Sunday, August 28, 2016

ነጻነትነጻነት የሰው ፍላጎት ብቻ ሳይሆን የሰው ተፈጥሮውም ነው። ነጻነት ስለፈለግን አይደለም ስለ ነጻነት የምንጮኸው ነጻ ሆነን ስለተፈጠርን ነው። ያለተፈጥሯችን እንድንሆን የሚፈልጉ ሁሉ ተፈጥሮን ለማበላሸት የሚደክሙ ናቸው። እግዚአብሔር በነጻነት ውስጥ ያስቀመጠው ታላቅ ምሥጢር አለ ይህ የእግዚአብሔር ጥበብ እጅግ በጣም አስደናቂ ነው። ማነኛውም የሰው ልጅ እውቀትና ችሎታ በሥራ ላይ ውለው ለሰው ጥቅም የሚሰጡት በዚህ በነጻነት ምሥጢር ነው።
ነጻነት በእግዚአብሔር መንፈስ የተሰጠ የሰው ማንነት ነው። ሰው ነጻ ፍጡር መሆኑን የሚያንጸባርቀው ገና ሲወለድ ጀምሮ ነው። ሕጻናት አቅም ካላነሳቸው በቀር ዝም ብለው መቀመጥ አይችሉም መሮጥ መጫወት ይፈልጋሉ እናት እና አባት እነርሱን ለመቆጣጠር ሲሞክሩ ተቃውሞአቸውን በለቅሶ ይገልጣሉ። ይህ ሁኔታ የነጻነት ፍላጎት በትምህርት ወይም በአካባቢ ሁኔታ የሚገኝ ሳይሆን በተፈጥሮ በውስጣችን ያለ የእግዚአብሔር ምሥጢር መሆኑን የሚያመለክት ነው። ነጻነትን በአግባቡ ማስተዳደር እንጂ መገደብ አደጋ አለው። ለመርከስም ሆነ ለመቀደስ ነጻነት አለን። ምርጫው የራሳችን ነው። እግዚአብሔር በጉልበት አይቀድሰንም። በኃይልና በግዴታ ቅድስና የለም። እግዚአብሔርን በመምረጥና ለቃሉ በመታዘዝ እንጂ። ይህን ሐሳብ በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ እናገኘዋለን።

 "በፊታችሁ ሕይወትንና ሞትን በረከትና መርገምን እንዳስቀመጥሁ እኔ ዛሬ ሰማይና ምድርን በአንተ ላይ አስመሰክራለሁ እንግዲህ አንተና ዘርህ በሕይወት ትኖሩ ዘንድ ሕይወትን ምረጥ” ዘዳ. ም 30 ቁ 19።
 "ምረጥ” የሚለው ቃል የሰውን ሙሉ ነጻነትና መብት የሚያመለክት ቃል ነው። መሞት ወይም በሕይወት መኖር የራሳችን ምርጫ ነው። እግዚአብሔር የመረጥነውን መንገድ አይቶ ፍርዱን ይሰጣል እንጂ በግዴታ አይገዛንም። በሌላ ስፍራ "ዓመፀኛው ወደ ፊት ያምፅ ርኵሱም ወደ ፊት ይርከስ፣ ጻድቁም ወደ ፊት ጽድቅን ያድርግ ቅዱሱም ወደ ፊት ይቀደስ አለ” ይላል ራእ ም 22 ቁ 11። ለመርከስም ሆነ ለመቀደስ የሰው ምርጫ ነው እግዚአብሔር ግን እውነተኛውና የሚያዋጣውን መንገድ መናገርና ማስጠንቀቅ ነው ሥራው። ከዚያም እንደየምርጫችን ዋጋችንን ያስረክበናል።
ስለዚህ ሰው ነጻ ፍጡር ነው፤ የፈጠረ ያሳደገ የሚያኖር እግዚአሔር እንኳ ለሰው የሰጠውን ነጻነት ነው ሰዎች ለመከልከል እየሞከሩ ያሉት። ይህ የማይሆን ነገር ነው። ነጻነት ግን ከተጠያቂነት እንደማያድነን ማወቅ ግዴታችን ነው፤ ወንጀልን እንዳንፈጽም ሕግ ወጥቶልናል፣ ወንጀል ብንሠራ በሕግ ልንጠየቅ እንችላለን፤ ምክንያቱም ነጻ ስለሆንን እና ነጻነታችንን ያላግባብ ስለተጠቀምነው ነው። ለመዳንም ሆነ ለመሞት መነሻው ነጻነታችን ነው። ሕግ ነጻ ለሆነው ፍጡር ለሰው እንጂ ለእንስሳ ወይም ለመላእክት አልተሰጠም።
በዓለም ላይ ታላላቅ የርስ በርስ ጦርነቶች ተደርገዋል፤ በየጊዜው የብዙ ሕዝብ ደም ብዙ ጊዜ ፈሶአል እየፈሰሰም ነው የሕዝብ አመጽ በየሀገሩ ይካሔዳል አብዛኛው ምክንያት ግን ነጻነት ነው። ነጻነትን በጣም የሚፈሩ ሰዎች ብዙ አፈና ሲያደርጉ እየነኩ ውይም እያበላሹ ያሉት የግዚአብሔርን ምስጢር ወይም የሰውን ዋና ነገር መሆኑን አይገነዘቡም። አምባ ገነኖች መጨረሻቸው ሳያምር የቀረው የነጻነትን ምሥጢር ሳያውቁ በመቅረታቸው ነው።
ነጻነት ውድ ስለሆነ ትልቅ ዋጋ ያስከፍላል፣ ነጻነት እስካሁን ድረስ ያለደም ተግኝቶ አያውቅም መንፈሳዊው ነጻነት እንኳ የተገኘው በደም ነው። ለምሳሌ፣ እስራኤላውያን ከፈርዖን ሁለንተናዊ አገዛዝ ነጻ የወጡት ነውር የሌለበት በግ ታርዶ ደሙ በር ላይ ከተረጨ [ከተቀባ] በኋላ ነበር። እንዲሁም ማንኛውም ኃጢአተኛ ከበደሉ ነጻ ሊሆን የሚችለው ስለበደሉ ያቀረበው መሥዋት ከተሠዋ በኋላ ነው። ነጻነት እንዲሁ በዋዛ የምናወራው ነገር አይደለም ፤ በነጻነት ምክንያት በዓለም ላይ ብዙ ደም ፈሷል። ነጻነት ይህን ያህል ዋጋ የሚያስከፍል ለምን ይሆን ብለን ብንመረምር በሰው ውስጥ ያለ የእግዚአብሔር ጥበብ ስለሆነና አፍኖ ማስቀረት ስለማይቻል ነው። ነጻነትን ከደም ጋር ሳያይዝ ዛሬም በደም ነጻነት ይመጣል እያልሁ ሳይሆን የነጻነትን ዋጋ ትልቅነት ለማሳየት መሆኑን አንባቢ ይረዳልኝ።
እውነተኛው የሕይወት ነጻነት የሚገኘው ግን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው። "እውነት ነጻ ያወጣችኋል” የሚለው የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቃል ብዙ ጥልቅ ትርጉም አለው። ይህ ነጻነት የዲሞክራሲ መሠረት ነው የመልካም አስተዳደር መንገድ ነው። የፍትሕ ዙፋን የእውነተኛ ፍርድ ወንበር ነው። ሰው የነጻነት ጥያቄው  በትክክል ተመልሶለት እረፍት የሚያገኘው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ ሲደርስ ነው። "ለታሰሩ መፈታትን፣ ለታወሩ ማየትን እሰብክ ዘንድ የተጠቁትን ነጻ አወጣ ዘንድ የተወደደችውን የጌታን ዓመት እሰብክ ዘንድ ልኮኛል” ይላል ሉቃ ም 4 ቁ 19። በሰው ውስጥ ያለው የእግዚአብሔር ጥበብ የሚገለጠው፤ ትርጉም ወይም ፍቺ የሚያገኘው ኢየሱስ ክርስቶስን በማወቅ ነው። በኢየሱስ ክርስቶስ ያልተገኘ ነጻነት በፖለቲካም ሆነ በኢኮኖሚ ይምጣ ሌላ ባርነት አለው። በክርስቶስ ነጻ ያልወጣ ሰው ሌሎችን ባሪያ ማድረጉ የማይቀር ነገር ነው። ባርነት ሙሉ ለሙሉ የሚወገደው በኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው ። ይህ የእግዚአብሔር ምሥጢር ነው።
ነጻ አውጭ  ነን ሲሉ የነበሩት  ሁሉ ዛሬ እጃችንን በአፋችን ላይ አስጭነው ባሪያ አድርገው እየገዙን ነው። በተለይም የአፍሪካ ነጻ አውጭዎች የሚገርሙ ናቸው። ዲያብሎስ ዓለምን እየገዛ ያለው በአምባ ገነን ባሪያዎቹ በኩል ነው። በነግራችን ላይ በክርስቶስ ነጻ ያልወጡ ገዥዎች ዕረፍት ያመጡልናል ብሎ ማሰብ ሞኝነት ነው። ነጻነት የእግዚአብሔር ጥበብ ነው። ያለክርስቶስ ደግሞ ይህን ድንቅ ምሥጢር ማወቅና መጎናጸፍ አይቻልም። ዛሬም በክርስቶስ ነጻ የወጡ ነጻ አውጭዎችና ነጻ የወጡ ገዥዎች ያስፈልጉናል። ከኃጢአት ማለት ከተንኮል ከግፍ ከክፋት ፍርድን ከማጣመም ከቂምና ከበቀል ከሐሰትና ከክህደት ከስስትና ከሌብነት ከዘርኝነት እና ከትዕቢት ነጻ የወጡ ነጻ አውጭዎች ያስፈልጉናል።
                     ከደብረ ሰላም መጽሔት ላይ የተገኝና ተሻሽሎ የቀረበ

7 comments:

 1. we know those countries have freedom but they did evil work like homo sex may be you are calling this freedom that is absolutely wrong you are calling this time in our country. the true freedom comes with jesses that through true believe and work with out this all thing is dead.
  God bless Ethiopia.

  ReplyDelete
 2. አሜን!!! ቃለሕይወት ያሰማልን።
  የሠላም የፍቅር አምላክ እንደዚህ ያሉትን ትምህርቶች ከመልካም አንደበተኞች መምህራን እንዲያዘንብልን የዕለት ዕለት ጸሎታችን ይሁን--የዓለም የጥላቻ፤ የጭቅጭቅ፤ የሰው ልጅ በሰው ልጅ ላይ ጭካኔ ድርጊት፤ ለአእምሮ በሚዘገንን ሁኔታ የሚሆነውን በየቤታችን TV መስኮት እየመጣ ናላችንን እያናወዘው ነውና እባካችሁ በየአለንበት የአርምሞ ጸሎት እናድርግ። ለዚህም አምላክ ይርዳን። አሜን!!!

  ReplyDelete
 3. This is Great. Blessings to you

  ReplyDelete
 4. በዚህ ወቅት የሚያጽናና መልኽክት ነው። ተባረክ!

  ReplyDelete
 5. አሁን የደርግ ስብስብ የሆነው ማቅ (ማ/ቅዱሳን)ተኩሶ በአገሪቱ ላይ በተለያየ አቅጣጫ ተኩሶ ጥይት ጨርሷል። ከዚህ በኋላ በቁጥጥረደ ስር ማዋል ብቻ ነው የሚቀረው።

  ReplyDelete
 6. ማ/ቅዱሳን ውድ የኢትዬጲያ ልጆች ናቸው። ትንሽ የክርስቶስ ወንጌል ላይ የአመለካከት ችግርም ቢኖረን ወንድሞቻችን ናቸው። ለመሆኑ ደርግ ከወያኔ በብዙ እጥፍ እንደሚበልጥ ተውቃለህ?

  ReplyDelete