Wednesday, May 10, 2017

በትግርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ላይ ተቃውሞ ያስነሳው የትግራይ ኦርቶዶክሳዊ ሕዝብ ሳይሆን ማህበረ ቅዱሳን ነውየማህበረ ቅዱሳን “ስውር ብሎግ” የሆነው ሐራ እና አዲስ አድማስ ጋዜጣ እየተናበቡ እንደሚሰሩ እንዱ ሌላውን እየጠቀሱ በተለይም ሐራ አዲስ አድማስን እየጠቀሰች ዘገባዎች እንደምትሠራ ይታወቃል፡፡ ሐራ እንዲህ የምታደርገው  የምታወጣው ጽሁፍ ከጋዜጣ የተወሰደ ነው ለማሰኘትና የጽሑፉን ተአማኒነት ከፍ ለማድረግ ነው፡፡ ይሁን እንጂ እንዲወጡ የሚፈልጓቸው ዜናዎች ወደ አዲስ አድማስ እንዲሄዱ የሚያደርጉት ራሳቸው እንደሆኑ ዘገባው ምስክር ከመሆኑም በላይ ውስጥ አዋቂዎችም የሚናገሩት ሐቅ ነው፡፡ “አስተምህሮን ይጻረራል የተባለ የትግርኛ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲታገድ የመቐለ ምእመናን ጠየቁ” በማለት አዲስ አድማስ ዜና አድርጎ ያወጣው ዘገባም ሁለቱ በዚህ መንገድ የተቀባበሉት ነው፡፡ እርግጥ በደብዳቤው መጨረሻ ላይ “ለሁሉም ሚድያዎች” ግልባጭ መደረጉ ቢታወቅም ይህ ከሽፋንነት አይዘልም፡፡
ይህ ዜና አዲስ አድማስ ጋዜጣን ትልቅ ግምት ውስጥ የሚከት፣ ዜናው እንዲሠራላቸው የጠየቁትንም ክፍሎች ማንነት በግልጽ የሚያሳይ ነው፡፡ ዜናውን ስንመለከት የአንድ ማህበር ሐሣብ እንጂ የትግራይ ኦርቶዶክሳውያን ሐሣብ እንዳልሆነ መገመት አያስቸግርም፡፡ ይህን ተራ አሉባልታና የአንድ ጽንፈኛ ማህበር ፍላጎት ያጠላበትን ዜና የሠራው አዲስ አድማስ ጋዜጣ እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ የማህበረ ቅዱሳን ልሳን መሆኑን በገሃድ ያሳየበት ዘገባ ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያኗ ሊቃውንት የተዘጋጀውን መጽሐፍ ቅዱስ ተሳስቷልና ከሥርጭት ይታገድልን ይወገድልን አሉ በሚል ነው አፍቃሬ ማህበረ ቅዱሳን የሆነው አዲስ አድማስ ዜናውን የሰራው፡፡ ሐራ ዜናውን ተቀብላ ምንጭ ጠቅሼ ነው ያቀረብሁላችሁ በሚል የአጽራረ መጽሐፍ ቅዱሱን ደብዳቤ ጭምር ይዛ ወጥታለች፡፡

ደብዳቤው በግልባጭ እንዲደርሳቸው ከተደረጉት አካላት መካከል አንዱ የማህበረ ቅዱሳን ዋና ማእከል ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያን መዋቅራዊ አሰራር ግን እርሱን የተመለከተ ጉዳይ ካልሆነ በቀር ማኅበረ ቅዱሳን እንደ አንድ ይህን የመሰለ ጉዳይ እንደሚመለከት ተቋም ተቆጥር በግልባጭ ለእርሱ አይጻፍም፡፡ ነገር ግን ማህበሩ ራሱን ከቤተ ክርስቲያን በላይ አድርጎ ስለሚመለከትና ስለዚህ ጉዳይ ተግቶ ስለሚሰራ ባይመለከተውም በግልባጭ ለእርሱም እንዲደርሰው አስደርጓል ማለት ነው፡፡
ጋዜጣው ዜናውን እንደ ዜና ከማቅረቡ በፊት መጽሐፍ ቅዱስን በሚመለከት ተሳስቷል ለማለት እነዚህ ምእመናን ምን ሥልጣንና ኃላፊነት አላቸው የሚለውን መጠየቅና ያን ከግምት ማስገባት ነበረበት፡፡ ሃይማኖት አባቶች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተመስርተው የሚያስተምሩት ሳይሆን ምእመናን የሚፈልጉት ነገር እየሆነ መጥቷል፡፡ እነዚህ ከ40 በላይ ሰዎች ያቀረቡትን ጥያቄ በክልሉ ባሉ አህጉረ ስብከት ያሉት አራቱ ጳጳሳት ያልተቀበሉት ለምንድነው? እነዚህ 40 ሰዎች ያውቃሉ ወይ? አንዳች እንደማያውቁማ ጋዜጣው እነርሱን ዋቢ አድርጎ ተፈጸመ ያሉትን ስሕተት ሲጠቅስ መረዳት ተችሏል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ከ40 በላይም ሆነ (ለነገሩ ፊርማው አርባም አይሞላ) በመቶዎችና በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በሚያቀርቡት ጥያቄ መሠረትና በእነርሱ ፍላጎት ላይ ተመሥርቶና የሰዎችን ሃይማኖታዊ ፍላጎት ለማሟላት በሚል የሚተረጎም ሳይሆን የዕብራይስጡን ብሉይ ኪዳንና የግሪኩን ሐዲስ ኪዳን መሠረት አድርጎና ለእግዚአብሔር ቃል ታማኝ ሆኖ የሚሠራ ታላቅ ሥራ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ሃላፊነት ያለባቸው የሚመለከታቸው የቤተ ክርስቲያን አባቶችና ሊቃውንት ናቸው እንጂ ምእመናን አይደሉም፡፡ ምእመናን መጽሐፍ ቅዱሱ ልክ ነው ወይም ተሳስቷል ለማለት የሚያበቃ ሥልጣንም ሆነ ኃላፊነት የላቸውም፡፡ የጋዜጣው ስሕተት የሚጀምረው እንግዲህ እዚህ ላይ ነው፡፡
እንደ ጋዜጣው ዘገባ ተፈራርመው ጥያቄውን አቀረቡ ያላቸው አርባም ባይሞሉ ከአርባ በላይ የሆኑ ምእመናን ናቸው፡፡ ከላይ ለማሳየት እንደሞከርነው ጥያቄው በምእመናን መቅረቡ ተገቢ ካለመሆኑም በላይ የቁጥሩ ማነስ በራሱ የሚነግረን ጥያቄው የጥቂቶች እንጂ የብዙሃን አለመሆኑን ነው፡፡ የብዙሃን ጥያቄ ቢሆንም እንኳን የሃይማኖት ጉዳይ በድምጽ ብልጫ የሚወሰን ሳይሆን በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት ነው፡፡ ስለዚህ ከዚህ ጥያቄ በስተጀርባ ያለው ማነው? የሚለው ጉዳይ በሚገባ መፈተሽ አለበት፡፡ ጥያቄው መቅረቡ ብቻ ሳይሆን እንዲህ ያለው የቤተክርስቲያን መሪዎችን ሥልጣንና ኃላፊነት የመቀማት አካሄድ በዚህች ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እየተስፋፋና ሥር እየሠደደ መጥቷል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ስሙ በስፋት የሚነሣው ደግሞ ማህበረ ቅዱሳን ነው፡፡ ምንም ተባለ ምን ከዚህ ዜና በስተጀርባ ያለው ማህበረ ቅዱሳን ነው፡፡ ስለዚህ የማህበረ ቅዱሳን ፍላጎት ስለነበር ዜናው ባይመጥንም አዲስ አድማስ ዜና አድርጎ አቅርቦታል ማለት ነው፡፡
በቅድሚያ የኦርቶዶክስ አስተምህሮ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ መሆን አለበት እንጂ በ2000 ዓ.ም ቤተ ክርስቲያኗ እንዳዘጋጀችው “መጽሐፍ ቅዱስ” የጥንቱን ሳይሆን አሁን እየሠለጠነ ያለውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆነ የኦርቶዶክስ አስተምህሮን ለማስጠበቅ የሚዘጋጅ መጽሐፍ አይደለም፡፡ ሆኖም ውንጀላው ማንንም የማያሳምንና ለመጽሐፍ ቅዱስ ሳይሆን አሁን በቤተክርስቲያኒቱ ላይ ለሰለጠነው የተሳሳተ ትምህርትና ልምምድ የወገነ ነው፡፡ ምክንያቱም የእግዚአብሔርን ቃል ምንም ለውጥ ሳያደርግ ጠብቆ የማስተላለፍ ትልቅ አደራና ኃላፊነት ያለበትና በዘፈቀደ ሳይሆን የትርጉምን ሥነ ምግባር በታላቅ ጥንቃቄ ጠብቆ ለዕብራይስጡና ለግሪኩ ንባብም ታማኝ ሆኖ ወደአገራችን የተለያዩ ቋንቋዎች መጽሐፍ ቅዱስን ሲተረጉም የቆየው የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበርን ሥራ ለማንኳሰስ ሆን ተብሎ የተሸረበ ሴራ እንጂ ከእውነተኛ የቤተክርስቲያን ልጆች የመጣ ተቃውሞ አይደለም፡፡
እነዚህ ከ40 በላይ የተባሉ ሰዎች በራሳቸው ተነሣስተው የተፈራረሙበትን ማመልከቻ ለትግራይ አህጉረ ስብከት 4 ሊቃነ ጳጳሳት በግንቦት 2008 ዓ.ም. ያቀረቡ መሆናቸውንና ለጥያቄያቸው ግን እስካሁን ምላሽ እንዳልተሰጣቸው ለአዲስ አድማስ ማስተዋቃቸውን ጋዜጣው ነግሮናል፡፡ ለምን ምላሽ አልሰጧቸውም? ጥያቄያቸው የዕውቀትና የኃላፊነት ደረጃን ያልጠበቀ ስለሆነ ነው፡፡ እንዲህ ያለውን ነገር ያልተረዳው አዲሰ አድማስ ጋዜጣ ግን ነገሩን ፖለቲካዊ አድርጎ እንጂ ሃይማኖታዊነቱን ጠብቆ ለማቅረብ አልሞከረም፡፡ ሃይማኖታዊ ጉዳይ በሃይማኖት አባቶችና በሊቃውንቱ የሚወሰን እንጂ ከሃይማኖት ጉዳይ ውጪ እንዳለ ሌላ ጉዳይ በሕዝብ ድምፅ የሚወሰን አስመስሎ ነው ያቀረበው፡፡ ለ40ዎቹ አፅራረ መጽሐፍ ቅዱስ ድጋፍ በመስጠት ጉዳዩን በሃይማኖት አባቶችና በሊቃውንቱ መመራት ያለበትን የመጽሐፍ ቅዱስ ጉዳይ ስለሃይማኖት ምንም በማያውቁ ጎጋዎች እንዲመራ ለማድረግ ቦታ የማለዋወጡ ሥራ አሁን የተጀመረ ሳይሆን፣ ይበልጥ ካለፉት 20 እና 25 ዓመታት ወዲህ በቤተክርስቲያኒቱ እጅግ እየተለመደ የመጣ ክፉ ልማድ ነው፡፡ ለዚህ በከፍተኛ ሁኔታ የተንቀሳቀሰው ማኅበረ ቅዱሳን ሲሆን የእርሱ ፍሬዎችም ደርሰው ከእነርሱ እንግዳ ትምህርት ጋር ሳይስማሙ ሲቀሩ ሊቃውንቱንና የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችን መናፍቃን ናቸው ተሐድሶ ናቸው እያሉ በመመነጠርና በማስመንጠር ሥራ ተጠምደው ይገኛሉ፡፡ ስለዚህ ቤተክርስቲያኒቱን የቤተክርስቲያኒቱ አባቶች ሳይሆኑ ምእመናን እንዲመሩም እየተደረገ እንደሆነ ከዚህ የ40ዎቹ ሰዎች ተግባር መረዳት ይቻላል፡፡ አሁን በተግባር የሚታየው እውነታም ይህ ነው፡፡
ስለዚህ ከ40 በላይ የተባሉት አፅራረ መጽሐፍ ቅዱስ “መጽሐፍ ቅዱሱ ታትሞ በገበያ ላይ ከዋለ በኋላ 92 በመቶ የሚሆነውን የክልሉን የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታይ ግራ እያገባ” ነው ብለው ማቅረባቸውና አዲስ አድማስም ምንም ሳያጣራ እነርሱን ምንጭ አድርጎ ተቃውሞውን የብዙዎች ማድረጉ በየትኛውም መለኪያ አሳማኝ ካለመሆኑም በላይ የጋዜጠኛነትን የእውነተኛነት መስፈርት የጣሰ ያደርገዋል፡፡ ከክልሉ 92 በመቶ የሚሆኑት ኦርቶዶክሳውያን ግራ ከተጋቡ የተሰበሰበው ፊርማ እንዴት ከአርባ በላይ ሰዎች ብቻ ሆነ? እነርሱን የወከላቸው ይህ 92 ከመቶ የሚሆነው ኦርቶዶክሳዊ ለመሆኑ ምን ማስረጃ አለ? ስለዚህ የጥቂቶችን የተለየ የግል ፍላጎት የክልሉ ኦርቶዶክሳውያን ሁሉ ፍላጎት አስመስሎ ማቅረብ የማህበረ ቅዱሳን አጀንዳ እንጂ የሌላ የማንም አይደለም፡፡ ይህን ዜና አድርጎ ያቀረበው አዲስ አድማስም የማን ወገን እንደሆነ አሳይቶበታል፡፡
ጋዜጣው የኦርቶዶክስን አስተምህሮ ይጻረራል ካለው የትግርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ማስረጃ አድርጎ ያቀረበው “የክርስቶስን የባሕርይ አምላክነት የሚክድ የቅድስት ሥላሴን አንድነትና ሦስትነት የሚያዛባ ሥልጣን ክህነትን የሚሽርና የማይቀበል፣ የቤተ ክርስቲያናን ፊደልና ቁጥር አቆጣጠር የማይቀበል እንዲሁም ቤተ ክርስቲያንዋ የምትቀበላቸውን 81 መጽሐፍ ቅዱስ ወደ ጎን በመተው 66 መጻሕፍትን ብቻ ያካተተ” በማለት ነው፡፡ በአቤቱታ አቅራቢዎቹ ደብዳቤ ላይ እንደተጠቀሰውም፦
1.      “የክርስቶስን የባሕርይ አምላክነት የሚክድ” በሚለው አንጻር ሮሜ 8፥26-34ን ተጠቅሷል፡፡
2.     “የቅድስት ሥላሴን አንድነትና ሦስትነት የሚያዛባ” ለሚለው ደግሞ “ዘፍጥረት 18 አርእስቱ ላይ” ይላል፡፡
3.     “ሥልጣን ክህነትን የሚሽርና የማይቀበል” ለሚለው ደግሞ ያዕቆብ 5፥14 ነው ማስረጃ ተደርጎ የተጠቀሰው፡፡
4.     “ተዋሕዶ ቤተክርስቲያናችን ለበርካታ ሺዎች ዓመታት ትጠቀምበት የነበረው ፊደል ቁጥር አቆጣጠርም ተሰርዞዋል” በመጨረሻም “የቤተ ክርስቲያናን ፊደልና ቁጥር አቆጣጠር የማይቀበል”
5.     “ቀዳሚትዋ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ለሺዎች ዓመታት ትመራበት የነበረው የራስዋ የሆነ 81 መፅሓፍት ቅዱስ ጽሀፍ ቅዱስወደ ጎን በመተው 66 መጻሕፍት ብቻ ተተርጉሞ መታተሙ እንቃወማለን” ተብሏል፡፡
እስኪ እነዚህን በጥቅስ ተደግፈው የቀረቡ ክሶች አንድ በአንድ እንመልከታቸው፦
1.    “የክርስቶስን የባሕርይ አምላክነት የሚክድ”
ለዚህ ክስ የቀረበው ሮሜ 8፥26-34 ያለው የእግዚአብሔር ቃል ነው፡፡ በዚህ ክፍል መንፈስ ቅዱስ ስለ ቅዱሳን እንደሚማልድ እና ክርስቶስ ኢየሱስም ስለ እኛ እንደሚማልድ ይናገራል፡፡ የትግርኛው መጽሐፍ ቅዱስ ግሪኩን መሠረት አድርጎ የተተረጎመ ስለሆነ መንፈስ ቅዱስ እንደሚማልድ፣ ክርስቶስም ስለእኛ እንደሚማልድ በግልጽ ጽፏል፡፡ በግርጌ ማስታወሻው ላይ ግን ግእዙ የሚለውን አስፍሯል፡፡ በአቡነ ጳውሎስ ዘመን ግእዙን መሰረት አድርጎ የተዘጋጀ በተባለውና በብዙ ሁኔታ ለግእዙ ንባብ ሳይሆን አሁን ለሚታየው የተሳሳተ አስተምህሮ ታማኝነቱን ያሳየው ትርጉም በግርጌ ማስታወሻው ይህን ክፍል የግሪኩ ይማልዳል ይላል ብሎ ነው ያቀረበው፡፡ የትግርኛውም የግሪኩን መሠረት አደርጎ ስለተዘጋጀ የግሪኩን በመጠቀም በግርጌ ማስታወሻው ላይ ግን ግእዙ “ይትዋቀስ” ወይ ይከራኸር ይብል” ይላል ሲል አስፍሯል፡፡ ታዲያ ምን አጠፋ?  
እንደሚታወቀው ይህን በሮሜ 8፥26 እና 34 ላይ የሰፈረውን እውነት ውሸት ለማድረግ በፀረ ወንጌል ቡድኖች ብዙ ጥረትና ድካም ተደርጓል፡፡ ነገር ግን ይህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነት በተሳሳተ እይታ ላይ የተመሠረተውን የቅዱሳን ምልጃ ጥያቄ ውስጥ የሚከት ሆኖ ስለተገኘ በግሪኩ ከሰፈረው ስለምልጃ ከሚናገረው ሐሣብ በመውጣትና የግእዙም ንባብ የማይለውን ክርስቶስን ይፈርዳል እንዲል ተደርጓል፡፡ ግእዙ ከሚለው ውጪ “ይፈርዳል” የተባለው አለቦታው የገባ መሆኑን የምናውቀው ቀድሞት በገባውና “ስለእኛ” በሚለው ቃል ነው፡፡ አማርኛችን ስለእኛ ካለ ይማልዳል እንጂ ይፈርዳል አይልም፡፡ ለእኛ ይፈርዳል ነው መባል ያለበት፡፡ ይፈርዳል ተብሎ የተተረጎመው ቃልም “ይትዋቀሥ” በቁሙ (መዋቀሥ) መሟገት መከራከርን እንጂ መፍረድን አያሳይም፡፡ እስካሁን ሲሰራበት በቈየው የጳውሎስ ምልእክት አንድምታ ላይም ስለእኛ ይከራከራል ነው የሚለው፡፡
በ2000 ዓ.ም ተበርዞና ለእግዚአብሔር ቃል ሳይሆን ለኦርቶዶክስ ኢመጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርት እንዲስማማ ተደርጎ የተዘጋጀውና የታተመው ሰማንያ ወአሐዱ መጽሐፍ ቅዱስም ትርጉሙን አዛብቶ ቢያቀርብም ከታች በግርጌ ማስታሻው ላይ “ግሪኩ ግን ይማልዳል ይላል” ሲል የግሪኩን ንባብ ትክክለኛ ፍቺ አቅርቧል፡፡ ታዲያ ይፈርዳል የሚለው ከየት የመጣ ነው? ከግእዙ ነው እንዳንል ግእዙ “ይከራከራል እንጂ ይፈርዳል አላለም (አንድምታውን ይመልከቱ) ግእዙን መሠረት ያደረገ የተባለው የ2000 ዓ.ም እትም 81 መጽሐፍ ቅዱስ ግእዙን ሳይሆን የሠውን ሀሳብና ፍላጎት መሰረት ያደረገ፣ የስሕተት ትምህርቶችንም በእግዚአብሔር ቃል ከማረም ይልቅ ለስህተት ትምህርቶች መጠናከር ሲባል የእግዚአብሔርን ቃል የሠዋና በብዙ መልኩ የተሳሳተ ትርጉም ነው፡፡ ትግርኛው ለግሪኩ ታማኝ በመሆን ያስቀመጠውን ወደ ስህተት እንውሰድ ከሆነ ጉዳዩ ተቀባይነት የለውም፡፡ ስለዚህ ክርስቶስን አማላጅ ያለው መጽሐፍ ቅዱስ ከሆነ ምልጃው እንዴት እንደሆነ ተረድቶ በስሙ ወደ ሰማያዊው አባት ወደ አብ መጸለይ እንጂ ይህን መሰረዝ ለሰው የተሰጠ ስልጣን አይደለም፡፡ የእግዚአብሔርን ቃል ተሳስቷል ብለን የምናርም እኛ ማነን? ክርስቶስ አማላጅ ስለተባለ የባሕርይ አምላክነቱን መካድስ እንዴት ይሆናል?
እርሱ በሰውነቱ የምልጃን ሥራ ፈጽሞ በአብ ቀኝ ተቀምጧል፡፡ የማለደው አምላክ በሰውነቱ ነው፡፡ በሰውነቱ ለዚያውም በሥጋው ወራት ያከናወነውንና ዛሬ በዚያ ምልጃው አምነው በእርሱ በኩል የሚመጡትን የሚያድነበትን አስታራቂነቱን መመስከር እንዴት የባሕርይ አምላክነቱን መካድ ሊባል ይችላል? ስለባሕርይ አምላክነቱ ሽንጣቸውን ገትረው የሚከራከሩት ሰዎች ምነው ስለ ሰውነቱ ግድየለሽ ሆኑ? መቼም የአውጣኪ ትምህርት ተከታይ ስለሆኑ በረቀቀ ስልት ሰውነቱን በአምላክነቱ አስውጠውት ወይም አስመጥጠውት ካልሆነ በቀር እርሱ ዛሬም በአብ ቀኝ አምላክ ብቻ ሳይሆን ፍጹም ሰውም ነው፡፡ ዛሬ ወደሌላ መሄድ ሳያስፈልገን፣ ወይም ሌላ ማንንም አማልደን ብለን መጥራት ሳይኖርብን በእርሱ የአድኅኖት ሥራ አምነን በስሙ ስንጸልይ አብ ይሰማናል፡፡ ይህንንም የተናገረው ሌላ ሰው ሳይሆን ራሱ ባለቤቱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ በዚያን ቀንም ከእኔ አንዳች አትለምኑም። እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ አብ በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ ይሰጣችኋል። እስከ አሁን በስሜ ምንም አልለመናችሁም፤ ደስታችሁ ፍጹም እንዲሆን ለምኑ ትቀበሉማላችሁ።” (የዮሐንስ ወንጌል 16፥23-24)፡፡ ታዲያ ከባለቤቱ በላይ ማን ሊመጣ ነው? ማህበረ ቅዱሳን ሆይ እባክህ የእግዚአብሔርን ቃል ለልማዳዊ ትምህርት ከምትሰዋ ልማዳዊ ትምህርትህን በእግዚአብሔር ቃል አስተካክል፡፡          
2.   “የቅድስት ሥላሴን አንድነትና ሦስትነት የሚያዛባ”
ለዚህ ክስ ደግሞ “ዘፍጥረት 18 አርእስቱ ላይ” የሚል ማስረጃ ነው የቀረበው፡፡ ከሳሾቹ መጽሐፍ ቅዱሱ ተሳስቷል ለማለት ሥልጣንም ሆነ ኃላፊነት ብቻ ሳይሆን ብቃቱም እንደሌላቸው አንድና ብዙን ባልለየው አጻጻፋቸው መለየት እንችላለን፡፡ ርእስ ለአንድ ሲሆን አርእስት ደግሞ ለብዙ ቁጥር ነው፡፡ ይህን ሳይጠነቅቁና ጨዋነታቸውን በሚያጋልጥ ሁኔታ “ርእሱ ላይ” ማለት የነበረባቸውን “አርእስቱ ላይ” በማለት ጽፈዋል፡፡ ትግርኛው ለዘፍጥረት 18 የሰጠው ርእስ “ኣብርሃምን ሰለስተ ኣጋይሽን” “አብርሃምና ሦስት እንግዶቹ” የሚል ነው፡፡ የ2000 ዕትሙ 81 መጽሐፍ ቅዱስ ደግሞ “እግዚአብሔር ለአብርሃም እንደ ተገለጠ” ነው እንጂ ሥላሴ ለአብርሃም ተገለጡለት አይልም፡፡ ታዲያ ርእሱ አብርሃምና ሦስት እንግዶች ቢል ስሕተቱ ምን ላይ ነው? የግድ ሥላሴ ማለት አለበት ነው? እንዲህ ለማት የሚያበቃ ምንም መሰረት በተጠቀሰው ክፍል ስለሌለ ሥላሴ ማለት አላስፈለገም፡፡    
ምስጢረ ሥላሴ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጠ ትምህርትና ተረፈ ሰባልዮሳውያንና አርዮሳውያን ካልሆኑ በቀር ክርስቲያን ተብለው የሚጠሩ ሁሉ የሚያምኑበት ትምህርት ነው፡፡ በኢኦተቤ በብዙዎች ዘንድ ለትምህርቱ ማስረጃ ተደርገው ከሚጠቀሱት ማስረጃዎች መካከል ዘፍጥረት 18 አንዱ ነው፡፡ በእዚህ ላይ ለተመሠረተው ትምህርትም በዓል ተሠርቶለት ይገኛል፡፡ ይሁን እንጂ ሌሎች መምህራን ደግሞ ይህ ምዕራፍ ለሥላሴ ትምህርት ማስረጃ ተደርጎ መቅረብ የለበትም የሚል አቋም አላቸው፡፡
ብፁዕ አቡነ መርሐ ክርስቶስ በአንድ ወቅት ስለ ምስጢረ ሥላሴ በአንድ ሰንበት ት/ቤት አዳራሽ ውስጥ ለተሰበሰቡ ወጣቶች ሲያስተምሩ ዘፍጥረት 18ን ለምስጢረ ሥላሴ ማስረጃ አድርገው መጥቀስ እንደሌለባቸው ተናግረው ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ወጣቶቹ ይህ ከተለመደው ትምህርት ወጣ ስላለባቸው ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል በሚል ጥያቄ አቅርበው ነበር፡፡ እርሳቸው ግን ለወጣቶቹ ብለው እውነቱን ሳይሸፋፍኑ ሐቁ ይህ ነው ብለው ደግመው ሲናገሩ አንድ ወጣት “እንዴ አባታችን የኔብጤዎች እንኳን ሲለምኑ እኮ ‘ስለ አብርሃሙ ስላሴ’ ነው የሚሉት? ይህ እንዴት ይሆናል?” ብሎ በደም ፍላት ሲጠይቃቸው፣ እርሳቸውም መልሰው “እሱ የለማኝ ተረት ነው እንጂ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት አይደለም፤ መቀበል ያለባችሁ ይህን ነው” ማለታቸው ይታወሳል፡፡ እንደተባለው እውነቱ ይህ ነው፡፡
ይህን መቀበል ግን ለቤተክርስቲያኒቱ የማይሞከር ነው፡፡ ምክንያቱም የሐምሌ ሥላሴ በዓል በዚህ ታሪክ ላይ ተመስርቶ እንዲከበር የተደረገ ስለሆነ ይህን መለወጥ ከባድ ስለሚሆን ነው፡፡ ይህ ግን በአተረጓጎም ስሕተት የመጣ እንጂ ዘፍጥረት 18 ለአብርሃም ሥላሴ እንደተገለጡለት ሳይሆን እግዚአብሔርና ሁለት መላእክት እንደተገለጡለት ነው የሚያስረዳው፡፡ በገጸ ንባቡ ውስጥ ሦስትነትንና አንድነትን የሚያሳዩ አገላለጾች ያሉ ቢመስልም ምዕራፉና የምዕራፉ ቀጣይ ታሪክ በምዕራፍ 19 ላይ ሲቀጥል “ሰዎቹም ከዚያ ተነሥተው ወደ ሰዶም አቀኑ፤ አብርሃምም ሊሸኛቸው አብሮአቸው ሄደ።” (ዘፍጥረት 18፥16) በሚለውና “ሁለቱም መላእክት በመሸ ጊዜ ወደ ሰዶም ገቡ፤” (ዘፍጥረት 19፥1) በሚለው ላይ ግልጽ ሆኗል፡፡
አንዳንድ የቤተ ክርሰእቲያን መጻሕፍትም የዘፍጥረትን ታሪክ ከሥላሴ ጋር ሳይሆን ከእግዚአብሔርና ከሁለቱ መላእክት ጋር አገናኝተው ነው የሚናገሩት፡፡ ለምሳሌ በመጽሐፈ ቅዳሴ አንድምታ ትርጓሜ ላይ “ኦ ዘአፍቀርከ ትሕትናሁ ለእጓለ እመ ሕያው እም ዕበዮሙ ለመላእክት። ኦ ዘአፍቀርከ ንዴተ ዚኣሁ ለአዳም እመዛግብቲሆሙ ለነገደ አብርሃም።” ትርጉም፡- “ከመላእክት ታላቅነት ይልቅ የሰውን ልጅ ትሕትና የወደድክ፥ ከነገደ አብርሃም መዝገቦች ይልቅ የአዳምን ንዴት የወደድክ …” የሚለውን ባብራሩበት ክፍል ውስጥ ሊቃውንቱ አብርሃም በእንግድነት የተቀበለው መላእክትን መኾኑን ጠቍመዋል፤ እንዲህ በማለት፡ “ከመላእክት ባሕርይ ይልቅ የአዳምን ሥጋ ለመወሐድ የመረጽህ፥ አብርሃም እንግድነት ከተቀበላቸው ከመላእክት ከባሕርያቸው ይልቅ የአዳምን ባሕርይ የወደድህ” (መጽሐፈ ቅዳሴ ንባቡና ትርጓሜው ገጽ 376)። መቼም ከዚህ ክፍል በቀር አብርሃም መላእክትን እንግድነት የተቀበለበት ሌላ ታሪክ በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ውስጥ የለም፡፡ ስለዚህ ይህ ታሪክ የሚጠቁመው አብርሃም በእንግድነት የተቀበለው እግዚአብሔርንና ሁለት መላእክትን ነው ከማለት ማምለጥ አይቻለም፡፡
ድርሳነ ሚካኤል ላይም ለአብርሃም የተገለጹት መላእክት መሆናቸው ተጠቅሷል፡፡ “ዳግመኛም መላእክት ወደ አብርሃም ዘንድ መጥተው ይስሀቅ እንዲወለድ ነገሩት” (የሚያዝያ ድርሳነ ሚካኤል ቁጥር 11)፡፡ ምንም እንኳን የይስሀቅን መወለድ ለአብርሃም የነገረው ራሱ እግዚአብሔር ቢሆንም (ዘፍጥረት 18፥10) በእንግድነት የተገኙት መላእክት ጭምር መሆናቸው በድርሳነሚካኤል እንደተገለጸ መረዳት ይቻላል፡፡
ለዘፍጥረት 18 የተሰጠው ይህ ትርጓሜ መጽሐፍ ቅዱስን በትክክል ባነበቡና በተረዱ የቤተ ክርስቲያን ሰዎች ዘንድ ቀደም ብሎም እንደነበረ፣ አፄ ዘርዓ ያዕቆብ ለደቂቀ እስጢፋኖስ ስለዚህ ክፍል ጠይቆ ካገኘው መልስ እንረዳለን፡፡ የንጉሱ ጥያቄ “በአብርሃም ቤት የተስተናገዱት ሰዎች እነማናቸው ትላላችሁ” የሚል ነበር፡፡ ደቂቀ እስጢፋኖስ የሰጡት መልስ “መጽሐፉ ሦስት ሰዎች ይላል” የሚል ነበር፡፡ (ደቂቀ እስጢፋኖስ በሕግ አምላክ ገጽ 128)፡፡    
እዚህ ላይ መዘንጋት የሌለበት እየተባለ ያለው ዘፍጥረት 18 ስለ ሥላሴ አይናገርም ነው እንጂ ትምህርተ ሥላሴ መጽሐፍ ቅዱሳዊና ከዚህ ውጪ ባሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች እውነተኛነቱ የሚታመን ትምህርት መሆኑ ነው፡፡ ሰው ትምህርቱን ከተቀበለና በሥላሴ አንድነትና ሦስትነት የሚያምን ከሆነ ዘፍጥረት 18 ስለ ሥላሴ አይናገርም ስላለ ሊተች አይገባውም፡፡ የትግርኛው መጽሐፍ ቅዱስም ለዚህ ክፍል የሰጠው ርእስ ዕብራይስጡን መሠረት አድርጎ “ኣብርሃምን ሰለስተ ኣጋይሽን” ማለትም “አብርሃምና ሦስት እንግዶች” ነው፡፡ ለዕብራይስጡ ወይም ለእግዚአብሔር ቃል ሳይሆን ለልማዳዊው ትምህርት የወገነው የ2000 ዓ.ም መጽሐፍ ቅዱስም እንኳን ለዚህ ክፍል የሠጠው ርእስ “እግዚአብሔር ለአብርሃም ተገለጠለት” የሚል እንደሆነ ከላይ ተመልክተናል፡፡
3.     “ሥልጣን ክህነትን የሚሽርና የማይቀበል”
ለዚህ ውንጀላ የተጠቀሰው ያዕቆብ 5፥14 ነው፡፡ በዚህ ቁጥር ላይ ግሪኩ “ሽማግሌዎች” ሲል ግእዙ ደግሞ “ቀሳውስት” ይላል፡፡ ትግርኛው የተተረጎመው ግሪኩን መሠረት አድርጎ በመሆኑ “ሽማግሌዎች” ሲል በግርጌ ማስታወሻው ላይ ግን ግእዙ “ቀሳውስት” ይላል የሚለውን አስፍሯል፡፡ የ2000 ዓ.ም 81 መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ጥቅስ አዟዙሮ ነበር ያቀረበው፡፡ ምክንያቱም እርሱ ግእዙን መሰረት አድርጎ ነውና ተተረጎመ የተባለው፡፡  ሰዎቹ አላዋቂዎች ስለሆኑ እንጂ ግሪኩን መሰረት አድርጎ መተርጎም ሥልጣነ ክህነትን መሻርና አለመቀበል ተብሎ መቅረብ አልነበረበትም፡፡
“ክህነትን የሚሽርና የማይቀበል” የሚለው በሌላ በኩል ከቤተ ክርስቲያኒቱ የሚመነጭ እንጂ ከመጽሐፍ ቅዱስ የሚጠበቅ ትምህርት ሊሆን አይገባም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቶስ የአዲስ ኪዳን ሊቀ ካህናት፣ በእርሱ ያመንን ሁላችን ደግሞ የንጉሥ ካህናት መሆናችንን ይናገራል፡፡ በክርስቶስ ካህናት ከተደረጉት መካከል ደግሞ ቤተ ክርስቲያንን ለመምራትና ለማስተዳደር የተሾሙ አገልጋዮች ከጳጳሳት ጀምሮ አሉ፡፡ ከዚህ ውጪ መጽሐፍ ቅዱስ እንደ ኦሪት ስርዓት ካህናት ብሎ በተለየ መንገድ የሚቆጥራቸው ካህናት ግን የሉም፡፡ ይህን እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ያልሆነውን የካህናት ጉዳይ መጽሐፍ ቅዱስ ያጽድቅልን ከሆነ እርሱ ሌላ ጉዳይ ነው፡፡ ይህን መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት የሌለውን ትምህርትና ልምምድ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ለማድረግ ሲባል መጽሐፍ ቅዱሱ ይቀየርልን እስከሚለው ጥግ ድረስ ከመሄድ የቤተ ክርስቲያኒቱን ትምህርትና ሥርዓት በመጽሐፍ ቅዱስ ማረሙ የተሻለና ትክክለኛም አካሄድ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አስተምህሮ የተመሠረተበት የክርስትና ትምህርት ምንጭ ነው እንጂ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ትምህርት ተብሎ ለእርስዋ በሚስማማ መልኩ ሊዘጋጅ የሚችል የአንድ ቤተ እምነት መጽሐፍ አይደለም፡፡
4.   “ተዋሕዶ ቤተክርስቲያናችን ለበርካታ ሺዎች ዓመታት ትጠቀምበት የነበረው ፊደል ቁጥር አቆጣጠርም ተሰርዞዋል”
ይህ ክስ የራስን ሥራ በሚገባ ሳይሰሩ ሌላው አካል እንዲሰራ ከመጠበቅ የመጣ ነው፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስ ማህበር በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግስት ያሳተመው የ1954 ዓ.ም መጽሐፍ ቅዱስ የግእዙን ቁጥር ተጠቅሟል፡፡ ከጊዜ በኋላ የግእዝ ቁጥርን መጠቀም እያሽቆለቆለ መጥቷል፡፡ ለዚህ ደግሞ ተጠያቂዋም ሃላፊነቱን መውሰድ ያለባትም ራስዋ ቤተ ክርስቲያኒቷ ናት እንጂ ሌላ ማንም ሊሆን አይገባም፡፡ ትውልዱን እንደጊዜውና እንደ ዘመኑ ሁኔታ በተገቢው መንገድ ለማስተማርና የግእዙን ቁጥር እንዲጠቀምበት ለማድረግ አልታገለችም፡፡ የዘመናዊው ትምህርት አብዮት ሲፈነዳ ራሷን ከወቅቱ ሁኔታ ጋር ማሰለፍ ሲገባት ባለችበት ስትረግጥ ትውልዱ አመለጣት፡፡ ስለዚህ ዛሬ ለዚህ ትውልድ የግእዙ ቁጥር ከባድ ቅኔ ሆኖበታል፡፡ ይህን ቁጥር ስላልተማረም ወደአረብኛው ቁጥር ማዘንበሉ አልቀረም፡፡
ምንም እንኳን የግእዙን ቁጥር ሁሉም እንዲጠቀምበት ማበረታታት የሚደገፍ ቢሆንም ብዙ ጊዜ ከወሬና ከትችት ያለፈ ሥራ ሲሠራ አልታየም፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስ ማህበር በዚህ በትግርኛው እትም መጽሐፍ ቅዱስ የግእዙን ቁጥር መጠቀም ያልፈለገው ለምን ይሆን? ቢባል የራሱ የሆኑ በቂ ምክንያቶች እንዳሉት መገመት አይከብድም፡፡ ያንን ከግምት ማስገባትና ምክንያቱን ማወቅ ተገቢነት ይኖረዋል፡፡ የግእዙ ቁጥር አለመግባቱ ግን በራሱ ያን ያህል ሃይማኖት የፈረሰ ያህል የሚያስጮህ አልነበረም፡፡
ከዚሁ ጋር ተያይዞ የፊደልም ጉዳይ ተነስቷል፡፡ በፊደል አጠቃቀም ላይ ትግርኛ የራሱን መንገድ የተከተለ ቋንቋ በመሆኑ መተቸት የተፈለገው ያንን ከሆነ አያስኬድም፡፡ ፊደሉ ትግርኛውን ተከትሎ የተዘጋጀ ከሆነ መቃወም አግባብነት አይኖረውም፡፡ ምክንያቱም የተዘጋጀው ለትግርኛ ተናጋሪዎች ስለሆነ የቋንቋውን የፊደል ሥርዓት ተከትሎ ነው መዘጋጀት ያለበት፡፡ ለነገሩ 40ው አፅራረ መጽሐፍ ቅዱስ የተፈራረሙበትን አቤቱታቸውን እንኳን የጻፉት የትግርኛውን የፊደል አጻጻፍ የግእዙን የአጻጻፍ መንገድ መቼ ተከትለው ጻፉ? ይህ ጉዳይ እንዲህ “ያዙኝ ልቀቁኝ” ያሰኛቸው በተሐድሶ አይቀሬነት ካለማመናቸውና ተሐድሶን ካለመቀበላቸው የተነሳ ነው፡፡ ዘመን ይለወጣል ነገሮች እየታደሱ ይሄዳሉ፡፡ ባለበት የሚቀር ማንም የለም፡፡ እነርሱ ባይፈልጉትም እንኳን ተሐድሶ አይቀርም፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ግን ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል፡፡ 
5.   “ቀዳሚትዋ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ለሺዎች ዓመታት ትመራበት የነበረው የራስዋ የሆነ 81 መፅሓፍት ቅዱስ ጽሀፍ ቅዱስወደ ጎን በመተው 66 መጻሕፍት ብቻ ተተርጉሞ መታተሙ እንቃወማለን”
ከ81 መጻሕፍት ጋር ተያይዞ የተነሣው ይህ ነጥብ አካሄዱን ያልተከተለ ነው፡፡ 81 የተባለው መጽሐፍ ቅዱስ ኦርቶዶክስ የእኔ ነው የምትለው መጽሐፍ ቅዱሷ ነው እንጂ የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር የግዴታ ሊያሳትመው የሚገባ አይደለም፡፡ እርሱን ማሳተም ያለባት ራሷ ቤተ ክርስቲያኗ ናት፡፡ አቆጣጠር ላይ 81 ናቸው መባሉና  በውስጡ የያዛቸው መጻሕፍት ካሰፈሩት አንዳንድ የተሳሳተ ነገር አንጻር መጻሕፍቱ እንደ ቅዱሳት መጻሕፍት ይታዩ የሚለው ሐሣብ ግን ገና ያልተፈታ ብዙ ውዝግብ ያለበት ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ቤተክርስቲያኗ በ2000 ዓ.ም. ያሳተመችው መጽሐፍ ቅዱስ በብዙ ሕጸጾች የተሞላ፣ ከዚያ በፊት ለነበረው የቤተ ክርስቲያኒቱ አስተምህሮ እንኳን ታማኝ ያልሆነና አሁን በቅርቡ እየሰለጠነ ለመጣው የስሕተት ትምህርት ዕውቅና ለመስጠት ሲባል ሆን ተብሎ የተዘጋጀ በመሆኑ ብዙ ተቀባይነት እንዳላገኘ ይታወቃል፡፡ ያ በትግርኛውም ይደገም ከሆነ ነገሩ ብዙ ተቀባይነት አያገኝም፡፡
ትግርኛ ቋንቋ የሕዝቡ እንጂ የቤተ ክርስቲያኒቱ አይደለም፡፡ ሕዝቡ ደግሞ በቋንቋው መጽሐፍ ቅዱስን የማግኘት መብቱ ሊጠበቅለት ይገባል፡፡ በአንድ በኩል የትግርኛውን የፊደል አጠቃቀም ተከትሎ የተዘጋጀውን መጽሐፍ ቅዱስ ከፊደል አጠቃቀሙ አንጻር መቃወም፣ በሌላ በኩል ደግሞ ለአንድ ቤተ እምነት ሳይሆን ለሁሉም ቤተ እምነቶች በጋራ የቆመውንና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንን ጨምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሁሉም አብያተ ክርስቲያናት የተቀበሏቸውን (ኢኦተቤ በ66ቱ ላይ ጨመረች እንጂ ከ66ቱ አልቀበልም ያለችው የለም) 66ቱን መጻሕፍት የሚያሳትመውን የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማህበርን የእኛን 81 ካላሳተመ ብሎ ዘራፍ ማለት ተገቢ አይደለም፤ መብትም አይደለም፡፡      

15 comments:

 1. ለነገሩ 40ው አፅራረ መጽሐፍ ቅዱስ የተፈራረሙበትን አቤቱታቸውን እንኳን የጻፉት የትግርኛውን የፊደል አጻጻፍ የግእዙን የአጻጻፍ መንገድ መቼ ተከትለው ጻፉ?
  Waw what a nice comment

  ReplyDelete
 2. Mk behulem neger tilik libel eyale lerasu gera eyetegaba new.

  ReplyDelete
 3. ይህ ሁሉ እንቶ ፈንቶ ፅሁፍ ምንድን ነው?
  ተሃድሶ ጋር ኑሮ ከእንግዲህ በኋላ አበቃ
  ተንጫጫ እንግዲህ ምድረ ግሩሳ

  ReplyDelete
  Replies
  1. መስሎሽ ነው ቆማጢት። አለ ያገሬ ሰው

   Delete
  2. It is the time of " memnter & masmenter"

   Delete
 4. ተሃድሶ ጋር ኑሮ ከእንግዲህ በኋላ አበቃ

  ReplyDelete
 5. ማህበረ ቅዱሳን ቢሆንስ ምን ይጠበስ፡፡እዉነትም ጊሪሳ ሁላ

  ReplyDelete
 6. It is - The time of "memnter & masementer" _ tewahedo lezelalm tnur!!

  ReplyDelete
 7. ሁላችሁ የማቅ ሴራ አላገኛችሁትም፤ ልፋት ብቻ ሆነ ሥራችሁ!
  ጉዳዩ እንዲህ ነው:-
  የሰሜን ህዝብ ቃለ እግዚአብሔር በአፍ መፍቻ ቋንቋው ሰምቶ እንዳያውቅ በማያውቀው ግእዝ ተብትበው በመስበክ ለአስራት በኩራት ብቻ ባርያ ሆኖ ለዘመናት እየኖረ እንዲመጣ ያደረጉ የጅል- ጥንቶቹ ሰርተዋል። አሁንም የነዚህ አሰር የሚከተል ማቅ የትግራይ ገበሬዎችና ነጋዴዎች ቅዱስ መጽሐፍ በሚያውቁት ቋንቋ ከተነገራቸው ሚስጢሩን ተረድተው እኛ የምንከተለው ቤተ ክርስቲያን እንጂ ማህበር አይደለምና ወግድ! እንዳይባል ነው እየተቁነጠነጠ ያለው፤
  ማቅ??? መስሎህ ነው እንጂ ጉድህን እንደ ቀይሥር ተነቅቶብሃል፤

  ReplyDelete
  Replies
  1. please could you mention some of the Tigrian farmers who offer money to MK. I am sure you will never mention even one, get out of this with your idiot politics.

   Delete
  2. ስማ አፍህን እንደለመደብህ የዕለት ጉርስህን ለመጉረስ ብትከፍተው ነው የሚሻለው ምክንያቱም አፍህ ሲከፈት ስለምግብ ብቻ የሚያስበው ባዶ ጭንቅላትህ ይታያል፡፡ አንተም እዚህ ብሎግ ላይ የሚጽፉትም ስለሆድ ከማሰብ የዘለላችሁ አይደላችሁም ከእውቀት የተጣላችሁ እንደሆናችሁ ጽሑፋችሁ ይናገራል፡፡ ሃገር ከምታሰለቹ ለምን ሥራ አትሰሩም?

   Delete
 8. kikiki haratka tehadiso akerkariw eyetemta new. kewedeku behual menferaget lemelalat wef yelem ale Zemedie

  ReplyDelete
 9. KOMOSE Aba,Haile who have replaced Abazelebanose creating false statment and defamation and misrepersentation of fact regarding to Aba,zelebanose. ABAZELEBANOSE IS A true father of all that reside in Atlanta.Incontrast, those gang none ethical fake priest trying to damage good image of our truthouse father of Abazelebanose. This is an intent to induce another to rely on the misrepersentation. In Atlanta, severals fake Eotc priest they have made fraudlant marriage to gain immigration status. In some circumstances thay have violated finacial crime theft money from the church including to no paying taxes.

  ReplyDelete
 10. You are correct. The managmet of church why is not monitoring such kind of rubish ethical standards. The divorecee fake priest also actively serving Church currently having black girl friend her name is Shineka.

  ReplyDelete