Friday, May 19, 2017

ሲኖዶሱ በአዋልድ መጻሕፍት ላይ ያሳለፈው ውሳኔ መንፈሳዊ ተሐድሶ ወይስ ፖለቲካ?የሰሞኑ የሲኖዶስ ስብሰባ በአዋልድ መጻሕፍት ላይ ውሳኔ ማሳለፉ ትልቅ እርምጃ ተደርጎ የሚወሰድ ነው፡፡ ውሳኔው አዋልድ መጻሕፍት የያዟቸውን ጉዶች እየተቹ ሲያቀርቡና ካህናቱንና ሕዝቡን ሲያነቁ ለቆዩ የቤተ ክርስቲያን ልጆች ትልቅ ድል ነው፡፡ የዓመታት ጩኸታቸው በሲኖዶስ መሰማትና ውሳኔ ማግኘት በመጀመሩ ይበል ያሰኛል፡፡ በዚህም ምክንያት አለስማቸው ስም እየተሰጣቸው ለውግዘትና ለስደት መዳረጋቸው ግን ቤተ ክርስቲያኒቱን ብዙ ዋጋ የሚያስከፍላት መሆኑ ከወዲሁ እየታየ ነው፡፡ እውነት እውነትነቱ እየፈካ ውሸት ደግሞ እየተጋለጠና እየኮሰመነ መሄዱ አይቀርምና፡፡ ብዙዎች እየፈለሱ ያሉት የአዋልድ ውሸት አስጠልቷቸውና እውነቱን ፍለጋ መሆኑን መረዳት በጣም ይጠቅማል፡፡
ውሳኔው የተወሰነበት መነሻ ግን ከሃይማኖታዊነት ይልቅ ፖለቲካዊነቱ ያመዝናል፡፡ በራእየ ማርያም ላይ የአንዳንድ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ብሔረሰቦች ስም በክፉ መጠቀሱ ሲሆን በተአምረ ማርያም ላይ ደግሞ ስለ አቡነ ጳውሎስና ስለ መንግሥቱ ኃይለማርያም የተጻፈ “ተአምር” መኖሩ እነዚህና መሰል አዋልድ እንዲታረሙ ምክንያት ሆኗል፡፡ ስለ አቡነ ጳውሎስና ስለ መንግስቱ ኃ/ማርያም የተጻፈው “ተአምር” የሚነግረን ነገር ቢኖር የተጻፈው ውሸት መሆኑን ብቻ ሳይሆን የቀሩትም የተአምረ ማርያም ጽሑፎች ዘመኑ ይርዘም እንጂ የተዘጋጁት በዚህ መንገድ መሆኑንና የሐሰት ድርሰቶች መሆናቸውን ነው፡፡ ለአዋልድ መጻሕፍት የተሳሳቱ መሆን ግን ከእነዚህ የበለጠ ብዙ ሥነ መለኮታዊ ተፋልሶን የሚያስከትሉ ከመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ ጋር የሚጋጩ ጽሑፎች ሞልተዋል፡፡ 

ስለ ተአምረ ማርያም ጥቂት እንበል ሲጀመር የማርያም የሚባል ተአምር የለም፡፡ ተአምር የእግዚአብሔር ብቻ አስደናቂ ሥራ ነው፡፡ ቅዱስ መጽሐፍም ብቻውን ተአምራትን የሚያደርግ የእስራኤል አምላክ ይባረክ ይላል፡፡ ከዚህ ሌላ ተአምረ ማርያም በተበለው መጽሐፍ ውስጥ ስፍር ቁጥር የሌለው ሐሰትና የሥነ መለኮት ተፋልሶ ይገኛል፡፡ ለመጥቀስ ያህል እንኳ ከመቅድሙ ብንነሣ “አዳምና ሔዋን እመቤታችን ለማመስገን ተፈጠሩ፣ … ተአምሯን ሰምቶ የሄደ ሥጋወደሙን እንደ ተቀበለ ይቆጠርለታል ይደረግልኛል ብሎ ቢሰማ፣… ሰባ ስምንት ሰዎች የበላው ሰው በማርያም ምልጃ ዳነ፣ ይኸውም ማርያም በሚዛን ላይ ጥላዋን ጥላ (አጭበርብራ እንደማለት ነው) የእርሱ እፍኝ ውሃ እንዲመዝን በማድረጓ ነው፡፡ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስን ክዶ በእርሷ ምልጃ ዳነ፣ … ሳውልን ለመጀመሪያ ጊዜ የጠራችው ማርያም ናት፣ ሳውል ሳውል ልጄን ልምን ታሳድዳለህ? በማለት የሚሉትና ሌሎችም በርካታ ችግሮች ያሉበት ሐሰተኛ ድርሰት ነው፡፡ ይህ ድርሰት ታዲያ ምኑ ይታረማል? የሚታረመው እኮ በውስጡ ጥሩ ነገር ቢገኝ ነበር፡፡ የያዘው በሙሉ ስሕተት ከሆነ ግን ማረም ሳይሆን ተነቅሎ መጣል ነው ያለበት፡፡ አረምን ይነቅሏል እንጂ አያርሙትምና ማለትም ወደ ሙዚየም ማስገባትና የምናምነው እንዲህ ነበረ አሁን ግን ብዙ አማልክትን ከማምለክ ወደ እውነተኛው አምላክ ፊታችንን መልሰናል የሚል ጥሩ ትውፊት ለቀጣዩ ትውልድ ማውረስ ይገባል፡፡ ወይም ቀጥሎ በምንጠቅሰው የፕሮፌሰር ጌታቸው አንድ ንግግር ውስጥ እንደ ተመለከተው እነዚህ ሐሰተኛ ትምህርት ያዘሉ ድርሰቶች ‘ከቤተ ክርስቲያን ሃይማኖትነት ወደ ቤተ ክርስቲያን ታሪክነት’ መሸጋገር ይገባቸዋል፡፡   

ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ የቅዱስ ያሬድ ታሪክና የግዕዝ ሥነ ጽሑፍ” በሚል ርእስ በርእሰ አድባራት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ጥቅምት 5 ቀን 1999 ዓ.ም. በተከበረው የቅዱስ ያሬድ በዓል ላይ በተደረገ ንግግራቸው ላይ እንዲህ ሲሉ ያሰፈሩት ጽሑፍ አለ፡፡ “የሌሎች እንደኛ ያሉ ሐዋርያዊ አብያተ ክርስቲያን የሚኖሩባቸው ሀገሮች የተራመዷቸውን ታሪካዊ እርምጃዎች ሀገራችንም ባለመራመዷ የእኛ ትውልድ በገድል መልክ የቆየልንን የአባቶቻችንን ታሪክ ለማድነቅ ችግር እንደሚገጥመው እገምታለሁ፡፡ ገድል ጻድቁ መምህር ሲያርፍ እንደ አባቱ አድርጎ የሚያየውና የሚያደንቀው መንፈስ ቅዱስ ለሥራው የጠራው ደቀ መዝሙር የሚጽፍለት የሕይወት ታሪክ ነው፡፡ ደቀ መዝሙሩን መንፈስ  ቅዱስ ይጥራው እንጂ መምህሩን ከሌሎች ጻድቃን ለማስበለጥ የራሱ መንፈስ ጣልቃ እየገባ ከጥሪው በላይ እንዲጽፍ ይገፋፋውና እውነቱን ሳይቀር ከጥርጣሬ ላይ የሚጥል ነገር ይጽፋል፡፡
ይህ ዓይነቱ አጻጻፍ በሐዋርያዊ አብያተ ክርስቲያን ሁሉ ዘንድ የተለመደ ነበር፡፡ ግን እነዚያን አብያተ ክርስቲያን ከመካከለኛው ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ የተደረገው ምርምርና ጥርጣሬ ያጋጠሟቸው በየጊዜው በመንጠባጠብ ስለሆነ ምርምሮቹንና ጥርጣሬዎቹን እንደ መጡ ተቋቁመዋቸዋል፣ ተላምደዋቸዋልም፡፡ በምርምሮቹና በጥርጣሬዎቹ አሳሳቢነት ከክርስቶስ ትምህርት ራቅ ብለው የተገኙትን ትረካዎች ከቤተ ክርስቲያናቸው አካል ቆርጠው ሲጥሉ  ሕመሙ ቤተ ክርስቲያናቸውን ብዙ አይሰማትም ነበረ፡፡ እኛ ግን በአስተሳሰብ ረገድ ከመካከለኛው ዘመን (ከዘመነ ጠጅ) እንዳለን ከምዕራቡ ዓለም ስለ ተገናኘን የሃያኛው ክፍለ ዘመን መጋረጃ ከበራችን ወለል ብሎ ተከፈተብን፡፡ አንዱ አካላችን ዘመኑን ከድቶ ዘው ሲል ሌላው ከቆመበት ለመነቃነቅ እድል አላገኘም፡፡ ዛሬ የእነዚያ አብያተክርስቲያናት መምህራን አንዳንድ ዱሮ የቀሩ ነገሮችን ከቤተ ክርስቲያናቸው ታሪክ እየጠቀሱ ታሪክ ሲያስተምሩ ከቆመበት ለመነቃነቅ ዕድል ያላገኘው አካላችን ቢሰማ ‘ታዲያ ምን ስሕተት ኖሮበት ቀረ? በእኛም ዘንድ አሁንም እንዲህ ነው መቅረትም መቀየርም የለበትም’ ይል ይሆናል፡፡ ሌሎቹ ግን ከዚያ የተለየ ስሜት ሲፈጥርባቸው ማለት ንጽሕት ሃይማኖታችንን ከመጠራጠር ላይ ሲወድቁ ይታያል።
ሌሎቹ ሐዋርያዊ አብያተ ክርስቲያናት ለዘመኑ የተስማሙ በኋላ ትውልድ ግን የማይሆኑ የተጋነኑ ተአምራቶቻቸውን የምእመናኑን እምነት ሳያናጉ በጊዜው ከቤተ ክርስቲያን ሃይማኖት ወደ ቤተክርስቲያን ታሪክ አዛውረዋቸዋል። በእኛ ዘንድ እድሉ ሳይገኝ ቀርቶ ይህን ዓይነት እርምጃ በጊዜው መውሰድ ባለመቻሉ፥ የሚጠሉን መስሏቸው በደስታ ወይን ሰክረዋል”
ስለዚህ የፕሮፌሰርን ምሁራዊ ምክር በመስማት አዋልድ መጻሕፍት ላይ ሌሎቹ ጥንታውያን አብያተክርስቲያናት የያዙትን አቋምና የወሰዱትን እርምጃ አስቦና አቅዶ መውሰድ እንጂ ችግር በተፈጠረ ቁጥር እሳት የማጥፋት ዓይነት እንቅስቃሴ ማድረግ ወይም እነርሱን የማሻሻል ሥራ መስራት ትርፉ ሌላ ድካም መጨመር ነው የሚሆነው፡፡ ስለዚህ መፍትሔው አዋልድን ወደ ታሪክነት አዛውሮ በመጽሐፍ ቅዱስ መመራት ነው፡፡
ከሁሉም የሚገርመው በተግባር ከተሻረ 50 ዓመታት ያለፉትና ኢትዮጵያውያን ከሊቃውንቶቻቸው መካከል ጳጳሳትን አይሹሙ የሚለው የፍትሐ ነገሥት አንቀጽ እስካሁን ድረስ እየታተመ መዝለቁና “ለምን አይፋቅም?” የሚለው የብዙዎች ጩኸት አለመሰማቱ ነው፡፡ በአንድ በኩል  የአሁኑ ሲኖዶስ ይህን በስርዋጽ ገብቶ ለ1600 ዓመታት ሲጨቁነን የኖረ ሐሰተኛ ሕግ እንዲፋቅ ኃላፊነት መወስዶ መወሰኑ የሚያስደንቅ ታሪካዊ ውሳኔ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ውሳኔ ግን በሌሎችም ለቤተ ክርስቲያን እንቅፋት በሆኑ ጉዳዮችም ላይ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል እንጂ እዚህ ላይ ብቻ ከቆመ ምንም ትርጉም የለውም፡፡ በጥቅሉ ሲታይ በተለይም ከላይ በተጠቀሱት ራእየ ማርያምና ተአምረ ማርያም ላይ እንዲደረግ የተወሰነው ጥገናዊ ለውጥ እንጂ የማያዳግም ፍቱን መፍትሔ አይደለምና በነካካ እጃችሁ አባቶች ሆይ በደንብ ሂዱበትና ነቀፌታን ከቤተ ክርስቲያናችን ላይ አንሡ፡፡     

7 comments:

 1. you protestants shut your mouth in your hall! you can not shut your mouth in our church.can you proof that bible is not a fiction?

  ReplyDelete
 2. አማርኛ አትችልም ! ገና ልጅ ነሽ አቡሽ ! አጭበርብራ ! መናፍቅ መሆንህን አሁን አወኩ ገና

  ReplyDelete
 3. አጋንንታዊ የሆነ ታአምርና ድንቅ ነገርም እኮ አለ:: እንዲያውም የተመረጡትን እንኳን እስኪያስት ድረስ በልዩ ታአምር ይገለጣል:: ከጌታ ታአምራት የሚለዩበትን መንገድ ማስተማር ይበጃል የሚል አስተያየት አለኝ!!!

  ReplyDelete
 4. ከሁሉ የገረመኝ እናንተ መናፍቃን ቀላል አመርኛ እያላችሁ የእግዚአበሔርን ቃል መጽሐፍ ቅዱስን አጣማችሁ ስንቱን ከህይውት መንገድ አወጣችሁ እናም እንደአሽን በፈሉ ህገወጥ ማተሚያ ቤት አወልድ መጽሐፍትን እያሳተማችሁ በተናችሁ ይሄም አብሮ እንዲጠራ በቀጣይ ይደረጋል እስከዚያው ግን ማንነታችሁ ታውቋል እና ብዙ አትድከሙ ፡፡

  ReplyDelete