Friday, January 6, 2017

«እነሆ፥ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ፤ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና።» ሉቃስ 2፡10-11ይህ እንደ ኢትዮጵያውያን ዘመን አቆጣጠር ከዘሬ ሁለት ሺሕ ዓመት  በፊት የተነገረ የምስራች ቃል ነው፡፡ ይህን የምስራች የተናገረው የጌታ መልአክ ነው፡፡ የምሥራቹን የተናገረው ደግሞ መድኃኔ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደበት አቅራቢያ ሌሊቱን መንጋቸውን ይጠብቁ ለነበሩ እረኞች ነበር፡፡ የምስራቹን በመጀመሪያ የሰሙት እነርሱ ቢሆኑም የምሥራቹ ግን ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ነው፡፡

የምስራቹ ቃል “መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ የሆነ ጌታ ተወልዶላችኋል” የሚል ነው፡፡ አዎን እንደ ኢትዮጵያውያን ዘመን አቆጣጠር የዛሬ 2009 ዓመት የተወለደው ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ ጌታ እና መድኃኒት ነው፡፡ እርሱ በነቢያት ይመጣል ተብሎ በተስፋ ሲጠበቅ የነበረው መሲሕ ነው፤ እርሱ የጌቶች ሁሉ ጌታ ነው፡፡ ይልቁንም እርሱ ጻድቅ የለም አንድስ እንኳ፣ ሁሉ ኀጢአትን ሠርተዋል የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሏቸዋል ተብሎ እንደ ተነገረው ሰው ሁሉ በኃጢአት በሽታ ተይዞና የሚያድነው አዳኝም ሆነ መድኃኒት ጠፍቶ በነበረበት ሁኔታ እግዚአብሔር በተናገረው ቃልና በገባው ተስፋ መሠረት አንድያ ልጁን መድኃኒት አድርጎ ላከው፡፡ ቃል ሥጋ ሆኖ በመወለዱ መልአኩ ያበሠረንም ይኸንኑ የምስራች ነው፡፡

የሚያድነው አዳኝም መድኃኒትም አጥቶ በቀቢጸ ተስፋ ይኖረው ለነበረው የሰው ልጅ ማለትም ለሕዝቡ ሁሉ ይህ ትልቅ የምሥራች ነው፡፡ የጌታ ሰው ሆኖ መወለድ ይህን ትልቅ የምሥራች ይዞልን ነው የመጣው፡፡ የልደቱን በዓል የምናስብ ክርስቲያኖች ሁሉ ከቅድስት ድንግል ማርያም የተወለደው እኛን ከኃጢአታችን የሚያድነን መድኃኒት ሆኖ ነው የመጣው፡፡ መድኃኒት ሆኖም በቀራንዮ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ በሞቱ ሞትን በመደምሰስ ሕይወትን እንዲሁ ሰጥቶናል፡፡
ዛሬ የልደቱን በዓል ስናከብር ይህን መድኃኒት አምነንበትና ተቀብለነው፣ በእርሱም ድኅነትን እንደ ተቀበለና ዳግም ተወልዶ የመንግሥተ ሰማያት ዜጋ አንደ ሆነ አዲሱ ሰው እየኖርን መሆን አለበት፡፡ ይህ በሕይወታችን ሳይከናወን ልደቱን በዘልማድ ባህላዊ በሆነ መንገድ በመብልና በመጠጥ በገና ጨዋታ ወይም ስጦታ በመለዋወጥ …  ብናከብር ከምሥራቹ ቃል በእጅጉ የራቅን ነንና ከተወለደው መሲሕ ጋር አልተገናኘንም፡፡ ስለዚህ ምስኪኖች ነን፡፡ የልደቱ በረከት የዳር ተመልካችም እንሆናለን፡፡
መድኃኒት ተወልዶላችኋል የሚለው የምሥራቹ ቃል ለሁላችንም ነውና የተወለደው ኢየሱስ መድኃኒት መሆኑን ሳናስተውልና በመድኃኒትነቱ መዳንን ሳንቀበል አሁንም ስለዘላለማዊ ሕይወት ጉዳይ በጭንቀትና በስጋት እንዲሁም ማን ያድነኛል በሚል ምላሽ ያጣ ጥያቄ ውስጥ ወድቀን የምንገኝ ሁሉ እነሆ መድኃኒት ተወልዶልናልና እጅግ ደስ ይበለን፡፡ በተወለደው መድኃኒትም መዳናችንን እናረጋግጥ፡፡ ለዚህም ቃሉን በእምነት በመቀበል ራሳችንን ለዚህ ጌታ በእምነት እናቅርብ፡፡
ይህን መድኃኒት ችል ብንለው ወይም እርሱን ትተን ሌሎች መድኃኒቶችን ብንፈልግ እውነተኛ መዳንንም ሆነ ከእግዚአብሔር ጋር መታረቅን አናገኝም፡፡ እግዚአብሔር እኛን ከኃጢአትና ከዘላለም ሞት ለማዳን የላከልን መድኃኒት አንድያ ልጁ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው፤ ሌላ ማንንም አይደለም፡፡ ቃሉም እንዲህ ይመሰክራል፤ «መዳንም በሌላ በማንም የለም፤ እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰዎች የተሰጠ ስም ከሰማይ በታች ሌላ የለምና።» የሐዋርያት ሥራ 4፡12፡፡ የምሥራቹ ቃል ይህን እውነት ላላስተዋሉ፣ ላላመኑና ላልተቀበሉ ሁሉ ነው፡፡ ዛሬም ይህን መድኃኒት ለሚፈልጉ ሁሉ መድኃኔዓለም ክርስቶስ ሕያው ነውና ወደ ሕይወታችን መድኃኒት በመቅረብ በዓለ ልደቱን ትርጉም ሰጪ እናድርገው፡፡
መልካም የጌታ የልደት በዓል ይሁንልን

1 comment:

  1. But, you did not insult fathers, and talk about some conspiracy by MK. (እኩያን ሆይ፡ ከወትሮው ልቅለቃችሁ ጋር ቤት አልመታም፡፡)

    ReplyDelete