Tuesday, March 15, 2016

ለምን መሬት መሬት ታያለህ?

ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል
March 3, 2016
የተደረገልን እኔና አንተ ከምናደርግለት በላይ ነው! ለምን መሬት መሬት ታያለህ?
የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በአሁን ሰዓት ስለምትገኝበት ገፅታ ለምስክርነት አልበቃም። መልካም - ለጊዜው ብዙ ርቄለሁ። ይህ መልዕክት በቀንና በሌሊት በመንፈሴ ሲመላለስ ግን ቢያንስ ስድስትና ሰባት ወራት ሆኖታል። የዚህ ጽሑፍ ዓላማ እንደሆነም ከመልዕክቱ ይዘት ለመረዳት እንደሚቻለው ግቡ ግልፅ ነው። ይኸውም፥ አንድ ሰው ቢሆንም ለዚያ ከወንጌል የተነሳ በመከራ ውስጥ የሚገኝ/የምትገኝ የእግዚአብሔር ባሪያ የእውነት ቃል ለማካፈል ተጻፈ።
መሪ ጥቅስ፥
እውነት እላችኋለሁ፥ ስለ እኔና ስለ ወንጌል ቤትን ወይም ወንድሞችን ወይም እኅቶችን ወይም አባትን ወይም እናትን ወይም ሚስትን ወይም ልጆችን ወይም እርሻን የተወ፥ አሁን በዚህ ዘመን ከስደት ጋር ቤቶችን ወንድሞችንና እኅቶችንም እናቶችንም ልጆችንም እርሻንም መቶ እጥፍ፥ በሚመጣውም ዓለም የዘላለም ሕይወት የማይቀበል ማንም የለም።” የማርቆስ ወንጌል 10፥ 29, 30
ለምን መሬት መሬት ታያለህ?
ወንድሜ ሆይ! እነሱ የአመፃና የክፋት ሰይጣንዊ አጀንዳቸውን በአማኞችና በቤተ ክርስቲያን ብሎም በሀገር ላይ ለመጫን ተደራጅተውና ቆርጠው ከተነሱ አንተ ደግሞ ከምን ጊዜ በላይ የእምነትን ጋሻ የማዳን ራስ ቁር የመንፈስም ሰይፍ ይዘህና አንስተህ፤ ወገብህን በእውነት ታጥቀህ፥ የጽድቅንም ጥሩር ለብሰህ መልካሙን ውጊያ የምትዋጋበት ሰዓቱ አሁን ነው።
እነሱ አንተን ለማስቆምና አደናቅፈው ለመጣል፣ ለመቅጨትና ለማስወገድ፣ ለማጥፋትና ለመደምሰስ፣ ለማድማት ብሎም ነፍስህን ከስጋህ ለመለየት (ለመግደል) ቆርጠው ከተነሱ አንተ ደግሞ ሞት በነገሰባት ምድር ላይ ህይወት ለሰጠህ፥ ሰው ላደረገህ፣ ሰው ታጥቶ ሳይሆን አጀንዳውን ትሸከም ዘንድ ለጠራህ - በሰው ፊት የሚታይ የሌለህ - ሚዛን የማትደፋ፣ ዳሩ ግን በመንግሥቱ በክብር ለሾመህና ሰው ላደረገህ ለእግዚአብሔር ልጅ ለኢየሱስ ወንጌል ብትሰደድ፣ ብትገረፍ፣ ብትንገላታ፣ ብትራብና ብትጠማ፣ ብትራቆትና ብትጎሳቆል፣ ብትቆሳስልና ብትደማ፣ ሞትም ቢሆን ደስ እያለህ (በደስታ) የማትቀበልበትና የማታስተናግድበት ምንም ምክንያት የለህም። የተደረገልን እኔና አንተ ከምናደርግለት በላይ ነው። ለምን መሬት መሬት ታያለህ? ኢየሱስ ባይደርስልን ኖሮ የእኔ የአንተ/አንቺ ህይወት ጨው ቢነሰነስበት ጥንብ አንሳ (ጅብ/ውሻ) የማይቀምሰንና የሚጸየፉን ዓይነት ሰዎች ነበርን።
  v የጠራህ ተመሳስለህ እንድትኖር አይደለም።
  v የቀባህ ሞት ሞት በሚሸቱ መካከል ራስህን እንድትደብቅ አይደለም።
  v ያስተማረህ በጨለማ ውስጥ ብርሃን ሆነህ እንድታበራ እንጅ የጣላቶችህ ማስፈራራት ውጦህ ተስፋ እንደሌለው ሰው እንድትመላለስም አይደለም።
  v ሂድ ብሎ የላከህ ልዑል እግዚአብሔር የሚሰራውን የሚያውቅ ፃድቅ አምላክ ነው። በስህተት አልጠራህም፤ በስህተት አይልክህም፤ በስህተትም ህይወትህ አታልፍም። ከዋሽንግተን በሚወጣው ትዕዛዝ በየመን፣ በአፍጋኒስታን፣ በሊብያና ሲሪያ የንጹሐን  ዜጎች ህይወት (ደም) በከንቱ ሊያልፍና ሊፈስ ይችላል። ከሰማይ የሚወጣ ትዕዛዝ ግን ከዚህ ሁሉ በላይ ነው። ስህተትም ሆነ ህጸጽ አይገኝበትም። አያውቀውምም።
ወንድሜ ሆይ! ወደኋላ ልመልስህና - ለእግዚአብሔር የተማረክባትን ዕለት አስባት። ያቺ ቀን በእግዚአብሔር ፊት የምስክርነት ሐወልት ሆና ቆማለች። የዛሬ ሃያ፣ አሥር ወይንም ሁለት ዓመት …  ሊሆን ይችላል፡፡ ታድያ ያኔ የእግዚአብሔር ሃሳብ ይበልጥብኛል ብለህ ጨርቄና ማቄ ሳትል እንደውም የነበረህን አካፍለህ፣ በትነህና አርደህ እግዚአብሔርን ታምነህ የአባትህን ቤት ወደሃላ ጥለህ የወጣህበት ቀን የመራችህ እጅና የተሸከመችህ ትክሻ - ዛሬ በህይወትህ ከሚያልፈው ሰይፍ ብዛት የተነሳ ግር ብሎህ እንደሆነ ነው እንጅ ያቺ እጅ አትዝልም፡፡ ትክሻውም አይደክምም። በክርስቶስ ኢየሱስ ወንድሜ ለሆንከው፥
Ø ወንጌል ብሎ ምቾት፥
Ø ወንጌል ብሎ ድሎት፥
Ø ወንጌል ብሎ ዕረፍት፥
Ø ወንጌል ብሎ ሰላም፥
Ø ወንጌል ብሎ ባለጠግነት፥
Ø ወንጌል ብሎ ጌትነት እንደሌለ ለእኔም ሆነ ለአንተ የተሰወረ አይደለም።
እንዲህ ስልህ ግን በክርስቶስ ኢየሱስ የሆነው ውስጣዊ ምቾትህ፣ ድሎትህ፣ ዕረፍትህ፣ ሰላምህ፣ ባለጠግነትህ እንደተጠበቁ ናቸው፡፡ ቁምነገሩ፥ በእውነት ያየኸውን አይተህ የወጣህ እንደሆነ ወዳሰብከው ሳትደርስ ሞትም ቢሆን በአንተ ላይ ሥልጣን እንደሌለው አስታውስህ ዘንድ ይህችን ደብዳቤ በሥልጣን ጻፍኩልህ። ዛሬ ባለህበት ሁኔታ፣ መልክና ገጽታ ወደ መቃብር አትወርድም። በውኑ የእግዚአብሔር ጣት የጻፈችው ጽሑፍ ይደመስሰ ዘንድ የተቻለው ፍጥረት ማን ነው? የፈለገው አውሎ ነፋስ ቢነሳ፤ አሁን የምትገኝበት ሁኔታ የፈለገው አሰቃቂና ዘግናኝ ቢመስልም እግዚአብሔር በህይወትህ ወደፃፈልህ ስፍራ ትደርሳለህ። ይህ ሁሉ ወከባ፣ ውጣ ውረድ፣ ወጥመድና አሽክላ ከግብህ የሚያደርስህ ድልድይ እንጅ የጠላት ጦር ወግቶ እንደማይጥልህ እግዚአብሔር ምስክሬ ነው። በላይህ ላይ የፈሰሰው ቅባት፣ በውስጥህ የሚነደው እሳትና የተወለደው አዲስ ሰው (ማንነት) ዒላማውን ሳይመታ እንዲሁ በከንቱ አይመለስም።
ወንድሜ ሆይ! ያለህበት (የምታልፍበት) ህይወት በእግዚአብሔር ዘንድ የተሰወረ አይደለም። ያለ እግዚአብሔር እውቀት የሚሆን አንዳች ነገር የለም። በህመም፣ በማጣት፣ በስደትና በወከባ ውስጥ ያለፈው ጌታ ህመምህ ይገባዋል። በህይወትህ የሆነውና እየሆነ ያለው ገና መሆኑ የማይቀረው ሁሉ የአንተም የእግዚአብሔርም ጥፋት አይደለም። የመረጥከው ህይወትና ያየኸውን ራዕይ መንገድ እንጅ።
Ø የእኔና የአንተ ሀብት፣ ንብረት፣ ጌጥ የእግዚአብሔር ህዝብ ዕረፍትና ደስታ ነው።
Ø የእኔና የአንተ ደስታ ወንጌል ለፍጥረት ሁሉ መስበክ መናገርና ማስተማር ነው።
Ø የእኔና የአንተ ዕረፍት የጠፉትን ነፍሳት እያነፈነፍን መፈለግና ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መጨመር ነው።
Ø የእኔና የአንተ ደመወዝ ብርና ወርቅ ሳይሆን ወንጌል የሚያስከፍለውን ዋጋ (መስዋዕትነት) ደስ እያለን መቀበል ነው። ቁልቁል ተደፍተን መገረፍ ካለብንም ያ ነው የእኔና የአንተ ደመወዝ።
Ø የእኔና የአንተ ክብር በሰዎች ዘንድ ስምና ዝና ማትረፍ ሳይሆን በጊዜውም አለጊዜውም እግዚአብሔር ባስቀመጠን ስፍራ ላይ በታማኝነት ፀንተን መቆም ነው።
የእግዚአብሔር ባሪያ ሆይ! ሐዋርያት ለፍጥረት የሰበኩት፣ ያስተማሩትና የመሰከሩለትን ወንጌል ሳትበርዝ፣ ሳትሸቃቅጥና ሳታመነታ እግዚአብሔር እንዳስተማረህ እንዲሁ ተሸክመህ እስከ ዞርክና እስከ መሰከርክ ድረስ ወድቀህ መነሳትህ ነው የማይቀረው እንጅ መውደቅህ ግድ ነው። ካርታህ እስኪጠፋብህ ድረስ ከመከራ ብዛት የተነሳ መድቀቅህ የማይቀር ነው። ሰዎች ከወይን ጠጅ ብዛት የተንሳ ሲሰክሩ አንተ ደግሞ በችግር ብዛት መንገዳገድህ አይቀርም። ሰዎች ምግብን በየዓይነቱ እያማረጡ ሲመገቡ አንተ ደግሞ የመከራ በየዓይነቱ ይፈራረቅብህ፣ ያጣድፍህና እያገለባበጠ ይጠብስህ ዘንድ ግድ ነው። በዚያን ጊዜ ህይወትም ብትሆን ተጸየፋኸለች። በዚያ ወቅት ወዳጅ ዘመዶችህ ቀርቶ አባትና እናትህም አይፈልጉህም። ታድያ በዚያ ፈታኝ ሰዓት (በችግርህ ጊዜ) ከልብ የሆነ መሳቅና መደሰት ካልተማርክ ህይወትን አልኖርካትም። ለወደፊቱም ቢሆን አታጣጥማትም።
ወንድሜ ሆይ! እንደ እግዚአብሔር ያለ ቃል ኪዳኑን የማይረሳ መልካም ማንም የለም! እግዚአብሔር በእውነትና በጽድቅ ለሚያገለግሉት (ላገለገሉት) ለባሪያዎቹ ታማኝ አምላክ ነው። የባሪያውን አጥንት ቆጥሮ ዘሮቹን የሚባርክ፣ የሚዘክር፣ የሚታደግ፣ ከፍ ከፍ የሚያደርግ፣ የሚክስ እንደ እግዚአብሔር ያለ አምላክ ማንም የለም። በምንም ዓይነት ሁኔታ ብትዘፈቅም በጌታ ዘወትር ደስ ሊልህ ይገባል። በችግርህ ጊዜ እርዳታ ፍለጋ ሳይሆን ስለሚገባ ብቻ ዝማሬና ምስጋና ከንደበትህ አይታጣ።
ወንድሜ ሆይ! የሚላስና የሚቀመስ ብታጣም እግዚአብሔር ለዚህ ልዩ (ዓለም የማትሰጠው) የህይወት ትምህርት ስላጨህ ብቻ ለእግዚአብሔር የሚገባ አምልኮና ውዳሴ አይጉደልብህ። ሰዎች ፊትህን ካነበቡ አይቀር ብርና ወርቅ የማይገዛውን የሚቀናለትን ሰማያዊ ደስታ ከፊትህ ያንብቡ። ስዎች በኑሮህ ይገረሙ። ያን ጊዜ አንተ በቤትህ ተቀምጠ ሳለህ በአንተ ላይ እጆቻቸውን ባነሱ በአሳዳጆችህ ቤትና ጤና ደግሞ ሁከትና መታወክ ይሆናል።
በመጨረሻ አንዲት መልካም ዜና ላካፍልህና ለዛሬው በዚህ ልለይህ። ተስፋ አስቆራጭ በሚመስሉ ሁኔታዎች ብታልፍም የታመንከው እግዚአብሔር በዚያ ሁኔታ ውስጥ መልካም ነው። እነዚህ የመከራ ቀናቶች እንደ ጥላ ማለፋቸው የማይቀር ነው። ታድያ በእነዚህ ቀናቶች ከእግዚአብሔር መማር ያለብህና የሚገባህ የህይወት ትምህርት እንዳያመልጥህና እንዳያልፍህ ትተጋ ዘንድ ደግሜ ላስታውስህ እወዳለሁ። ይህ ቀን ሲያልፍ በእግዚአብሔርም በሰውም ፊት የምትመሰክረው ነገር ይኖርሃል። በተረፈ ሰው ቀብሮ እንደማይቀብርህ፤ ይዞም እንደማይዝህ ሌላ ቢቀር እኔ ምስክር ልሁንህ። ሰዎች ዓይናቸው እያየች ቁልቁል እንደወረድክ እጆቻቸውን በአፋቸው እስኪጭኑ ድረስ ደግሞ ከፍታህን ያያሉ። ጠላቶችህ ይህችን ዕለት ያዩ ዘንድ (ለምስክርነት) ሞትም ቢሆን ይጸየፋቸዋል።  ለእግዚአብሔር ክብር ይዘገያሉ።

የእግዚአብሔር ምህረትና ጸጋ ከአንተ ጋር ይሁን

10 comments:

 1. ወልዴ በጣም የሚያበረታታ መልእክት ስላመጣህልን እናመሰግናለን ስነ ፅሑፍህም በጣም ተሻሽሏል አሜሪካ ስትሄድ ትቀየራለህ ብዬ ፈርቼ ነበር ግን በወንጌል ላይ ያለው አቋምህ እነደዚያው ሆኖ ስላገኘሁት ራሴን ታዘብሁት እኔ ደክሜያለሁ እንደገና አነቃሃኝ። አሁን እንደገና በድፍረት ለወንጌል እነሳለሁ ግን እንደዚህ ያሉ ፅሁፎችን እየፃፍህ አበረታታን።

  ReplyDelete
 2. TRUE!! THANK YOU VERY MUCH AND IT IS VERY ENCOURAGING!!! WE NEED TO HEAR MORE OF THIS TO BE STRONG, TO STICK TO OUR LORD JESUS CHRIST, JOHN 14:6 Jesus answered, "I am the way and the truth and the life. No one comes to the Father except through me."

  ReplyDelete
 3. Wendma hoy mikirh tiru newu please continewu

  ReplyDelete

 4. may the Almighty God bless you
  it is right and it true. in the name of the our Lord Jesus Christ, I thank you very much and please keep going writing kind of this article With Christ Love

  ReplyDelete
 5. ምን አድርገህ ከዚህ አገር እንደሄድክ ታውቃለህ አይደል? የአራዳ ምድብ ችሎት የሚጠብቅህ የወንጀል ፋይልፋ
  አስታው! ለወንጌል ብለህ የተሰደድክ ሳይሆን ወንጀለኛ ሆነህ ነው!
  መልካም የንስሐ ጊዜ::

  ReplyDelete
 6. “አባ ሰላማዎች” ስለማኅበረ ቅዱሳን የሚዘገብ ነገር ጠፋ፤ ዝም አላችሁሳ፤ ምንድን ነው? ከቤተ ክህነት ወሬ ታጣ? ማኅበሩን አዘግታችሁ፤ የቤተክርስቲያኒቷን ምዕመናን ለማጋዝ ወደምትሹት የፕሮቴስታን ስብከታችሁ ገባችሁሳ፡፡

  ዛሬ ግን ተመችታችሁኝ ነበር፡፡ ግን ይህንን ጽሑፍ ገድረ ገጻችሁ ላይ ስላገኘሁት ፕሮቴስታንት ፕሮቴስታን ሸተተኝ፤ ይቅርታ ለዛ ነው፡፡ ያ ማነው ከናንተ ጋር ሲጣላ “ሰዶማዊ ነው” ያላችሁት ..... እሱ፣ ሲሰብክ ልክ እንደዚህ ነው፡፡ በስተመጨረሻ ማኅበረ ቅዱሳን ሲነቃበት ቤተ ክርስቲያኒቷን አይንሽ ላፈር ያላት እሱ.. እንዲህ ነበር በአስራ ምናምን መጽሐፍቶቹ ሲሰብክ የነበረው፡፡ አይዟህ፣ ድነሀል፣ ተፈውሰሀል፣ ቀሎልሀል፣ ኮረብታው ሜዳ ሆኗል፣ ነበልባሉ እሳት ተፍቷል፣ ተምዘግዛጊው ሚሳኤል ጨረፍ ሳያደርግህ አልፏሀል፣ ቀና በል፣ ሰላምህ ተመልሷል... ምናምን ምና ምን እያለ ሰው ኃጥያቱን ተናዞ፣ ንሰሐ እንዳይገባ የማያደርግ ጽሑፍ እየጻፋችሁ፡፡ አጽናኝ መስሎ ጎታች አትሁኑ፡፡ በጎሳና በሙስና ተተብትባ ወደኋላ እየሄደች ያለችውን ቤተ ክርስቲያን እንወክላልን ካላችሁ፤ ተነሱና ውክልናችሁን አሳዩን፡፡ ሰውን እያቆሰላችሁና ሰው ባልዋለበት እየዋላችሁ ስላንድ ማኅበር አመጽ እንድንወጣ ከምትነዘንዙህን እስቲ ሥራችሁን እንየው፡፡ አሁን በያዛችሁት መንገድ ግን ዕሩቅ ምትሄዱ አይመስለኝም፡፡

  እንደሰነፍ እረኛ ከሩቅ ለመመለስ እትሞክሩ... ጨረስኩ!

  ReplyDelete
 7. የማከብርና የምወድህ ወንድሜ ሙለር!!!

  ጌታ በቃሉ የሚከተለውን ይለናልና የመንፈስ አንድነትን ጠብቀን እንበርታ፡

  1/ ያላረፈ ወገን/ሕዝብ/አገር አለንና ያንተና የእኔ እረፍት ትርጉም እንዲኖረው ለማሳረፍ ተጠርተናልና አንዘናጋ ወይም ቸል አንበል አንዛል /ኢያሱ 1፡15/

  2/ በጌታ የተቀበልኸውን አገልግሎት እንድትፈጽመው ተጠንቀቅ በሉልኝ /ቆላ 4፡17/

  ስለዚህ በሌሎቻችን ዘንድ የማይገኘውን የተሰጠህን ልዩና ውብ ጸጋ ለወገናችን ማረፍ ስትል ሥራ ላይ ለማዋል ትጋ ትጋ ትጋ!

  እግዚአብሔር አምላክ በአሜሪካ የስልጣኔ ስልጡን ሰይጣን
  ለሌሎች ጥቅም ከሰማይ የተሰጠህን ጸጋ እንዳይላጨው ንቃበት።

  በጌታ ፍቅር

  ሕሊና ነኝ

  ReplyDelete
 8. we have passed through fire and storm! and we came out alive. How could i came out untouched from those fierce battles! What a mighty Lord we are worshiping! thank you Lord for the suffering it helps me to be humble and compassionate. Now my soul knows very well who the true shepherd is. i run to Christ my escaping rock. God bless you brother! i smell a fragrance of life from your life (script). You shared your life and it lifts me up. we are called to witness the life we taste and the Lord we see and touch!

  ReplyDelete