Monday, June 27, 2016

ሰማዕትነት በክርስቶስ ስም እንጂ በማርያም ስም ወይም በእምነት ተቋም ስም የለምከዘሩባቤል
በክርስትና ትምህርት መሠረት ሰማዕትነት በክርስቶስ አምነው የዳኑ ክርስቲያኖች ስለ ክርስቶስ ሲመሰክሩ በክርስቶስ ስም የሚቀበሉት መከራ ነው፡፡ ጌታም በሰው ፊት ለሚመሰክርልኝ ሁሉ እኔ ደግሞ በሰማያት ባለው በአባቴ ፊት እመሰክርለታለሁ፤” (ማቴ. 10፡32) ባለው መሠረት የሚፈጸም የሕይወት መሥዋዕትነትን የሚጠይቅ ምስክርነት ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የመጀመሪያውን ሰማዕትነት የተቀበለው ቅዱስ እስጢፋኖስ ነው፡፡ ከእርሱም በኋላ ብዙዎች በዚሁ የምስክርነት መንገድ ስለ ክርስቶስ ስም ልዩ ልዩ መከራዎችን በመቀበል ሰማዕትነትን እንደ ተቀበሉ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ያስረዳል፡፡ ይሁን እንጂ ሰማዕትነት ከጊዜ ወደ ጊዜ ትርጉሙ እየ ሰፋና እየ ተለዋወጠ በመሄዱ ስለ ክርስቶስ ስም ብቻ ሳይሆን በሌላም ምክንያት ሁሉ እስከ ሕይወት መሥዋዕትነት የደረሰ ዋጋ የሚከፍሉ ሰዎችም ሰማዕታት እየተባሉ ይጠራሉ፡፡ ለምሳሌ በፖለቲካው መድረክ ስለ አገር ነጻነት በተለያየ ጊዜ መሥዋዕትነትን የከፈሉ ሰዎች ሰማዕታት እየተባሉ ይጠራሉ፡፡ ይህ ግን በዚያው በፖለቲካው መድረክ እንጂ በክርስትና ውስጥ ስፍራ ያለው አይደለም፡፡ ምክንያቱም በክርስትና ውስጥ ያሉ ሰማዕታት ሰማዕትነትን የሚቀበሉበት ብቸኛው ምክንያት በክርስቶስ ስም ስላመኑና ስለ ክርስቶስ ስም ነው፡፡ ቅዳሴውም “በአሚነ ዚኣሁ ሰማዕታት ከዓዉ ደሞሙ በእንቲኣሁ” ትርጉም፡- “ሰማዕታት እርሱን በማመን ደማቸውን ስለ እርሱ አፈሰሱ”  ይላል፡፡

በክርስትና ዐውድ ሰማዕትነት ይህ ሆኖ ሳለ ከዚህ ውጪ ሰማዕትነት እንዳለ የሚሰብኩና በልዩ ልዩ መከራ ውስጥ የሚያልፉ ሰዎችን “ሰማዕታት” እያሉ የሚሰይሙ ሞልተዋል፡፡ ቁም ነገሩ ሰዎቹን ሰማዕት ለማለት ሰዎቹ መከራውን የተቀበሉት ስለ ክርስቶስ ሲመሰክሩ ነው? እና መከራው የደረሰባቸው በክርስቶስ ስም ነው? የሚሉት ወሳኝ ነጥቦች ከግምት መግባት አለባቸው፡፡ ይህን ለማለት ያነሣሣኝ ሰሞኑን በሐራ ብሎግ ላይ ያበብኩት ጽሑፍ ነው፡፡ የጽሑፉ ርእስ “ስለ ድንግል ማርያም ፍቅር የተመተረውን የእናት ወሰን የለሽ ፈቃዱን እጅ አየሁት፤ የሰማዕትነት ቋጠሮ ነው፤ ንሥኡ ፍሬ ሃይማኖት!” የሚል ነው፡፡ ጽሑፉ በብዙ ሕጸጾች የተሞላ ቢሆንም እኔ ግን በአንዱ ጉዳይ ላይ ብቻ ነው የማተረኩረው፡፡ በጽሑፉ ውስጥ ጉዳቱ የደረሰባቸው አንዲቱ ምእመን “በቀዶ ሕክምና የማይመለሰውን የግራ እጃቸውን ስለ ተዋሕዶ ሃይማኖታቸው እና ስለ ድንግል ማርያም ስም ሳይመለስላቸው ዐጡት፤” ይላል፡፡ ይህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት የሌለው መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሰማዕትነት ከሚያስተምረው ውጪ የሆነ “ሰማዕትነት” ነው፡፡

Saturday, June 25, 2016

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የ24 ሰዓት የቴሌቪዥን ፕሮግራሟ መጀመሩ ተበሠረ

Read in PDF

ቤተ ክርስቲያኒቱ የ24 የቴሌቪዥን አገለግሎት መጀመሯ ተበሠረ፡፡ ሰኔ 16/2008 ቅዱስ ፓትርያርኩ ባሰሙት ንግግር የቴሌቪዥን ሥርጭቱ የተበሠረ ሲሆን፣ የንግግራቸው መጀመሪያ ያደረጉት ቃለ ወንጌል ‹‹አማን አማን እብለክሙ ዘይሰምዕ ቃልየ ወየአምን በዘፈነወኒ ይረክብ ሕይወተ ዘለዓለም፤ እውነት እውነት እላችኋለሁ ቃሌን የሚሰማ በላከኝም የሚያምን የዘለዓለም ሕይወትን ያገኛል፤ ከሞትም ወደ ሕይወት ተሻገረ እንጂ ወደ ፍርድ አይሄድም›› (ዮሐ. 524) የሚል ነው፡፡ መልእክቱ ለሰው የዘላለምን ሕይወት ለማግኘት፣ ከሞት ወደ ሕይወት ለመሸጋገርና ወደፍርድ ከመሄድ ለመዳን ቃሉን መስማት ወሳኝ መሆኑን የሚያስገነዘብ የጌታችን ቃል ነው፡፡ በዚህ ቃል ንግግራቸውን የጀመሩት ፓትርያርኩ ምእመናንንና ምእመናትን በሚዲያ የእግዚአብሔርን ቃል ለመስማት በመብቃታችሁ እንኳን ደስ ያላችሁ በማለት ይህን ያደረገ እግዚአብሔርን “ክብርና ምስጋና፣ አምልኮትና ስግደት ለእርሱ ይሁን” በማለት እግዚአብሔርን ወድሰዋል፡፡

የእግዚአብሔር ቃል ከሁሉ በላይ ነው፤” ያሉት ቅዱስነታቸው የቃሉን ታላቅነትና ሕያውነት ተግባሩንም በጥልቀት ያብራሩ ሲሆን ቃሉ በሰው ሕይወት ውስጥ የሚያከናውነውን ዋና ግብር እንዲህ ሲሉ ገልጠዋል፡፡ ፍጡራንም በእርሱ ሕይወትነት ሕያዋን ሆነው ይኖራሉ፣ ዛሬም ሆነ ወደፊት ሰዎች ከፍርድ ነጻ ሆነው የዘለዓለምን ሕይወት የሚያገኙ ይህንን ቃል በመመገብ ነው፤ ከእግዚአብሔር ቃል ውጭ የሆነ ሕይወት ሊኖር አይችልምና፡፡ ይህ እውነት የታወቀውና ሊታወቅ የሚችለው በእግዚአብሔር መገለጥ ብቻ ነው፤” ከዚህም ንግግራቸው የተከፈተው የቴሌቪዥን ጣቢያ በዋናነት ይህ የእግዚአብሔር ቃል ሊተላለፍበት የሚገባ መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ 

Thursday, June 23, 2016

ማኅበረ ቅዱሳን ወንጌልን ማቆም ያልቻለው ለምንድነው?ምንጭ፦ ደጀ ብርሃን
ከዙፋን (ተስተካክሎ የቀረበ)

ማኅበረ ቅዱሳን ከተመሰረተ 25 አመት ሞላው። ድርጅቱ ከተመሰረተ ጀምሮ የፕሮቴስታንት፣ የካቶሊክና ሌሎች የክርስትና ክፍሎች የወንጌል ስብከት በፊት ከነበራቸው ውስንነት በበለጠ ሲሰፉ እንጂ ሲጠፉ አልታየም።

በተለይም የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አማኞች የሆኑና ቤተክርስቲያኒቱ ከወንጌል ጋር አንዳንዴም ከወንጌል በላይ ስፍራ የምትሰጣቸው ትውፊቶች፣ ድርሳናት፣ ገድላት ከዚያም ባለፈ ልዩ ልዩ አስማትና ተረቶች የእግዚአብሔርን የክብር ስፍራ ወስደውና ጋርደው መገኘታቸውን ያስተዋሉና ከውስጥ የተነሱ የተሃድሶ እንቅስቃሴዎች ከነበሩበት ሁኔታ እየሰፉና እያደጉ መጥተዋል። ግንዛቤያቸውን በሁሉም ዘንድ በማዳረስ ረገድ ሰፊ ተቀባይነት በማግኘታቸው ከነበሩበት የተወሰነ ሁኔታ ወጥተው ዛሬ ከማኅበሩ 25 ዓመታት ቁጥጥር ውጪ ናቸው። ማኅበሩ የተሐድሶ እንቅስቃሴን ለመጨፍለቅ ያልቆፈረው ጉድጓድ፣ ያልፈነቀለው ድንጋይ አልነበረም። ከንግድ ድርጅቶቹ የሚያገኘውን ግዙፍ ገንዘብ፣ የሰው ኃይልና ማቴሪያልም ጭምር ለዚህ ስራ ያውላል። በተሐድሶ ላይ ግንዛቤ ማስጨበጫ፣ ዐውደ ርእይ፣ ስብሰባ፣ ወርክሾኘ፣ በንግሥ በዓላት፣ በዐውደ ምሕረት፣ በፅሑፍ፣ በምስል ወዘተ ልዩ ልዩ መንገዶች ህዝቡን ያስተምራል፣ ያስጠነቅቃል ቪዲዮ ይበትናል፣ ካሴት ይለቃል፣ በራሪ ወረቀቶችን ያሰራጫል። በዩኒቨርሲቲዎች፣ በኮሌጆች፣ በሕጻናት፣ በወጣቶች፣ በጎልማሶች፣ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት ባሉ ሰንበት / ቤት ተማሪዎች ላይ ሥር ነቀል ለውጥ ለማምጣት ሰርቷል። ተጽእኖውና መልእክቱ ያልገባበት ቤት የለም። ተሐድሶ፣ ሃራጥቃ፣ መናፍቃን፣ የአውሬው ተከታዮች፣ ፀረ ማርያሞች፣ ጠላቶች፣ ነካሾች፣ ቡችሎችወዘተ ብዙ ስም አውጥቶ ለማስጠላት ሞክሯል። በስለላ፣ በክትትል፣ በጥርጠራና በድጋፍ አብሮት ያልቆመውን ሁሉ ስም እየለጠፈ በማባረርና በማስፈራራት ብዙ ቢጓዝም ትምህርተ ተሐድሶ ግን ሊቀንስ አልቻለም። ከዚህ ሁሉ ልፋት በኋላ በውጤቱም 25 አመት በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ታይቶ በማታወቅ መልኩ 15 ሚሊዮን ህዝብ በላይ ከኦርቶዶክስ አካውንት ወደ ፕሮቴስታንት እምነት ጎርፏል።

Tuesday, June 21, 2016

ጵጵስና ወደ ቀደመ ክብሩ ተመለሰ


 Read in PDF
ከዚህ በፊት እንደ ዘገብነው ሁለቱ ቆሞሳት ማለት አባ አቢዩና አባ ሀብተ ኢየሱስ በቪዛ ምክንያት ከመዘግየታቸው በቀር ስድስቱ ለጵጵስና ማዕረግ በቅተዋል። ጵጵስና እንደ ሰባራ እቃ ወደ ታች በተጣለበት በዚህ ዘመን የነአባ ወልደ ትንሣኤ አያልነህ መሾም በሰባ አምስት ፐርሰንት ወደ ክብሩ ተመልሷል ማለት ይቻላል። የኦርቶዶክስ ምእመናን ለተሰጠው የጵጵስና ማዕረግ በደስታ ሲፈነጥዙ የታየበት ታሪካዊ ክስተት ነው ብንል ማጋነን አይሆንም። አንድ የከበረ ነገር በተገቢው ሥፍራ ሲቀመጥ ተገቢ ክብር ይሰጠዋል። የጵጵስናን ክህነት ለማክበር የሚያስችል በጎ እርምጃ ተወስዷል የሚል እምነት አለን። ይህን ያልንበት ምክንያታችንና የተሾሙትን ኤጲስ ቆጶሳት ማንነት እንደሚከተለው ለማቅረብ እንሞክራለን፡፡
1ኛ አባ ወልደ ትንሣኤ አያልነህ ባሳደጓቸው ባባታቸው ስም አባ በርናባስ ተብለዋል። በ1954 ዓ.ም. የተወለዱት አባ ወልደ ትንሣኤ አያልነህ ከጎንደሩ የኔታ ዲበ ኩሉ ከፊደል ጀምሮ የሚሰጠውን ጸዋትወ ዜማ፤ ከአባ ወልደ ትንሣኤ ጥሩነህ እና ከጎጃሙ መምህር ከተክለ ጻድቅ ቅዳሴ ተምረዋል። ከጎንደሩ  የኔታ ጥበቡና ከዝዋዩ መምህር አበበ ቅኔ ተምረዋል። በዘመናዊ ትምህርት ደግሞ በእንፍራዝና በፋሲለ ደስ ትምህርት ቤቶች የ1ኛ እና 2ኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቀዋል። በዝዋይና በቅዱስ ጳውሎስ ከፍተኛ ት/ቤት የመጻሕፍት ትምህርት ተምረው በዲፕሎማ ተመረቅዋል።
 የምንኩስናን ሕይወት የጀመሩት በአሰብ ራስ ገዝ በ1978 ዓ.ም በአቡነ በርናባስ እጅ እንደነበር ታሪካቸው ያስረዳል። አባ ወልደ ትንሣኤ የሚታወቁት ወንጌልን በመስበክ ነው የስብከት አያያዛቸውም ከቀድሞው ይልቅ እየቆየ እየበሰለ እያደገና እያፈራ የመጣ መሆኑን የሚከታተሉ ሰዎች ይናገራሉ። በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በመከራና በከባድ ፈተና ወንጌልን ከሰበኩ ሰዎች ውስጥ የመጀመሪያውና ምሳሌ የሚሆኑ ናቸው። ብዙዎች ከመከራው የተነሣ ኦርቶዶክስን እየለቀቁ ጠፍተዋል፣ አንዳንዶች አንገታቸውን ደፍተዋል፣ ሌሎች ከቤታቸው ተቀምጠው አፋቸውን ዘግተዋል። አባ ወልደ ትንሣኤ ግን አንገት ሳይደፉ በማንም ሳያኮርፉ ተልኳቸውን በመፈጸም ሊያቆማቸው የቻለ የለም። የብርታታቸው ምስጢር  ወይም በከሳሾቻቸው ዘንድ መሸነፍ ያልቻሉበት ምክንያት ይላሉ ታዛቢዎች፣ በጣም እምነት ስላላቸው የጌታ ዕርዳታ ያላቸው መሆናቸው፤ ይቅር የማለት ችሎታቸውና በምንም ዓይነት የዚህ ዓለም ነውር የማይያዙ መሆናቸው ነው።

Saturday, June 18, 2016

ሰበር ዜና - በስደተኛው ሲኖዶስ የሚሾሙ ኤጲስ ቆጶሳት ስም ዝርዝር ታወቀበስደተኛው ሲኖዶስ የሚሾሙ ኤጲስ ቆጶሳት ስም ዝርዝር ታወቀ። አባ ወልደ ትንሣኤ አያልነህና ዶ/ር አባ ገብረ ሥላሴ ጥበቡ ከሚሾሙት መካከል ናቸው።
እነዶክተር አምባቸውና መሰሎቻቸው በከፍተኛ ድንጋጤ ላይ ወድቀዋል። የአባ ወልደ ትንሣኤ እና የአባ ገ/ ሥላሴ መሾም እውነተኛ የቤተ ክርስቲያንን ልጆች ያስደሰተ ሲሆን በቤተ ክርስቲያን ሊነግዱ ያሰቡ ቡድኖች ሁሉ ግን በተስፋ መቁረጥ እያለቃቀሱ ነው። ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ ተቃዋሚዎችን አሁን ስለነቃሁባችሁ ዘወር በሉ በማለት በአቋማቸው ጸንተዋል፡፡ እነ ዶክተር ነጋ የራሳቸውን ጀሌ መነኮሳትን ጳጳስ በማድረግ ሲኖዶሱን ለመቆጣጠር ያቀዱትት እቅድ ነበር፣ ጳጳሳት ይሾሙ የሚለውን ሐሳብ ያመጡትም እነርሱ ነበሩ፡፡ እግዚአብሔር ግን ከነእርሱ ስለቀደመና ያላሰቧቸው ሰዎች ስለተሾሙ ራሳቸው ያመጡትን ሐሳብ ራሳቸው ተቃውመውታል። እነ አቶ ዘውገ ደግሞ የሲያትሉን አባ ገብረ ሥላሴን ተቃውመው ደብዳቤ ጽፈዋል። ተቃውሞዎች ሁሉ ዋጋ ባለማግኘታቸው ቅዱስ ፓትርያርኩን ጨምሮ  ሁሉም ከየአቅጣጫው በኦክላንድ መካነ ሰላም መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን በመሰባሰብ ፕሮግራሙን በመጠባበቅ ላይ ይገኛል።
በዚህ መሠረት፦
1. አባ ወልደ ትንሣኤ አያልነህ፣ ከሎስ አንጀለስ ድንግል ማርያም
2. አባ ገ/ሥላሴ ጥበቡ፣ ከአትላንታ ቅዱስ ገብርኤል፣
3. አባ ጽጌ ደገፋው፣ ከሎስ አንጀለስ ቅድስት ማርያም፣
4. አባ ሳሙኤል ወንድ ይፍራው ከዴንቨር ቅድስት ማርያም፣ (ደቡብ አፍሪካ የነበሩ ናቸው)
5. አባ አቢዩ ከኡጋንዳ
6. አባ ሀብተ ኢየሱስ ከኖርዌይ
7. አባ ሳሙኤል ከካናዳ ኤድመንተን መድኃኔ አለም
8. አባ ገ/ ሥላሴ  ከሲያትል ቅ/ገብርኤል ይሾማሉ። የኡጋንዳውና የኖርዌዩ ይገኙ አይገኙ አልተረጋገጠም።
ያሁኑ ሹመት የውጩን ሲኖዶስ ጠንካራ ያደርገዋል የሚል ተስፋ ተጥሎበታል። በተለይም ወንጌል በሲኖዶስ ውስጥ ክብር ሊያገኝ ይችላል ተብሎ ይታመናል። ከተራ ቁጥር አንድ እስከ ስድስት ያሉት አባቶች የቤተ ክርስቲያን ታማኞችና የሚገባቸው ናቸው የተባለ ሲሆን ተራ ቁጥር ሰባትና ተራ ቁጥር ስምንት ግን ምን ዓይነት መንፈሳዊ ሕይወት እንዳላቸው ብዙም አልታወቀም፤ እግዚአብሔር ሁሉንም በእውነት እንዲቀባቸው እየጸለይን ጠቅላላ ዝርዝሩን እንደ ደረሰን እናቀርባለን።