣልና ልዩ ወንጌል በመስበክ አንደኛ፣
  3. የተበላሸውን ለማስተካከል ተሐድሶን በመጀመር /ከካቶሊኩ ሉተር በፊት/ አንደኛ
  4. የተሐድሶ/የእንመለስ/ ፋና ወጊ አባቶችን በመውገር፣ በማሰር፣ በማሳደድና በመግደል አንደኛ ስንሆን ማጠቃልያው የዜሮ ብዜት ውጤት ሆኖብናልና ታሪካችን ተፈትሾ ወደ ቀደመ መልካም የወንጌል ጅማሬያችን እንመለስ በማለት አሁንም ደግመው ደጋግመው ያገር ያለህ በማለት ይጮሃሉ::

  ReplyDelete
 17. በነዚህ በሁለቱ ማህበራት ላይ የተገነዘብኩትን ብርታትና ድካም ከዚህ በላይ ባጭሩ ለመግለጽ ሞክሬያለሁ፤ ሆኖም ግን የእኔ እይታ ፍንጭ ብቻ ሊሰጥ ይችል ይሆናል እንጂ በቂ ግንዛቤ አያስጨብጥም፤ ስለዚህ ነገሩን እንደ ዜጋ እንደሚባ ለማጥናት ሞክረን ማን ምን እንደሆነ በመረጃ በማወቅ እውነትና ለሃገር/ለወገን የሚጠቅመውን ይበል፣ የማይጠቅመንን ደግሞ አይሆንም በማለት ተገቢውን አቋም መያዝ አለብን፤ አገሬን/ወገኔንና ቤተ ክርስቲያኔን እወዳለሁ የሚል ሰው ተመልካች መሆን የለበትምና ዛሬውኑ በማወቅና በማድረግ ጨክነን እንድንነሳ በዚህ ለዘመናት በታረዘና የሕይወት ትርጉም በጠፋበት የዋህ ወገናችን ስምና ፍቅር እየጠየቅሁ ለማህበረ ቅዱሳንና ለተሃድሶ ማህበር ደግሞ የሚከተሉትን ጥያቄዎች አቀርባለሁ፡
  1. የጓዳ ሥራችሁንና ዓላማቸሁን ለሕዝባዊ ውይይት ማቅረብ ፈቃደኞች ናችሁን?
  2. በአገር ሽማግሌዎችስ ለመዳኘት ፈቃደኞች ናችሁን?
  3. እስቲ ሁላችሁም ቆም በማለት የእራሳችሁን መንገድ ለማዬት ብትሞክሩስ?
  4. በእውነት በእናንተ ምክንያት ነፍሱ እረፍት አጥታ የሚቅበዘው የወገናችሁ ሕይወት እንቅልፍ ነስቷችሁ ያውቃል??????????


  በመጨረሻም ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ አንዲት ጥያቄ ብቻ ላቅርብና ያገር/የወገን ያለህ ጮኸቴን ላቁም፡
   እውነቱንና ሃሰቱን እንዴት እንወቅና የሚጠቅመንን እንያዝ??? መልሱ በመጽሐፍ ቅዱስ ቃል በጥንቃቄ መዝነን መሆን አለበት።

  ReplyDelete
 18. እንዲያውም እነዚህ ሰዎች የቤተ ክርስቲያናችን ወይም ያገራችን ታሪክ ይፈተሽና ይመርመር፤ ይዘነው የተነሳነውንም የተሐድሶ ጥያቄና ሃገራዊ አጀንዳ ያገራችን ሽማግሌዎች፣ ጳጳሳት፣ ምሁራን፣ ተማሪዎች በአጠቃላይ ሕዝቡ ይስማውና ማን የኦርቶዶክስ ጠላትና ወዳጅ እንደሆነ ጠቅላላ ምእመኑ እውነቱን ይረዳ በሚል ግልጽነት በይፋ እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን መረዳት ችያለሁ።

  ReplyDelete
 19. Time of panic for this generation
  We have to discern what we see read and do
  May God turn you from hatrd to peace
  We have to have peaceloving.

  ReplyDelete