Monday, September 26, 2016

የሚያድነው መስቀል የቱ ነው?


Read in PDF

የእግዚአብሔር የእግሮቹ መቆሚያ ስፍራ
“ወደ ማደሪያዎቹ እንገባለን እግሮቹ በሚቆሙበት ስፍራ እንሰግዳለን” (መዝ. 131/132፥7)
ክርስቶስ ስለ ተሰቀለበት መስቀል በቤተ ክርስቲያን የሚሰጠውን ትምህርት የሚከታተል ሁሉ ይህ ቃል ለመስቀል ስለ መስገድ እንደሚጠቀስ ያውቃል፡፡ መስቀል ሦስት ፍቺ አለው፡፡
   የመጀመሪያው፥ ክርስቶስ ለዓለም ቤዛ ሆኖ የተሰቀለበት የተመሳቀለ ዕንጨት ሲኾን (ዮሐ. 19፥17፤ 1ጴጥ. 2፥24)
   ሁለተኛው ደግሞ፥ በዚህ የተመሳቀለ ዕንጨት ላይ ክርስቶስ የተቀበለው መከራና ሞት፥ በጥቅሉ የቤዛነቱ ሥራ ሁሉ መስቀል ይባላል (ኤፌ. 2፥16፤ ቆላ. 2፥14)፡፡
   ምእመናን ስለ ክርስቶስና ስለ ወንጌል የሚቀበሉት መከራም መስቀል ተብሎ ይጠራል (ማቴ. 10፥38፤ 16፥24፤ ማር. 8፥34፤ ሉቃ. 9፥26፤ 10፥21፤ 14፥27)፡፡
ዓለም ሁሉ በእምነት የሚድንበትና የሚመካበት መስቀል በሁለተኛው ፍቺ ውስጥ ነው የሚገኝው፡፡ በተለይ በአዲስ ኪዳን ክፍል ውስጥ ስለ መስቀል የተነገሩት ሁሉ የክርስቶስን ቤዛነት የሚያመለክቱ ናቸው (1ቆሮ. 1፥18፤ ገላ. 6፥14፤ ፊል. 3፥18)፡፡ ከዚህ በተቃራኒ በቆሙ በብዙዎች ዘንድ ግን እነዚህ የተጠቀሱትና የቀሩት ሁሉ “መስቀል” የሚል ቃል ይዘው ስለ ተገኙ ብቻ፥ ክርስቶስ ለተሰቀለበት መስቀል ተሰጥተው ነው የሚተረጎሙት፡፡ ስለዚህ የብዙ ምእመናን ዐይኖች የመስቀልን ቅርጽ እንጂ የተሰቀለውን ክርስቶስን ለማየት አልታደሉም (ገላ. 3፥1)፡፡ እዚህ ላይ አንድ ወንድም ነገሮችን ሁሉ አስተውሎ በአንድ ወቅት፣ “ቤተ ክርስቲያናችን እየሰበከች ያለችው በመስቀል ላይ የተሰቀለውን ክርስቶስን ሳይሆን ክርስቶስ የተሰቀለበትን መስቀል ነው” አለ፡፡

እርግጥ ዛሬ ጐልቶ የሚታየው የሚሰማውና የሚነገረው ይህ ቢሆንም በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ተቀብሮ ያለው እውነት ግን ስለ መስቀል ዕጹብ ድንቅ ምስጢርን ይናገራል፡፡ “ስለ እኛ ተሰቀለ፤ በመስቀሉም ሃይላችን ቤዛችን ድኅነታችን ተደረገልን፡፡ ይኸውም ከእግዚአብሔር የማትርቅ መቼም መች የማትለይ ሁል ጊዜ የማትመጠን የቸርነቱን ብዛት በመናገር የማይፈጸም ደስታ ያለበት ረቂቅ ምስጢር ነው፡፡ በእነዚህ በላይና በታች ከናፍር እሷን ጠንቅቆ መናገር አይቻልም፡፡ ምእመናን መርምረው የማይደርሱበት ረቂቅ ምስጢር ነው፡፡ ግን ምንም የማይመረመር ቢሆንም እነርሱ ያውቁታል፡፡ እናመሰግነው ዘንድ የምንመካበት መስቀል ይህ ነው” (ሃይማኖተ አበው 1986፣ ገጽ 5)፡፡
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “እኔን መከተል የሚወድ ቢኖር ራሱን ይካድ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ” ሲል ቁሳዊ የኾነ መስቀልን ስለ መሸከም ሳይሆን የእርሱን መከራና ሞት እያሰብን ስለ መኖርና በመከራውም ስለ መካፈል እየተናገረ ነው (ማቴ. 16፥24)፡፡ ይህን ሲያስረዳ ሐዋርያው “የኢየሱስ ሕይወት ደግሞ በሥጋችን ይገለጥ ዘንድ ሁል ጊዜ የኢየሱስን መሞት በሥጋችን ተሸክመን እንዞራለን” ብሏል (2ቆሮ. 4፥10)፡፡
ክርስቶስ የሞተው በመስቀል ላይ በመሆኑ መስቀል የተሰቀለውን ክርስቶስን ስለሚያሳስባቸው ክርስቲያኖች ሁሉ ክቡር ዐርማቸው አድርገው ይጠቀሙበታል፡፡ የቤተ ክርስቲያናችንም እምነት ይኸው ነው፡፡ ከዚህ በቀር በፈጠራ ትምህርትና ታሪክ ጌታ ለተሰቀለበት መስቀል በሚል ሽፋን፥ ቅርጻ ቅርጽ ሠሪዎች በተለያየ መጠንና ቅርጽ እየሠሩ ለተጠበቡበት ጥበበ እድ የሚሰጠው የክርስቶስ የአዳኝነት የቤዛነት የመመኪያነት ስፍራ አግባብነት የለውም (ኢሳ. 42፥8)፡፡
የእስራኤል ልጆች ከግብጽ ምድር ወጥተው ወደ ተስፋዪቱ ምድር እየተጓዙ ሳለ በእግዚአብሔርና በሙሴ ላይ በማጕረምረማቸው እግዚአብሔር በቅን ፍርዱ ተናዳፊ እባቦችን አስነሥቶ እንዲነደፉ አደረገ፣ በመቅሠፍቱ ብዙዎች ሞቱ፡፡ በሕይወት ተርፈው በመርዙ የተነደፉቱ ሁሉ በደላቸውን አምነው በመጸጸት በመካከለኛቸው በሙሴ በኩል እግዚአብሔርን በጠየቁ ጊዜ ሙሴ የናስ እባብ ሠርቶ በዐላማ ላይ እንዲሰቀልና የተነደፉት ወደ ተሰቀለው እባብ በማየት የሚድኑ መሆኑን ተናገረ፡፡ ሙሴም እንዲሁ በማድረጉ በመርዘኛው እባብ የተነደፉቱ ሁሉ የናሱን እባብ አይተው ዳኑ (ዘኁ. 21፥4-9)፡፡ ይህም ወደ ፊት የሚሆነውን የክርስቶስን መሰቀልና ዲያብሎስ የገዛቸው ሁሉ የተሰቀለውን በእምነት በማየት የሚድኑ መሆኑን የሚያሳይ ምሳሌ ነበር (ዮሐ. 3፥14-15)፡፡
በመርዘኛው እባብ የተነደፉት ሁሉ እርሱን በማየት ብቻ ፈውስን ካገኙ በኋላ የናሱ እባብ አገልግሎት አብቅቷል፡፡ ሕዝቡ ግን የአገልግሎት ዕድሜውን በገዛ ፈቃዳቸው በማራዘም ትውልድ ዐልፎ ትውልድ ሲተካ ዘመናትም እንዲሁ በጨመሩ ቁጥር የናሱን እባብ ወደ ማምለክ ተሸጋገሩ፡፡ ይህ ድርጊታቸው ትክክል ባይሆንም፥ ለዚያው ለአንዱ ጊዜ እንኳን ያዳናቸው የናሱ እባብ እንጂ እባቡ የተሰቀለበት ዐላማ (ዕንጨት) አለመሆኑን አስተውለው ነበር፡፡ ዛሬ ዐይኖቻቸውን በተሰቀለው ክርስቶስ ላይ ሳይሆን በመስቀል ቅርጽ ላይ ላሳረፉ ወገኖች ይህ ጥሩ ትምህርት ይሆናል፡፡
ሕዝበ እስራኤል ከጊዜያዊ መቅሠፍት የዳኑበትን የናስ እባብ እንጂ የናሱ እባብ የተሰቀለበትን ዐላማ አልተመለከቱም፡፡ የታዘዙትም የናሱን እባብ ብቻ እንዲመለከቱ ነው (ቁጥር 8-9)፡፡ ይህን በእርግጥ ተረድተዋል፡፡ ከመጀመሪያው ጣዖት ያልነበረውና በቆይታ ግን የሕዝቡ ልብ እያመለከው ወደ ጣዖትነት በመሸጋገሩና እንደ ጣዖት በመቆጠሩ፥ ንጉሡ ሕዝቅያስ ሰባብሮ እስካስወገደበት ዘመን ድረስ እንኳን ይዘው የተገኙት የናሱን እባብ ብቻ እንጂ ዐላማውን ጭምር አልነበረም (2ነገ. 18፥14)፡፡
ስማቸውና ወደ ቤተ ክርሰቲያናችን የገቡበት ትክክለኛ ዐላማ የጣዖት ያልሆነ የኛ አቀባበል፣ አያያዝ፣ አመለካከትና የዘመን ርዝመት መልካቸውን ቀይሮ ጣዖት ያደረጋቸው ስንት ነገሮች ይኖሩብን ይሆን? በመስቀል የተሰቀለው መድኀኔ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ጊዜ የማይሽረው ዘላለማዊ አዳኝ አምላክ በመሆኑ አንዳች ነገር ሳያግደንና ሳይገድብን ለዘላለም ወደ እርሱ እንመለከታለን፡፡ ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋርም በአንድነት እናመልከዋለን፡፡ ክብርና ምስጋና አምልኮትና ስግደት ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ለእርሱ ብቻ ይኹን!!
ዛሬ ያ የሕዝበ እስራኤል ታሪክ ክርስቶስ በተሰቀለበት መስቀል አቅጣጫ ራሱን ደግሟል፡፡ ይህን ስሕተት የሚያራምዱት አፈ ጮሌዎች ያቆሙትን አምልኮተ መስቀል ትክክለኛ ለማስመሰል ተገን ያደረጉት “እግሮቹ በሚቆሙበት ስፍራ እንሰግዳለን” የሚለውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ቃል ሲሆን እንዲስማማቸው አድርገው የሰጡት ትርጉም ደግሞ ‘የክርስቶስ እግሮች በምስማር ተቸንክረው ለሦስት ሰዓታት ያኽል በመስቀል ላይ ስለ ቆሙ ለመስቀል ስግደት ይገባል’ የሚል ነው፡፡
በትክክለኛው መንገድ ከተረዳነው ቃሉ በምድር ላይ ለእግዚአብሔር መስገድን ያሳያል፡፡ በስፍራ የማይወሰነው አምላካችን እግዚአብሔር ለእኛ በሚገባን መጠን የራሱን የታላቅነት ቦታ በሰማይና በምድር ወስኖ “ሰማይ ዙፋኔ ነው፤ ምድርም የእግሬ መረገጫ ናት” ብሎ እንደ ተናገረው የእግሩ መረገጫ በሆነችው በምድር ላይ ሰግደን እናከብረዋለን እንገዛለታለን (ኢሳ. 66፥1)፡፡
በብሉይ ዘመን የእግዚአብሔር ከተማና ማደሪያው ኢየሩሳሌም (ጽዮን) ነበረች (መዝ. 131/132፥13-14፤ 121/122፥1)፡፡ “እግሮቹ በሚቆሙበት ስፍራ እንሰግዳለን” ያለውም በተመረጠችው ቅድስት ስፍራ በኢየሩሳሌም እንሰግዳለን ሲል ነው፡፡ በኢየሩሳሌም የነበረው መቅደስ የእግሩ መረገጫ ነበር (ሕዝ. 43፥7)፡፡ ክርስቶስ ሰው ሆኖ የእግዚአብሔርን በቦታ ሳይወሰን በእውነትና በመንፈስ መመለኩን ሳያውጅልን በፊት የእግዚአብሔር ሕዝብ በዚህች ስፍራ ይሰግድ ነበር (መዝ. 5/6፥7፤ 23/24፥2፤ ሐ.ሥ. 8፥27)፡፡
እንዲያው ቢቸግራቸው ወይም ሌላ አማራጭ ስላጡ ቃሉን ምንም ቢሆን ስለ መስቀል ሊናገርልን ይችላል ብለው ጠቀሱት እንጂ የእነርሱን ሐሳብ የሚደግፍበት አንድም ነጥብ እንኳ የለውም፡፡ በእነርሱ አተረጓጐም እንሂድ ቢባል እንኳን “እግሮቹ በሚቆሙበት ስፍራ እንሰግዳለን” ይላል እንጂ “እግሮቹ ለሚቆሙበት ስፍራ እንሰግዳለን” አይልም፡፡ በሌላ አገላለጥ ለስፍራው ሳይሆን ስፍራው ላይ ለሚቆመው እንሰግዳለን ነው የሚለው፡፡ እንደ እነርሱ ሐሳብ እግሮቹ የሚቆሙበት (የቆሙበት) ስፍራ መስቀል ነው ተብሏልና እንግዲህ መስቀሉ ላይ ቆመን መስገድ ሊኖርብን ነው፡፡ ይህ ታዲያ ተፈጻሚ ሊሆን ይችላልን? ደግሞስ ዕፀ መስቀልን ረገጣችሁ የሚል ክስ ቢመሠረትብንስ?
ይህ ብቻም አይደለም፤ ሰዎች ስለ መስቀል ሌላም ብዙ እንግዳ ትምህርት አላቸው፡፡ ሊቀ ጠበብት አያሌው ታምሩ በጽሑፍ ያሰፈሩትን ለአብነት ያህል እንመልከት “… በአምላክ ደም የከበረ የቅድስና ተቀባይ አስተላላፊ ቦይ ቅዱስ መስቀል ነው” (ምልጃ ዕርቅና ሰላም 1992፣ ገጽ 61)፡፡ ሁሉም ይህንና የመሳሰለውን የስሕተት ትምህርት በመተው ወደ አእምሮው ተመልሶ ነገሮችን ሁሉ ለማጤን ቢሞከር፣ ጌታ ሲሰቀል በፈሰሰው ክቡር ደም የተነካው መስቀሉ ብቻ ሳይሆን የተቸነከረባቸው ምስማሮች፣ የተወጋበት ጦር፣ የተገረፈባቸው ጅራፎች፣ በራሱ ላይ የደፋው የእሾህ አክሊል፣ ደሙ የነጠበበት ምድር፣ ወዘተ. ቁሳቁሶችና ግዑዛን ነገሮች ሁሉ ናቸው፡፡ ታዲያ ለጸጋው አስተላላፊነት መስቀሉ ብቻ እንዴት ሊታጭ ቻለ?
የመጽሐፍ ቅዱስ ምስክርነት ከዚህ እንግዳ ትምህርት ይለያል፡፡ በክርስቶስ ኢየሱስ በኩል ከእግዚአብሔር እንዲያው የተሰጠን ጸጋ ወደ እኛ የሚፈስስበት ቦይ የዕንጨት መስቀል ሳይሆን እምነት ነው (ኤፌ. 2፥10፤ ዕብ. 4፥16)፡፡ ስለ መስቀል የተሳሳተ አስተምህሮ በቤተ ክርስቲያናችን ይበልጥ የተስፋፋው በዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ዘመነ መንግሥት (15ኛው ምእት ዓመት) መሆኑ ይታወቃል፡፡ “ወከመዝ ግበሩ” (እንዲህ አድርጋችሁ ሥሩ) ብሏል የሚለው ታሪክ ዘለል የጥራዝ ነጠቆች አጠቃቀስ፣ እንደ ታቦቱ መስቀልንም ከተለያዩ ነገሮች (ከዕንጨት ከብረትና ከተለያዩ ማዕድናት) በተለያየ መጠን፣ ቅርጽና ዐይነት ለመቅረጽ ያገለገላቸው ይመስላል (ዘፀ. 25፥9)፡፡
መስቀል ይበልጥ እየተሠራ ቀሳውስት እንዲይዙት፣ ምእመናን እንዲሳለሙት፣ በአንጻረ ቤተ ክርስቲያን በርቀት ተተክሎ እንዲሰግዱለት የድንጋይ ስጦታ[i] እንዲያበረክቱለትና የመሳሰለው የተለየ ክብር ሁሉ እንዲደረግለት የታወጀው በዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ዘመን ነው፡፡ “ወካዕበ ናስተበቁዖ ለዕፀ ቅዱስ መስቀል ጽኑዐ ሥልጣን ወኀይል - ጽኑ የሆነ ኀይልና ሥልጣን ያለውን ቅዱስ የዕንጨት መስቀልን ዳግመኛ እንለምነዋለን” ተብሎ በቤተ ክርስቲያናችን ወደ ዕፀ መስቀል መጸለይ የተጀመረው “ለእሉ ክልኤቱ ፍጡራን ስብሐተ ፈጣሪ ይደልዎሙ እስመ ተዐረዩ በክብሮሙ፡፡ - ለእነዚህ ለሁለቱ ፍጡራን (ለማርያምና ለዕፀ መስቀል) የፈጣሪ ክብር ይገባቸዋል፡፡ በክብራቸው ከፈጣሪ ጋር ተካክለዋልና” ተብሎ ቅድስት ማርያምና የዕንጨት መስቀል እንደ ፈጣሪ እንዲመለኩ የታወጀውም በዚሁ ‘ለማይረባ አእምሮ ተላልፎ በተሰጠው’ (ሮሜ 1፥28) በዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ዘመን ነው፡፡
ምናልባት እነ አልሰሜ ‘ቤተ ክርስቲያን መስቀልን ታከብራለች እንጂ ከፈጣሪ ጋር አስተካክላ አታመልከውም’ ብለው ይከራከሩ ይሆናል፡፡ ከላይ የተጠቀሰው ድርሰት ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ይኸው እስካሁን ድረስ መሻሻል ሳይደረግበት ቤተ ክርስቲያናችን እየተጠቀመችበትና ወደ መስቀል እየጸለየችበት ይገኛል፡፡ ታዲያ ይህ መስቀልንም እያመለከች ነው አያሰኛትምን? (መስተብቁዕ ዘመስቀል)፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ “ለእሉ ክልኤቱ ፍጡራን ስብሐተ ፈጣሪ ይደልዎሙ እስመ ተዐረዩ በክብሮሙ፡፡ - ለእነዚህ ለሁለቱ ፍጡራን (ለማርያምና ለዕፀ መስቀል) የፈጣሪ ክብር ይገባቸዋል፡፡ በክብራቸው ከፈጣሪ ጋር ተካክለዋልና” የሚለውን ንባብ በ2002 ዓ.ም. በግእዝ፥ በዐማርኛ እና በእንግሊዝኛ ቤተ ክርስቲያኗ ባሳተመችው መጽሐፈ ቅዳሴ ላይ እንዲህ ተብሎ ታርሟል፤ “ለእሉ ክልኤቱ ፍጡራን ስብሐት ይደልዎሙ እስመ ተዐረዩ በክብሮሙ፡፡ - ለእነዚህ ኹለት ፍጡራን (ለማርያምና ለዕፀ መስቀል) የጸጋ ምስጋና ይገባቸዋል፡፡ በክብር ተስተካክለዋልና” (መጽሐፈ ቅዳሴ 2002፣ ገጽ 454)፡፡
ይህ አገላለጥ ትክክል አይደለም፡፡ መስቀል ሮማውያን ወንጀለኛን የሚቀጡበት መሣሪያ ሲሆን፥ ማርያም ግን የጌታችን እናት ናት፡፡ ስለዚህ ሁለቱን ለማስተካከል ቀርቶ ለማቀራረብ የሚያስችል በቂ ምክንያት የለም፡፡
ከላይ የተመለከትነው ዕርማት በሊቃውንት ጉባኤ ወይም በሚመለከተው አካል እንደ ተደረገ ግልጥ ነው፡፡ ይህም በአንድ በኩል ድርሰቱ (መስተብቍዕ ዘመስቀል) ስሕተት የነበረበት መሆኑን ቤተ ክርስቲያኗ ማመኗን ያመለክታል፡፡ ነገር ግን፥
·        ‘የቀደመው ንባብ ስሕተት ስለ ነበረበት በዚህ መልክ ተስተካክሏል፤ ከዚህ በኋላ ቤተ ክርስቲያን መጠቀም ያለባት ይህን የታረመውን ንባብ ነው’ የሚል መግለጫና መመሪያ በመጽሐፉ ላይም ኾነ በሌላ መንገድ በይፋ አልተሰጠም፡፡
·        መመሪያም ወደየቅዳሴ ቤቶች[ii] ወይም ወደየአድባራቱና ገዳማቱ የተላለፈ ባለመሆኑም በወረቀት እንጂ በተግባር ታርሟል ማለት አይቻልም፡፡ ስለዚህ የተሳሳተው ድርሰት ከሥራ ውጭ አልሆነም፤ አሁንም በሥራ ላይ ነው፡፡
·        ምንም እንኳን መስተብቁዕ ዘመስቀል ወደ እንግሊዝኛ ባይተረጐምም መጽሐፈ ቅዳሴው በእንግሊዝኛ ቋንቋም የተዘጋጀ ስለ ሆነ አገልግሎቱ በአገር ውስጥ ላለችው ቤተ ክርስቲያን ሳይሆን በውጭ አገር ላለችው ቤተ ክርስቲያንና ለውጪ ዜጎች ይሆናልና፣ የታረመው በአገር ውስጥ በሥራ ላይ ይውላል ብሎ ማሰብ ያስቸግራል፡፡ ከዚህ አንጻር ዕርማቱ በድርሰቱ ላይ ጠያቂ ቢነሣ “ይኸው ታርሟል እኮ!” ከማለት ያለፈ ፋይዳ አይኖረውም፡፡
·        ተሰጠ የተባለው ዕርማት ከመጽሐፍ ቅዱስ እውነት አንጻር የተሰጠ ሳይሆን ከጥንት ያልነበረውና ከጊዜ በኋላ እያቆጠቆጠ በመጣው ምስጋናንና ስግደትን “የአምልኮት” እና “የጸጋ” በሚል በከፋፈለው እንግዳ ትምህርት መሠረት የተቃኘ ነው፡፡ ግእዙ “ስብሐት” ያለውን ዐማርኛው “የጸጋ ምስጋና” ብሎታልና፡፡ አምልኮት ስግደትና ምስጋና ተጠቅልሎ መቅረብ ያለበት ብቻውን አምላክ ለሆነው ለእግዚአብሔር መሆን ሲገባው፣ የአምልኮት እና የጸጋ ተብሎ መከፋፈሉ በአንድ በኩል ከስሕተት ላለመውጣትና የኖረውን ልማድ ለማጽናት የሚደረግ ጥረት ሲሆን ለአምልኮ ባዕድ በር የሚከፍት ኢመጽሐፍ ቅዱሳዊ አመለካከትም ነው፡፡[iii] ስለዚህ እርማቱ “አልሸሹም ዘወር አሉ” ነው፡፡
·        ታረመ የተባለው አንድ ሐረግ (“ስብሐተ ፈጣሪ” የሚለው) ብቻ መኾኑ ድርሰቱን በሙሉ ታርሟል አያሰኝም፡፡ ግዑዝ ወደ ኾነው መስቀል የመጸለዩ የክርስቶስን መከራ መስቀል ሳይሆን ግዑዙን መስቀል ቤዛችን ኀይላችን ብሎ የመጥራቱ፣ “ጻድቃንንና ኃጥኣንን አድኗል፤ ከሰይጣን ባርነትም ነጻ አውጥቷል” ወዘተ. መባሉ አሁንም ድርሰቱ አልታረመም፤ ባለበት ነው ያለው ያሰኛል፡፡
·        “በበትረ ዝንቱ መስቀል ሐዋርያቲሁ ለዘሞተ እንዘ ይገብሩ መንክራተ ሰደዱ አጋንንተ ወሰበሩ ጣዖታተ፡፡ በእንተ ዝንቱ አዘዙ መምህራነ ቅዱስ ወንጌል አምሳለ ፈጣሪ ልዑል ንስግድ ለመስቀል ወለማርያም ድንግል፡፡ - በዚህ በትረ መስቀል፥ በመስቀል ላይ የሞተው የክርስቶስ ሐዋርያት ድንቆችን ሲያደርጉ፣ አጋንንትን አሳደዱ፤ ጣዖታትንም ሰበሩ፡፡ ስለዚህ የቅዱስ ወንጌል መምህራን በልዑል ፈጣሪ አምሳል ለመስቀልና ለድንግል ማርያም እንሰግድ ዘንድ አዘዙን፡፡” ተብሏል፡፡ በዚህ ንባብ ውስጥ ሐዋርያት በመስቀል ድንቆችን እንዳደረጉ አጋንንትን እንዳሳደዱና ጣዖታትን እንደ ሰበሩ ተነግሯል፡፡ ከዚህ የተነሣ የቅዱስ ወንጌል መምህራን በልዑል ፈጣሪ አምሳል ወይም ለልዑል እግዚአብሔር በምንሰግደው ዐይነት ለድንግል ማርያምና ለዕፀ መስቀል እንድንሰግድ አዝዘዉናል ተብሏል፡፡ እነዚህ ሁሉ ግን በሐዋርያት ስም የተጻፉ እንጂ ሐዋርያት ያደረጓቸውና ለእኛም ያዘዙት አይደለም፤ ሊሆንም አይችልም፡፡
   1ኛ. ሐዋርያት ድንቅና ተኣምራትን ያደረጉት በኢየሱስ ስም ነው (ሐ.ሥ. 4፥29-30፤ 5፥12፤ 14፥3፤ 15፥12)፡፡
   2ኛ. ሐዋርያት ጌታ እንዳዘዛቸው (ማር. 16፥17) አጋንንትን ያወጡት በኢየሱስ ስም ነው (ሉቃ. 10፥17፤ ሐ.ሥ. 8፥5-7፤ 16፥18)፡፡
   3ኛ. ሐዋርያት ጣዖታትን ስለ መስበራቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጻፈ ነገር ባይኖርም ከአምልኮተ ጣዖት ጋር በተገናኘ ሐሰትን ያፈረሱት እውነትን በመስበክ ነው (ሐ.ሥ. 14፥11-18፤ 19፥17-20)፡፡
በዚህ ሕይወት ውስጥ ያለፉ እውነተኞቹ የወንጌል መምህራን በፈጣሪ አምሳል (የአምልኮት ስግደት) ለማርያምና ለመስቀል ስገዱ ብለው አዘዋል ማለት ግን ፈጽሞ የማይታሰብ ነው፡፡ ይህን አዘዋል የተባሉት ሰዎች ምናልባት፥ “የክርስቶስን ሐዋርያት እንዲመስሉ ራሳቸውን እየለወጡ፥ ውሸተኞች ሐዋርያትና ተንኮለኞች ሠራተኞች” ከተባሉት ወገን የሚመደቡ ናቸው (2ቆሮ. 11፥13)፡፡
የተቀበረ መክሊት ከተሰኘው መጽሐፍ የተወሰደ ገጽ 111


[i] በገጠር በአንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት አንጻር በርቀት መስቀል ይተከላል፤ በዚያ የሚያልፍ ኦርቶዶክሳዊ ምእመን ድንጋይ ወይም ዕንጨት እየወረወረ ይሄዳል። ከዚህ የተነሣ መስቀሉ ሥር የተከመሩ ድንጋዮችና ዕንጨቶችን ማየት የተለመደ ነው። እንዲህ የሚደረገው ለምን ይኾን?
[ii] “ቅዳሴ ቤት” የሚባለው የቅዳሴ ትምህርት የሚሰጥበት ትምህርት ቤት ነው።
[iii] ብፁዕ አቡነ መርሐ ክርስቶስ፥ “ትምህርተ ቤተ ክርስቲያን - ከሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን በከፊል” በተሰኘች አነስተኛ መጽሐፋቸው ላይ እንዲህ ብለዋል፤
·   “መቸም ስግደት የሚሰገድ ለእግዚአብሔር ነው።
·   “ማቴ. 4፡ ቍ 10ን፣
·   “ራእ. 19፡ ቍ 10ን፣
·   “ራእ. 22፡ ቍ 9ን፣
·   “ኢሳ. 45፡ ቍ 23ን፣
·   “መዝ. 80፡ ቍ 9ን አንብቡና ተረዱ። የስግደት ምስጢሩ ምንድነው? ቢባል፦ ስግደት የአምልኮ፣ የተገዥነት መግለጫ ነው (መዝ. 5፥7)።”
ይህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነት ነው። አክለው ግን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃ ባያቀርቡም በቤተ ክርስቲያናችን ለሌሎች ቅዱሳን መላእክትና ሰዎች እንዲሁም ለንዋያተ ቅድሳት የሚቀርበው እማኄ ወይም የአክብሮት ስግደት ነው ይላሉ (ገጽ 8-16)። እማኄ ማለት ግን እጅ መንሣት፣ እጅ አነሣሥ፣ ሰላምታ አሰጣጥ፣ አድንኖ፣ ሰላምታ ከበሬታ” ማለት ነው እንጂ ስግደት ማለት አይደለም። (ኪዳነ ወልድ 1948፣ ገጽ 226)።
 

6 comments:

 1. "ስብሐተ ፈጣሪ ይደልዎሙ" የሚለው ቤተ ክርስቲያን የምትተረጉመው አንተ ባልከው ሳይሆን(ፊደል ይገላል ትርጓሜ ያድናል፣2 ቆሮ 3፥6) የፈጣሪ ምስጋና ይሰጣቸዋል፣ልክ እንደ ፈጣሪ ይመሠገናሉ ማለት ሳይሆን፣ፈጣሪ እንደሚመሠገን እነሱንም እናመሠግናቸዋለን ማለት ነው።ልክ አንተ ጥሩ ከሠራህ አመሠግንሀለሁ እንደምልህ ማለት ነው።በዚህም አንተ ራስህ ሳመሠግንህ ደስ ይልሀል።መዝሙር 32፥1 ለቅኖች ምሥጋና ይገባል እንዲል።እመቤታችን እና መስቀል በክርስቶስ ፈቃድ ታላቅ ቅን ነገር አድርገውልናልና እናመሠግናቸዋለን።"እስመ ተዐረዩ በክብሮሙ"በክብራቸው ይስተካከላሉ የተባሉት እመቤታችን ድንግል ማርያምና በደሙ የከበረው መስቀሉ ሁለቱን ነው እንጂ ከፈጣሪ ጋር አይደለም፣አይልም፣አታምታታው፣አምታታው በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አንተ ነህ።አሁን ለመስቀል የሚሰግዱና የሚያመሰግኑ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተከታዮች ብቻ ቢሆኑ ኖሮ አጼ ዘርዓ ያዕቆም ነው ያመጡት የሚለው የአንተ ውሸት እውነት በሆነ ነበር፤ግን ሂድ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ፣ሂድ ምሥራቅ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያን ሩስያ፣ግሪክ፣ወዘተ...ለእመቤታችንና ለቅዱስ መስቀል ይሰግዳሉ፣ምሥጋና ያቀርባሉ።አንተ እያልከን ያለው አጼ ዘርዓ ያዕቆብ ለእመቤታችንና ለቅዱስ መስቀል እንዲሰግዱና ምሥጋና እንዲያቀርቡ ከፕሮቴስታንቶች በስተቀር ካቶሊክና የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናትን በ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አዝዘዋቸው ነው ?ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባ ይሉሀል ይህንን ነው።ጉደኛ ጸሐፊ ነህ(የጉድ ሙዳይ ማለት አንተ ነህ)።

  ReplyDelete
 2. ሉተራዊ አሉባልታ .... አይሰማም እስኪ ድገመው

  ReplyDelete
  Replies
  1. ይህ ሰዉ ስለ መስቀል ታሪክ ብዙም የሚያዉቅ አይመስልም፡፡ ስለ ጥንት ክርስቲያኖች ማነበብ ኣለበት፡፡
   ለሰዎች የተደረገ የአክብሮስግደት 2ኛ ሳሙ 1፡2፣ዘፍጥ 42፡6፡፡
   አሁን ግን እናንተ በፊት ርቃችሁ የነበራችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ ሆናችሁ በክርስቶስ ደም ቀርባችኋል።14-15፤ እርሱ ሰላማችን ነውና፤ ሁለቱን ያዋሐደ በአዋጅ የተነገሩትንም የትእዛዛትን ሕግ ሽሮ በመካከል ያለውን የጥል ግድግዳን በሥጋው ያፈረሰ፤ ይህም ከሁለታቸው አንድን አዲስን ሰው በራሱ ይፈጥር ዘንድ ሰላምንም ያደርግ ዘንድ፥16፤ ጥልንም በመስቀሉ ገድሎ በእርሱ ሁለታቸውን በአንድ አካል ከእግዚአብሔር ጋር ያስታርቅ ዘንድ ነው። ኤፌ 2፡13-16
   ከዚህም የተነሳ የእርግማን ምልክት የነበረዉ መስቀል የሰለም እና የእርቅ ምልክት እንዲሁም ጌታችን ለእኛ የከፈለዉን መስዋዕትነት ማሰቢያ ምልክት ሆነ፡፡ መስዋዕቱንም ያቀረበዉ በዚሁ ላይ ነዉ፡፡ መጽሃፍ ቅዱስም ጌታ ደቀ መዛሙርት የሚሆኑት ምን አይነት እንደሆኑ እንዲህ ይገልጻል፡፡ ‹‹ ሕዝቡንም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ጠርቶ እንዲህ አላቸው። በኋላዬ ሊመጣ የሚወድ ቢኖር፥ ራሱን ይካድ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ። ማር 8፡34›› ‹‹ መስቀሉንም የማይዝ በኋላዬም የማይከተለኝ ለእኔ ሊሆን አይገባውም።ማቴ 10፡38›› ‹‹ ማንም መስቀሉን ተሸክሞ በኋላዬ የማይመጣ፥ ደቀ መዝሙሬ ሊሆን አይችልም። ሉቃ 14፡27›› ፡፡ በመሆኑም ጌታ ደቀመዝሙር የሆነዉ ፓዉሎስ ‹‹እኔስ ከጌታችን ከእየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ›› ገላ 6፡14 በማለት የደቀመዝሙርነቱን መስፈርት መቀበሉን ገልጾኣል፡፡ እኛም ክርስቲያኖች ይህን የመጽሃፍ ቅዱስ ቃል እና የሃዋሪያዉን ተምሳሌት ምክንያት በማድረግ የጌታን መስቀል እናከብራለን፣ጌታ ደቀ መዝሙር ስለ ሞናችን እና እሱን ስለ መከተላችን ምልክታችን እናደርገዋለን፡፡ ይህን ጌታ ጥልን የሸነፈበትን መሳሪያ ምልክታችን አድርገነዋል፡፡ ክርስቲያኖች የሚጠቀሙት መጽሃፍ ቅዱስ ከአገልግሎቱ አንጻር ፣ከቃሉ እና ከባለቤቱ አንጻር ቅዱስ እንደተባለዉ ሁሉ ፤የጌታ መስቀልም ፣ከአገልግሎቱ፣ከባለቤቱ፣እና ከሰጠን ጥቅም አንጻር ቅዱስ ነዉ፡፡
   እኛ ኦርቶዶክሶች የክርስቶስን መስቀል ስንሸከም፣አርማችን ስናደርገዉ፣ስናከብረዉ መከራዉንም በማሰብ ነዉ፡፡ማን ነዉ እለት እለት በቅዳሴዉ መከራዉን የሚያስበዉ ? ማን ነዉ በህማማት ወቅት ሙሉ ሳምንት ስለ መከራዉ የሚያስበዉ ? በጾም የሚያስበዉ ?
   በፊልጵስዩስ ምዕራፍ 3 ላይ በዚህ በክርስቶስ መስቀል ላይ ጠላቶች እንደሚነሱ መጽሃፍ ቅዱስ ይገልጻል፡፡ ‹‹ብዙዎች ለክርስቶስ መስቀል ጠላቶቹ ሆነው ይመላለሳሉና፤ ብዙ ጊዜ ስለ እነርሱ አልኋችሁ፥ አሁንም እንኳ እያለቀስሁ እላለሁ። መጨረሻቸው ጥፋት ነው፥ ሆዳቸው አምላካቸው ነው፥ ክብራቸው በነውራቸው ነው፥ አሳባቸው ምድራዊ ነው።ፊልጵ 3፡18-19፡፡›› ታዲያ ለክርሰቶስ መከራ ጠላቶች እንዴት ይኮናል ? ነገር ግን ዛሬ ብዙዎች በክርስቶስ መስቀል ላይ የተለያዩ ክህደቶች እያስተማሩ ይገኛሉ፡፡
   አባታችሁ የሞተበት ጥይት በማለት ይገልጹታል፡፡ ለእነሱ አባታቸዉ ጥል ነዉ ምክንያቱም ጥልንም በመስቀሉ ገድሎ ይላል (ኤፌ 2፡13-16)፡፡ ጥል አባታቸዉ የሆኑት መስቀልን አያከብሩም፡፡ መጽኃፍቅዱስን የሚያዉቅ ግን መስቀልን ያከብራል፡፡

   Delete
 3. ለዓለም ሁሉ ቤዛ ሆኖ የተሠዋበትን ቅዱስ መስቀሉን እየተፃረሩ ለጌታችን፣ለአምላካችን፣ለመዳኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ክብር ቀናኢ መስሎ መታየት ክህደት ነው ።

  ReplyDelete
 4. የሚወደኝ ቢኖር መስቀል ተሸክሞ ይከተለኝ ያለዉ ጌታ የሃይማኖት አባቶች ነን የሚሉ አንድ የቅርፃቅርፅ ባለሞያ የቀረፀዉን የእንጨት መስቀል ይዞ ማሳለም ሳይሆን ሁሌ በህሊናችን ጌታ እየሱስ ስለኛ ስለ አንተ በደላችንን ስለኛ መስዋዕትእንደሆነ በደም ዋጋ የተገዛን ሀሌ ከህሊናችን የማይፋቅ ነዉ እንጂ የተቀረፀዉ እያነሳን መሳለምና መስገድ ተገቢ አይደለምምምምምምምምም
  ወገኖቼ ዋና አላማዉ ክርስቶስ ወደ ምደር በድንግልማርያም ሲመጣ ፊልም ለመስራት አይደለም ጌታ እየሱስ በእለተ አርብ መጨረሻ በነየ የሚያምን የዘላለም ህይወት አለዉ ነዉ ያለዉ ስግደት የሚገባ ለአንድ አምላክ ብቻ ነዉ መፅሃፍ ቅዱስ ብታነቡ እንዲህ በንፋስ እንደሚገፋ ወረቀት አትሆንም ነበር ነገሩ መፅሃፉን አትመርምሩ እንዲሁ ተለን ስላደግን የሆናል በሃይማኖት አባቶች
  ወንድሜ ስማ ድንግል ማርያም እኮ ቅዱስ ገብርኤል ሊያበስራት ሲመጣ እኮ አልሰገደችለትም እኔ ለጌታየ ባሪያዉ ነኝ የባሪያቱን ዉርደት ተመልክቶአልና ነዉ ያለችዉ ቅዱስ ገብርኤልም እኮ ስግደትን አይፈልግም

  ReplyDelete
 5. እውር እውርን ቢመራው ገደል ነው ይሉሃል እንዳንተ ያለው ውሉደ አርዮስን ነው ደግሞ ምን አለ ኦረቶዶክስ አንዲተላአለች እንዲ አትልም ከማልት አንተ ለተጠመቅከለት ዲያቢሎስ ባጠመቀህ መጽሓፍ ላይ ያለውን እያነሳህ ላሳስታችሁ ብትል ካልሆነ ቢቀርብህ

  ReplyDelete