Tuesday, June 27, 2017

«ውግዘቱን እንቃወማለን!!!»«የተወገዘ ሲኖዶስ ማውገዝ አይችልም!!»
ከሃያ ዓመታት በፊት ለሁለት የተከፈለው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሲኖዶስ የመከፈሉ ዋነኛው ምክንያት የቀነኖ ጥሰት እንደ ነበር ሁላችን የምናውቀው የአደባባይ ምሥጢር ነው። 


በቤተክርስቲያኒቱ ጥብቅ ቀኖና መሰረት አንድ ፓትርያርክ በህይወት እያለ ሌላ ፓትርያርክ መሾም ፍጹም የተወገዘና በእግዚአብሔር ፊት እርም የሆነ ግብር እንደ ሆነ በግልጽ ተቀምጦ ሳለ ኢትዮጵያ ያለው ሲኖዶስ ግን ለእግዚአብሔርና የቀደሙ አባቶቻችን ላስቀመጡልን መንፈሳዊ ቀኖና ከመገዛት ይልቅ ለመንግስት ፖለቲካ በመንበርከክ በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር በአቶ ታምራት ላይኔ በተሰጠው ትዕዛዝ መሠረት ሲኖዶሱ አራተኛውን የኢትዮጵያ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስን ከአገር ተሰደው እንዲወጡ በማድረግ በእርሳቸው መንበር ላይ ሌላ ፓርያርክ አምስተኛ አድርጎ ሾሟል ይህ ፍጹም ሕገ ቤተክርስቲያንን እና ቀኖና ቤተክርስቲያንን የጣሰ አካሄድ አግባብ አለመሆኑን በብፁዓን አባቶችና በአገር ሽማግሌዎች ለሲኖዶሱ አባላት ቢገለጽላቸውም እግዚአብሔርን ባለመፍራትና ለሚመሩት መንጋ መከፋፈል ባለመጠንቀቅ በእምቢታቸው ስለ ጸኑ በስደት ላይ የሚገኘው ሕጋዊው ቅዱስ ሲኖዶስ በማይፈታ ጽኑ ማሰሪያ ኢትዮጵያ የሚገኘውን ሲኖዶስ አውግዞታል በዚህ ከባድ ውግዘት ታስሮ ያለ ሲኖዶስ ከታሰረበት ውግዘት ሳይፈታ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችን በተለያየ ጊዜ ማህበረ ቅዱሳን ቀምሮ በሚያመጣለት የሐሰት የክስ ዶሴ በመመራት ጠርቶ ሳይጠይቅና ምላሻቸውን ሳይሰማ አውግዣለው እያለ የሚያውጀው ውግዘት ፍጹም የማይሰራና ተራ የሆነ ኢቀኖናዊ ውግዘት በመሆኑ «ወፈ ገዝት» ከመባል የዘለለ ቁም ነገር የሌለው ከንቱ ወሬ ነው። ወፈ- ገዝት በረባው ባልረባው ጉዳይ ላይ አውግዣለው የሚል የሰነፍ ካህን ማስፈራሪያና በስልጣነ ክህነት የዋሕ ክርስቲያኖችን ማስደንገጫ መሳሪያ ነው፤ አንዲት ወፍ ከዛፍ ዛፍ ስትበር መስቀል፡ እያወጣ ባለሽበት ቁሚ ገዝቼሻለው የማለት ያህል ነው።