Thursday, May 18, 2017

“ሲኖዶሱ” በግብጽ ቤተ ክርስቲያን ላይ ያቀረበው ትችት “ልጅ ለእናቷ ምጥ አስተማረች” አያሰኝምን?የሰሞኑ የሲኖዶስ ስብሰባ ከተወያየባቸውና ውሳኔ ሰጠባቸው ከተባሉ ጉዳዮች መካከል ከግብጽ ቤተ ክርስቲያን ጋር ያለውን ግንኙነት የተመለከተው አንዱ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱ እናቴ ስትላት ከቆየችው ከግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ጋር ያላትን የዶግማና የቀኖና አንድነትና ልዩነት ለመመርመርና ከአንድ ውሳኔ ላይ ለመድረስ የተነሳችው ግን የሮማው ካቶሊክ ፖፕ ፍራንሲስ በቅርቡ ግብጽን በጎበኙበት ወቅት ከግብጹ ፓትርያርክ ጋር በተለይ ምስጢረ ጥምቀትን በተመለከተ ስምምነት ማድረጋቸውን ተከትሎ መሆኑ፣ ነገሩን የሌላ አስመስሎታል፡፡ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ እንዲወጣ በተደረገው ዜና ላይ እንደ ተመለከተውም ምንጮች (ማኅበረ ቅዱሳን እንደ ሆነ አያጠራጥርም) “የግብጽ ቤተ ክርስቲያን አካሄድ የነገረ መለኮትና የምስጢራተ ቤተ ክርስቲያን አንድነት ባላቸውና ኦሬንታል  ተብለው በሚታወቁት የኢትዮጵያ የሶርያ፣ የአርመንና የሕንድ እኅትማማቾች አብያተ ክርስቲያናት (የኤርትራ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አልተጠቀሰችም) ቅዱስ ሲኖዶሶች ያልተመከረበት እንደሆነ አስረድተዋል፡፡” ይላል፡፡  
በመሠረቱ እነዚህ አኅትማማች አብያተ ክርስቲያናት በጋራ ያላቸው የአስተምህሮና የሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን አንድነት እንደ ተጠበቀ ሆኖ በተናጠል ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ጋር ግንኙነት ሲያደርጉና ስምምነት ሲፈራረሙ በሁሉም ሲኖዶሶች መመከር አለበት የሚል ሕግ ወይም የጋራ ስምምነት ያለ አይመስልም፡፡ የጋራ ነገር ቢኖራቸውም በየራሳቸው የሚያምኑበትና የሚኖሩበት ትምህርትና ሥርዓት እንዳላቸውም አይካድም፡፡ ለምሳሌ በጥንተ አብሶ ትምህርት ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታምን የነበረው እንደ ግብጽ ቤተ ክርስቲያንና እንደ ሌሎቹም ኦሬንታል አብያተ ክርስቲያናት እንደ ነበረ ቀደም ያሉ ሊቃውንት በየጽሑፎቻቸው ያሰፈሩበት ሁኔታ አለ፡፡ ለምሳሌ ያህል የቀሲስ አስተርአየ ጽጌን ጥናት መቃኘቱ እንኳ በቂ ነው፡፡ በሊቁ የተደረጉት ጥናቶችና ከግብጽ ቤተ ክርስቲያን ጳጳሳት ጋር የተደረጉት የሐሳብ ልውውጦችና በደብዳቤም የተገለጸው ማርያም ጥንተ አብሶ ነበረባት የሚለው ትምህርት የኦርቶዶክስ ትምህርት መሆኑን ነው፡፡ ይሁን እንጂ አንዳንዶች በዚህ ትምህርት ከኦርቶዶክሳውያን ይልቅ ከካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ጋር ስምምነት ባይፈራረሙም፣ የካቶሊክን እምነት ቤተ ክርስቲያኗ እንድትከተል በማድረግ ማርያም ጥንተ አብሶ ነበረባት የሚለውን ኦርቶዶክሳዊ ትምህርት ጥንተ አብሶ የለባትም በሚለው ካቶሊካዊ ትምህርት ለውጠዋል፡፡ በዚህ ጊዜ የግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ምነው እኔና ሌሎቹ ኦርቶዶክሶች ሳንመክርበት በሚል ተቃውሞ አላነሣችም፡፡ በትክክል ከታየ ደግሞ በአስተምህሮ ረገድ ከኦርቶዶክሳዊ ትምህርት እየራቀች የሄደችው ግብጽ ሳትሆን ኢትዮጵያ ናት፡፡ ስለዚህ አስቀድሞ ራስን መመርመሩ የተሻለ ነው፡፡
  ታዲያ ካቶሊክና የግብጽ ኦርቶዶክስ በጥምቀት ረገድ አንዱ ያጠመቀውን ሌላው እንዳይደግም  ከስምምነት ላይ መድረሳቸው ለምን ሲኖዶሱን አሳሰበውና አጀንዳ ይዞ እንዲነጋገር አደረገው? አጀንዳውስ የማነው? ያን ያህልስ አንገብጋቢ ነወይ? አጀንዳውስ በዚህ ወቅትና በዚህ ሁኔታ መቅረቡ ተገቢነት አለው ወይ? ጥምቀት ሰው በክርስቶስ አዳኝነት አምኖ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም የሚጠመቀው እንጂ ለቤተ ክርስቲያን መለያየት ምክንያት በሆነው የተከፋፈለችው ቤተ ክርስቲያን አካላት በሚያራምዱት አስተምህሮ መሠረት የሚፈጸም አይደለም፡፡ በሁሉም ዘንድ ጥምቀት በኢየሱስ ክርስቶስ አዳኝነት አምኖ፣ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም በውሃ መከናወኑና ከክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ጋር መተባበርን መግለጫ መሆኑ ይታመናልና ሌሎች ልዩነቶች ቢኖሩም እንኳ፣ ያ ሰዎች የፈጠሩት እንጂ የእግዚአብሔር ትእዛዝ ባለመሆኑ እንዴት ጥያቄ ሊነሣበት ይችላል? የሚለው ሊያወያይ ይገባል፡፡ ከሁሉም የሚገርመው ሐራ “የእነ ቅዱስ አትናቴዎስንና የእነ ቅዱስ ዲዮስቆሮስን ውግዘት ወዴት አድርገውት ነው?” በማለት የጥንቱ ውግዘት ማተኮሯ ነው፡፡ ይህም  ውግዘትን ለኦርቶዶክስ “መስፋፋት” እንደ አንዱ ስልት አድርጎ እየተጠቀመበት ያለው የማቅ አቋም እንደሆነ ይታወቃል፡፡  
የአትናቴዎስን ትምህርቱን የማይከተሉትና ውግዘቱን ማስታወስ የቀናቸው እነሐራ ውግዘቱን ያሰቡት በኢትዮጵያዊ ልባቸው ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ የቅዱሳት መጻሕፍትን ቁጥር ብሉይ ኪዳኑን ከአይሁድ እንደ ሰማሁት ነው ሐዲስ ኪዳን ላይ ግን 27 ነው ብሎ ቀንኖ የሠጠውን አባት ትምህርት ሳይከተሉና ከሰሞኑ እየሰማን እንዳለው አዋልድን ሁሉ ቅዱሳት መጻሕፍት እያሉ የሚቆጥሩበት ሁኔታ ባለበት ሁኔታ ከትምህርቱ በተቃራኒ እየሄዱ ስለ እርሱ ውግዘት ማንሣታቸው ተገቢነት ያለው አይደለም፡፡ ደግሞም ውግዘት ሊነሣ የሚችልበት ዕድል መኖሩን ያስተዋሉ አይመስሉም፡፡ ለአትናቴዎስና ለዲዮስቆሮስ ከግብጻውያን ይልቅ ማን ይቀርባል? በዚህ ውስጥ የግብጹ ፓትርያርክ ከካቶሊኩ ፖፕ ጋር ሲፈራረሙ ግብጻውያን ምንም ተቃውሞ አላነሡም፡፡ ምክንያቱም ዘመኑ ተለውጣል፤ በዚያ ትልቅ መንፈሳዊ ተሐድሶ አለ፡፡ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ባለፈው አዲግራትን በጎበኙ ጊዜ ግን እዚያ ከሚገኙት የካቶሊክ መሪ ጋር ተነጋግረው “ብዙ ልዩነት እኮ የለንም? በብዙ ነገር አንድ ነን” ማለታቸውን ተከትሎ ሐራ ወሬ የምትመግበው ሌላው የማቅ ልሳን አዲስ አድማስ ዜናውን አካብዶ እንዲዘግበው ተደርጎ እርሳቸው ላይ ሃይማኖት ለወጡ በሚል ጦርነት የማስነሣት ያህል ሙከራ ተደርጎ ነበር፡፡ ምክንያቱም ይህን ያሉት ኢትዮጵያ ውስጥ ስለሆነ ነው፡፡ ግብጻውያን ግን በዚህ ላይ ተቃውሞ አላነሡም፡፡ በዚህ ሁኔታ ላይ ከግብጽ ጋር በሃይማኖት ጉዳይ ጠብ ውስጥ መግባት አስፈላጊነቱ አይታይም፡፡ ለእግዚአብሔር ክብር ሳይሆን በራስ ክፉ ልማድ በመያዝ የሚደረግ ነውና መለየት የሚወድድ ምኞቱን ይከተላል፥ መልካሙንም ጥበብ ሁሉ ይቃወማል።” (መጽሐፈ ምሳሌ 18፡1) የሚለው የመጽሐፍ ቃል እንዳይፈጸምብን መጠንቀቁ መልካም ነው፡፡         
በአቡነ ጳውሎስ ዘመነ ፕትርክና ግብጽ ግብጽ ሲል የኖረው ማኅበረ ቅዱሳን አሁን ከዚህ ሐሳቡ የተንሸራተተው ለምን ይሆን? አዲስ አድማስ ቆጠብ ብሎ ይዘግበው እንጂ የእርሱ መጋቢ የሆነችው ሐራ የግብጽን ቤተ ክርስቲያን በዚህ ብቻ ሳይሆን በአንዳንድ የዜማ ዕቃዎቿ ከፕሮቴስታንቱ ጋር መሳሳሰል እያሳየች ነው ሲል ጽፏል፡፡ አርጋኖን (ኦርጋን) በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሲሰራበት የቆየ ቢሆንም ማቅ ባደረገው ከፍተኛ ትግል ቤተ ክርስቲያኒቱ እንዳትገለገልበት ተደርጓል፡፡ ቀደም ሲል በኦርጋን የተዘመሩ መዝሙሮች በባህላዊ የዜማ ዕቃዎች እንዲዘመሩ ግዴታ ተጥሏል፡፡ ይህ በራሱ ችግር ባይኖረውም እንደ ሃይማኖት መታየቱና የወጣቱን ትውልድ ፍላጎት ማእከል ያላደረገና ዘመኑን ያልዋጀ ለብዙዎች ወደሌሎች አብያተ ክርስቲያናት መፍለስ አንዱ ምክንያት መሆኑ ግን ከቶ አይዘነጋም፡፡ የግብጽ ቤተ ክርስቲያን መሠረታዊው አስተምህሮ ባሻገር የራሷ የሆነ ባህልና ሥርዓት አላትና በዚህ መመሳሰል አለብን ማለት ወይም የዜማ ዕቃዎቿን ክራርና መሰንቆ ማድረግ አለባት ማለት የጤነኛነት አይደለም፡፡ የፍጥረት ሁሉ አባት የሆነውንና በግብረ ሐዋርያት እንደ ተጻፈው የሰውን ወገኖች ሁሉ ከአንድ ፈጠረ፥ የተወሰኑትንም ዘመኖችና ለሚኖሩበት ስፍራ ዳርቻ መደበላቸው።” (የሐዋርያት ሥራ 17፡26-27) ተብሎ የተጻፈለትን እግዚአብሔርን ኢትዮጵያዊ ለማድረግ መሞከር ነው፡፡
ይህ ጠባብ አእምሮ ካለውና በአብያተ ክርስቲያናት መካከል ያሉ ልዩነቶች እየጠበቡ እንዲመጡና በጥንት የቤተ ክርስቲያን ጉባኤያት በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረትነት የተወሰነው የቤተ ክርስቲያን አንድነት (ወነአምን በአሐቲ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እንተ ላዕለ ኵሉ ጉባኤ ዘሐዋርያት) እውን እንዲሆን ከማይሻው ማኅበረ ቅዱሳን የሚመነጭ እንጂ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተሳሰብ አይደለም፡፡ (ማኅበሩ ለ5ኛ ዙር ዐውደ ርእዩ ያዘጋጀው ልዩ መጽሔት ላይ ስለቤተ ክርስቲያን በሰጠው ፍቺ ውስጥ ስለ አንድነቷ ሲገልጽ አምስቱን ኦሬንታል ብቻ መቁጠሩና ሌሎችን ከአንዲት ቤተ ክርስቲያን ክፍልነት ውጪ ማድረጉ፣ እርሱ በልኩ የሰፋው የራሱ ክፉ ጥፉ ትምህርት እንጂ መጽሐፍ ቅዱሳዊም የኦርቶዶክስም ትምህርት አይደለም፡፡ ይህን በተመለከተ የዐውደ ርእዩን መጽሔት ዝርዝር ወደፊት እናቀርባለን)፡፡ ከማኅበረ ቅዱሳን ይልቅ እርሱ አጀንዳውን የሚጭንበት ሲኖዶስ ማኅበሩ በልኩ እየሰፋ የሚያቀርብለትን ሁሉ አሜን ብሎ በመቀበልና የስብሰባው አጀንዳ በማድረግ ራሱን በዓለም ፊት ትልቅ ትዝብት ላይ እንዳይጥል ያሰጋል፡፡
ሲኖዶሱ የአስተምህሮ አንድነት እንደ ተጠበቀ ሆኖ በሌሎች ጉዳዮችም አንድነትን ብቻ ሳይሆን ልዩነትንም አክብሮ መጓዝ እንጂ ያንን ለመጨፍለቅ መሞከር ሊሆን የማይችል ነውና በጉዳዩ ላይ ሊያስብበት ይገባል፡፡ ግብጾችና ሌሎቹም ኦሬንታል አብያተ ክርስቲያናት ብቻ ሳይሆኑ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም ከሌሎቹ የምትለይባቸው ዶግማዎችና ቀኖናዎች እንደተፈጠሩ መካድ አይቻልም፡፡ ለምሳሌ በአዲስ ኪዳን ታቦትን ተሸክሞ የንግስ በዓል በማድረግ ታቦት እንዲመለክ ማድረግ በሌሎቹ ዘንድ የሌለ የእርሷ ብቻ ሥርዓት ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያኗ ይህን ከየት አመጣችው? ታዲያ ራስን ሳያርሙ ሌላውን ተስተካከል ለማለት የሞራል ብቃት ይኖራል ወይ? በግብጾች የደረሰብን ሃይማኖታዊ ተጽዕኖ ቀላል ባይሆንም ታሪካችን ሲመረመር ተመሥርተንበታል ከምንለው ኦርቶዶክሳዊ ትምህርት ምን ያህል ርቀን እንደሄድንና በብዙ አይሁዳዊና አሕዛባዊ ትምህርቶችና ልማዶች እንደተወረስን አለመገንዘቡ፣ እዚህ ላይ ቆሞም ግብጽን ላርምሽ ማለት ለእናቷ ምጥ አስተማረች እንደ ተባለችው ልጅ መሆን ነው፡፡
የግብጽ ከካቶሊክ ጋር ስምምነት መፈራረሟ ለተሐድሶ የተከፈተ በር ያላት መሆኗን ነው የሚያሳየው፡፡ በበርካታ ሚዲያዎቿ ላይ እንደምናየው ቤተክርስቲያኒቱ በተሻለ ደረጃ ላይ የምትገኝ ናት፡፡ ለሁሉም ትውልድ የሚሆንና የሚመጥን ነገር እያቀረበች ትውልዱን መያዝ ችላለች፡፡ በአስተምህሮም ጥራት ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በተሻለ ይዞታ ላይ ነው ያለችው፡፡ ስለዚህ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ከእርሷ ብዙ መማር እንጂ እርሷን ተሳስተሻል ማለት አያስኬድም፡፡
ከምስጢራተ ቤተ ክርስቲያን ጋር በተያያዘም የሥጋ ወደሙን አቀራረብ በስውር እንጂ በግልጽ መሆን የለበትም በሚል፣ ግብጾች በግልጽ አደረጉት የሚለው ክስም የራስን አጉል ልማድ ላለመተው የሚደረግ እንጂ ምንም ችግር የሌለው ነው፡፡ ጌታ ህብስቱንና ወይኑን አመስግኖ እንካችሁ ብሉ ጠጡ ብሎ ለደቀመዛሙርቱ ሲሰጣቸው አልሸፋፈነውም፡፡ ታዲያ መሸፋፈኑን ምን አመጣው? ሌላ ነገር አስመስሎ ከመሸፋፈንና ሰዎች ስጋ ወደሙን እንዲሸሹት ከማድረግ በግልጽ አድርጎ የክርስቶስን የሞቱንና የትንሣኤውን መታሰቢያ እንዲያደርጉበት በቃልም በተግባርም ለማስተማር እንደ ግብጾች በግልጽ ማድረጉ የጌታን ምሳሌ መከተል ነው፡፡ ሸፋፍኖ ማቅረቡ ግን ሕዝቡ ሥጋ ወደሙን ባልተጻፈ በሌላ መንገድ እንዲመለከተው የሚያደርግ ነው፡፡ ተረፈ መሥዋዕቱን ካህናት ብቻ የሚበሉበት ልማድም ከኦሪት የተቀዳ እንጂ የሐዲስ ኪዳን አይደለም፡፡ በዚህ ሁሉ ራስን መፈተሽ እንጂ የግብጽን አስተምህሮ ለመፈተሽ አቅሙም አይፈቅድም፡፡ ስለዚህ በማቅ አጀንዳዎች ሲኖዶሱ ራሱን ለምን እንደሚወጥር ሊመረምር ይገባል፡፡ በቀጣይ በአዋልድ መጻሕፍት ላይ ስለተወሰነው ውሳኔ ሐተታ እናቀርባለን፡፡

7 comments:

 1. አስብሏል እንጂ አስብሏል

  ReplyDelete
 2. Protestantism speaking loud! Whenever you write, I understand how Mahbere Kidusan is right.

  ReplyDelete
 3. ENANTE ENEMAN NACHIHU????????????????????

  ReplyDelete
 4. ታድያ ግብጽ እንዳትሄዱ ምን ከለከላችሁ? እዚህ ከምታምሱ ብትሄዱ ይሻላል፡፡ እንደተማረና እንደመረመረ ሰው የአትናትዮስን የነዲዮስቆሮስን ስም ማንሳታችሁ የሚያሳዝን ነው፡፡ ደግሞ የአትናትዮስን የነዲዮስቆሮስን እንዲሁም የሌሎቹን አባቶች ትምህርት ለመመርመር ግብጻዊ ወይም ሌላ መሆን ትምህርቱን ለመመርመር ዋስትና አይሆንም እናንተ ግን ለሊቃውንቱ አስተምህሮ ግብጽ እንደምትቀርብ ተናግራችኋል ፍጹም የተሳሳተ ነው፡፡ስህተቱም የግብጽንና የኢትዮጵያን አብያተ ክርስትያናት ታሪክ ባለመረዳት የመጣ ነው፡፡ በካቶሊክና በኦሪየንታል አብያተክርስትያናት መካከል ያለውን ልዩነት ተራ አድርጎ ለማቅረብ መሞከራችሁ ነገረ ሥጋዌ እንዳልገባችሁ በግልጽ ያሳያል፡፡ለማንኛውም እናንተ በወንጌል አለት ላይ የተመሠረተችውን የኢትዮጵያን ቤተክርስትያን አስተምህሮና ታሪክ ለመመርመር የሚያስችል እውቀትም ብቃትም የላችሁም፡፡

  ReplyDelete
 5. በወንጌል አለት ላይ????በወንጀል ማለትህ ነው?ቤተክርስቲያኗ ለወንጌል ቦታ የላትም።

  ReplyDelete
 6. ሞኝ የሰማለት ያብዳል
  ለምን ከሺ ዐመታት በላይ ቆየ
  አሁንማ ሲያልቅ አያምር ነው

  ReplyDelete
 7. Avoid your illiterate expression before trying to give theological analysis!

  ReplyDelete