Sunday, June 12, 2016

ይድረስ ለዲያቆን ዳንኤል ክብረት-ያንተ ደማስቆ የት ነው?ከጆን ማሞ                                        
ድሮ ባይባልም ከጥቂት ዓመታት በፊት ምላሽ የሚሰጠው ለለየላቸው የመናፍቃን ትምህርት ነበር። አሁን ግን ኦርቶዶክሳዊ ለኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮ ምላሽ የምንሰጥበት ዘመን ሊሆን ሁኔታዎች አስገድደዋል። ይሄ ደግሞ የቤተክርስቲያንዋ አስተምህሮ ወጥነት (ይጠብቃል) የጎደለው ብቻ ሳይሆን የቤተክርስቲያኗን ትክክለኛ አስተምህሮ ጠንቅቀው ያላወቁ በልማድ ተተክለው በልማድ የበቀሉ ሰባኪያን የሚዘሩት እንክርዳድ ችግሩን ይበልጥ ውስብስብ አድርጎታል። በዚህም ምእመናን በአንዲት ቤተክርስትያን ሁለት ሦስት ዓይነት ተቃራኒ ትምህርት እየሰሙ ግንባር ቀደም የችግሩ ሰለባ ሲሆኑ ማየት ያማል።
 በክርስቶስ ወንድሜ የሆንከው ዲ.ን ዳንኤል ክብረት ዛሬ ልጽፍልህ ያሰብኩት ጉዳይ ቢኖር በ2005 ዓ.ም. ባሳተምከው “ውዳሴ መስቀል” የትርጉም መጽሐፍ ላይ ነው። መጽሐፉን አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ እንደጻፈው አንተ ከግዕዝ ወደ አማርኛ እንደተረጎምከው ነው የሚገልጸው። ምንም እንኳ አንተ ከግዕዝ ወደ አማርኛ መልስከው ብሎ ለማመን ቢያስቸግርም።  መጽሐፉን ሳነበው ስለክርስቶስ መከራ የሚተርኩ ጥሩ ጥሩ መልእክቶችን የማንበቤን ያህል የዚያኑ ያህል ደግሞ በሕይወቴ እንደዚህ ዓይነት በስህተት የታጨቀ መጽሐፍ አይቼ እስከማላውቅ ድረስ ጽሑፉ የቤተክርስቲያንን አስተምህሮ የሚያፋልስ፣ ቤተክርስቲያኗ የማትለውን እንደምትል ተደርጎ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የማይሄድ ፍጹም ዓይን ያወጣ ስህተት ሆኖ አግኝቸዋለሁ።
 ለመሆኑ አንተ ይሄንን መጽሐፍ በትክክል አባ ጊዮርጊስ ነው የጻፈው ብለህ ታምናለህ? ምናልባት በሳቸው ስም የተጻፈ(ሊነገድበት) ታስቦ ከሆነስ አጣርተሃል? ይኸ ጽሑፍ የያዛቸው አሳቦች ሁሉ ትክክል ናቸው ብለህ ታምናለህ? አባ ጊዮርጊስን በዚህ መጽሐፍ እንመዝናቸው ለሚል ሰው ይሄ መጽሐፍ ሊቅ የሚያስብላቸው (ጻድቅ) የሚያሰኝ ይመስለሃል? /
የዚህ ጽሑፍ ጸሐፊ  በአባ ጊዮርጊስ ሊቅነትም ሆነ ጻድቅነት ያምናል?/
 ምናልባት ለጠየኩህ ጥያቄዎች ሁሉ አሉታዊ መልስ ልትሰጠኝ ትችል ይሆናል። ተረጎምኩ እንጂ ጸሐፊው እኔ አይደለሁም ልትለኝ ትችል ይሆናል። እሱም ጥሩ ነው! መጽሐፉን ከመተርጎምህ በፊት ይሄ መጽሐፍ የቤተክርስቲያንትዋን አስተምህሮ እያፋለሰ እያየህ ለምን ተረጎምከው ታዲያ? ወይስ ፍልሰቱን ትጋራዋለህ? ስህተትን ተርጉመህ ለምን ለሕዝብ ታሰራጫለህ? ወይስ ገንዘብ መሰብሰቢያ ነው? ወይስ የሰው ጆሮ መሳቢያ? ይህን መጽሐፍ ካለበት ጎርጉረህ አውጥህ በአማርኛ ያስነበብከው አንተ ነህ። የአንድን መጽሐፍ ትክክለኛነት ሳታጣራ እንዴት ለሕዝብ ትበትናለህ? ሐዋርያት ካስተማሩት ውጭ የሰማይ መልአክም ቢሆን የተለየ ትምህርት ቢያስተላልፍ መርገም ከሆነ ከዚህ እርግማን ነጻ የሚያወጣ ላንተ የተለየ ፈቃድ የለህም። ገላ 1፡8 ለማንኛውም የዚህ ጽሑፍ አንባብያን ሁሉ ዳንኤልን ጨምሮ ህሊናችሁን ዳኛ አድርጋችሁ ዳንኤል ተረጎምኩት ያለውን ሁሉንም እንኳን ባይሆን የተወሰኑትን እንመልከታቸውና ፍርዱን ለእናንተና ለህሊናችሁ እተወዋለሁ።
 ገጽ 42  “ኦ ኬ ዕፅ ዘአንጠብጠቦ እምኔሁ ደመሕግ ወሥርዓት በደመ አምላኩ ዘቀደሰ ወበማይ  ዘውሕዘ እምገቦ ፈጣሪሁ ዘተጠምቀ” 
 ትርጉም፡ “ ከእርሱ ምእመናንን ለማከም የሚሆን የሕግና የስርአት ደምን ያንጠባጠበ ዕፅ ምን ዓይነት ነው?” ይላል።
እስቲ ልብ በሉ ዕፅ ማለት እንጨት ማለት ነው። ዕፅ መስቀል ስንል የእንጨት መስቀል እያልን ነው። ዳንኤል ስለ እንጨት መስቀሉ ነው የሚተርክልን። አሁን አእምሮ ያለው ሰው የጌታ ደም ከእንጨቱ ጎን ፈለቀ(ተንጠባጠበ) ብሎ ይጽፋል? አሁን ይሄንን ጤነኛ ሰው ያስብለዋል?  አንድ ጸሐፊ ተምሪያለሁ፣ አስተምራለሁ ብሎ ይኸን ከጻፈ ባይማር ምን ሊለን ነበር? ቤተክርስቲያን  ብዙ ጥያቄ በሚነሳባት በአሁኑ ወቅት ሌላ ጥያቄ የሚያስነሣ ነገር መጻፍ ምን ይሉታል?

መጻሕፍት ተባብረው እንደሚሉት የሕይወት ምንጭ ከእንጨቱ አልፈለቀም። የሕይወት ምንጭ ከክርስቶስ ፈለቀ ብትል ምን ይከብደሃል? እስቲ በምሳሌ እንማር። ሙሴ ዓለቱን በበትር ሲመታው ለእስራኤላውያን ውኃ ፈለቀላቸው። ቅዱስ ጳውሎስ “ዓለቱም ክርስቶስ ነበር” እንዳለው 1 ቆሮ 10፡4። ዓለቱ ክርስቶስ፣ ምንጩ ከእርሱ የፈለቀው የሕይወት ውኃ፣ በትሩ የመስቀል ምሳሌ ነው። ውኃው ከዓለቱ እንጂ ከእንጨቱ እንዳልፈለቀ የሕይወትም ምንጭ ከክርስቶስ እንጂ ከመስቀሉ አልፈለቀም። እናም እስራኤል “ አንተ ምንጭ ሆይ ፍለቅ እናንተም ዘምሩለት።” ሲል ተቀኘ። ዘኁ 21፡17 አሁንም ዝማሪያቸው ለምንጩ እንጂ ለበትሩ እዳልሆነ ልብ እንበል። የሕይወት ምንጭ ክርስቶስ ነው። ራዕ 21፡6 “አልፋ ኦሜጋ መጀመሪያም መጨረሻም እኔ ነኝ ለተጠማ የሕይወት ውኃ ምንጭ እንዲሆነው እኔ እሰጠዋለሁ።” ይላል ዮሐ 4፡14 “እኔ ከምሰጠው የሚጠጣ ሁሉ ግን ለዘላለም አይጠማም። እኔ የምሰጠው ውኃ በእርሱ ውስጥ ለዘላለም የሕይወት የውኃ ምንጭ ይሆናል።” አለ እንጅ ከእንጨት ይፈልቃል አላለም። ዳዊትም በመዝሙሩ “የሕይወት ምንጭ ካንተ ነውና በብርሃንህ ብርሃንን እናያለን።” ይላል መዝ 36፡9 ልጁ ሰሎሞንም “ከጉድጓድ ውኃ ከምንጭህ የሚፈልቀውንም ውኃ ጠጣን” ሲል ከጌታ ጎን ስለሚፈልቀው የሕይወት ውኃ አስቀድሞ ነገረን። ምሳ 5፡15 በኤርምያስም “እኔን የሕይወት የሕያውን ምንጭ ትተውኛልና” በማለት መጻሕፍት ተባረው የሕይወት ምንጭ ክርስቶስ መሆኑን ነገሩን እንጂ ዳንኤል እንዳለው አንድም ቦታ
የሕይወት ምንጭ ከመስቀሉ ፈለቀ ብሎ ያስተማረ ነቢይም ሐዋርያም የለም።
ይቀጥላል ዳንኤል ገጽ 64 “ መስቀል በሙሴ እጅ ወደ ውስጥ በተጨመረ ጊዜ መራራውን ውሃ በሱር በረሃ ያጣፈጠ ነው?” ይላል
መስቀል ለመሆኑ በዘመነ ኦሪት እንኳንስ ውኃን ሊያጣፍጥ ይቅርና የርጉማን መሰቀያ አልነበር እንዴ? “በእንጨት ላይ የተሰቀለ በእግዚአብሄር ዘንድ የተረገመ ነው”  ይላል ዘጸ 21፡23 የመስቀል ክብሩ እኮ ክርስቶስ ከተሰቀለበት በሁዋላ እንጂ ከስቅለት በፊት አይደለም። እንዴት ነው አንተ በሙሴ ዘመን መራራውን አጣፈጠ ብለህ ልትተረጎምንልን የቻልከው? ይሄ የቤተክርስቲያን ትምህርት ነው?
ገጽ 44
ኦ.ኬ ዕፅ “ዘኮነ ነቅዓ ወይነ ምስጢር ዘውሕዘ እምኔሁ ምንዛዕ ዘአጺባ አባግዕ ቡሩካን
ትርጉም፡ የሚስጥር ወይን መፍለቂያ የሆነ ዕፅ እንዴት ያለ ነው? ቡሩካን በጎችን ለማጠቢያ የሚሆን ምንጭ ያወጣ?” ይላል
ቡሩካን የሆኑ በጎች ምዕመናንን ከእንጨት መስቀሉ በተገኘው ደም ታጠቡ ብለን እናስተምር? ያጠበን ያነጻን ያዳነን ክርስቶስ እንጂ የእንጨት መስቀሉ ነው ብላ ቤተክርስቲያን አታምንም አላስተማረችምም። ቤተክርስቲያን የከበረው ደሙን በአምሳለ ወይን ሥጋውን በአምሳለ ሕብስት አዘጋጅታ የበጉን ፍሪዳ ትሠዋለች። ዮሐንስ እንዳለው “ ወደሙ ለኢየሱስ ክርስቶስ ያነጻሃነ እምኩሉ ኃጣውኢነ” የልጁ የእየሱስ ክርስቶስ ሥጋና ደም ከኃጢያት ሁሉ ያነጻናል” እንዳለ ያኔ ከኃጢያት እንነጻለን። 1 ዮሐ 1፡7 ይሄ ነው የቤተክርስቲያኗ ትምህርት እንጂ ዳንኤል እንዳለው መስቀሉ ያነጻል ብላ አላስተማረችም። 
ገጽ 44 “ኦ ኬ ዕፅ ዘቀደሳ ለምድር ወአሰቦ ለሰማይ ወባረከ ኩሉ ዓለመ በበረከተ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ”
ትርጉም፡- ምድርን የቀደሳት ሰማይንም ያማተበበት ዓለምንም ሁሉ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም የባረከ ዕጽ እንዴት ያለ ነው”
 ወንድሜ ምድር የተቀደሰችው በክርስቶስ ደም ነው። የአንተ ትርጉም ግን ጭራሽ እንጨት መስቀሉን በሥላሴ ስም ባራኪ አደረግከው። ሕያው ነፍስ ያለው አደረከውኮ? ቤተክርስቲያን እንዲህ ብላም አታስተምርም። የመቀደሳችን ውጤት የክርስቶስ ኢየሲስ ቤዛነት ብቻ ነው። ይሄን ሰዎች ተረት ተረት ቢሉህ ትፈርድባቸዋለህ? አእምሮ ያለው ሰው እንጨት ሰማይንና ምድርን ባረከ(አስታረቀ) ብሎ ያምናል?” ለፈጣሪ መባል ያለበትን ወርቃማ አሳብ ሁሉ ለእንጨት መስጠት ለምን አስፈለገ? አንተን ከእግዜአብሄር ጋር አስታርቆ አልጫውን ሕይወትህን ያጣፈጠ  ሕይወት የሌለው ግዑዝ አካል ነው? ቅዱስ ጳውሎስ ነገር ግን የሆነውን ሁሉ በክርስቶስ ከራሱ ጋር ካስታረቀን” አለ እንጅ የእንጨት መስቀሉን አስታራቂ አድርጎ አላስተማረንም 2ኛ ቆሮ 5፡20 እናም ለምዕመናን የበተንከው መጽሐፍ ከሐዋርያት መጽሐፍ ጋር በእጅጉ ይጣረሳል።
ገጽ 44“ ኦ.ኬ ዕፅ ዘአመሥረታ ለቤተክርስቲያን ዲበ ሃይማኖት ኢየሱስ ክርስቶስ”
ትርጉም፡- ቤተክርስቲያንን በኢየሱስ ክርስቶስ ሃይማኖት ላይ የመሠረታት ዕፅ እንዴት ያለ ነው?
የሰዓታት መጽሐፋችን “ኢሰማዕነ ወርኢነ ወኢነገሩነ አበዊነ” ይላል። አልሰማንም፣ አላየንም አባቶቻችንም አልነገሩንም። ይህ ድርሰት ዳንኤል ላዘጋጀው የትርጉም መጽሐፍ  ትክክለኛው ምላሽ ነው። ቤተክርስቲያንን በክርስቶስ ትምህርት ላይ መሠረታት ለማለት እንኳን ተፈልጎ ቢሆን ያም የሐዋርያት ትምህርት እንጂ ዕፅ መስቀሉ አይደለም። አንድ ግዑዝ አካል እንዴት ቤተክርስቲያንን በክርስቶስ ትምህርት ላይ መሠረታት ይባላል? ህሊና ያለው ሰው እንዴት እንዲህ ይላል?
ገጽ 44 “ኦ.ኬ ዕፅ ዘ አልአሎ ለነጻ ወአጽደቆ ለጊጉዩ ዘአጽንኦ ለድኩም ወኃጣእዮ ለህሙም”
ትርጉም፡- “ደካማውን ያበረታ ሕመምተኛውን ያዳነ ዕፅ እንዴት ያለ ነው?”
እዚህ ጋር አንድ የምጋራህ ሃሳብ አለ። ክርስቲያኖች ደሙ በፈሰሰበት በመስቀሉ  ተሻሽተው፣ ተባርከው ከሕመማቸው ሊድኑ፣ ሊባረኩ፣ ሕመም ካደቀቃቸው ደዌ ሊፈወሱ ይችላሉ። በዚህም ብርታትን ሊያገኙበት ይችላሉ።  ይሁን እንጂ ይሄ ችግር ጊዜያዊ መሆኑን ግን አትርሳ። 
 ከዘለዓለም ህመማችን ፈውስ ያሳረፈን ግን የክርስቶስ ኢየሱስ ቤዛነት ብቻ ነው። ቅዱስ ጳውሎስ “ በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛነት በኩል እንዲየው በጸጋው ይጸድቃሉ” አለ እንጂ በዕፀ መስቀሉ ይጸድቃሉ አላለም። ሮሜ 3፡24
ገጽ 42 “ኦ ኬ ዕፅ ዘአስተባዝሆ ለውሁድ ወአስተጣበቦ ለአብድ”
ትርጉም፡- ጥቂቱን ያበዛ ሰነፉንም ጥበበኛ ያደረገ ዕፅ እንዴት ያለ ነው?
የዳንኤል ዓላማ የክርስቶስ ሥራ ሁሉ ለመስቀሉ እየሰጡ የእግዚአብሔርን ውብ ሥራ ሆን ብሎ ማዳፈን ይመስላል። ጉድ በል ያገሬ ሰው! እዚህም ደርሰናል፤ የእንጨት መስቀል ወይስ ክርስቶስ ሰውን ጠቢብ የሚያደርግ? እኛን ያበዛን እግዚአብሄር ወይስ መስቀል? ልብ ያለው ያስተውል ወዴት እየተሄደ እንደሆነ። ሰዎች ወዴት እየነዱን እንደሆነ ይስተዋል። ይህ መጽሐፍ መስቀል አራቱን የዓለም ማዕዘናት የሚያጠጣ፣ ወደ በጉ ሠርግ ለተጠሩት ሁሉ የሠርግ ልብሳቸው የሰማዕታት የድል አክሊላቸው ሁሉ እንደሆነ ይተርክልናል። እንደ መጽሐፍ የምነቅፍብህ ነገር አለኝ የሚያስብል ብዙ ስህተቶች አጭቆ ይዘዋል። ``ለተርጓሚው`` ለአንተ ዳንኤል ግን አፈርኩብህ።
 “ካህኑ በቅዳሴ “ጥበብሰ መድኃኒነ ውዕቱ” እንዳለው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም። የእግዚአብሄር ኃይልና ጥበብ የሆነው ክርስቶስ ነው።” ብሎ ነው ያስተማረን 1 ቆሮ 1፡24 ዕፅ መስቀሉ ጥበብ ነው ብሎ ያስተማረ አንድም ሐዋርያ የለም። ታዲያ ከተመሠረተው ውጭ ለምን ሌላ መሠረት መጣል አስፈለገ? ወይንስ አንተ “እኔ ከሄድኩ በኋላ ለመንጋው የማይራሩ ጨካኞች ተኩላዎች እንዲገቡባችሁ ደቀመዛሙርትንም ወደ ኋላቸው ይስቡ ዘንድ ጠማማ ነገርን የሚናገሩ ሰዎች በመካከላችሁ እንዲነሱ እኔ አውቃለሁ” ከተባለባቸው ውስጥ ነህ? ሐዋ 20፡29
 መድኃኒታችን ለሐዋርያቱ “ወደረኞቻችሁ ሁሉ ሊቃወሙትና ሊከራከሩት የማይችሉትን አፍና ጥበብ እሰጣችኋለሁ” ነው ያላችው ሉቃ 21፡15 በዚህ መሠረት እስጢፋኖስ በከሳሹቹ ፊት በቆመ ጊዜ “ ይናገርበት የነበረውን ጥበብና መንፈስ ይቃውሙ ዘንድ አልቻሉም” ነው የሚለው ሐዋ 6፡10 ስለዚህ እኛም እንደሐዋርያነቱ “ብቻውን ጥበብ ላለው ለእግዚአብሄር ለኢየሱስ ክርስቶስ እስከ ዘላለም ድረስ ክብር ይሁን” እያልን እንቀኛለን እንጂ እንጨቱን ጥበብ ሰጭ የሚል ውዳሴ የለንም። ሮሜ 16፡27
 ዳንኤል አንተ ያስተላለፍካቸው የስህተት ትምህርቶች በዚህ ቢቆሙ መልካም ነበር። ነገር ግን አልቆሙም። በቃል ያስተላለፍከውንስ የስህተት ትምህርት ልብ ብለኸው ታውቃለህ? አንተ ሰውን “መናፍቅ” እያልክ ታሳድዳለህ አንተ ግን እንክርዳድ እየዘራህ ተመቻችተህ ትኖራለህ። እስኪ አስበው ከዚህ በፊት፡- “አፄ ዘርዓይቆብ ደቂቀ እስጢፋን ያረዳቸው ትክክል ነው። በዚያን ዘመን ሕጉ ስለሚፈቅድለት ነው።” ብለህ ሳታፍርም ሳትፈራም አስተማርክ። ለመሆኑ ለአፄ ዘርዓያዕቆብ ስትመሰክርለት የትኛውን የቤተክርስቲያን መጽሐፍ ዋቢ አድርገህ ነው?
አንዱም የቤተክርስቲያን መጽሐፍ ግድያን አይደግፍም። እና ቤተክርስቲያን ያለ እረኛ ነው ያለችው፤ የሚጠይቀኝ የለም ብለህ ትውልዱ ላይ እንክርዳድ ትዘራበታለህ? አንተ ጻድቅ ያደረከው አፄኮ ዛሬ በሕይወት ቢኖር ኖር በሕግ የሚፈለግ ሰው ነበር። ስንት ንጹሐን የክርስቶስ ባሪያዎችን በክፉ ታሪክ የፈጀ ሰው እንዴት ግድያን ለወጣቶች ታበረታታለህ? በግድያ የተስፋፋ ክርስትናስ አይተህ ታውቃለህ? እንዲህ ከሆነማ ዛሬ ሰይፍ የሚያነሱትም ሰዎች ልክ ናቸው ማለት ነዋ? ደግሞስ ለአፄ ዘርዓያቆብ ይህንን ስላልክላቸው የጠቀምካቸው መሰለህ? በዚህ በሰለጠነ ዘመን ገዳይነቱን ብትሰብክለት እያዋረድከው እንጂ አንዳች ነገር አትጠቅመውም። ክርስትና በፍቅር ላይ እንጂ በሰይፍ ላይ አልቆመችም “ ሰይፈ የሚያነሱ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉ።” በምትለዋ ቤተክርስቲያን አንተ ሰይፍን ታበረታታለህ። ማቴ 25፡52 ታዲያ አንተ የፈለፈልካቸው ተማሪዎችህ በየማህበራዊ ሚዲያው ቄስ ጳጳሱን ሲዘረጥጡ ቢታዩ ምን ይገርማል? አንተ ወጣቶች ላይ በምትዘራው እንክርዳድ የቤተክርስቲያን ሊቃውንት ሲዋረዱ፣ ሲሰደቡ ይኖራሉ። እድሜ ላንተ።
ዛሬ ያንተ ተከታዮች አጼ ዘርአያዕቆብ ልክ ነው ያደረገው ስለተባሉ መናፍቅ መስሎ የታያቸውን ሰው እንዴት በስድብ እርቃኑን እንደሚያስቀሩት፣ እንዴት  እንደሚያጠቁት፣ እንዴት ከሰው እንደሚያገሉት  እንጂ እንደሊቃውንት አበው አንድን ሰው መጽሐፍ ቅዱስ ገልጠው እንኩዋንስ ሊያስተምሩት አስበውትም አያውቁም።  ግን የዘራኸውን ታጭዳለህ።
 የሰው ማንነቱ ከሚዘራው ብቻ ሳይሆን ከሚለቅመውም ፍሬ ነውና በየፌስቡኩ ጳጳስ የሚዘረጥጡት ተማሪዎችህ ያንተን ማንነት በደንብ ይገልጡታል። የክፉ ዛፍ ውጤትነታቸውን ቀን በቀን እያሳዩን ነው። ቤተክርስቲያን እነዚህን በማፍራትዋ በእውነት ሊለቀስላት ይገባል።
የእንክርዳድህ ስልታዊነት

የሰውን ስሜት እየፈለገ የሚጮህ የጠላ ቤት አዝማሪ እንጅ ሰባኪ የሰውን ስሜት እየተከተለ አይጽፍም። አዝማሪ ሰው የሚወድለትን ብቻ ነው የሚያቀነቅነው። እውነተኛ ሰባኪ ግን የእግዚአብሄር አሳብ ይሁን እንጅ ሰው ለመስማት የማይፈልገውንም እንኩዋን ተናግሮ ይወርዳል እንጅ በእግዚአብሄር ቃል ላይ አይሸቅጥም።
 ብዙ ጊዜ “አንድ ሞኝ የተከለውን 50 ሊቃውንት አይነቅሉትም” እያልክ ታስተምራለህ። አንተስ የምትተክለውን እንክርዳድ ማን ይንቀለው? ያንተን ተረት ተረት ማን ያስተካክለው? ይሄም አንሶ የአንተን ወፍ ዘራሽ ትምህርት ያልተቀበለውን መናፍቅ እያልክ ታሳድዳለህ። አልቀረብህም። ቅዱስ ጳውሎስ ለልጁ ለቲቶ “ ስለ ነውረኛ ረብ የማይገባውን እያስተማሩ ቤቶችን በሞላው ስለሚገለብጡ አፋቸውን መዝጋት ይገባል።” እንዳለው ከዚህ በኋላ አንተም ሆንክ መሰሎችህ ለምትዘሩት እንክርዳዳችሁ ሁሉ አፍ የሚዘጋ የብዕራችንን ሰይፍ ልንመዝ እንገደዳለን። ይህንን የምናደርገው ጠያቂም ተጠያቂም በሌለበት፣ እረኛው በተኛበት ቤተክርስቲያን የጥፋታችሁ ሰለባ ስለምትሆነው ቤተክርስቲያን ስንል ይህን እናደርጋለን። ቲቶ 1፡11
 እንግዲህ ምን እንላለን? በጽሑፍና በአስተምሕሮቶችህ ቤተክርስቲያን የማትለውን ብዙ ነገር ለትውልድ እያሰራጨህ ነው። በነቢያት ዘመን እግዚአብሄር ያላለውን “አለ” እያሉ የሕዝብን ቀልብ የሚቆጣጠሩ ሐሰተኛ ነቢያት በዚያን ዘመን በሕዝቡ ላይ ነግሠው ነበር። በዚህም የኤርምያስ  ልብ በብርቱ ተሰብሮ ነበር። ስለ ነቢያት ልቤ በውስጤ ተሰብሯል። አጥንቶቼም ሁሉ ታውከዋል ከእግዜአብሄርም የተነሣ ከቅዱስ ቃሉም የተነሣ የወይን ጠጅ እንዳሸነፈው እንደ ሰካራም ሰው ሆኛለሁ” ይላል ኤር 23፡9 እንዳንተ ቅዱስ ቃሉን በዘመኑ የሚያጣምሙ ነበሩ የኤርምያስን ልብ የሰበሩት።
 በእውነት የክርስቶስን የስቃዩን ውጤት ለእንጨት ሰጥተህ ጌታን ስትጋርደው ልብ ይሰብራል። አውቃለሁ በተረት ተረቶችህ ብዙ ተከታይ አትርፍሃል ግን ፍጻሜው ምን ይመስልሃል? ኤርምያስ “ነቢያት በሐሰት ትንቢት ይናገራሉ። ካህናት በእነዚህ እጅ ይገዛሉ። ሕዝቤም እንዲህ ያለውን ነገር ይወዳሉ በፍጻሜአቸውስ ምን ታደርጋላችሁ” ያላል። ኤር 5፡31 እኔስ ለአንተና አምነውህ ለሚከተሉህ መጨረሻ አዘንኩላቸው። ወደድክም ጠላህም ግን አንተ የምታስፋፋው ተረታ ተረትና የአፄ ዘርዓያዕቆብ ትምህርት አሁን መሽቶበታል። ቤተክርስቲያን በደሙ በመሠረታት በኢየሱስ ክርስቶስ ወርቃማ ትምህርት እንጅ በነፍሰ በላ ትምህርት አትመራም።
 ኣስቲ አስበው ከእንጨት ደም ፈሰሰ ብለህ ታሰራጫለህ? ምን ለማለት ፈልገህ ነው? ከክርስቶስ ጎን ደም ፈሰሰ ብትል ከበደህ? ወይስ የአንተ ዓላማ ክርስቶስን መጋረድም ማሳደድም ነው? ቤተክርስቲያን ጥያቄ እየጎረፈባት ባለበት በዚህ ዘመን አንተ ደግሞ ለምን ሌላ ጥያቄ ልታስነሳባት ፈለግህ? ለምን የማትለውን እንደምትል አድርገህ ጣት ታስቀስርባታለህ?
ቤተክርስቲያን በመናፍቃን ብትተች አንተ ምን ትጠቀማለህ? ወይስ ተቆርቋሪ ከእኔ በቀር ላሳር እያልክ  ከጀርባህ ሌላ አጀንዳ ሰንቀሃል? ያልታረመ ነገር እያሰራጨህ እራስህን የሃይማኖት አርበኛ ስታደርግ ማፈር ነበረብህ።  ወደድክም ጠላህም አንተ ነህ እንጂ ይኸን ያልከው ቤተክርስቲያኗ ከእንጨት በፈሰሰ ደም ድኛለሁ ብላ ማስተማር ቀርቶ አስባውም አታውቅ። አንተ እገሌ ከሚባል መጽሐፍ አገኘሁ ልትል ትችላለህ። እሱ ያንተ የቤት ሥራ ነው። ያልታረመ ነገር ተርጉመህ ለሕዝብ አንብቡት ይሄ የቤተክርስቲያን ትምህርት ነው ብለህ እስካቀረብከው ድረስ ግን ተጠያቂው አንተ ነህ። ደግሞም ያወጣኸው ብታምንበት እንጅ ባታምንበት አይደለም። እና በእንጨት ነው የዳንከው ማለት ነው? መሥዋዕቱ ሳይሆን መሠዊያው ነው ያዳነህ ማለት ነው? ትንሽ እንኳን ሰው ይታዘበኛል አትልም?
 አንተ “ኦርጋን ቤተክርስቲያን ለምን ገባ” ብለህ ቡራ ከረዩ ትላለህ። እስኪ አስበው አንተ የተሳሳትከው ስህተት ነው ወይስ ኦረጋን ነው ክርስቶስን የሚያሳዝነው። የትኛው ነው ሰውን ከቤተክርስቲያን የሚያስኮበልለው? ላንተ ኦርጋን ቁም ነገር ነው በቃ? የዕቃን ጉዳይ የዶግማ ያህል ትከራከርበታለህ። “ከእንጨት የሕይወት ውኃ ፈለቀ” ስትል ግን ቅር አይልህም።
በዚህም ላይ ያንተን ድፍረት ያልተጋሩልህን ሰዎች  መናፍቅ እያልክ አረጋውያንን ጳጳስ ሳይቀር ትዘረጥጣለህ። ለመሆኑ ኦርጋን ይሄን ያህል የሚያሰድብ አጀንዳ ነው? በዚህ ምክንያት ሰው መናፍቅ ሊባል ይገባል? ያንተ የእውቀት ጫፍ እዚህ ድረስ ነው በቃ? ይሄ ነው ሙዓዘ ጥበብነት? ስለዚህ በኦርጋን የሚዘምሩ እህት አብያተ ክርስትያናት ሁሉ መናፍቅ ናቸው ማለት ነው? ደግሞስ የቤተክርስቲያን ስርአት የሚደነግገው ዲያቆን ነው ወይስ ጳጳስ? እግር ስትሆን እራስን ልከክልህ እያልክ አይመስልህም? ሰሎሞን “ አባቱን የሚረግም እናቱንም የማይባርክ ትውልድ አለ ለራሱ ንጹህ የሆነ የሚመስለው ከርኩሰቱ ያልጠራ ትውልድ አለ” የሚለው ቃል አንተን አይመለከተህ ይሆን እንዴ? ምሳ 30፡11-12
ሐይማኖተ አበው ም 22-12  “ሕዝባዊ ሆይ አንተ ግን ስለ መሥዕዋት አቀራረብ ካህኑን ትዘልፈው ዘንድ ስልጣን የለህም” ያላል። ዝማሬ በእግዚአብሄር ፊት የሚቀርብ መሥዋዕት መሆኑን አትርሳ። ይህንን መሥዋዕት ካህኑ እንዴትም ቢያቀርበው ሕዝባዊው በምን ስልጣኑ ነው ካህኑን ሊነቅፍ ወገቡን የሚታጠቀው? ወይስ ሃይማኖተ አበውም እናንተን አይመለከትም? ሊቀ ጳጳስን ያህል “አንተ’ ወይም “ሉተራዊ” ብላችሁ ካህን እንዳልሆነ ስትዘረጥጡት ድፍረቱን ከየት አገኛችሁት? ቅዱስ ዮሐንስ ዘቡርልስ የተባለ ቅዱስ አባት ያለውን ልንገርህ “ የቀና ሃይማኖት ያለውን ኤጲስ ቆጶስ ወይም ካህን ወይም ዲያቆን ይህ ካህን አይደለም ለሚል ውጉዝ ይሁን” ካለ በኋላ ይህ ማለት ጥምቀት የለም፣ ሥጋወደሙ የለም፣ ኦርቶዶክስ ሃይማኖት አልፋለች እንደማለት ነው” ብሏል። ምክንያቱም ጥምቀትም የሚፈጸመው ሥጋወደሙም የሚፈተተው በዚህ ሃይማኖቱ በቀናች ካህን ስለሆነ ነው። የእስክንድርያው ሊቀ ጳጳስ ቅዱስ አትናቴዎስም “የተሾማችሁ ካህናት ሆይ ከሰማይና ከምድር ጌታ ጋር ለማገልገል ትላላካላችሁና ክብር ይገባችኋል” ይላል። ቅዳሴ  አት ቁ.95 ይህንን የመሳሰሉትን የሊቃውንት ቃል ሳነብና ለምን ካህኑ በመሳሪያ ፈጣሪውን አወደሰ ብለህ መጻሕፍትን ባልመረመሩ ወጣቶች ፊት ክብራቸውን ስትዘረጥጥና ራስህን ብቸኛ ሊቅ እንዳደረክ ሳይ አፈርኩብህ።
 የሚገርመው ኦርጋን ለቤተክርስቲይኗ አደጋ እንደሆነ ደጋግመህ ትናገራለህ። ለቤተክርስቲያንዋ አደጋው ያንተ ጸለምተኛ አስተሳሰብ ነው። ደግሜ ልንገርህ  አንተ ነህ አደጋ። የመሳሪያ አደጋ የለም። ይኸንን በማስረጃነት ላሳይህ? የግብጽ ቤተክርስቲያን በአቡነ ሺኖዳ ዘመን ነው መሣሪያ የፈቀደችው። በዚያን ጊዜ ስምንት ሚሊዮን ብቻ ነበሩ የግብጽ ክርስቲያኖች። አሁን 25 ሚልዮን ደርሰዋል። በአሁኑ ጊዜ በኢ.ኦ.ተ.ቤ አንድም የኦርጋን ድምጽ የለም። ቁጥራችን ግን በአስደንጋጭ ሁኔታ ቀንሷል። ኦርጋን አደጋ ከሆነ የግብጻውያኑ ቁጥር ለምን ጨመረ?የኛስ ለምን አሽቆለቆለ? ወንድሜ ምክንያቱ ኦርጋን ሳይሆን እናንተ በምትጽፉትና በምታሳትሙት ከወንጌል ያፈነገጠ ትምህርት እሄን ከምሰማ እያለ ሕዝቡ የመናፍቃን እራት ሆነ። እውነታው ይሄ ነው እንጅ አንተ እንደምትለው የኦርጋን ዓላማ ቤተክርስቲያኗን ለሁለት መክፈል አይደለም። በዕቃ የተከፈለች ቤተክርስቲያን በምድር ላይ የለችም። ብትከፈል ኖሮ በእኛና በግብጽ ቤተክርስቲያን መካከል ምንም ግንኙነት ባልነበረን ነበር። ግን እስከ አሁን ድረስ እህት ቤተክርስቲያን እንዳልናት አለን። የተከፈለ ቢኖር አንተና ማሕበርህ ብቻ ናቸሁ።
 ወይንም ደግሞ አንተ እንዳልከው “ኦርጋን መንፈሳዊ መሳሪያ አይደለም” ብለሃል። የመሳሪያ መንፈሳዊና ዓለማዊ መኖሩንም ከአንተ መስማታችን ነው። እነ መሰንቆ ታዲያ ምነው ጠላ ቤቱን እያሞቁ ወደ ቤተክርስቲያን ገቡ? ሁሉን የዝማሬ ዕቃዎች መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ካላገኘን ካልንማ መቋሚያን የትኛው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ልታገኘው ነው?
 ምክንያቱ እሱ አይደለም። ምክንያቱ በኦርጋን ሰበብ ያው የለመድከውን ሰው የማሳደድ ጥማት ለማርካት ነው። በቃ ላንተ ቅድስና ማለት ሰውን ከቤተክርስቲያን ማሳደድ ነው። አንተ ሰው ላይ የምትጭነውን ሁሉ ያልተጫነልህ መናፍቅ ነው። ኤልዛቤል በነቢያት ደም እንደሰከረች አንተም በንጹሐን ደም ሰከርክ። መቼም ክርስቲያኖችን ማሳደድ ክርስቶስን ማሳደድ እንደሆነ ላንተ አልነግርህም። ሐዋ 9፡13 ግን ያንተ ሳውልነት የሚያበቃው የት ነው? ያንተ ደማስቆስ የት ነው? የዋህ ወጣቶችን እያሳደምክ የእውነት ወንጌል ላይ ዘመትክባት። ቤተክርስቲያናችን እረኛ የላትም ብለህ ነው? ባዶ ቤት አገኘሁ ብለህ ነው? ይህች ቤተክርስቲይያን ስንት ሊቃውንት እንዳልፈለቁባት፣ የሐገር መሪዎች እንዳልወጡባት ዛሬ ሚልክያስ እንዳያት ቤተልሄም እሾህ የሚበቅልባት ትሁን? በታረደው በግ ፈንታ እንጨት የሚያመልክ ትውልድ ይብቀልባት?ሐዋርያው “እኛ ብንሆን ወይም ከሰማይ መልአክ ከሰበክንላችሁ ወንጌል የሚለይ ወንጌል ቢሰብክላችሁ የተረገመ ይሁን” እንዳለ አንድም ሐዋርያ ከእንጨት መስቀሉ የሕይወት ውኃ ፈለቀ ብሎ እንዳላስተማረ በእውነት ጽሑፍሕ የተረገመ ነው። ገላ 1፡8 ይሄ ደግሞ ላንተ ይጠፍሃል ብዬ አልገምትም።
ለአንባቢያን ያለኝ መልዕክት ጊዜው የመናፍቃን ትምህርቶች በእውነተኛዋ ማሳ በኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ላይ እንደ አሸን የሚፈሉበት ነው። እናም ወደፊት የሚሰበኩና የሚጻፉትን የማንኛውም አስተማሪ የስህተት ትምህርቶች ሁሉ እየለቀምን ኦርቶዶክሳዊ መልስ የምንሰጥበት መሆኑን እንገልጻለን። መንፈሳዊ ጽሑፎች ጋዜጣ አይደሉም እያስተዋላችሁ አንብቡ። ሰዎች ለንግዳቸው ሲሉ የእግዚአብሄርን ቃል እየሸቃቀጡት ይገኛሉ። ቤተክርስቲያን የማታስተምረውን ሁሉ እንደምትል እያደረጉ በድፍረት እያቀረቡ ናቸው።
 አንድ ጽሑፍ “ የኢ.ኦ.ተ ስርዓት የጠበቀ” ስለተባለለት ሁሉ የቤተክርስቲያን መጽሐፍ ነው ማለት አይደለም። በቤተክርስቲያን ስም ምንፍቅናንና ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የሚቃረኑ ሃሳብ የያዙ ጽሑፎች እንደ ጎርፍ ገብተዋል። ዛሬ እነዛ ጽሑፎች የአመድና የዱቄት ያህል መሃላችን ተቀላቅለዋል። ይሄ አንሶ ዳንኤል ክብረት ደግሞ ሌላ አመድ የጨምርብናል። ዳንኤል የሃይማኖት ሰው ቢሆን ኖር አያደርገውም ነበር።  ወንጌል “ ገንዘብ የሚወዱ ፈሪሳውያን ይህን ሁሉ ሰምተው ያፌዙበት ነበር” ይላል ሉቃ 16፡14 ዛሬም የቤተክርስቲያን ውስጥ ፈሪሳውያን ለገንዘብ ሲሉ ከእንጨት የሕይወት ውኃ ፈለቀ እያሉ ያፌዙበታል። የሚገርመው ቅዱስ ጴጥሮስ እንደነዚህ አይነት ሰዎችን “ ገንዘብን በመመኘት በተፈጠረ ነገር ይረቡባችኋዋል” እንዳለ በየጊዜው ቤተክርስቲያን ውስጥ እንደ አሜባ መራባታቸው ነው - 2ኛ ጴጥ 2-3 ታዲያ በዚህ ጊዜ ይህን የክህደት አነጋገር ዳንኤል በተቃወመ ነበር። ቢያምንበት ነው እንጂ አትሞ ለሰው ሁሉ ባላሰራጨ። ይህን ጹሑፍ እምነቱን በሚገባ ካልተረዳ የሃይማኖት ሰው በቀር ሌላ ይጽፋል ብዬ አላምንም።
እንዲህ አይነትስ የክህደት ጽሁፎች ሲሰራጩ ለቤተክርስቲያን የሚቆጣጠርላት አካል የለም? ሲኖዶስ እንዳለ እናምናለን። ሥራውን ግን እያየን አይደለም። ኳስ ጨዋታው ተጀምሯል። ብቃት ያለው ዳኛ ግን ስለሌለ ጨዋታው ማንም እንደፈለገ የሚናኝበት ሥርዓት አልባ ሁኗል። በዚህም የተሰላቸው ተመልካች እስቴዲይዮሙን ለቆ እየወጣ ነው።
ሃይማኖትን መጠበቅ ማለት በዱላ እኮ አይመስለኝም። በሐዋርያት ዘመን ሐዋርያት ያልጻፉትን እንደጻፉ አድርገው የቶማስ ወንጌል፣ የናትናኤል ወንጌል፣ የያዕቆብ ወንጌል፣ የእንድርያስ ወንጌል እያሉ በስማቸው መናፍቃን እንክርዳዳቸውን ለመዝራት እንቅልፋቸውን እንዳጡ እናስታውሳለን። በሐዋርያት ያደረ መንፈስ ቅዱስ ክብር ይግባውና እነሱን አሥነስቶ የመናፍቃኑን ምንፍቅና ከንቱ አደረገው።
 ዛሬ በቅዱሳን ስም ንግድ ተይዟል። እነሱ ተብትበው ከየትም የለቃቀሙትን የሐሰት ትምህርት ያሬድ እንዲህ አለ፣ አባ እገሌ እንዲህ አለ ይባልልኛል። ሲኖዶስ ይህን ካልተቆጣጠረ ጠባቂነቱስ ሀላፊነቱስ ዳኝነቱስ  ምን ላይ ነው? አስር ሚሊዮን ሰው ሄደ ብሎ የተቆጨ ሲኖዶስ ገና ሌላም እስከሚሄድ ነው እንዴ የሚጠብቀው? ሕዝቡ ለምን ጥሎን ሄደ ብለን ቆም ብለን እንጠይቅ?እውነት በሚሰበክባት ቤተክርስቲያን እንደዚህ አይነት እንክርዳድ ትምህርትና ጽሁፍ ሲሰራጭ ሰዎች ምርጫቸውን ቀየሩ። ወደድንም ጠላን ሰዎች ከቤተክርስቲያን የሚወጡበት አንደኛውና ዋናው ምክንያት ይሄ ነው። እነዚህን ሰዎች አደብ ካላስገዛን ነገም ፍልሰቱ ይቀጥላል። እናም ቅዱስ ሲኖዶስ ዳንኤልንና መሰሎቹኑ አደብ ያስገዛልን እላለሁ።
ወስብሃት ለእግዚአብሄር  
ከጆን ማሞ 

25 comments:

 1. It is horrible! I'm not worried Orthodox believers leaving for good to bible based church as far as the church is preaching the word of God based on the Father ,the Son and the Holy spirit.

  ReplyDelete
 2. "ጆን" "ማሞ" ጉራማይሌነትህን ከስምህ መረዳት ይቻላል በመፅሐፍ ትችት ጀምረህ በኦርጋን ጨረስከው። እውነት አሁን ያንተ ማንነት የሚጠፋን ይመስልሃል? እነ "አባ ኦርጋን" እነ... ፓስተር...የኦርጋን ጉዳይ እንዲህ ያስጨነቃችሁ ለነገ ላዘጋጃችሁት ትልቁ የክህደት የኑፋቄ ትምህርት በር ከፋች እንዲሆን የታቀደ መሆኑንስ ያላወቅን ይመስላችኋል? እንዴ ኦርጋኑ የሞላበት የሉተር አዳራሽ ከነሙሉ የኑፋቄ ትምህርቱ ሞልቷል ለምን እዚያ ሄዳችሁ አትጨፍሩም? በተረፈ በፅሁፍህ ላይ "እናም ወደፊት የሚሰበኩና የሚጻፉትን የማንኛውም አስተማሪ የስህተት ትምህርቶች ሁሉ እየለቀምን ኦርቶዶክሳዊ መልስ የምንሰጥበት መሆኑን እንገልጻለን።" ያልካት ተመችችኝ ለምን መሰለህ? ለእነ "አባ" መልኬ፣ "አባ" ወ/ትንሳኤ፣ ለእነ ፓ/ልዑለ ቃል፣ፓ/መላኩ፣በጋሻው ወ.ዘ.ተ. የስህተት ትምህርቶች ሁሉ መልስ ልትሰጥ ስለሆነ። አደራ ታዲያ ማዳላት የለም።

  ReplyDelete
 3. ተርታ አማርኛ ለለመደ ሰው የአባ ጊዮረጊስ ቅኔያወዊና ምስጥራዊ አገላለጽ ይገባዋል ተብሎ አይጠበቅም… ለምሳሌ ልክ እንደስምህ ወዳጄ… ጆን…

  ReplyDelete
 4. It's interesting to see that you guys quote from "Metshafe Seatat". I am sure you don't believe in it. Why are you using it here? The answer is simple. You are Devil's workers. Anyone with a simple understanding of the scriptures will understand the meaning of the statements you are trying hard to accuse. Go Go Go Satan...use all your arsenal. The Church of God will take up all your weapons and continue to shine in spirit.

  ReplyDelete
 5. 2005? Denkoro Yesema elet Yabidal Alu Emuhay.

  ReplyDelete
 6. በህይወት እያላችሁ ተሸማቃችሁ በቀሳጮች የማቅ አራማጆች አንገታችሁን ደፍታችሁ ያላችሁ ሊቃዉንተ ቤተክርስቲያን የአምላክን ረዳኢነት በመማጸን መንጋዉን አድኑ አስትምሩን አስታጥቁን እኛም በአምላክ ተራዳኢነት ቤተክርስቲናችንን ከነዚህ ጉግማንጉጎች እንጠብቃት። ጆን ማሞን የህይወት መርህ የዉቀት ብርሃን የሆነዉን ቃል መንፈስቅዱስ በህይወትዎ ያሥርፅልን። አሜን!!!

  ReplyDelete
  Replies
  1. እግዚአብሔር ይባርክህ ወንድሜ ጥሩ አስትውለሃል።

   Delete
 7. egziabher ykir ybelh!

  ReplyDelete
 8. መልካም አቀራረብ ይበል ነው።በተሳሳተ መንገድ የሚሄድ ፈር እየለቀቀ የሚነጉድ ማቅና ተከታዩ
  ብቻ አይዶሉም፤ሌሎች ሰባኪዎችና ጳጳሳቱም ሳይቀሩ ምእመናንን የሚያስጐፋ ትምህርት ለበስ ዘለፋ ያስተላልፋሉ ለዚህም መረጃ ካለማወቅ እንደሆነ፤ መጽሐፍ መጥቀስ አያሻም የሽማግሎችን አባባል መጥቀስ ብቻ ይበቃል።(የምን ቄስ ቅዳሴ ቢጐልበት ሽለላ ሞላበት)እናም የተባሉት ሰዎች እውነተኛውን ስብከት እውነተኛውን መልእክት በማስተላለፍ ፈንታ የስድብ ናዳ እያወረዱ
  የክርስቶስ መጋዎችን ይበትናሉ ስለበትኗቸውም በፍርድ ቀን ይጠየቃሉ።

  ReplyDelete
  Replies
  1. ኧረ እንዳው የት ሄጄ ልሳቅ!!! እናንተም እንዳዋቂ እነ ዳንኤልን ልትተቹ? ትገርማላችሁ!!! .....መናፍቅ የሰው ልብ አድርቅ አንዱን ይዞ አንዱን የሚለቅ!!! እንደው ማንን ገደለ እውነት መናገር!! በእውነት ድርቅ የተመታችሁ!! እግዚአብሔር ልብ ይስጣችሁ!!!

   Delete
 9. [ዘቦ እዝን ሰሚአ ለይስማዕ]
  በእዉነቱ ግሩም ጽሑፍ ነዉ።

  ወጣቱ ትዉልድ የእግዚአብሔርን ቃል ሳይሆን የተራ ሰዎችን ቃል በመስማት ወደ እሸባሪነት እየሄደ መሆኑ ግልጽ ነዉ
  እግዚአብሔር ማስተዋልን ይስጠን

  ReplyDelete
  Replies
  1. ትክክል። መልካም ማሰተዋል

   Delete
 10. Eraseh acheberbare...... Dedeb.....

  ReplyDelete
 11. ጆን ማሞ እንደአባትህ እውነትም ማሞ ነህ :የሰይጣን ማደሪያ ነህ ::

  ReplyDelete
 12. " 7፤ እነዚህም ደግሞ ከወይን ጠጅ የተነሣ ይስታሉ፥ ከሚያሰክርም መጠጥ የተነሣ ይፋንናሉ፤ ካህኑና ነቢዩ ከሚያሰክር መጠጥ የተነሣ ይስታሉ፥ በወይን ጠጅም ይዋጣሉ፥ ከሚያሰክርም መጠጥ የተነሣ ይፋንናሉ፤ በራእይ ይስታሉ፥ በፍርድም ይሰናከላሉ።
  8፤ ማዕዱ ሁሉ ትፋትንና ርኵሰትን ተሞልቶአታል፤ ንጹሕ ስፍራ እንኳ የለም።" (Isyas 28).............
  "9፤ ተደነቁ ደንግጡም፤ ተጨፈኑም ዕውሮችም ሁኑ፤ በወይን ጠጅ አይሁን እንጂ ሰከሩ፤ በሚያሰክር መጠጥ አይሁን እንጂ ተንገደገዱ።

  10፤ እግዚአብሔር የእንቅልፍ መንፈስ አፍስሶባችኋል ዓይኖቻችሁን ነቢያትንም ጨፍኖባችኋል ራሶቻችሁን ባለ ራእዮችን ሸፍኖባችኋል።

  11፤ ራእዩም ሁሉ እንደ ታተመ መጽሐፍ ቃል ሆኖባችኋል፤ ማንበብንም ለሚያውቅ። ይህን አንብብ ብለው በሰጡት ጊዜ እርሱ። ታትሞአልና አልችልም ይላቸዋል፤

  12፤ ደግሞም መጽሐፉን ማንበብን ለማያውቅ። ይህን አንብብ ብለው በሰጡት ጊዜ እርሱ። ማንበብ አላውቅም ይላቸዋል።

  13፤ ጌታም። ይህ ሕዝብ በአፉ ወደ እኔ ይቀርባልና፥ በከንፈርቹም ያከብረኛልና፥ ልቡ ግን ከእኔ የራቀ ነውና፥ በሰዎች ሥርዓትና ትምህርት ብቻ ይፈራኛልና
  14፤ ስለዚህ፥ እነሆ፥ ድንቅ ነገርን በዚህ ሕዝብ መካከል፥ ድንቅ ነገርን ተአምራትንም፥ እንደ ገና አደርጋለሁ፤ የጥበበኞችም ጥበብ ትጠፋለች፥ የአስተዋዮችም ማስተዋል ትሰወራለች።

  15፤ ምክራቸውን ጥልቅ አድርገው ከእግዚአብሔር ለሚሰውሩ፥ ሥራቸውንም በጨለማ ውስጥ አድርገው። ማን ያየናል? ወይስ ማን ያውቀናል? ለሚሉ ወዮላቸው!
  16፤ ይህ የእናንተ ጠማምነት ነው፤ እንደ ሸክላ ሠሪ ጭቃ የምትቈጠሩ አይደላችሁምን? በውኑ ሥራ ሠሪውን። አልሠራኸኝም ይለዋልን? ወይስ የተደረገው አድራጊውን። አታስተውልም ይለዋልን?" (Isayas 29)

  ReplyDelete
 13. አንድ ማወቅ የሚገባን ጉዳይ ዳንኤል የያዘዉ ስራ ንግድ ነዉ፡፡ ነጋዴ ደግሞ ገንዘብ እስካስገኘለት ድረስ ማንኛዉንም ስራ እንደሚሰራ የታወቀ ነዉ፡፡ ሰዉየዉ የራሱን ማተሚያ ቤት ከፍቶ አርቲ ቡርቲዉን ሁሉ እየደረተ ገንዘብ እያገኘበት ነዉ፡፡ ከኮተቤ መምህራን ኮሌጅ በዲፕሎማ የተመረቀ ሰዉ መቼም የሙያ ስራ ሰርቶ ኑሮዉን ሊደጉም ቢፈልግ ምን ሊሰራ እንደሚችል የታወቀ ነዉ፡፡ ታዲ ዳንኤል ብልጥና ስራ ፈጣሪ ስለሆነ በአንድ በኩል ከየት እንደተገኘ የማይታወቅ የዲያቆንነት ማዕረግ ደርቦ ራሱን ለማግዘፍ ይታትራል በሌላ በኩል ያችን እዉቅና ተጠቅሞ ገንዘብ ለመቃረም ከፖለቲካዉም፣ ከእምነቱም እየነካካ የሚጽፋቸዉን ተረታ ተረቶች የሚያትምበት የራሱ ማተሚያ ቤት ከፍቶ፣ ጽሁፎቹን በራሱ ብሎግ እያስተዋወቀ ገንዘብ እያገኘ ነዉ፡፡ እንደሱ አይነት ሰብዕና ላለዉ ሰዉ በቃ ህይወት ማለት ይሄ ነዉ፡፡ ስለ እምነት መፋለስ፣ ሰዉ መፍለስ….ወዘተ ብትነግረዉ እሱ አይሰማህም፡፡

  ReplyDelete
  Replies
  1. ተራ አሉባልተኛ መንደሬ እንደሆንክ የገዛ አፍህ አሳበቀብህ።

   Delete
  2. hahhaha pro Daniel Kisret

   Delete
 14. ሳስበዉ ይሄ ብሎግ 90% ስድብ በማህበረ ቅዱሳን ላይ 4% ስብከት እና 6% አሉባልታ በዲ/ን ዳንኤል ላይ በመያዝ የተዋቀረ ይመስለኛል:: ካላመናችሁ ደግማችሁ እዩት

  ReplyDelete
 15. keshm hula neger seri metsihafu benante af yemitera aydelem

  ReplyDelete
 16. 2005? “ደንቆሮ የሰማ ዕለት ያብዳል” አሉ እማሆይ! አቦ ተመችታኛለች!!!

  ReplyDelete
 17. Abet Techit...! Techiteh motehal. Mejemeria amregna, tirgum, emareyawina fekareyawi betemare ayeshalehim? Yalebelezia eziawu adarasheh wuset hedeh betechohebachewu yishalal. Menafik Hula!!!

  ReplyDelete
 18. ለኔ ያልታየኝ ምን ስህተት አግኝተውበት ሆን ብዬ በጣም በከፍተኛ ጉጉት ነበር ያነበብኩት፡፡ ምን ዋጋ አለው ታድያ ገና የመጀመሪያውን ትችት ማንበብ ስጀምር ነው አንኳን ቅኔ የሚገባው የአማርኛ ቋንቋን ራሱ ያልተማረ ሰው የጻፈው እንደሆነ ተረዳሁና ሳልጨርሰው ተውኩት፡፡
  እባካችሁ ለኑፋቄ እንኳ የማይበቃ ትችት ነውና ደረጃችሁን እንዳያወርድባችሁ አጥፉት!!!
  ለኔ ያልታየኝ ምን ስህተት አግኝተውበት ሆን ብዬ በጣም በከፍተኛ ጉጉት ነበር ያነበብኩት፡፡ ምን ዋጋ አለው ታድያ ገና የመጀመሪያውን ትችት ማንበብ ስጀምር ነው አንኳን ቅኔ የሚገባው የአማርኛ ቋንቋን ራሱ ያልተማረ ሰው የጻፈው እንደሆነ ተረዳሁና ሳልጨርሰው ተውኩት፡፡
  እባካችሁ ለኑፋቄ እንኳ የማይበቃ ትችት ነውና ደረጃችሁን እንዳያወርድባችሁ አጥፉት!!

  ReplyDelete