Sunday, September 4, 2016

ግመሉን በዝምታ ትንኙን በጫጫታ


Read in PDF
ከአሸናፊ በላይ
የመጨረሻ ክፍል
ከኑፋቄ ሁሉ የከፋ ኑፋቄ
ለጥምቀት (2007 ዓ.ም) የታተመውና በነፃ የተሠራጨው «በእርሱ አምሳል እንወለድ ዘንድ ስለ እኛ ተጠመቀ»የሚለው መጽሔት እጅግ አደገኛ ኑፋቄ ይዞ ወጥቶአል፡፡
«እመቤታችን ጥንቱን ሰው ሊፈጠር ንጽሕት ዘር ሆና ተወልዳለች፡፡ ጥንተ አብሶ የለባትም የልጇም ንጽሐ ባሕርይነት ከምንጩ ከእናቱ ከድንግል ማርያም ፍጹም ንጽሕና የተነሣ ነው» ገጽ 36፡፡ ቀደም ብሎ በሁለት የሐመር መጽሔቶች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ባልሆነ መንገድ የቅድስት ድንግል ማርያም ንጽሕናና ቅድስና በአፅንኦት የተነገረን ለዚህ ለተሳሳተ ትምህርት መሠረት ይሆን ዘንድ እንደሆነ ልብ እንበል፡፡ እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት እግዚአብሔር ወልድ (በጽሑፉ ልጃE የተበሰረው) በራሱ ንጽሐ ባሕርይ የሌለውና የባሕርይውን ንጽሕና ያገኘው ሰብአዊ ፍጡር ከሆነችው ከእናቱ ከድንግል ማርያም አይደለም፡፡ የባሕርይ ንጽሕናውን ከሰብአዊ ፍጡር አገኘ ማለት የወልድን የባሕርይ አምላክነት የሚያስክድ አጋንንታዊ ትምህርት ነው፡፡
ወልደ እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ በባሕርይው እውነተኛ አምላክ በመሆኑ ቅዱስ ነው፡፡ የባሕርይ ንጽሕናውን ከሌላ ሰብአዊ ፍጡር የሚቀበል ፍጡር አይደለም፡፡ «እኔና አብ አንድ ነን» ብሎ የተናገረ ጌታ ከፍጡር ንጽሕናውን የሚበደር አምላክ አይደለም፡፡ በቤተ ክርስቲያን ቅዳሴም አንዱ አብ ቅዱስ ነው÷ አንዱ ወልድ ቅዱስ ነው÷ አንዱ መንፈስ ቅዱስ ቅዱስ ነው እየተባለ ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ እኩል ይመሰገናል፡፡» እርሱ ሕጸጹን የሚያሟላ ረዳት አያሻውም (ጎርጎርዮስ (አባ) የቤተ ክርስቲያን ታሪክ በዓለም መድረክ ገጽ 98)፡፡
በጣም የሚገርመው ይህ አጋንንታዊ ትምህርት  የያዘው መጽሔት በቤተ ክርስቲያኒቱ ልሳን አዘጋጅ መዘጋጀቱ÷ በቤተ ክርስቲያኒቱ ተቋም በትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት መታተሙ÷ ቤተ ክርስቲያኒቱ በምታከብረው የጥምቀት በዓል ላይ በነፃ መታደሉ ነው፡፡ የበለጠ የሚያስገርመው ደግሞ ቅዱስ ሲኖዶስና የሊቃውንት ጉባኤው በቸልታ ጉዳዩን ማየታቸው ነው፡፡ የኑፋቄው ጸሐፊ ብቻ ሳይሆኑ የቤተ ክርስቲያን አለቆችም በልዑል እግዚአብሔር ፊት ይጠየቁበታል፤ በታሪክም ይወቀሱበታል፡፡ 

ባለፈው ጽሑፍ ማኅበረ ቅዱሳን ከሚያደርጋቸው ጥቃቅን ክፉ ሥራዎቹ ይልቅ ለክፉ ሥራው ምንጭ በሆነው የኑፋቄው ጉዳይ ላይ ትኩረት ማድረግና ተገቢውን እርምጃ መውሰድ አስፈላጊ እንደሆነ ኑፋቄውን በማስመልከት ሐሳብ መስጠታችን ይታወሳል፡፡ በዚህ ቀጣይ ጽሑፍ ደግሞ ማህበረ ቅዱሳን እንዴት ኑፋቄውን እንደልቡ መዝራት የሚችልበት ደረጃ ላይ እንደደረሰና የማኅበሩ ቀጣይ ዕጣ ፋንታ ምን ሊሆን እንደሚችል እንደዚሁም በስብከተ ወንጌል እያገለገሉ ያሉ የቤተ ክርስቲያን ልጆችና የቤተ ክርስቲያን አለቆች ድርሻ ምን ሊሆን እንደሚገባው ሐሳብ እንሰጣለን፡፡
የማኅበሩ ምሥረታ መንስኤ
እውስጥ ባሉ ካህናተ ደብተራና በአንዳንድ ውጫዊ ግፊቶች ብቅ እያለ የሚጻፍን በቤተ ክርስቲያኒቱ ቀደም ብለው የተጠቀሱት ኑፋቄዎች ጥንስስ ነበረ፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱ በፖለቲካና በኢኮኖሚ የነበራትን ሥፍራ እያጣችና እየተዳከመች ስትመጣ፤ «የቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ ተሐድሶ» በሚል አደረጃጀት ሥልጣን ለመያዝ የሚጥር ቡድን በአብዮቱ ወቅት ማለት ነው ብቅ አለ፡፡ ይህ ቡድን በአገኘው አጋጣሚ ሁሉ በመጠቀም ሥልጣን ላይ ለመውጣት አሰፈሰፈ፡፡ በፖለቲካው ሰበብ የቤተ ክርስቲያን መሪዎችን በመጋፋት ለማንሰራራት ጣረ፡፡
ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ደግሞ የፍጡራንን አምልኮ በቤተ ክርስቲያኒቱ እንዲቀጥል÷ በቤተ ክርስቲያኒቱም በጊዜ ሄደት የገቡት ስህተቶችም ከቤተ ክርስቲያኒቱ ምሥረታ ጀምረው የነበሩ የጽድቅ ሥራዎች ሆነው እንዲታዩ «ጻድቃን፤ ሰማዕታትን» በአማላጅነታቸው እዘክራለሁ የሚል ቡድን የሃይማኖት ተቆርቋሪ መስሎ ብቅ አለ፡፡ የቤተ ክርስቲያኒቱን አባላት ድጋፍም ለማግኘት ሽርጉዱን ተያያዘው ይህ ለጽድቅ ፋይዳ በሌለው በተለያዩ ቡድኖች ተከፋፍሎ በተለያዩ ቅዱሳንና መላእክት ስም ጽዋ የሚጠጣ ቡድን ነበር፡፡ ይህን በተለያዩ ፍጡራን ስም ጽዋ የሚጠጣ ቡድን በአንድ ስያሜ ማደራጀት እንዲቻልም «ማኅበረ ቅዱሳን» የሚል ስያሜ ተሰጥቶት በአደረጃጅቱ ቀጠለ፡፡ ቀደም ብሎ የተቋቋመው «የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ተሐድሶ» የማኅበረ ቅዱሳን አስኳል ሆኖ ተቀላቀለ፡፡ ሁለቱ ቡድኖች የሥልጣን የጋራ ጥማታቸውን ለማርካት በጥምረት ቀጠሉ፡፡
ማኅበረ ቅዱሳን እንዴት እዚህ ደረጃ ላይ ደረሰ?
ለዚህ ጥያቄ የተለያዩ መልሶችን መዘርዘር ቢቻልም የተወሰኑ ምክንያቶችን እንመልከት፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን ራሱን «የክፉ ቀን ልጅ» ለማስባል ከርሱ አቋም ጋር የማይመሳሰሉትን እውነተኛ የቤተ ክርስቲያን ልጆችን ስም ማጥፋትን ሥራዬ ብሎ ተያያዘው፡፡ አያቴ ቀደሞ ብሎ የአራዳና የመርካቶ ሌቦች ከሰው ኪስ ገንዘብ ከመነተፉ በኋላ የሚያመልጡበትን ዘዴ ብዙ ጊዜ ያጫውቱን ነበር፡፡ ሌቦቹ ከሰው ኪስ ገንዘብ ከመነተፉ በኋላ «ሌባ - ሌባ - ሌባ - ሌባ» እያሉ ይሮጣሉ፡፡ «አይይይ… ምን ሰርቀውባቸው ይሆን?» እያለ መንገደኛው ሌቦቹን ሳይዝ ያሳልፋቸዋል፡፡ ሌቦቹ «ሌባ  ሌባ - ሌባ - » ብለው ስለለፈለፉ ንጹህ አድርጐ ይገምታቸውና ሳይዝ ያሳልፋቸዋል፡፡ ሌቦቹም እልፍ ብለው በመሰወር  ሳይያዙ በቀላሉ ያመልጣሉ፡፡
ማኅበረ ቅዱሳን የራሱ መናፍቅነት እንዳይነቃበት የርሱን ተረታተረቶች የሚያፈርሰውን ወንጌል የሚሰብኩትን የቤተ ክርስቲያን ልጆች ስም « መናፍቃን - መናፍቃን አፅራረ ቤተ ክርስቲያን ጴንጤዎች… ወዘተ» በማለት ስማቸውን ለማጥፋት የሚቻለውን ሁሉ ሲያደርግ ቆየ፡፡ ዛፍ በክፉ ፍሬው ይታወቃልና ማኅበሩ በክፉ ፍሬው እየተገለጠ እስከመጣ ድረስ ይህንን የማታለያ ዘዴ ሲጠቀም ቆይቷል፡፡ ማኅበሩ በዚሁ በሐሰት ውንጀላው ብዙ የወንጌል ሰባኪዎች ከቤተ ክርስቲያን እንዲሰደዱ አድርጓል፡፡ ብዙዎችንም አስደብደቧል፡፡ ብዙ ሌሎች ግፎችንም ሲፈጽም ቆይቷል፡፡ ማኅበሩ በሐሰት የብዙዎችን እውቅ የቤተ ክርስቲያን አባቶችን ሳይቀር እርሱን ስላልመሰሉ ብቻ ስማቸውን ሲያጠፋ ቆይቷል፡፡ የማኅበሩን ዋሾነትና ከሳሽነት አንዳንዶች እንዲህ ገልጠውታል፡፡
ማኅበረ ቅዱሳን የግብር ስሙ ነው በከሳሽነቱ ቁርጥ አባቱን ነው፤ ራእይ 12÷1ዐ
የቤተ ክርስቲያን ተቆርቋሪ መስሎ መታየት ድግድጋቱን አሳምሮ፤ ክሩን አወፍሮ፤ የወንጌሉን እውነት እየተጋፋ ወግ ወጉን አጠንክሮ ክፉ ሥራው እየገለጠው እስከመጣ ጊዜ ድረስ የብርሃን መልአክ መስሎ ለመታየት ጥረት አድርጓል፡፡ በሕንፃ እድሳት ተሳትፎው በስማቸው ገንዘብ  እየሰበሰበ የአብነት ትምህርት ቤቶችን በመርዳት ስም ደፉ ቀና ማለቱ የቤተ ክርስቲያኒቱን ቅርሶች በመጠቀም ባዘጋጃቸው አውደ ርእዮች «እውነተኛ የቤተ ክርስቲያን ልጅ- የቤተ ክርስቲያን ተሟጋች- ፀረ መናፍቃን» ለመባል ችሏል፡፡ አንዳንድ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ሳይቀሩ ማኅበረ ቅዱሳን የቤተ ክርስቲያን ዕጣን ነው የቤተ ክርስቲያን ጠባቂ ነው» ብለዋል፡፡ ይሁን እንጂ ዛሬ አንዳንዶች በተገለጠው ክፉ ሥራው በማፈር እጃቸውን አፋቸው ላይ ጭነዋል፡፡ አንዳንድ የቤተ ክርስቲያን አባቶች አውቀውም ይሁን ሳያውቁ ለማኅበሩ የሰጡትን ሙገሳ የታዘቡ ሰዎች እንዲህ በማለት ትዝብታቸውን ገልጸዋል፡፡
አፍንጫ የለም ወይ የሚያሸቱበት
ጥንባቱን ግማቱን ዕጣን የሚሉት
ይህ አባባላችሁ እጅጉን ይደንቃል
ተኩላ በግ ጠባቂ መቼ ሆኖ ያውቃል?
በተለያዩ መንገዶች ሰዎችን ለዐላማው መጠቀሚያ በማድረግ ማኅበረ ቅዱሳን ከቤተ ክርስቲያን ውጭና በቤተ ክርስቲያን ያሉ ሰዎችን ለክፉ ዐላማው ሲጠቀምባቸው ቆይቷል፡፡ ብዙ አባላቱን ገፉፍቶ አመንኩሷቸዋል፤ ቀስ በቀስም በቅዱስ ሲኖዶስና በሊቃውንት ጉባኤ ውስጥ በማስገባት የውስጥ አርበኝነት ሥራቸውን እንዲሠሩ አድርጓል፤ ያልተሸቃቀጠ ወንጌል የሚሰብኩትን ሰባኪያን «የማርያምን ስም አልጠሩም የመላእክትና የሰማዕታትን ስም አላነሱም ጴንጤዎች ናቸው ተሐድሶ ናቸው መናፍቃን ናቸው» እያለ በውሸት በመወንጀል ከክፉ ሥራው ጋር ባበሩ አለቆች ከቤተ ክርስቲያን እንዲባረሩና ከነቤተሰባቸው በረሃብ አለንጋ እንዲገረፉ አድርጓቸል፡፡
አንዳንድ የቤተ ክርስቲያን ከበርቴዎችና የዋህ ምእምናንን በመጠቀም በንጹሐን ላይ አድማ እንዲካሄድ አድርጓል፡፡ ደጋፊዎቹ ለሆኑ የሲኖዶስና የሊቃውንት ጉባኤ አባላት በእውነትና ስመ ጥር በሆኑ የቤተ ክርስቲያን አባቶች የመጽሐፍ ቅዱስንም ሆነ የቤተ ክርስቲያን ሥርዓትን ባልተከተለ ሁኔታ ወፈ ገዝት ውሳኔ እንዲሰጥ አድርጓል፡፡ የቤተ ክርስቲያን አለቆች ባስተላለፉቸው ወፈ ገዝት ውሳኔዎች በእግዚአብሔር ፊት ፍርደ ገምድልና በደለኞች፣ በታሪክዋ ፊት ተወቃሾች አድርጓቸዋል፡፡ ትክክለኛ ዳኝነት ባለመስጠታቸውም ትዝብት ላይ ጥሏቸዋል፡፡
የማኅበሩ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ምን ይሆናል?
ከሁሉም በላይ ማኅበረ ቅዱሳን የበደለው ልዑል እግዚአብሔርን ነው፡፡ ስለዚህም ሁሉን ገልጦ የሚያየውና በፍርዱም የማያዳላው ልዑል እግዚአብሔር በማኅበሩ ላይ መፍረዱ አይቀርም፡፡ ኢያኔስና ኢያንበሬስ እግዚአብሔር በሙሴ ይሠራ የነበረውን ታላቅ ሥራ ተቃውመው እንደጠፉ የማኅበረ ቅዱሳንም ዕጣ ፈንታ በንስሐ እስካልተመለሰ ድረስ መጥፋት ነው፡፡ ውሎ ይደር እንጂ ይህ መቼም የማይቀር ነው፡፡ ታላቁ እግዚአብሔር የማኅበሩን አለቆች ጉልበት በፍርሃት ያብረከርካል፤ ይህ አሁንም በአንዳንዶች እየሆነ ነው፡፡ ልዑል እግዚአብሔር ያልተገለጠውን የማኅበሩን ኃጢአት ወደ ብርሃን በማውጣት የማኅበሩ አለቆች በሃፍረት እንዲከናነቡ ያደርጋል፡፡ እግዚአብሔር በሚያደርገው ታላቅ ሥራ የማኅበሩ አለቆች፤ የማኅበሩ አባላትና ደጋፊዎች ሌሎችም ታላቁንና ጻድቁን እግዚአብሔርን ያውቁታል፤ ሕዝ. 7÷1-4፡፡ ብዙዎች ስለተሳሳተ መንገዳቸው ንስሐ እየገቡ ትክክለኛውን የጽድቅ መንገድ ይከተላሉ፡፡ እምቢተኞችም ተገቢውን ቅጣታቸውን ያገኛሉ፡፡
የቤተ ክርስቲያን አለቆች ማኅበሩን በተመለከተ ምን ማድረግ አለባቸው?
የቤተ ክርስቲያን አለቆች በመጽሐፍ ቅዱስና በአባቶች ትምህርት የማኅበሩን ኑፋቄ መዝነው ተግሣፅ መስጠትና ማኅበሩ እንዲመለስ ማድረግ እምቢ ካለም አውግዞ መለየት ጊዜ የጣለባቸው ግዴታ ነው፡፡
በቤተ ክርስቲያን ያሉ ወንጌል ሰባኪዎችስ ምን ማድረግ ይገባቸዋል?
የወንጌል ሰባኪዎች በቤተ ክርስቲያን የተንሰራፋውን የኑፋቄ ሐሳብ እስከሞት ድረስ በጽናትና በቁርጠኝነት ለመዋጋት መወሰን ይገባቸዋል፡፡ ያልተሸቃቀጠ ንጹሕ ወንጌል በእምነትና በጽናት መስበክና በጸሎትም ትጋት ኑፋቄውን ዒላማ አድርገው መዋጋት ይኖርባቸዋል፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን የቱንም ያህል ድጋፍ ይኑረው የቱንም ያህል ንብረትና ገንዘብ ያከማች እግዚአብሔርን ታምኖ በጽድቅ በቆመ ሰው ፊት የትንኝ ያህል ክብደት የለውም፡፡
እናንተ ሰባኪዎች ጽናቱን ይሰጣችሁ
ወንጌል እንድትሰብኩ ጸጋው ያበርታችሁ
የወንጌሉን ቋያ እሳቱን አንድዱት
ተረታረቱን ዶግ አመድ አድርጉት፡፡

ክብር ምስጋና ውዳሴ ለልዑል እግዚአብሔር ይሁን!

8 comments:

 1. ማኅበረ ቅዱሳን እንዴት እዚህ ደረጃ ላይ ደረሰ? መልሱ በእግዚአብሔር አጋዥነት፣በድንግል አማላጅነት፣እግዚአብሔር ባከበራቸው ቅዱሳን መላዕክት፣ ነቢያት፣ ሐዋርያት፣ ሰማዕታት፣ ጻድቃን ምልጃ

  ReplyDelete
  Replies
  1. ማኅበረ ቅዱሳን እንዴት እዚህ ደረጃ ላይ ደረሰ? መልሱ በእግዚአብሔር አጋዥነት፣በድንግል አማላጅነት፣እግዚአብሔር ባከበራቸው ቅዱሳን መላዕክት፣ ነቢያት፣ ሐዋርያት፣ ሰማዕታት፣ ጻድቃን ምልጃ

   Delete
 2. Lebinetun yetemarkew ke ayathi norual leka, wendime hoi. Tewahedo lay yetehadiso Lebinetun...

  ReplyDelete
 3. ለኦርቶዶክስ ተዋህዶ አማንያን በሙሉ ከዚህ ውስጥም የመራራዋና የአሳሳቿ በለስ ተሳታፊና ደንዛዥ የማቅ አባላትና ተሳሳች ወጣት ደጋፊዎች ምዕመናን ኧረ ጥግ ያዙ፟------- የተበረዘው የበጎ አዕእምርዋችሁ አምልኮታችሁና የአምላክን መንገድ ፍላጎታችሁ ጊዜ አልተሟጠጠምና ዘቦ ዕዝን ሰሚዓ አሁን መሆኗን አውቃችሁ ትምህርቱን ተረድታችሁ ፤ ተገንዝባችሁ፤ እውነተኛዋን የቤተ ክርስቲያናችሁን ሥረዓት ጠብቃችሁ ተከተሉ። ካለበለዚያ ከቀደመው ጊዜ ሂደት የተማርነው የሰማነው በጎ ያልሆነው ሁሉ የፈጣሪያችንን መንገድ ሳናገኝ እንዳይደርስብን ወደልቦናችን እንመለስ። አሜን !!!

  ReplyDelete
 4. አባ ሰላማዎች "የልጇም ንጽሐ ባሕርይነት ከምንጩ ከእናቱ ከድንግል ማርያም ፍጹም ንጽሕና የተነሣ ነው" የሚለውን የ ኑፋቄ ትምህርት የተላለፈበትን መጽሔት ለምን ስካን አድርጋችሁ አታያይዙልንምና በማስረጃ ትምህርቱን ለመቃወም እንችላለን።

  ReplyDelete
 5. ምድረ ቀጣፊ ሁላ ማኀበረ ቅዱሳን ያድጋል ይመነደጋል ተዋ ህደ ታድጋለች ታበራለች ይብላኝ ለሉተር ተላለኪ አድርባዩች

  ReplyDelete
 6. አያቴ አልክ? ምነው አራቅከው? የስራ ልምድህን ለመተረክ አያቴ ምናምን ማለት አያስፈልግም፡፡

  ReplyDelete