Thursday, August 25, 2016

ግመሉን በዝምታ ትንኙን በጫጫታ
ከአሸናፊ በላይ

ኑፋቄ ሁለት ፡- ማኅበሩ የክርስቶስ ተቃዋሚ ነው
ማኅበረ ቅዱሳን በተለያዩ መንገዶች የክርስቶስ ተቃዋሚ መሆኑን በግልፅ አሳይቷል፡፡ የክርስቶስ ተቃዋሚ መንፈስ እየሠራበት እንደሆነ ወደፊት በዝርዝር ማስረዳት የሚቻል ቢሆንም ለዛሬው ጥቂት ሐሳቦችን ብቻ መጠቆም የማኅበሩን ምንነት የበለጠ ለመረዳት ይጠቅማል፡፡ ቀጥሎ የተጠቀሱት ጥቂት ነጥቦች ማኅበሩ የኢየሱስ ክርስቶስ ተቃዋሚ መሆኑን ያመለክታሉ፡፡

«ኢየሱስ» የሚለውን ስም አጥብቆ መቃወሙ
ማኅበሩ በግልፅ ይህንን ስም መቃወሙን ባይናገርም የጌታን አዳኝነት የሚያሳየውን «ኢየሱስ» የሚለውን ስም የሚጠሩትን የቤተ ክርስቲያን ልጆች «መናፍቃን ናቸው» ብሎ በክፉ ስማቸውን በማጥፋት እንዲሳደዱ ሲያደርግ መቆየቱ ይታወቃል፡፡ ምንም እንኳ እንዳሰበው ባይሳካለትም የጌታ ስም እንዳይጠራ ለማድረግ ብርቱ ጥረት አድርጓል፡፡ አንዳንድ ዘማርያን
«ማልደራደርበት ማልቀብረው እውነት
አንገት የማያስደፋ የማላፍርበት
ኢየሱስ የሚለው ስም እስትንፋሴ ነው
እውነቱ ይኸው ነው»
በማለት ግሩም ዝማሬ አቅርበዋል፡፡ ኢየሱስ የሚለው ስም እንዳይጠራ ማኅበሩ መቃወሙ የክርስቶስ ተቃዋሚ መንፈስ በግልፅ እየሠራበት መሆኑን ያመለክታል፤ (1ቆሮ 12÷3)፡፡

የጌታን የማዳን ሥራ ለፍጡራን መስጠቱ የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስን ቤዛነትና ብቸኛ የአዳኝነት ሥራ ለፍጡራን በመስጠትና የተለያዩ የደኅንነት /የመዳን/ መንገዶች እንዳሉ በማስተማር ብዙዎች እንዳይድኑ ማኅበሩ እንቅፋት ሆኖአል፡፡ ከተጠቀሱት ሐመርና ዕንቁ መጽሔቶች አንዳንድ ሐሳቦችን እንመልከት፡፡

«በአማናዊቱ መርከብ በድንግል ማርያም አማላጅነት በመታመን የምንኖር እንደምንድን ተስፋ አለን» ሐመር 1985 ገጽ 19፡፡ «ሥላሴ ዓለምን ሲያድኑ ድንግል ማርያም የሥላሴ ማደሪያ ለእኛ ደግሞ የመዳናችን ምክንያት ነች ማለት ነው» ዕንቁ 2ዐዐ3 ገጽ 18፡፡ በነዚህ መጽሔቶች ድንግል ማርያም የመዳናችን ተስፋና ምክንያት እንደሆነች ተገልጾአል፡፡ ማህበረ ቅዱሳን ድንግል ማርያምን ብቻ ሳይሆን መላእክትንና ቅዱሳንን ሁሉ አዳኞች እንደሆኑ በትምህርቱ ውስጥ  እየገለጸ  ይገኛል፡፡ ንስሐ ሳይገቡና በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ሳያምኑ ሰዎች በፍጡራን ምልጃ ይጸድቃሉ፤ መንግሥተ ሰማያት ይገባሉ ብሎ ያምናል ማኅበሩ÷ ይሁን እንጂ ሐሳቡ የጌታን የማዳን ሥራ ወደ ጐን ትቶ የፍጡራንን ምልጃ በክርስቶስ የቤዛነት ሥራ መተካት የመጽሐፍ ቅዱስንና የቤተ ክርስቲያንን የሃይማኖት ትምህርት የሚቃረን ግልፅ ኑፋቄ ነው፡፡ «ያለ ድንግል ማርያም አማላጅነት ዓለም አይድንም» የሚለውንና በየታክሲው ላይ ተለጥፎ የሚገኘውን አደገኛ ኑፋቄ እንደምሳሌ መጥቀስ ይቻላል፡፡

የመጽሐፍ ቅዱስም ሆነ የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ከልዑል እግዚአብሔር በቀር ሌላ ማንም (ቅዱሳን መላእክትም ሆኑ ቅዱሳን ሰዎች) ሰውን ማዳን እንደማይችሉ ይናገራሉ፡፡
የመጽሐፍ ቅዱስ የመዳን ሐሳብ
አምላካችን የደኅንነት አምላክ ነው
ከሞት መውጣትም ከእግዚአብሔር ነው፤ መዝ (67)፤2ዐ
እኔ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ከእኔ ሌላም የሚያድን የለም፤ ኢሳ.43÷11
ሰው ክርስቶስ መስዋዕት ሆኖ በመስቀል ላይ የፈጸመውን የቤዛነት ሥራ ሲያምን ብቻ ይድናል፡፡ ሰው የሚድነው በዚህ መንገድ ብቻ ነው፤ ዮሐ 3÷16-18፤ ገላ.2÷16፤ 1ጢሞ 1÷15፤ “ያለ ደም ስርየት የለም” (ዕብ 9፤22) ፡፡ ይህም ደሞ ለኃጢአተኞች ስርየት ማስገኘትና ማዳን የሚችል የክርስቶስ ደም ብቻ ነው፤ ሮሜ 3÷24-25፡፡ ስለዚህም የድንግል ማርያምን አዳኝነት የሚሰብከው የማኅበረ ቅዱሳን ትምህርት አደገኛ ኑፋቄ ነው፡፡

 የቤተ ክርስቲያን የመዳን ትምህርት
«ስለ እኛ ስለ ሰዎች እኛን ለማዳን ከሰማይ ወረደ» (ጸሎተ ሃይማኖት)፡፡ «ስለዚህ እኛ ሁላችን ይህንን የማያሳስት እውተኛውን የጽድቅ መንገድ ክርስቶስን ብቻ ይዘን ከሄድን ዘወትር እየናፈቅን አባታችን ሆይ እያልን ከምንጠራው ከሰማያዊ አባታችን ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ ሰማያዊት አገራችን ወደ መንግሥተ ሰማያት እንገባለን ብለን አንመካም፤ የምንጸድቅበት ሃይማኖታችን ክርስቶስ ብቻ ነውና» (የቤተ ክርስቲያን ጸሎት ገጽ 53)፡፡

«በፊት በረድኤት ሲመግበው ኖረ፤ ኋላም በፍጹም ይቅርታ ለመታረቅ ልጁን ሰደደው፤ በልጁም ሞት ዓለምን አዳነ» (ጎርጎርዮስ /አባ/ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ በዓለም መድረክ፤ 1978 ዓ.ም ገጽ 102)፡፡
«ነገር ግን ስለ እኛና ስለ እኛ መዳን ብቻ ሰው መሆኑን ገለጠ» (መልከ ጸዴቅ (አባ) ትምህርተ ክርስትና 2ኛ መጽሐፍ ገጽ 102 ይህን የመዳንን ትምህርት በአቡነ ጎርጎርዮስ ትምህርት እንቋጨው፡፡ «ፍጡር ፍጡራንን ማዳን አይችልም፤ ሰውን የሚያድነው እግዚአብሔር ብቻ ነው» (የቤተ ክርስቲያን ታሪክ በዓለም መድረክ ገጽ 112)፡፡

የተሸቃቀጠ የነገረ ደኅነት ትምህርት በማዘጋጀት
 ነገረ ድኅነት ወይም የመዳን ትምህርት አጭር ግልፅና በክርስቶስ የማዳን ሥራ ላይ ብቻ ያተኮረ ኃጢአተኛ ሰው «እንድጸድቅ ወይም እንድድን ምን ላድርግ?» ብሎ ለሚጠይቀው ጥያቄ ግልፅና ተገቢውን ምላሽ የሚሰጥ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ነው፡፡

የመዳን ትምህርት ከአእማድ የሃይማኖት ትምህርቶች አንዱ ንዑስ ዘርፍ እንጂ የሃይማኖት ትምህርት ዘርፎችን ሁሉ የያዘ ወይም ያጠቃለለ አይደለም፡፡ ክርስቶስ  «በእኔ እመኑ… እኔ ኃጢአተኞችን ለማዳን መጣሁ» እያለ በብዙ ቦታዎች በወንጌላት የሰጠው ትምህርት የመዳን ትምህርት ነው፤ ለምሳሌ ማቴ. 2ዐ÷28፤ ዮሐ 3÷16-18፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ በሐዋርያት ሥራ 2÷22-42 ያስተማረው ወንጌላዊው ፊልጶስ ለኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ያብራራለት በሐዋርያት ሥራ 8÷22-35 ያለውና በቤተ ክርስቲያንም «የጽድቅ መንገድ» በሚል ርዕስ በቤተ ክርስቲያን ጸሎት መጽሐፍ ገጽ 93 ላይ ተጽፎ የሚገኘው ለመዳን ትምህርት ወይም ለነገረ ድኅነት እንደ ምሳሌ ሊወሰዱ ይችላሉ፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን ነገረ ድኅነት ወይም የመዳን ትምህርት ብሎ የሚያስተምረው ግን ከዚህ የተለየ ነው፡፡ ሰውን ወደ ክርስቶስ የሚመራና የሚድንበትን መንገድ የሚያሳይ ሳይሆን የድኅነትን እውነት ወይም የጽድቅን መንገድ የሚሸፋፍን÷ አዳናጋሪና የሚያምታታ ነው፡፡ ለምሳሌ በ1993 ዓ.ም ነገረ ድኅነት ብሎ ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ያዘጋጀው ብዙ የተለያዩ የሃይማኖት ትምህርት ሐሳቦችን ቀነጫጭቦና በአንድነት አጭቆ የያዘ ነው፡፡ ይህ በማኅበሩ በተዘጋጀ የ«ነገረ ድኅነት»ጽሑፍ ሰው ስለመዳን ማድረግ ያለበትን የሚያሳይ ሳይሆን «የቱን ልያዘው የቱን ልልቀቀው» እያለ ግራ ገብቶት ሁሉን ለመጨበጥ እንዲታትር የሚያደርግ ነው፡፡

ይህ የማኅበረ ቅዱሳን «የነገረ ድኅነት ጽሑፍ እንዲህ በማለት ይጀምራል፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስም ሆነ የሌሎች መጻሕፍት» ዋና ዐላማ ሰው የሚድንብትን መንገድ ማሳየት ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ የሞተው የሰውን ልጅ ለማዳን ነው»፤ ገጽ 3፡፡ ከዚህ ከመቅድሙ ስንጀምር የመጽሐፍ ቅዱስም ሆነ የሌሎች መጻሕፍት ዋና ዐላማ ሰው የሚድንበትን መንገድ ማሳየት ነው የሚለው አገላለፅ የተሳሳተ መነሻ ነው፡፡ ምክንያቱም የሚያድን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ብቻ ነው፡፡ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጭ ያሉ ሌሎች ማንኛቸውም መጻሕፍት ሰውን የሚያድን እውነት የላቸውም፡፡ ማኅበሩ መጽሐፍ ቅዱስን የሚመለከተው የመዳንን እውነት የያዘ ብቸኛ መጽሐፍ አድርጐ ሳይሆን የመዳንን እውነት ከያዙ መጻሕፍት መካከል አንዱ አድርጐ ነው፡፡ የማኅበሩ የኑፋቄ መነሻም ይኸ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ የመዳንን ትምህርት መያዙን የማይቀበል ሁሉ የመጽሐፍ ቅዱስን ሥልጣን የሚጋፋ የኑፋቄ ሐሳብ ያለው ነው፡፡ 

ማኅበሩ ሌሎች መጻሕፍት የሚላቸው እነዚያኑ የፈረደባቸውን በፍጡራን ስም የተጻፉ የተሳሳቱ ድርሰቶችን እንደሆነ መገመት ይቻላል፡፡ ማኅበሩ ሌሎች መጻሕፍት የሚለውን ሐረግ ያስገባው እንደፈለገው ለመሸቃቀጥ እንዲመቸው ነው፡፡ የተሸቃቀጠ «ነገረ ድኅነት» የማኅበሩን አባላት እንዳላዳነ ሁሉ ማንንም አያድንም፡፡ ይህ የማኅበሩ ነገረ ድኅነት ጽሑፍ ሰዎች እንዲድኑ የሚረዳ ቢሆን ኖሮ የማኅበሩ መሪዎችና አባላት እንዲህ ጽድቅ በሚመሰል በቃሉ ሲፈተሽ ግን ኃጢአት በሆነ በብዙ መንፈሳዊ ችግር ውስጥ አይዘፈቁም ነበር፡፡

ሰው በሚያድነው የወንጌል እውነት ብቻ ማመን እንዳለበት ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ እና ሐዋርያቱ አበክረው አስተምረዋል፡፡ ጌታ ገና አገልግሎቱን ሲጀምር «ዘመኑ ተፈጸመ የእግዚአብሔር መንግሥት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ በወንጌልም እመኑ» እያለ አገልግሎቱን ጀምሯል ማር. 1÷15፡፡ በአገልግሎቱ ፍጻሜም፤ «በሙሴ ሕግና በነቢያት በመዝሙራትም ስለ እኔ የተጻፈው ሁሉ ይፈጸም ዘንድ ይገባል» ሉቃ. 24÷49 በማለት እውነተኛ እምነት በቅዱሳት መጻሕፍት ላይ መመሥረት እንዳለበት አረጋግጦአል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስም «…ለመዳን በእርሱ እንድታደርጉ አሁን እንደተወለዱ ሕፃናት ተንኩል የሌለበትን የቃልን ወተት ተመኙ» 1ጴጥ. 2÷2-3 በማለት ለመዳን የቃሉን አስፈላጊነት ተናግሯል፡፡ «እንድንበት ዘንድ ከሰማይ በታች የተሰጠ ሌላ ስም የለም» ሐዋ. 4÷12 በማለትም የእግዚአብሔርን የማዳን መንገድና እውነት አረጋገጠ፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም «በወንጌል አላፍርምና አስቀድሞም ለአይሁዳዊ ደግሞም ለግሪክ ሰው የእግዚአብሔር ኃይል ለማዳን ነውና፡፡ ከሕፃንነትህም ጀምረህ ክርስቶስ ኢየሱስን በማመን መዳን የሚገኝበትን ጥበብ ሊሰጡህ የሚችሉትን ቅዱሳት መጻሕፍትን አውቀሃል» በማለት መዳን የእግዚአብሔር እስትንፋስ ባለባቸው መጻሕፍት እውነት ላይ ብቻ የተመሠረተ እንደሆነ አረጋግጧል፡፡ ሮሜ 1÷16፤ 2ጢሞ 3÷15፡፡ ከወንጌል ጋር የማይስማማውን ሌላ ትምህርትም፤ «ነገር ግን እኛ ብንሆን ወይም ከሰማይ መልአክ ከሰበክንላችሁ ወንጌል የሚለይ ወንጌልን ቢሰብክላችሁ የተረገመ ይሁን»በማለት ጽኑ ውግዘትን አስተላልፏል፡፡  ይህንን ውግዘት ያስተላለፈበት ምክንያት ከቅዱሳት መጻሕፍት በቀር ሌሎች መጻሕፍት የመዳንን እውቀት የማይሰጡና ሰዎችን ከመዳን እውነት የሚያርቁ ወደ ጥፋትም የሚመሩ የኑፋቄ ሐሳብ የያዙ በመሆናቸው ነው፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን የክርስቶስ ስም የወንጌልም ተቃዋሚ ነው በፍጡራን ስም የተጻፉ የተሳሳቱ ድርሰቶች መንፈሳዊ መጻሕፍት ተደርገው እንዲቆጠሩ ብርቱ ጥረት አድርጓል፡፡ ይህም ብቻ አይደለም አልተሳካለትም እንጂ ለሚሊኒየሙ (2008 ዓ.ም) በተዘጋጀው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለ ክርስቶስ የተጻፉ ብዙ እውነቶችን የተዛባ ትርጉም በመስጠት ለመሸቃቀጥ የሚያመቸውን ሁኔታ ለመፍጠር ብርቱ ጥረት አድርጓል፡፡ ይህንኑ የተበለሻሸ መጽሐፍ ቅዱስ «የእኛ መጽሐፍ ቅዱስ» በማለት ከተገዛበት ዋጋ በብዙ እጥፍ በመሸጥ ትልቅ ንግድ አካሂዷል፡፡

ይህ 36 ገጾች የያዘው የማኅበሩ የትምህርተ ድኅነት ጽሑፍ በመቅድሙ ያስፈረውን የድኅነት መንገድን የማሳየትን ዐላማ በውስጥ ገጾች በመሻር የመዳንን መንገድ የሚሸፋፍኑ ሐሳቦችን ይዞ ቀርቦአል፡፡ ጽሑፉ በውስጥ ገጾቹ «የነገረ ድኅነት መነሻው የአዳም ውድቀት ጉዳይ ነው» ገጽ 4 በማለት ማብራሪያውን ይጀምራል፡፡ ይህ ፈጽሞ ስህተት ነው፡፡

የመዳን ትምህርት መነሻው የአዳም ውድቀት ሳይሆን የእግዚአብሔር ፍጹም ፍቅር ነው፡፡ እግዚአብሔር ከታላቅ ፍቅሩ የተነሳ የጠፋውን ሰው ሊያድን ወደደ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያረጋግጠው ይህንን እውነት ነው፤ ዮሐ. 3÷16፤ዮሐ. 15÷13 ሮሜ 5÷8፡፡ እግዚአብሔር ሰውን አፍቃሪ ባይሆን ኖሮ የጠፋውን /በኃጢአት የወደቀውን/ ሰው እንደዚያው እንደወደቀ መተው ይችል ነበር፡፡ ሰውን ለማዳን ያቀደው ከታላቅ ፍቅሩ የተነሳ ነው፡፡ ስለዚህም የአዳም ውድቀት የድኅነት መነሻ ሲሆን አይችልም፡፡

ጽሑፉ ጥቅልል ሐሳቦችን ከመስጠትና ከመዳን ትምህርት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት የሌላቸውን ሐሳቦች ይዘረዝራል እንጂ «እንድትድኑ ይህንን አድርጉ» ብሎ ግልፅና ቀጥተኛ ምክር አይሰጥም፡፡ ጽሑፉ በሌላ ርዕስ ሥር ትኩረት ሊያገኙ የሚገባቸውንና ከትምህርተ ድኅነት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት የሌላቸውን ሐሳቦች አካቷል፡፡ በጽሑፉ የዲያብሎስ ማሳትና የአዳምን ውድቀት የተቀነጫጨቡ የሃይማኖት ትምህርቶችን (ለምሳሌ ምሥጢረ ሥላሴ፣ ጥምቀት፣ ቅዱስ ቁርባን፣ መልካም ሥራ፣ መንፈሳዊ ተጋድሎ፣ ጾም፣  ጸሎት፣ ስግደት … ወዘተ የሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ተካተዋል፡፡

«ቃል ኪዳን በነገረ ድኅነት» የሚለው በማኅበሩ የአመራር አባል በዲ/ን ያረጋል አበጋዝ በ2006 ዓ.ም የተዘጋጀው መጽሐፍ ከላይ ከቀረበው የማኅበሩ የነገረ ድኅነት ጽሑፍ በብዙ መልኩ የተሻለ ነው፡፡ በአንዳንድ መልኩም ልዩነት አለው ለምሳሌ «የአዳም ውድቀት ለነገረ ድኅነት መነሻ ነው» በሚለው ሐሳብ ላይ «የሰው ድኅነት የእግዚአብሔር የቸርነቱ ስጦታና ለሰው ያለው የማይለወጥ ፍቅር ውጤትና መገለጫ ነው ገጽ 72»  ይህም መጽሐፍ እንደዚሁ ከትምህርተ ድኅነት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት የሌላቸውን በርካታ ርዕስ ጉዳዮችን አጭቆ  ይዟል፡፡» የመጀመሪያዎቹ 62 ገጾች ስለተለያዩ ቃል ኪዳኖች ያትታሉ÷ እርስ በርሳቸው የሚጋጩ ሐሳቦችንም ይዟል፡፡ እንደምሳሌ የሚከተለውን እንመልከት፡፡

«ኃጥአን የሚፈረድላቸው የእግዚአብሔርን ቸርነት ለመጠቀም የሚያስችል ሥራ ስላልሠሩና በዓመፅ ስለኖሩ ነው እንጂ እግዚአብሔር በእነርሱ ላይ ስለሚጨክን አይደለም፡፡ አንድ ሰው ለዘላለም ሕይወት የሚበቃውም ሆነ የሚፈረድበት በራሱ ሥራ እንጂ በትውልድ ሐረግ ወይንም በሌላ ሰው ሥራ አይደለም» ገጽ 92፡፡
«በኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮ ሰው የዳነው በእግዚአብሔር ቸርነት (ጸጋ) ነው፡፡ የሰው ድኅነት የእግዚአብሔር ስጦታና ለሰው ያለው የማይለወጥ ፍቅር ውጤት መግለጫ ነው፡፡» ገጽ 72፡፡ የመጀመያው በገጽ 92 ያለው ከኤፌ 2÷8 ጋር ሲጋጭ ሁለተኛው ሐሳብ በገጽ 72 የተጠቀሰው ከዚህ የኤፌሶን ጥቅስ ጋር ይሰማማል፡፡ በገጽ 112 ደግሞ «የእግዚአብሔር ምሕረት የሚገለጥበት መንገድ ብዙ ነው» ይላል፡፡ ይህ ሐሳብ ክርስቶስ ብቸኛ አዳኝ (ዮሐ 14÷6) ሳይሆን ሰው ሊድንባቸው ወይም ምሕረት ሊያገኝ ከሚችልባቸው መንገዶች አንዱ እንደሆነ ያመለክታል፡፡ ሐሳቡ ከኤፌሶን 2÷4-7 እና 1ጢሞ 1÷16 ጋር ይጋጫል፡፡ መካናትን መሳለምም በረከት እንደሚያስገኝ ይናገራል፤ ገጽ 13፡፡ ይህንን ሐሳብ ከኤፌ. 1÷3 ጋር በአስተያየት አባባሉ ስህተት እንደሆነ በቀላሉ መረዳት ይቻላል፡፡

እነዚህ በማኅበሩ «ነገረ ድኅነት» ተብለው የቀረቡት ጽሑፎች አንድን ኃጢአተኛ በክርስቶስ በማመን ስለመዳኑ የልብ ምስክርነት እንዲኖረው አያደርጉትም ወይም አይረዱትም፡፡ ይልቁንስ ይህን ይህን አድርጌ ይህን ይህንንም ፈጽሜ እያለ መዳን ወደ ማያስችለው የራስን ጽድቅ  ወደ መሥራት የጥረትና የግለት አዘቅት ይከቱታል፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን በዚህ ዓይነት ትምህርት የክርስቶስን ግልፅ የማዳን እውነት በመጋረድ ብዙዎችን እውነትን ያጡ ተንከራታቾች አድርጓቸዋል፡፡ የሰው መዳን በክርስቶስ ቤዛነት ላይ የተመሠረተ እንጂ «በማኅበሩ ነገረ ድኅነት» በተጠቀሱት ድምር ውጤቶች ላይ አይደለም፡፡ ሰው ለመዳን የሚያበቃውን እምነትና ካመነ በኋላ መፈጸም ያለበትን ክርስቲያናዊ ግዴታ ማደበላለቅ ያደናግራል፡፡ መዳን ቅፅበታዊ እንጂ በሂደት የሚገኝ ክስተት አይደለም፡፡ ሰው ኃጢአቱን ተናዞ ክርስቶስን ባመነበት ቅጽበት ወዲያኑ የኃጢአት ስርየት ያገኛል፡፡ ከልዑል እግዚአብሔርም ጋር ታርቆ የእግዚአብሔር ልጅ ይሆናል ዮሐ 1÷12፡፡ በእግዚአብሔር ቸርነት ስለመዳኑም እርግጠኛ ይሆናል፡፡ ሰው ባመነበት ቅፅበት ቢሞት ወዲያውኑ ወደ ገነት ይገባል፡፡ ለዚህ በጌታ ቀኝ የተሰቀለው ወንበዴ ጥሩ ምሳሌ ነው፤ ሉቃስ 23÷42-43፡፡ በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 16 የተጠቀሰው የወህኒ ቤቱ ጠባቂ «እድን ዘንድ ምን ላድርግ?» ብሎ ስለጠየቀው ጥያቄ «በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ እመን አንተና ቤተሰቦችህም ትድናላችሁ» የሚለውን ትክክለኛ መልስ ተቀብሎ በማመኑ ወዲያውኑ ድኗል ሐዋ.16÷3ዐ-31፡፡ የነገረ ድኅነትን ዐላማ ይዘት የሚያመለክቱ በርካታ ምሳሌዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ 

ኃጢአተኛ ሰው ጌታ ኢየሱስ ክርሰቶስን ባመነበት ቅፅበት ይዳን እንጂ ከዚያ በኋላ ባለው ዘመኑ ትምህርተ ሃይማኖትን በመማርና በመጐልመስ÷ ቅዱሳት ምሥጢራትን በመፈጸም÷ መልካም ሥራ ወይም ጽድቀን በመፈጸም ራሱን በመግዛትና ክርስቶስን በመምሰል ሊመላለስ ይገባዋል፡፡ እነዚህን የኋለኞቹን ተግባሮች ለመፈጸም ሰው በቅድሚያ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ አምኖ መዳን ይገባዋል፡፡ ባመነ ሰው ሕይወት የእግዚአብሔር ጸጋ ስለሚሠራ እምነትና መልካም ሥራ በሰመረ ግንኙነት ይገለጻሉ፤ 1ተሰ. 1÷6-10፤ ቲቶ 2÷11-14፡፡ 

ስለ ክርስቶስና ስለ ድንግል ማርያም የተሳሳተ ትምህርት በማስተማር ማኅበረ ቅዱሳን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለ ክርስቶስ የሚናገሩ እውነቶችን በመለወጥና የተሳሳተ ትርጉም እንዲኖራቸው ከማድረግ ጀምሮ የነገረ ክርስቶስን ትምህርት ለማዛባት ተደጋጋሚ ጥረቶችን ከማድረጉም በላይ ቅድስት ድንግል ማርያምንም የአምላክነት ባሕርይ ለመስጠት እየሞከረ ይገኛል፡፡

በሁለት የሐመር መጽሔቶችና ማኅበሩ ከመቋቋሙ በፊት የመሰረት ድንጋይ በጣሉ ከተቋቋመም በኋላ ከፍተኛ አስተዋፅፆ ባደረጉና ሊቀ ትጉሃን ኃይለ ጊዮርጊስ ዳኜ  በተባሉ ሰው የቀረበውን ኑፋቄ ደግሞ እንመልከት፤-
«መርከቢቱ ባለ ሦስት ክፍል መሆኗ  እመቤታችን የሥላሴ ማደሪያ ለመሆኗ ምሳሌ ከመሆኑ በተጨማሪ የድንግል ማርያምን ንጽሐ ሥጋ ንጽሐ ነፍስና ንጽሐ ልቡና ያጠይቃል»  ሐመር መጀመሪያ ዓመት ቁጥር 1 ጥር 1985 ዓ.ም፤ «ከመፈጠሯ በፊት በእግዚአብሔር ስትታሰብ የነበረችውና በኋላም በንጽሕና አጊጣ በቅድስና የኖረችው የድንግል ማርያም ማሕፀን ሥሉስ ቅዱስን ለማስተናገድ የበቃቸው እግዚአብሔር በሚወደው ሕይወት ስለተገኘች ነው፡፡ ሐመር የመጀመሪያ ዓመት ቁጥር 5 ነሐሴ 1985 ዓ.ም ገጽ 11፡፡

«…እመቤታችን ከንጽሕናዋና ከቅድስናዋ የተነሣ የልዑል እግዚአብሔር አማናዊት ቤተ መቅደስና አማናዊት መንበረ ክብሩ እንደሆነች ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ታምናለች፡፡ ታስተምራለች፡፡ ሕዝ. 11÷2-4፤ ዕብ. 9÷11፡፡» (በእርሱ አምሳል እንወለድ ዘንድ ስለእኛ ተጠመቀ ጥር 2ዐዐ7 ዓ.ም ገጽ 36)፡፡ እነዚህ ጥቅሶች በፍጹም ከተጻፈው ሐሳብ ጋር የማይገናኙ መሆኑን ልብ እንበል፡፡

በሦስቱም መጽሔቶች ስለ ቅድስት ድንግል ማርያም የቀረቡት ሐሳቦች የኑፋቄ ሐሳቦች ናቸው፡፡ በባሕርይው ቅዱስ የሆነ፤ «በቅድስና የከበረ እንደ አንተ ያለ ማነው? አንተ ብቻ ቅዱስ ነህና» ዘፀአት 15÷11 ራእይ 15÷4 የተባለው እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡  የሰው ዘር በባሕርዩ ወይም በተፈጥሮው ቅዱስ ሊሆን በፍጹም አይችልም ሮሜ 3÷11፤ 5÷12፡፡ ሰው ቅድስናውን ወይም የሕይወት ንጽሕናውን የሚያገኘው ከእግዚአብሔር ጋር ባለው ሱታፌ ብቻ ነው፡፡ ቅድስት ድንግል ማርያምም ቅድስት የተባለችው ወይም የሕይወት ንጽሕናዋን ያገኘችው በተፈጥሮ ባላት ባሕርይ ሳይሆን መንፈስ ቅዱስ ስለቀደሳት ብቻ ነው ሉቃ. 1÷35፡፡ እርሱን እንድትወልድ ጌታ የመረጣትም እንዲያው በጸጋው እንጂ የእርስዋ ንጽሕና ማርኮት አይደለም፡፡ «መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ማርያም ሆይ በእግዚአብሔር ፊት ጸጋ አግኘተሻልና አትፍሪ» ሉቃ. 1÷30 አላት እንጂ ንጽሕናሽ ማርኮት እግዚአብሔር መርጦሻል አላላትም፡፡ «ድንግል ማርያም ጥንተ አብሶ የለባትም» የሚለውና የድንግል ማርያምን ንጽሕና ተፈጥሮአዊ የሚያደርገው ትምህርት የመጽሐፍ ቅዱስም ሆነ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ትምህርት አይደለም ከካቶሊኮች የተቃረመ ኑፋቄ ነው፡፡

ይቀጥላል8 comments:

 1. Sir yefeta min qobun qedo yisefal aluu...

  ReplyDelete
 2. Jiloch, you are becoming radiculous! Though you are totally anti-tewahido, please at least try to avoid being a clown.

  ReplyDelete
 3. Dear my brother in Christ,

  Being protestant,you can never write about the truth of the Holy Church.

  It is not write decision for you to write on this issue.

  Why you kill your precious time? If I could get a bulk of time like you, I will go to the Seminary, study and understand all there. Or I would ask the Doctors(liqawunts) of our Holy Church and assimilate all there.

  All your writings are the view of your fellow brothers and sisters.

  All your arguments do not convince any one and has been presented unsound, as well as contrary to the teachings of our Holy Church.

  First study, study, ask, ask, and have a good understanding on the matter then you can present all better.

  You can not reform Tewahedo, as she is united with the blood and flesh of her members.

  ReplyDelete
 4. ማቆች ታቦት ወደ ግብጽ ልከዋል የሚባለው ነገር እውነት ነው?

  ReplyDelete
 5. አንተ ማለት የበግ ለምድ የለበስክ ተኩላ ነሕ፡፡ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ክ ሆነ ማኅበረ ቅዱሳን ሰዎች ክብር ይግባውና በጌታችን በመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሳያምኑ ደግ ምግባራትን ሳይሰሩ በቅዱሳን ምልጃ ብቻ ይድናሉ ብለው አላስተማሩም፡፡
  ሰው ለመዳን ማመን አለበት፡፡ በመቀጠል ሚስጥራተ ቤ/ክ እና ደጋግ ስራዎችን መፈጸም አለበት፡፡ ይሕም ቤ/ክ ከጥንት ጀምሮ የምታምነው እምነቷ ነው፡፡ ነገር ግን አንዳንዴ ለሚገጥሙን ችግሮች እና ለምንፈጽማቸው ኃጥያት ስለቅዱሳን አማላጅነት እግዚአብሔርን እንማጸነው ዘንድ ይገባል፡፡
  ይሕ እምነታች ደግሞ ጥንት ከነብያት በኃላም ከሐዋርያት የተቀበልነው እንጂ ከማንም ተራ መናፍቃን ያገኘነው አይደለም፡፡ ስለዚሕ ያልተባለውን እንደተባለ አድርገሕ አታውራ፡፡
  አንድ ነገር ልንገርሕ፦
  የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ክ አይደለም መናፍቃን እና ተሃድሶ ቀርቶ የገሃነም ደጆች እንኳን አይችሏትም!!!

  ReplyDelete
 6. ቀላዋጭ ሁሉ! የምታምንበት ከሆነ ያንተንው እምነት አጥብቀ ያዝ፡፡ እዛው በአዳራሽህ!!!!!!!!!

  ReplyDelete
 7. ክርስቶስን ማመን ላይ የተመሰረተን ክርስትናን ነው የገሀነም ደጆች የማይችሏት።ክርስቶስ የተጠላባት ስሙ ገኖ የማይሰማባት ቤተ ክረስቲያን ወንጌል ወንጀል የሆነባት ቤተ ክርስቲያን።ሳይሸቀጥ ተሰብኮባት የማይታወቅ ።ብዙ አዳነኝ ብዙ ቤዛ ያላት ቤተ ክርስቲያን ሰባኪ ተብየዎችዋ ከእግዚአብሂር ይልቅ ሰውን ለማስደሰት የቆሙ።

  ReplyDelete
 8. The truth the life the only way to be saved it is only through Jesus Christ.there is no other way to be saved case closed. but after you saved you do good thing because you are oblegated by the grace of GOD. The holy spirit is the one helping you to do good thing. but first you saved by fith through Christ Jesus.If you are not saved by reciving Jesus no holy spirit in you so no good thing to come out from you. You need Holy spirit to help you to do the right thing.May the Lord Jesus open your inside of your eyes.

  ReplyDelete