Tuesday, June 21, 2016

ጵጵስና ወደ ቀደመ ክብሩ ተመለሰ


 Read in PDF
ከዚህ በፊት እንደ ዘገብነው ሁለቱ ቆሞሳት ማለት አባ አቢዩና አባ ሀብተ ኢየሱስ በቪዛ ምክንያት ከመዘግየታቸው በቀር ስድስቱ ለጵጵስና ማዕረግ በቅተዋል። ጵጵስና እንደ ሰባራ እቃ ወደ ታች በተጣለበት በዚህ ዘመን የነአባ ወልደ ትንሣኤ አያልነህ መሾም በሰባ አምስት ፐርሰንት ወደ ክብሩ ተመልሷል ማለት ይቻላል። የኦርቶዶክስ ምእመናን ለተሰጠው የጵጵስና ማዕረግ በደስታ ሲፈነጥዙ የታየበት ታሪካዊ ክስተት ነው ብንል ማጋነን አይሆንም። አንድ የከበረ ነገር በተገቢው ሥፍራ ሲቀመጥ ተገቢ ክብር ይሰጠዋል። የጵጵስናን ክህነት ለማክበር የሚያስችል በጎ እርምጃ ተወስዷል የሚል እምነት አለን። ይህን ያልንበት ምክንያታችንና የተሾሙትን ኤጲስ ቆጶሳት ማንነት እንደሚከተለው ለማቅረብ እንሞክራለን፡፡
1ኛ አባ ወልደ ትንሣኤ አያልነህ ባሳደጓቸው ባባታቸው ስም አባ በርናባስ ተብለዋል። በ1954 ዓ.ም. የተወለዱት አባ ወልደ ትንሣኤ አያልነህ ከጎንደሩ የኔታ ዲበ ኩሉ ከፊደል ጀምሮ የሚሰጠውን ጸዋትወ ዜማ፤ ከአባ ወልደ ትንሣኤ ጥሩነህ እና ከጎጃሙ መምህር ከተክለ ጻድቅ ቅዳሴ ተምረዋል። ከጎንደሩ  የኔታ ጥበቡና ከዝዋዩ መምህር አበበ ቅኔ ተምረዋል። በዘመናዊ ትምህርት ደግሞ በእንፍራዝና በፋሲለ ደስ ትምህርት ቤቶች የ1ኛ እና 2ኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቀዋል። በዝዋይና በቅዱስ ጳውሎስ ከፍተኛ ት/ቤት የመጻሕፍት ትምህርት ተምረው በዲፕሎማ ተመረቅዋል።
 የምንኩስናን ሕይወት የጀመሩት በአሰብ ራስ ገዝ በ1978 ዓ.ም በአቡነ በርናባስ እጅ እንደነበር ታሪካቸው ያስረዳል። አባ ወልደ ትንሣኤ የሚታወቁት ወንጌልን በመስበክ ነው የስብከት አያያዛቸውም ከቀድሞው ይልቅ እየቆየ እየበሰለ እያደገና እያፈራ የመጣ መሆኑን የሚከታተሉ ሰዎች ይናገራሉ። በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በመከራና በከባድ ፈተና ወንጌልን ከሰበኩ ሰዎች ውስጥ የመጀመሪያውና ምሳሌ የሚሆኑ ናቸው። ብዙዎች ከመከራው የተነሣ ኦርቶዶክስን እየለቀቁ ጠፍተዋል፣ አንዳንዶች አንገታቸውን ደፍተዋል፣ ሌሎች ከቤታቸው ተቀምጠው አፋቸውን ዘግተዋል። አባ ወልደ ትንሣኤ ግን አንገት ሳይደፉ በማንም ሳያኮርፉ ተልኳቸውን በመፈጸም ሊያቆማቸው የቻለ የለም። የብርታታቸው ምስጢር  ወይም በከሳሾቻቸው ዘንድ መሸነፍ ያልቻሉበት ምክንያት ይላሉ ታዛቢዎች፣ በጣም እምነት ስላላቸው የጌታ ዕርዳታ ያላቸው መሆናቸው፤ ይቅር የማለት ችሎታቸውና በምንም ዓይነት የዚህ ዓለም ነውር የማይያዙ መሆናቸው ነው።

ማህበረ ቅዱሳን ከተባለ የተደራጀ ቡድን ጋር ፊት ለፊት በመፋለም እስካሁን ለቤተ ክርስቲያን መስዋእትነት የከፈሉ ወንጌላዊ ናቸው። ወንጌላዊ ማለት እውነትን የሰበከ እንጂ ብዙ የሰበከ ማለት አይደለም። ማህበረ ቅዱሳን አንዳዶችን በጥቅም፣ አንዳዶችን በዘር፣ አንዳንዶችን በነውር ሌሎችን በፖለቲካ፣ በዚህ ያልተያዙትን ደግሞ መናፍቅ ብሎ ስም በማጥፋት፣ ከሥራቸው በማፈናቀል በጣም አስጊ ነው ያለውን ደግሞ በመደብደብና በመግደል ብዙዎችን ዝም አስኝቷል። አባ ወልደ ትንሣኤ ግን በቁጥጥሩ ሥር ሳይውሉ ወደ ከፍታ በመገስገስ ላይ ይገኛሉ "እሙንቱሰ በአፍራስ ወበሠረገላት ወንሕነሰ ነዐቢ በስመ እግዚአብሔር” እንዳለ ዳዊት። ለዚህ ነው ጵጵስና ወደ ቀደመ ክብሩ ተመለሰ ያልነው። ወንበዴዎች ጉቦ እየከፈሉ የተሾሙበትን ጵጵስና ለክርስቶስ ወንጌል ዋጋ የከፈሉ ሲሾሙበት መንፈስን ያሳርፋል። በአባ ወልደ ትንሣኤ ሹመት ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ ሊመሰገኑ ይገባል፡፡ 
ከማህበረ ቅዱሳንና ከፖለቲካ ኃይሎች ከባድ ተቃውሞ ውስጥ ለውስጥ በዘመድም ባገር ልጅነትም መጥቶ የነበረ ሲሆን ሁሉንም ዘወር በል በማለት በአቋማቸው ጸንተው ትክክለኛውን ነገር አድርገዋል። አባ ወልደ ትንሣኤ ሹመቱን እንቢ ብለው እንደነበረና በአቡነ መልከ ጼዴቅ አወግዝሃለሁ ባይነት እሺ እንዳሉ ለማወቅ ተችሏል። የአውሮፓ ሊቀ ጳጳስና የአቡነ ኤልያስ ረዳት ሆነው ተሹመዋል።
 ይህ በእንዲህ እንዳለ የነአባ ወልደ ትንሣኤ ሹመት በማህበረ ቅዱሳን ሰፈር አቧራ አስነሥቷል። እነ አቶ አባይነህ ካሴ የአባ ወልደ ትንሣኤ ሹመት ከሥጋቸው አልፎ አጥንታቸውን እንደወጋቸው በፌስቡካቸው መስክረዋል። በትዳር ላይ እየማገጡ ሰባኪ ነኝ ለሚሉ ሰዎች የነአባ ወልደ ትንሣኤ ቅድስና ያጥንት ስብራት ቢያመጣ አያስገርምም። ቁንጫና ቅማል ብሉ አሉን ብሎ ስም ለማጥፋት ሞክሯል፣ እነርሱ ግን ቁንጫና ቅማልን ስለት ብለው ለቁልቢ ገብርኤል ሲሰጡና በልዑል እግዚአብሔር ሲዘባበቱ ማንም አልከሰሳቸውም። የሰው ክብር እንጂ የጌታ ክብር አላሳሰባቸውምና።
 2ኛ አባ ጽጌ ደገፋው በሁለተኛው የኢትዮጵያ ፓትርያርክ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ስም አባ ቴዎፍሎስ ተብለዋል። በ1958 ዓ. ም በጎጃም ክፍለ ሃገር በደብረ ኢየሱስ ተወለዱ። ከመርጌታ አለሙ ተገኝና ከመምህር ርኁቀ መዓት ተፈራ ከፊደል እስከ ጸዋትወ ዜማ ያለውን ትምህርት ተምረዋል። በመንግሥቶ ኪዳነ ምህረት ከመርጌታ ደጉ፣ ቀራንዮ ከመርጌታ ተስፋ፣ ከመርጌታ ብዙአየሁ ደምበጫ ከመርጌታ ከብካባና ከመርጌታ ዳንኤል ቅኔ ተምረዋል። ምንኩስናን ከብፁዕ አቡነ መቃርዮስ በ1975 ዓ. ም ተቀብለዋል። በዲማ ጊዮርጊስ ከመምህር ማርቆስና ከመምህር ዲሜጥሮስ የሐዲስ ኪዳን አንድምታ ተምረዋል። በዝዋይ ገዳም ኮርሶችን በመከታተል ተመርቀው በዚያው ለሦስት ዓመት ያህል አገልግለዋል።  በዘመናዊ ትምህርት የአንደኛ የሁለተኛ ትምህርታቸውን አጠናቀዋል፡፡ ከካሊፎርኒያ እስቴት ዩኒቨርሲቲ ኖርዝ ሪክ በማህበራዊ ጥናትና በኢዝነስ አስተዳደር የመጀመሪያ ድግሪያቸውን አግኝተዋል፣ ካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ ደሚንገዝ ሂልስ ሁለተኛ ድግሪያቸውን አግኝተዋል፣ እንደገና በካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ በክሊኒካል ሳይኮሎጂ የማስተር ዲግሪያቸውን አግኝተዋል በአሁኑ ሰዓት በክሊኒካል ሳይኮሎኪ ፒ ኤች ዲ (ዶክትሪታቸውን ለመያዝ) የመመረቂያ ጽሑፋቸውን በመሥራት ላይ ናቸው ተብሏል።
በኢትዮጵያ በተለያዩ አድባራት በአስተዳዳሪነት አገልግለዋል። በካርቢያንም ምድር በስብከተ ወንጌል አገልግለዋል። በሎስ አንጀለስ ቅድስት ማርያም በአስተዳዳሪነት ለረጅም ጊዜ ያገለገሉ ሲሆን በቅዱስ ሲኖዶስም ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ ናቸው፤ ሁለቱን ሲኖዶስ ለማስታረቅ በተደረገው ሙከራ ዋና ተሳታፊ ነበሩ፤ በካህናቱ መካከል በተፈጠረው ክፍፍል ከነአባ ወልደ ትንሣኤ ተለያይተው እንደነበረ የሚታወስ ሲሆን ነገሩ ከገባቸው በኋላ ግን በፍጹም ተመልሰው ከወንድሞቻቸው ጋር ተሰልፈው ለወንጌል ከፍተኛ ድጋፍ እየሰጡ መሆናቸው ታውቋል። ባለፉት ሁለት ወራት ከራሳቸው ጋር የሚያገለግለው አባ ቶማስ ቤተ መቅደስ ውስጥ አንገታቸውን አንቋቸው እንደነበርና መርጌታ ደስ አለኝ እንዳተረፏቸው ታውቋል፣ ይህ ግፍ ለክብር ሆኖላቸው ለጵጵስና ማዕረግ አብቅቷቸዋል። አባ ጽጌ ይደልዎ ተብለዋል። የአባ ቶማስን ጉዳይ ወደፊት እንመለስበታለን።
3ኛ አባ ገብረ ሥላሴ ጥበቡ በ1950 ዓ.ም በጎንደር ተወለዱ ከመርጌታ ገበየሁና ከመርጌታ ሙሉጌታ ከፊደል ጀምሮ ጸዋትወ ዜማ ተምረዋል። ከመርጌታ ከሃሊና ከመርጌታ አክሊሉ ምዕራፍና ጾመ ድጓ ተምረዋል በጎጃም ከመርጌታ ተከስተ እና ከመላከ ምሕረት ጥበቡ ቅኔ ተምረዋል፤ ከመርጌታ ኤርምያስ ሞላ፣ ከመርጌታ ልዑል እና ከመርጌታ መዝገቡ በጎንደር አቋቋም ተምረዋል። ከሊቀ ሊቃውንት መንክር የመጻሕፍት ትርጓሜ፣ በቅዱስ ጳውሎስ ት/ቤት የነገረ መለኮት ትምህርታቸውን ተምረው ተመረቅዋል።
 በዘመናዊ ትምህርት የመጀምሪያ ደረጃ ትምህርት በአዲስ አበባ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በጎንደር ፋሲለደስ ተምረዋል። ከቭላድሚር ዩንቨርስቲ እስከ ማስትሬት ድግሪያቸውን ከያዙ በኋላ በሳንፍራሲስኮ ዩኒቨርስቲ የዶክትሬት ድግሬያቸውን እንደያዙ ታሪካቸው ያስረዳል።
 አባ ገብረ ሥላሴ የታወቁ ሰባኬ ወንጌል ናቸው በኢትዮጵያ በልዩ ልዩ ሥፍራ በሥራ አስኪያጅነትና በሰባኬ ወንጌልነት አገልግለዋል። በባሕርያቸው ገራገር እና ዘአልቦ ጽልሑት በጣም ቀና ሰው እንደሆኑ ይነገርላቸዋል፤ ግብዝነት የለባቸውም እንደ ቅዱስ ጴጥሮስ የተሰማቸውን ቀድሞ በመናገር ይታወቃሉ፡፡  ስለዚህ አቡነ ጴጥሮስ የሚለው ትክክለኛ ስማቸው ነው ተብሏል። የእግዚአብሔርን ቃል ከማነኛውም ሰው ቁጭ ብለው ለመማርና የተማሩትን ለማድነቅ አይቸገሩም በጣም ትሑት ከመሆናቸው የተነሣ ከትንሽ ከትልቁ ጋር ለመሰለፍ ይችላሉ ተብሎላቸዋል። በሲኖዶሱ ውስጥ ችግር በተፈጠረበት ቦታ ሁሉ ግንባር ቀደም ሆነው ችግር ለመፍታት የሚያደርጉት እንቅሥቃሴ ክሬዲት አሰጥቷቸዋል፡፡ ከዚህ በፊት ከነዶክተር ነጋ ጋር በኦሃዮ ባደረጉት ክርክር ብቻቸውን በመሆናቸው ጎል ጠባቂ የሚል ቅጽል ስም ወጥቶላቸው እንደነበር ይታወሳል፤ የቅድስና ሕይወት ስላላቸው ጵጵስናው ተገቢያቸው ነው። የአውስትራሊያ ሊቀ ጳጳስ ሆነው ተሹመዋል።
4ኛ አባ ሳሙኤል ዳኛው አባ ናትናኤል ተብለዋል።  በ1955 ዓ.ም ተወልደው ከመርጌታ መዝገቡ ለቃል ከፊደል እስከ ጸዋትዎ ዜማ ተምረዋል። ከመርጌታ በቀለ ጾመ ድጓና ምዕራፍ  ከመርጌታ ድረስ ሽታ ድጓ ተምረዋል። በጎጃም ቀራንዮ ከመርጌታ ተስፋ ቅኔን ተምረው እስከ አስነጋሪነት ደርሰዋል። ከዚያም በጎንጂ ጽላልሽ ከታዋቂዋ የቅኔ መምህር ከእመይት ገላነሽ ቅኔያቸውን ከነአገባቡ አደላድለዋል። በጎንደር ከመርጌታ ምሥራቅ አቋቋም፣ ከመርጌታ ውብ አገኝ ዝማሬ መዋሥእት ተምረዋል፡፡ በመቀጠልም ከመምህር አክሊለ ብርሃን ኃ/ ሥላሴ ቅዳሴ ተምረው በመምህርነት ተመረቅዋል። በቅዱስ ጳውሎስ ከፍተኛ መንፈሳዊ ት/ቤት ለአራት ዓመት የሚሰጠውን ትምህርት ተከታትለው በዲፕሎማ ተመርቀዋል። ሥርዓተ ምንኩስናቸውን በዝዋይ ገዳም በ1972 ዓ.ም ፈጽመው መአርገ ቅስና በ1986 ዓ.ም ተቀብለዋል።
 በደቡብ አፍሪካ የቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ በመሆን ሲያገለግሉ ቆይተው አሁን በሚገኙበት በዴንቨር ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን እያገለገሉ እያለ በልመና ብዛት የጵጵስና ማዕረግ ለመቀበል ችለዋል፣ አባ ሳሙኤል እጅግ መንፈሳዊ መናኝ ሰው ናቸው፣ አስተውለው የሚናገሩ፣ ቶሎ ነገር የማይቀበሉ እውነተኛ ሰው ናቸው። በቅድስናቸውም የተመሠከረላቸውን ናቸውና ይገባቸዋል፣ የደቡብ አፍሪካ ሊቀ ጳጳስ ሆነው ተመድበዋል።
5ኛ አባ ሳሙኤል ተሻገር አባ አብርሃም ተብለዋል። በ1945 ተወልደው ከአባ አበራ አለሙ ፈደል እና ዳዊት ተምረዋል፣ ከመርጌታ ጀምበር ጸዋትዎ ዜማ ተምረዋል ከመርጌታ ተሻገር ዘውዴ ዲቁና ተምረዋል፣ በጎጃም ከመርጌታ ብዙአየሁ በደብረ ኤልያስ ከመርጌታ መሠረት ቅኔ  ከመርጌታ ጥበቡ ዜማን ተምረዋል። በበአታ ለማርያም ቅዳሴ ተምረው በመምህርነት ተመርቀዋል፣ በቅዱስ ጳውሎስ ከፍተኛ መንፈሳዊ ት/ቤት ተምረው ተመርቅዋል። ዘመናዊ ትምህርትን በተመለከተ የመጀመሪያ ትምህርታቸውን በደብረ ታቦር፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በአዲስ አበባ በምሥራቅ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አጠናቀዋል። በ1987 ዓ.ም ሥርአተ ምንኩስናን ፈጽመው በ1988 ዓ.ም ቅስናን ተቀብለዋል። በኤድመንተን መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን እያገለገሉ የሚገኙ ሲሆን ሀገረ ስብከታቸውም በዚያው ሆኖአል። ስለመንፈሳዊ ሕይወታቸውና ስለ ወንጌል ያላቸው አመለካከት ምን እንደ ሆነ አላወቅንም።
6ኛ አባ ገብረ ሥላሴ የኋላ እሸት አባ ማርቆስ ተብለዋል። በ1958 ዓ.ም ተወልደው ከመርጌታ ጀምበር ዘማንና ሌሎችን ክፍለ ትምህርቶችን ተምረዋል። ከመርጌታ ፍቅረ ማርያምና ከመርጌታ ይሄይስ ፈንቴ በደብረ ታቦር ቅኔ ተምረዋል ከመርጌታ ሕሩይ ለገሰ ዝማሬ መዋስእት ተምረዋል፤ ከመምህር ተስፋ ወርቅነ ገነተ ኢየሱስ የቅዳሴ ማርያምና የኪዳን ትርጓሜ ተምረዋል። በዘመናዊ ትምህርት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በጽጌ ባሻህ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በእቴጌ መነን ትምህርት ቤት ተምረው አጠናቀዋል። በሲያትል ቮኬሽናል ኢንስቲትዩት በቢዝነስ ኮምፒዩተር አካውንቲንግ የተመረቁ ሲሆን በሲያትል ዩኒቨርሲቲ የፓስተራል ሊደርሺፕ እና ካውንስሊግ ትምህርታቸውን ተካታትለዋል፤ ሥርዓተ ምንኩስናን በዚያ በአሜሪካ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ እጅ ፈጽመው በሲያትል ቅዱስ ገብርኤል እያገለገሉ እያለ የጵጵስናን ማዕረግ ተቀብለው የኦሪገን ሊቀ ጳጳስ ሆነው ተሹመዋል። ስለ መንፈሳዊ ሕይወታቸውና ስለ ወንጌል ያላቸውን አመለካከት ያወቅነው ነገር የለም።
 ለማጠቃለል ያክል አሁን የተደረገው ሹመት ሰባ አምስት ፐርሰንት ጵጵስናን ከወደቀበት አንሥቶታል ማለት ይቻላል። ከሞላ ጎደል ልምድን ቅድስናን እውቀትን ሚዛን አድርጎ የተሰጠ ነው፤ ሌሎች የሚሾሙ አሉ የሚባል ወሬ የሰማን ሲሆን አንዳንድ ወንበዴዎችን ለይቶ በማወቅ መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ በእውነት ላይ የተመሠረተ አሠራር እንዲከናወን የቤተ ክርስቲያን ልጆች ሁሉ ምኞት ነው። በዚህ በሀገር ቤት ያለው ሲኖዶስም ወደ ክብሩ የሚመልሱትን ጳጳሳት እንዲሾም ጸሎታችን ነው፡፡           

26 comments:

 1. አባ ሰላማዎች ተባረኩ ጥሩ መረጃ ነው። እኛም እዚህ በሀገራችን ሰላምን የሚያሰፍኑ እውነተኛ አባቶች እንደሚሾሙ እምነት አለኝ፡ አቡነ አብርሃም፡ አቡነ ሳሙኤል፡ አቡነ ኤልያስ የሚባሉ የማህበሩ ገረዶች በዚህ በዚህ በጳጳሳት ምርጫ ካሉበት ከፍተኛ አማኝ ከቤተክርስቲያኗ ይፈልሳሉ ። ውሸት የማያውቁ ላመኑበት ነገር ቆራጥ የነደደ እሳት ማብረድ ችሎታ ያላቸው አንደበተ ርቱእ እና ቅን የማያወላውሉ የሚያደርጉትን የሚያውቁ ማህበር ሊያሽከረክራቸዉ የማይችል መልከ ቀና ልበ ቀና ምልስ ይቅር ባይ ሲቀልዱ ቀልደኛ ሲያስተምሩ ፍፁም ወንጌላዊ እጥር ምጥን ያለ ጣፋጭ መልእክት የሚያስተላልፉ ማንም ሰው እንዲጎዳና እንዲጠፋ የማይፈልጉ አድሎ የማያደርጉ እውነተኛ አባት የዛሬው የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ዲስቆሮስ፤ አስመራጭ ከሆኑ የኦርቶዶክስ ተዋህደ ልጆች አንሰጋም። በፀጥታ እና በፀሎት እንጠብቅ የአለም መድሀኒት መድሀኒተ ዓለም አባታችንን ይጠብልን ቸር ይግጠመን።

  ReplyDelete
 2. ሹመቱ ጥሩ ነው !!ግን ከጎጃምና ከጎንደር ብቻ ነው ታዲያ እንዴት ተብሎ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያንን መወከል ይቻላል?

  ReplyDelete
  Replies
  1. መልሱ ጕጃም ና ጕንደር ነዉ የሊቀውንቱ መፈለቂያ ።

   Delete
  2. ምን ማለት ነው? ካለው እና ከተገኘው ነው እንጂ የሌለ ሰው ይሾመልኝ ማለት ምንድነው?

   Delete
 3. ይሄ ፅሁፍ ወያኔ ይሸታል :-(

  ReplyDelete
 4. ከዚህም ከዚያም የሆናችሁ አደናጋሪዎች ደንጓሪዎች ናችሁ!

  ReplyDelete
 5. በጣም ፀሎትና ምህላ ያስፈልጋል። ሰይጣን እንዲርቅ መፀለይ ጠቃሚ ነው። የማህበረ አጋንንት ሤራ በእግዚአብሔር መንፈስ ይመታ።

  ReplyDelete
 6. Aba Woldetinsae be 1979 Zeway simaru endalmenekosu yitawekal. Teyikachu bitarmu tiru aymeskachum?

  ReplyDelete
 7. ጉድ ሳይሰሙ መስከረም አይጠባም፥፥፥ ብለው ብለው ይኸን ከሞት አምልጦ የወጣ የሚመስል ያረጋል አበጋዝ የሚባል ጣረሞት ምንኩስና ይሰጠው እና ጳጳስ ይሁን እያሉ ማቅ ይሮጣሉ። ህዝበ ክርስቲያናት ጉድ ፈልቶብናል።

  ReplyDelete
 8. አትንጫጩ ገና ሹመቱ ይቀጥላል ።

  ReplyDelete
 9. በጣም ፀሎትና ምህላ ያስፈልጋል። ሰይጣን እንዲርቅ መፀለይ ጠቃሚ ነው።

  ReplyDelete
 10. yihe neger yegondern synodos lematenaker calhone beker lebetekiristian minim fayda yelewim.

  ReplyDelete
 11. Aba Seklama are menafikan, but I agree with you today because you describe very well Aba Wolde Tinsae.I know Abba is a good preacher and spiritual. He also preached the real thing about the type of food consumed.He is not wrong but some misinterpret it because of lack of knowledge-In general, Aba Wolde Tinsae deserves to be bishop.

  ReplyDelete
 12. አባ ሠላማዎች የጎብኚአችሁ ቁጥር 5 ሚሊዮን ሊሞላ ነው፡፡ ለምን እንደሆነ ታውቃላችሁ? እውነትንና ሐቅን ስለምትዘግቡ፡፡ የእናንተን ብሎግ ለመጎብኘት በጣም የሚጓጓው ማን እንደሆነ ታውቃላችሁ? የማኅበረ ቅዱሳን ሠራዊት ነው፡፡ ሁልጊዜ ሐቅ ሐቁን ከመዘገብ ወደ ኋላ እንዳትሉ፡፡ ማን ያውቃል አሳዳጁ ማህበር ይፈወስበት ይሆናል፡፡ በርቱ!!

  ReplyDelete
 13. እውነተኞች የሰንጌል አባቶች ለጵጵስና ማዕረግ በመብቃታቸው በጣም ደስ ብሎናል። እስካሁን ወንጌልን ጠንቅቀው የማያወቁ የተረት ሰዎች ብቻ ነበር ስሾሙ ለዘመናት የከረምነው። እነሆ የወንጌል ብርሃን የሆኑ አባቶች ለታላቅ ክብር በመብቃታችው ሁላችንም የተዋህዶ ልጅች ደስ ብሎናል። የእግዚአብሔር ድንቅ ስራው ተነግሮ አያልቅም። እልልልል ብለናል ። ገና ብዙ እናያለን :፡ ማቆች አይናቸው ደም ለበሰ መቼ እግዚአብሔርን በጥቅም ማታለል አይቻልም፡፤ እርሱ ድንቅ አመላክ ነውና።ደስ ብሎናል።

  ReplyDelete
  Replies
  1. እንክርዳዶችም አብረው ትሾመዋል!!! ለአባ ወልደተንሣይ ግን በእውነት ይገባቸዋል። የወንጌል ገበሬ ናቸውና።

   Delete
 14. Abetu yehonebenen aseb!!!

  ReplyDelete
 15. ያስፈፅማችሁ

  ReplyDelete
 16. አባ ወልደ ትንሳኤ የወንጌል ገበሬ ።የሚያህሎት የለም።ይገባዎታል ።እግዚአብሄር ከዚህ በላይ እንዲያገለግሉት ሀይል እና ጉልበት ይሁንዎት።በእርሶ መሾም ዲያቢሎስ እና ማህበርተኞቹ ተሸብረዋል።

  ReplyDelete
 17. መዳን በሌላ በማንም የለም ( የሐ.ስራ ም.4 ቁ 12) ይህንን የእግዚአብሔር ቃል ለመጀመርያ ጊዜ የሰማሁት ከአባ ወልደትንሳኤ ከሃያ አመት በፊት አአ ኡራኤል ቤ/ክ የሰርክ መርሐ ግብር ላይ ነበር ፡፡ አባ ህይወታችን በእግዚአብሔር ቃል ላይ እንዲመሰረት በብዙ ድካም በጸሎት በስብከተ ወንጌል ያደረጉት ተጋድሎ መቼም አልረሳውም፡፡ታመው በነበረ ጊዜ ሞተዋል ተብሎ ተወርቶ የኡራኤል አጥቢያ ምእመናን ታላቅ ልቅሶ አሰምቶ ነበር ፡፡ ነገር ግን ጌታ ሞትን ወደ ህይወት ቀይሮ ለጵጵስና አበቃዎት ፡፡አሁን ለእግዚአብሔር ምን ይከፈለዋል ስሙ ይባረክ ይቀደስ ከፍ ይበል ድምጹን በዚህ መንገድ ላሰማን አምላክ ክብር ይሁን፡፡

  ReplyDelete
 18. አንዳንዶች እንደሚያወሩት ወንጌልን በመጀመሪያ የሰማንው ከሚሽነሪዎች ሳይሆን አባ ወ/ትንሳኤን ከመሰሉ ቅዱሳን አባቶቻችን ነው

  ReplyDelete
 19. ይህንን መልካም ዜና (የእነ አባ ወ/ትንሳዔ ስርአተ ጵጵስና) የሰማሁባት ቀን ትባረክ

  ReplyDelete
 20. ታላቅ የምስራች ታላቅ የምስራች ታላቅ የምስራች ለኢትዮጵያ ሐገሬ ሁለቱ ሲኖዶሶች ሲዋሃዱ ኢትዮጵያ በእነ አባ ወ/ትንሳኤ በወንጌል ትታረሳለች

  ReplyDelete
 21. አባ ወ/ትንሳኤ የሰበኩኝን ወንጌል ባሰብኩ ቁጥር ሁሌ እንደባረኩዋቸው እንደመረኩዋቸው ነው

  ReplyDelete
 22. አባ ወልደትንሳኤ ኃይማኖትን እና ህግ የሆነውን በመለየት እንድንከተል ለመጀመሪያ ያስተማሩ በሰፊው ያዳረሱ ወንጌልን ህይወታችን እንድናደርግ የረዱን የዘመ ናችን ኃዋርያ ናቸው።ወንጌልን ክርስቲያኑ እየተለማማደ መምጣቱ ያንገበገባቸው ክፍዎች ያልቀቡዋቸው ጥላሸት፣ቆርጠው ያልቀጠሉባቸው ርእስ፣ጉዳይ።አንቀፅ፣ ንግግር አልነበረም፤ ያላወላገዱት ነገር አልነበረም፤ ለወን ጌል ያልተቋቋሙት ለእንደ እኔአይነቱ የሚከብድ ፈተናን ሁሉ በእግዚአብሔር እየተወጡ እዚህ ደርሰዋል። " እንቲአሁ ለቃል ኮነ ለስጋ ወእንአሁ ስጋ ኮነ ለቃል" እያሉ የሚሰብኩ የመንጋው እረኛ ናቸው። አባ በርናባስ ከ ብሄራዊም በላይ ለአለም ህዝበ ክርስቲያን ብቁ ናቸው። እጅግ ትሁት፣ ይቅርታን በሁለቱም ገፅታው ቀድመው የሚተረጉሙ ወንጌላዊ ናቸው እና ገና ለበለጠው ኃላፊነት እንጠብቃቸዋለን።

  ReplyDelete
 23. ይህ ድህረ ገጽ ወገናዊነት የተሞላበት፤ምንም መንፈሳዊ መላእክት የሌለው የኢትዮጵያን ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ልጆችን ለማጋደል የተዘጋጀ የጦር ሜዳ ድህረ ገጽ ነው።የክፉ ግዜ ምልክቶች!!!

  ReplyDelete