Saturday, April 15, 2017

እነሆ ተነሥቷልኃጢአታችንን ተሸክሞ ስለእኛ የሞተውንና የተቀበረው ጌታ ከሙታን መካከል ይፈልጉት ዘንድ ማልደው ወደ መቃብሩ ለገሰገሱት ሰዎች ሁለት ሰዎች (መላእክት) ሕያውን ከሙታን መካከል ስለ ምን ትፈልጋላችሁ? ተነሥቶአል እንጂ በዚህ የለም።” በማለት ሕያው ጌታ ሞትን ድል አድርጎ መነሣቱን አበሰሯቸው (ሉቃስ 24፥5)፡፡ የትንሣኤ በዓል እየተባለ በየዓመቱ የሚከበረው በዓል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጎ መነሣቱ የሚታሰብበት በዓል ነው፡፡ እርሱ ስለ ኃጢአታችን ሞቶ ዕዳችንን በሞቱ ከከፈለ በኋላ በትንሣኤው ከእግዚአብሔር ጋር መታረቃችንንና የነፍሳችን ነጻነት መታወጁን አበሰረ፡፡ አይሁድን ስለፈሩ በዝግ ቤት ተሰብስበው ለነበሩት ደቀመዛሙርቱ ሰላም ለእናንተ ይሁን አላቸው፡፡ ይህም ትንሳኤው ያስገኘውን ዕርቅና ሰላም የሚመሰክር የምስራች ነው፡፡
ትንሣኤውን በመላው ዓለም የሚገኙ ክርስቲያኖች ሁሉ በተለያዩ ሥነ ሥርዓቶች ያከብሩታል፡፡ ነገር ግን በዓሉን ስናከብር እኛ ከምንፈጽማቸው የተለያዩ ስርዓቶች ባሻገር እግዚአብሔር የሚፈልገውን ዋና ነገር የምናደርግ ስንቶች ነን? አዎን እግዚአብሔር የሚቆጥርልን ጽድቅ እኛ በበዓል ስም የምናደርገውን ምድራዊ ግርግር አይደለም፡፡ ስለ በደላችን አልፎ የተሰጠውን እኛን ስለ ማጽደቅም የተነሣውን ጌታችንን ኢየሱስን ከሙታን ባስነሣው ለምናምን ለእኛ” ጽድቁ ይቆጠርልናል (ሮሜ 4፥24-25)፡፡ ታዲያ በትንሣኤው የተገኘው ይህ ሰላምና እረፍት የደረሰልን ስንቶች እንሆን? ይህን በረከት ሳይቀበሉ በዓሉን የሆድ ተዝካር ብቻ በማውጣት በመብልና በመጠጥ እንዲሁም ይህን በመሰለ ምድራዊ ነገር ብቻ የሚያከብሩ እጅግ ከስረዋል፡፡ በእርሱ ትንሣኤ የተረጋገጠውን የዘላለም ሕይወት በእምነት ሳይቀበሉ የትንሣኤን በዓል ቢያከብሩ ከትንሳኤው በረከት የራቁ ናቸው፡፡

ስለዚህ በዓለ ትንሣኤውን ስናከብር በእርሱ ሞትና ትንሣኤ የተገኘውን የዘላለም ሕይወት በእምነት መቀበላችንን ማረጋገጥ ይኖርብናል፡፡ ትኩረታችን በበዓሉ ግርግር ላይ ሳይሆን ጌታ በሠራለን ቁምነገር ላይ ማረፍ አለበት፡፡ መልካም በዓለ ትንሣኤ እንዲሆንላችሁ ስንመኝ ይህን የምሥራች ለእናንተ በመናገር ነው
ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን በመነሣቱ ለሕያው ተስፋና ለማይጠፋ፥ እድፈትም ለሌለበት፥ ለማያልፍም ርስት እንደ ምሕረቱ ብዛት ሁለተኛ የወለደን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ፤ ይህም ርስት በመጨረሻው ዘመን ይገለጥ ዘንድ ለተዘጋጀ መዳን በእምነት በእግዚአብሔር ኃይል ለተጠበቃችሁ ለእናንተ በሰማይ ቀርቶላችኋል።” 1ኛ ጴጥሮስ  1፥3-5

1 comment: