Monday, May 22, 2017

ማቅ በኦሮሚያ ተማሪዎች ላይ በቋንቋቸው የሃይማኖት ትምህርትን እንዳይማሩ በማድረግ ያደረሰው በደል እንዲጣራ ሲኖዶሱ ወሰነ


 Read in PDF

መግለጫ በማውጣት የተጠናቀቀው የግንቦቱ ሲኖዶስ ስብሰባ በመግለጫው በመግለጫው የተነሣው ሌላው ነጥብ ማቅ በኦሮምያ የተለያዩ ዞኖች ከወለጋ፣ ከጅማ፣ ከአዳማ፣ ከድሬዳዋ፣ ከአምቦ ከሐሮማያና ቡሌሆራ ዩኒቨርሲቲዎች የተሰባሰቡና ከዚህ ቀደም ለፓትርያርኩ ያቀረቡት አቤቱታ ታይቶ ውሳኔ ማግኘቱ ነው፡፡ በመግለጫው እንደ ተመለከተው በተማሪዎቹ ላይ ጠባቡና ትምክሕተኛው ማቅ የሃይማኖትን ትምህርት በቋንቋቸው እንዳይማሩ በማድረግ ያደረሰባቸውን በደል አስመልክቶ ጉዳዩ እንዲጣራ ተወስኗል፡፡
በአቤቱታው ላይ እንደተመለከተው ማቅ ተማሪዎቹን ወደግቢ ሲገቡ ከተቀበላቸው ጀምሮ “በአውደ ምህረቱ ላይ የሚተላለፈው የእግዚአብሔር ቃል መሆኑ ቀርቶ ነጋ ጠባ የአንድ ማህበር  የበላይነትና ልዕልና ትረካ፣ መቆምም ሆነ መስራት ያለብን ለቤተ ክርስቲያኗ ሳይሆን ለማህበሩ እንደ ሆነ፣ አጠቃላይ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያሉ ምንደኞች እንደሆኑና ብቸኛው የቤተ ክርስቲያን ተቆርቋሪ ማህበረ ቅዱሳን እንደሆነ የሚተርክ የአንድ ቡድን” ትረካ መሆኑ እንዳሳዘናቸው በደብዳቤያቸው ገልጸዋል፡፡ ሌሎችንም ነጥቦች በመንሣት ማቅን መስመር እንዲያሲዙላቸው ጠይቀዋል፡፡

Friday, May 19, 2017

ሲኖዶሱ በአዋልድ መጻሕፍት ላይ ያሳለፈው ውሳኔ መንፈሳዊ ተሐድሶ ወይስ ፖለቲካ?የሰሞኑ የሲኖዶስ ስብሰባ በአዋልድ መጻሕፍት ላይ ውሳኔ ማሳለፉ ትልቅ እርምጃ ተደርጎ የሚወሰድ ነው፡፡ ውሳኔው አዋልድ መጻሕፍት የያዟቸውን ጉዶች እየተቹ ሲያቀርቡና ካህናቱንና ሕዝቡን ሲያነቁ ለቆዩ የቤተ ክርስቲያን ልጆች ትልቅ ድል ነው፡፡ የዓመታት ጩኸታቸው በሲኖዶስ መሰማትና ውሳኔ ማግኘት በመጀመሩ ይበል ያሰኛል፡፡ በዚህም ምክንያት አለስማቸው ስም እየተሰጣቸው ለውግዘትና ለስደት መዳረጋቸው ግን ቤተ ክርስቲያኒቱን ብዙ ዋጋ የሚያስከፍላት መሆኑ ከወዲሁ እየታየ ነው፡፡ እውነት እውነትነቱ እየፈካ ውሸት ደግሞ እየተጋለጠና እየኮሰመነ መሄዱ አይቀርምና፡፡ ብዙዎች እየፈለሱ ያሉት የአዋልድ ውሸት አስጠልቷቸውና እውነቱን ፍለጋ መሆኑን መረዳት በጣም ይጠቅማል፡፡
ውሳኔው የተወሰነበት መነሻ ግን ከሃይማኖታዊነት ይልቅ ፖለቲካዊነቱ ያመዝናል፡፡ በራእየ ማርያም ላይ የአንዳንድ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ብሔረሰቦች ስም በክፉ መጠቀሱ ሲሆን በተአምረ ማርያም ላይ ደግሞ ስለ አቡነ ጳውሎስና ስለ መንግሥቱ ኃይለማርያም የተጻፈ “ተአምር” መኖሩ እነዚህና መሰል አዋልድ እንዲታረሙ ምክንያት ሆኗል፡፡ ስለ አቡነ ጳውሎስና ስለ መንግስቱ ኃ/ማርያም የተጻፈው “ተአምር” የሚነግረን ነገር ቢኖር የተጻፈው ውሸት መሆኑን ብቻ ሳይሆን የቀሩትም የተአምረ ማርያም ጽሑፎች ዘመኑ ይርዘም እንጂ የተዘጋጁት በዚህ መንገድ መሆኑንና የሐሰት ድርሰቶች መሆናቸውን ነው፡፡ ለአዋልድ መጻሕፍት የተሳሳቱ መሆን ግን ከእነዚህ የበለጠ ብዙ ሥነ መለኮታዊ ተፋልሶን የሚያስከትሉ ከመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ ጋር የሚጋጩ ጽሑፎች ሞልተዋል፡፡ 

Thursday, May 18, 2017

“ሲኖዶሱ” በግብጽ ቤተ ክርስቲያን ላይ ያቀረበው ትችት “ልጅ ለእናቷ ምጥ አስተማረች” አያሰኝምን?የሰሞኑ የሲኖዶስ ስብሰባ ከተወያየባቸውና ውሳኔ ሰጠባቸው ከተባሉ ጉዳዮች መካከል ከግብጽ ቤተ ክርስቲያን ጋር ያለውን ግንኙነት የተመለከተው አንዱ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱ እናቴ ስትላት ከቆየችው ከግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ጋር ያላትን የዶግማና የቀኖና አንድነትና ልዩነት ለመመርመርና ከአንድ ውሳኔ ላይ ለመድረስ የተነሳችው ግን የሮማው ካቶሊክ ፖፕ ፍራንሲስ በቅርቡ ግብጽን በጎበኙበት ወቅት ከግብጹ ፓትርያርክ ጋር በተለይ ምስጢረ ጥምቀትን በተመለከተ ስምምነት ማድረጋቸውን ተከትሎ መሆኑ፣ ነገሩን የሌላ አስመስሎታል፡፡ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ እንዲወጣ በተደረገው ዜና ላይ እንደ ተመለከተውም ምንጮች (ማኅበረ ቅዱሳን እንደ ሆነ አያጠራጥርም) “የግብጽ ቤተ ክርስቲያን አካሄድ የነገረ መለኮትና የምስጢራተ ቤተ ክርስቲያን አንድነት ባላቸውና ኦሬንታል  ተብለው በሚታወቁት የኢትዮጵያ የሶርያ፣ የአርመንና የሕንድ እኅትማማቾች አብያተ ክርስቲያናት (የኤርትራ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አልተጠቀሰችም) ቅዱስ ሲኖዶሶች ያልተመከረበት እንደሆነ አስረድተዋል፡፡” ይላል፡፡  
በመሠረቱ እነዚህ አኅትማማች አብያተ ክርስቲያናት በጋራ ያላቸው የአስተምህሮና የሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን አንድነት እንደ ተጠበቀ ሆኖ በተናጠል ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ጋር ግንኙነት ሲያደርጉና ስምምነት ሲፈራረሙ በሁሉም ሲኖዶሶች መመከር አለበት የሚል ሕግ ወይም የጋራ ስምምነት ያለ አይመስልም፡፡ የጋራ ነገር ቢኖራቸውም በየራሳቸው የሚያምኑበትና የሚኖሩበት ትምህርትና ሥርዓት እንዳላቸውም አይካድም፡፡ ለምሳሌ በጥንተ አብሶ ትምህርት ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታምን የነበረው እንደ ግብጽ ቤተ ክርስቲያንና እንደ ሌሎቹም ኦሬንታል አብያተ ክርስቲያናት እንደ ነበረ ቀደም ያሉ ሊቃውንት በየጽሑፎቻቸው ያሰፈሩበት ሁኔታ አለ፡፡ ለምሳሌ ያህል የቀሲስ አስተርአየ ጽጌን ጥናት መቃኘቱ እንኳ በቂ ነው፡፡ በሊቁ የተደረጉት ጥናቶችና ከግብጽ ቤተ ክርስቲያን ጳጳሳት ጋር የተደረጉት የሐሳብ ልውውጦችና በደብዳቤም የተገለጸው ማርያም ጥንተ አብሶ ነበረባት የሚለው ትምህርት የኦርቶዶክስ ትምህርት መሆኑን ነው፡፡ ይሁን እንጂ አንዳንዶች በዚህ ትምህርት ከኦርቶዶክሳውያን ይልቅ ከካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ጋር ስምምነት ባይፈራረሙም፣ የካቶሊክን እምነት ቤተ ክርስቲያኗ እንድትከተል በማድረግ ማርያም ጥንተ አብሶ ነበረባት የሚለውን ኦርቶዶክሳዊ ትምህርት ጥንተ አብሶ የለባትም በሚለው ካቶሊካዊ ትምህርት ለውጠዋል፡፡ በዚህ ጊዜ የግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ምነው እኔና ሌሎቹ ኦርቶዶክሶች ሳንመክርበት በሚል ተቃውሞ አላነሣችም፡፡ በትክክል ከታየ ደግሞ በአስተምህሮ ረገድ ከኦርቶዶክሳዊ ትምህርት እየራቀች የሄደችው ግብጽ ሳትሆን ኢትዮጵያ ናት፡፡ ስለዚህ አስቀድሞ ራስን መመርመሩ የተሻለ ነው፡፡

Sunday, May 14, 2017

የሲኖዶሱ ውግዘት መፍትሔ አያመጣምቤተ ክርስቲያን በክርስቶስ የተቋቋመችው የክርስቶስን ወንጌል በመስበክ በእርሱ የማዳን ሥራ የሚያምነውን ሰው ወደ እግዚአብሔር መንግስት እንዲገባ ለማገልገል ነው፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም ስትመሰረት ከዚህ የተለየ ዓላማ የላትም፡፡ ይሁን እንጂ ይህን ዓላማዋን ከዘነጋችና መንገዷን ከሳተች ዘመናት ተቆጥረዋል፡፡ ይህን በመገንዘብ ወደ ቀደመው የወንጌል እውነት ተመልሳ በክርስቶስ ኢየሱስ መዳን የሚገኝበትን ወንጌል እንድትሰብክ ለማድረግ የተንቀሳቀሱትን የገዛ ልጆቿን ሥርዓቱን ተከትላ፣ አነጋግራና የንስሐ ዕድል ሰጥታ፣ ሳይሆን አቅርባ ሳታነጋግር አውግዣለሁ ለይቻለሁ ስትል ኖራለች፡፡ በተለይም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ራሱ ከሳሽ ራሱ ምስክርና በእጅ አዙር ራሱ ዳኛ በሆነው ማኅበረ ቅዱሳን በኩል ልዩ ልዩ ስም በመስጠት ህገ ወጥ ውግዘቱን ገፍታበታለች፡፡ ይህን በማድረጓ ግን ከኪሳራ በቀር ያገኘችው ጥቅም የለም፡፡ እንዲያማ ቢሆን ኖሮ ከዚህ ቀደም ባስተላለፈችው ሕገ ወጥ ውግዘት የወንጌልን እንቅስቃሴ ማዳፈን በቻለች ነበር፡፡ ነገር ግን ሲያወግዙትና እናስቁምህ ሲሉት የሚብሰውና ይበልጥ የሚቀጣጠለው የወንጌል እንቅስቃሴ በአስገራሚ ሁኔታ በየቦታው እየጠቀጣጠለ ይገኛል፡፡ ሕገ ወጥ ውግዘትም አያስቆመውም፡፡
ማኅበረ ቅዱሳንም ሆነ አሁን ያለው የእርሱ ጉዳይ ፈጻሚ የሆነው ሲኖዶስ አላስተዋሉትም እንጂ እያወገዙ ያሉት የወንጌልን እንቅስቃሴ ነው፡፡ በሌላ ምንገድ እየተጣሉ ያሉት ወንጌል ለፍጥረት ሁሉ እንዲሰበክ ካዘዘው ጌታ ጋር ነው፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ ውግዘት ያስተላለፈው በክርስቶስ ቀጥሎም በሐዋርያት የተሰበከውን ወንጌል በማጣመም ሌላ ወንጌል በሚያስተምሩት ላይ ነው፡፡ በክርስቶስ ጸጋ እናንተን ከጠራችሁ ከእርሱ ወደ ልዩ ወንጌል እንዲህ ፈጥናችሁ እንዴት እንዳለፋችሁ እደነቃለሁ፤ እርሱ ግን ሌላ ወንጌል አይደለም፤ የሚያናውጡአችሁ የክርስቶስንም ወንጌል ሊያጣምሙ የሚወዱ አንዳንዶች አሉ እንጂ። ነገር ግን እኛ ብንሆን ወይም ከሰማይ መልአክ፥ ከሰበክንላችሁ ወንጌል የሚለይ ወንጌልን ቢሰብክላችሁ፥ የተረገመ ይሁን። አስቀድመን እንዳልን እንዲሁ አሁን ሁለተኛ እላለሁ፥ ከተቀበላችሁት የተለየውን ማንም ቢሰብክላችሁ የተረገመ ይሁን።” (ገላትያ 1፡6-9)፡፡ ዛሬ እየሆነ ያለው ግን ተገላቢጦሹ ነው፡፡ እውነተኛውን የክርስቶስን ወንጌል የሚሰብኩት ይወገዛሉ፡፡ እውነተኛውን ወንጌል የሚያጣምሙና ሌላ ባዕድ ወንጌል የሚሰብኩት ደግሞ ያወግዛሉ፡፡ በእርግጥ ይህን መለወጥ አይቻልም የወንጌል ባሕሪ ይህ ነውና፡፡   

Wednesday, May 10, 2017

በትግርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ላይ ተቃውሞ ያስነሳው የትግራይ ኦርቶዶክሳዊ ሕዝብ ሳይሆን ማህበረ ቅዱሳን ነውየማህበረ ቅዱሳን “ስውር ብሎግ” የሆነው ሐራ እና አዲስ አድማስ ጋዜጣ እየተናበቡ እንደሚሰሩ እንዱ ሌላውን እየጠቀሱ በተለይም ሐራ አዲስ አድማስን እየጠቀሰች ዘገባዎች እንደምትሠራ ይታወቃል፡፡ ሐራ እንዲህ የምታደርገው  የምታወጣው ጽሁፍ ከጋዜጣ የተወሰደ ነው ለማሰኘትና የጽሑፉን ተአማኒነት ከፍ ለማድረግ ነው፡፡ ይሁን እንጂ እንዲወጡ የሚፈልጓቸው ዜናዎች ወደ አዲስ አድማስ እንዲሄዱ የሚያደርጉት ራሳቸው እንደሆኑ ዘገባው ምስክር ከመሆኑም በላይ ውስጥ አዋቂዎችም የሚናገሩት ሐቅ ነው፡፡ “አስተምህሮን ይጻረራል የተባለ የትግርኛ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲታገድ የመቐለ ምእመናን ጠየቁ” በማለት አዲስ አድማስ ዜና አድርጎ ያወጣው ዘገባም ሁለቱ በዚህ መንገድ የተቀባበሉት ነው፡፡ እርግጥ በደብዳቤው መጨረሻ ላይ “ለሁሉም ሚድያዎች” ግልባጭ መደረጉ ቢታወቅም ይህ ከሽፋንነት አይዘልም፡፡
ይህ ዜና አዲስ አድማስ ጋዜጣን ትልቅ ግምት ውስጥ የሚከት፣ ዜናው እንዲሠራላቸው የጠየቁትንም ክፍሎች ማንነት በግልጽ የሚያሳይ ነው፡፡ ዜናውን ስንመለከት የአንድ ማህበር ሐሣብ እንጂ የትግራይ ኦርቶዶክሳውያን ሐሣብ እንዳልሆነ መገመት አያስቸግርም፡፡ ይህን ተራ አሉባልታና የአንድ ጽንፈኛ ማህበር ፍላጎት ያጠላበትን ዜና የሠራው አዲስ አድማስ ጋዜጣ እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ የማህበረ ቅዱሳን ልሳን መሆኑን በገሃድ ያሳየበት ዘገባ ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያኗ ሊቃውንት የተዘጋጀውን መጽሐፍ ቅዱስ ተሳስቷልና ከሥርጭት ይታገድልን ይወገድልን አሉ በሚል ነው አፍቃሬ ማህበረ ቅዱሳን የሆነው አዲስ አድማስ ዜናውን የሰራው፡፡ ሐራ ዜናውን ተቀብላ ምንጭ ጠቅሼ ነው ያቀረብሁላችሁ በሚል የአጽራረ መጽሐፍ ቅዱሱን ደብዳቤ ጭምር ይዛ ወጥታለች፡፡