Wednesday, June 21, 2017

በተሐድሶ እንቅስቃሴ ተጽዕኖ የተቀየሰው አዲሱ የማኅበረ ቅዱሳን መንገድማኅበረ ቅዱሳን ከተፈጠረ ወዲህ በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ብዙ ነገሮች የወንጌል መሠረታቸውን ለቅቀው ወደ ተረት ፈቀቅ ማለታቸውን ስንታዘብ ከሃያ በላይ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ይህንንም በዋና ልሳኖቹ ሐመርና ስምዓ ጽድቅ ሲሰራ ቆይቷል፡፡ በእነዚህ ዓመታት ያሉት አብዛኞቹ የቤተ ክርስቲያኒቱ አባላት በዚህ ቅኝት ውስጥ የገቡ መሆናቸውን ማስተዋሉ ቀላል ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ይታመንባቸው የነበሩ አስተምህሮዎች ሲለወጡና በሌላ አስተምህሮ ሲተኩ ማየት ችለናል፡፡ ለምሳሌ የኢየሱስ ክርስቶስን የአዲስ ኪዳን አስታራቂነትን ከሚገልጡ ቃላት መካከል አንዱ በሆነው “አማላጅነት” ሲነገር የኖረው የኢየሱስ ክርስቶስ ምልጃ በመጽሐፍ ቅዱስና እርሱን መሠረት አድርገው በተጻፉ እንደ ሃይማኖተ አበውና መጽሐፈ ቅዳሴ ላይ ያሉት ጽሑፎች እንደሌሉ ተቆጥረው በዚያ መሠረት ኢየሱስ አንድ ጊዜ በፈጸመው የማዳን ሥራው በሐዲስ ኪዳን የማይለወጥ ክህነት ያለው መካከለኛ ነው የሚለው ትምህርት እንደ “ኑፋቄ” ከተቆጠረ ከራርሟል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ቢልም፣ መጽሐፍ ቅዱስን ዋቢ አድርገው የተጻፉት ሃይማኖተ አበውና ቅዳሴው ቢመሰክሩም አንድ ጊዜ ባቀረበው ሕያው መሥዋዕት ኢየሱስ ዛሬም አስታራቂ ነው የሚለው ንጹሕ ትምህርት በስሕተት ትምህርትነት ተፈርጇል፡፡ እንዲህ ብለው ያስተማሩም ዕጣቸው እንደ መናፍቅ ተቆጥረው ከቤተክርስቲያን መባረር ሆኗል፡፡

ሁለተኛ ምሳሌ አድርገን ልንመለከተው የምንችለው ማርያም ጥንተ አብሶ ነበረባት የሚለው የሌሎቹ ኦርቶዶክሳውያን ሁሉ ትምህርት እንደ ኑፋቄ እየታየና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን “ሁለት ባሕርይ” ባይ ናት በሚለው አቋሟ በእምነት አትመስለኝም ከምትላት ከካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ጋር በጥንተ አብሶ ጉዳይ ላይ ራሷን አመሳስላለች፡፡ ከሌሎቹና ከዚህ ትምህርት በተጻራሪ ከቆሙት ከሌሎቹ ኦርቶዶክሳውያን ጋር ግን ተለይታለች። እነዚህ ለምሳሌ ያህል ተጠቀሱ እንጂ ሌሎችም እውነት ሆነው ዛሬ እንደ ስሕተት የተቆጠሩ፣ ቀድሞ ደግሞ ስሕተት ሆነው ይታዩና ይናቁ የነበሩ እና ዛሬ ግን የእውነት ስፍራ የተሰጣቸው ብዙ እንግዳ አስተምህሮዎች አሉ፡፡ ይህም የሆነበት አንዱ ምክንያት ራሱን ብቸኛ የኦርቶዶክስ ጠበቃ አድርጎ ለማቅረብ የሚሞክረው ማኅበረ ቅዱሳን አስተምህሮውን የቀየደው በዚህ አቅጣጫ በመሆኑ ነው፡፡ 

ይሁን እንጂ የተሐድሶ እንቅስቃሴ በአንድም በሌላም መንገድ ባሳደረው ተጽዕኖ ምክንያት አንዳንድ ጉዳዮች ላይ ከዚህ ቀደም ከያዘው አቋም ሸርተት የማለትና አስተምህሮውን ለየት ያለ ቅርጽ የማስያዝ አዝማሚያ እያሳየ ነው፡፡ በሐመርና በስምዓ ጽድቅ “አጣመው ያሳደጉትን እናቃናህ ቢሉት እሺ ይላል ወይ?” የሚለው ከባድ ፈተና እንደሚገጥመው ግን ከወዲሁ ይታወቃል፡፡ አስተምህሮውን ለየት ያለ ቅርጽ የማስያዝ አዝማሚያ እያሳየ ነው ሲባል ግን በትክክል አምኖበት ሳይሆን በተሐድሶ እንቅስቃሴ በኩል እየተፈጠረ ያለው ተጽዕኖ የማይሸሸው በመሆኑና ብዙ አባላቱ በየጊዜው በክርስቶስ ያላረፈ ልባቸውን ለማሳረፍ በሚያነሷቸው ጥያቄዎች በሚሰጧቸው ምላሾች ለማኅበሩ ጀርባቸውን እየሰጡና አባላቱን እያሳጣው በመሆኑ ጭምር ትልቅ የቤት ሥራ ስለሆነበት ነው፡፡
ማኅበሩ በዚህ አቅጣጫ እያሳየ ያለውን ተሐድሶ ከሚያመላክቱት ሥራዎቹ መካከል ለ5ኛ ዙር ዐውደ ርእዩ ያዘጋጀው ልዩ መጽሔትና ሐመረ ተዋሕዶ የጥር 2008 እትም አንዳንድ ጽሑፎች ማሳያዎች ናቸው፡፡ የዐውደ ርእዩ መሪ ቃል “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን እንጠንቅቅ ድርሻችንን እንወቅ” የሚል ሲሆን፣ አውደ ርእዩ እስካሁን ድረስ በየክልሉ በመታየት ላይ ይገኛል፡፡ በመጀመሪያ የዐውደ ርእዩን መጽሔት አንዳንድ ክፍሎች እንመልከት፡፡
1.    ስለ ማኅበረ ቅዱሳን ተልእኮ
መጽሔቱ ማኅበረ ቅዱሳን የተቋቋመው ለምን ዓላማ እንደነበር ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “በቤተ ክርስቲያን መዋቅር ያልታቀፈውን ወጣት ስበው እንዲያመጡ ኃላፊነት ተሰጥቶአቸው በማገልገል ላይ ከሚገኙ ማኅበራት አንዱ ነው።” (ገጽ 4)
ማኅበረ ቅዱሳን የተቋቋመው ለዚህ ዓላማ ከነበረ ለምን ታዲያ ወጣቶችን የቤተ ክርስቲያን ሳይሆን የራሱ ተከታይ አደረገ? ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ሲባል እንደ ነበረው የማኅበሩ አባላት ራሳቸውን በመጀመሪያ እኔ ኦርቶዶክሳዊ ነኝ ሳይሆን ማኅበረ ቅዱሳን ነኝ ሲሉ ነው የሚሰሙት። ቤተ ክርስቲያንን ሳይሆን ማኅበራቸውን ነው የሚያስቀድሙት ማለት ነው። ስለዚህ ማኅበሩ ወጣቱን የሣበው ወደማነው? የሚለው  ግልጽ ነው። ደግሞስ ማኅበሩ ቤተ ክርስቲያኒቱን በሞኖፖል መያዝ እንጂ ሌሎች እሱን የመሰሉ ማኅበራት እንዲፈጠሩ መቼ ይፈልግና ነው ሌሎች ማኅበራት እንዳሉ አስመስሎ ራሱን “ከማኅበራት አንዱ” አድርጎ የሚያቀርበው፡፡ ከእርሱ ቀድመው የተነሡትን ማኅበራት (ለምሳሌ ሃይማኖተ አበውን) እንዴት ጠልፎ እንደ ጣለና ስፍራቸውን እንደቀማ አሁንም ሌላ ተወዳዳሪና ተፎካካሪ ማኅበር እንዳይፈጠር ጠንክሮ እንዴት እንደሚታገል እየታየ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ተደራጅተው ቤተ ክርስቲያንን ለማገልገል የተሰለፉትን የቤተ ክርስቲያን ልጆች አስቀድሞ ስም በማጥፋት እንዴት አድርጎ እንዳይደራጁ በሩን እንዳዘጋባቸው ይታወቃል እኮ! አንዳንድ ማኅበራት አሉ ቢባሉ እንኳን እርሱ በአርአያውና በምሳሌው የፈጠራቸው የእርሱ ግልባጮች ናቸው፡፡ በአጠቃላይ ዓላማው ምን እንደሆነ ከሚናገረው ይልቅ የሚታየው በቂ ምስክር ነውና ሌላውን ባያታልል ጥሩ ነው፡፡         
2.   ለቤተ ክርስቲያን የሰጠው ትርጉም
በዚህ መጽሔት ውስጥ ለቤተ ክርስቲያን የተሰጠው ትርጉም አንዳንድ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆኑ ሐሳቦች ያሉበት፣ አንዳንድ ጽንፈኛ አስተሳሰብም የተጠናወተው ብያኔ የታከለበት ቢሆንም ሕንጻን እንደ ቤተ ክርስቲያን ያላከተተ ትርጉም መሰጠቱ የተሐድሶ እንቅስቃሴ ካሳደረው በጎ ተጽዕኖ የተነሣ የመጣ ነው፡፡ እንዲህ ሲባል ግን ይህን ትርጉም ቤተክርስቲያኗ የማታውቀው ነበር ለማለት ሳይሆን በቤተ ክርስቲያኒቱ የሚታወቅ ሆኖ የኖረ ቢሆንም በአሁኑ ጊዜ በአብዛኛው ሕዝብ አእምሮ ውስጥ ቤተክርስቲያን ሲባል የሚታሰበው ሰዎች የሠሩት ሕንጻ እንጂ ክርስቶስ በከበረ ደሙ የዋጃቸው የምእመናን ኅብረት ሆኖ አይታይም ለማለት ነው፡፡ በተሐድሶ እንቅስቃሴ ውስጥ ሲነገር የቆየው ቤተክርስቲያን የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅም ላይ የዋለው ሕንጻን ሳይሆን የምእመናንን ኅብረት ለማመልከት ነው እንጂ ሕንጻው ቤተክርስቲያን እየተባለ መጠራቱ በልማድ ወይም ከጊዜ በኋላ የመጣ ነው፤ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት የለውም በማለት ነው፡፡ ማኅበረ ቅዱሳንም ይህን የተቀበለ ይመስላል፡፡
ስለቤተ ክርስቲያን የሰጠው ትርጉም “ቅድስት ቤተክርስቲያን የቅዱሳን መላእክት በአጸደ ሥጋ ያሉ አበው ካህናትና ምእመናን እንዲሁም የዚህን ዓለም ተጋድሎ ፈጽመው በአጸደ ነፍስ የሚኖሩ ቅዱሳን፣ የብሉይ ኪዳንና የሐዲስ ኪዳን ምእመናን አንድነት ናት፡፡” የሚል ነው (ገጽ 3)፡፡ በዚህ ውስጥ ሕንጻ ስፍራ አልተሰጠውም ወይም ቤተክርስቲያን ተብሎ አልተጠራም ይህ ትክክል ነው፡፡ ነገር ግን ቤተክርስቲያን ክርስቶስ በገዛ ደሙ የዋጃት እንደ መሆኗ በዚህ አንጻር መላእክት አባላቷ ተብለው የሚጠሩበት ሁኔታ የለም፡፡ የእነርሱ ማንነትና ተልእኮ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደ ተጻፈው የሚታይ ነው፡፡
በፊት ለፊት ሕንጻን ቤተ ክርስቲያን ብሎ አይጥራ እንጂ በዘወርዋራ መንገድ ግን ስያሜውን ከምእመናን ላይ አንሥቶ ለሕንጻው የሰጠበት ሁኔታ አለ፡፡ ገጽ 10 ላይ በጥቅስ መልክ ያቀረበውን እንመልከት፡፡
“ስለዚህ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በምናያቸውና በምናውቃቸው ሰዎች ደረጃ ብቻ አትለካም፣ አትመዘንም፡፡ እነዚህ እንደየሥራቸው ዋጋቸውን ይቀበሉ ዘንድ በእርሷ ሊቀደሱና ሊከብሩ ዕድል የተሰጣቸው ናቸው፡፡”
ይህ ምን ማለት ነው? በዚህ ውስጥ ቤተ ክርስቲያን ማናት? ሕንጻ ናት ወይስ የእምነት ተቋም? ብዙ ግልጽ አይደለም፡፡ ቤተክርስቲያን በክርስቶስ ደም የተዋጁ የሰዎች ስብስብ ናት ስንል የሰዎች ስብስብ ናት ማለት ነው እንጂ ከሰዎቹ ውጪ ያለች ግኡዝ ወይም ረቀቂ ነገር ናት ማለት አይደለም፡፡ እርስዋ በክርስቶስ አዳኝነት ያመኑ ሰዎች ስብስብ ናት ባልነው መሠረትም መቀደስዋ በክርስቶስ በኩል እንጂ እርስዋ ራሷ ሰዎችን ትቀድሳለች የሚል ትምህርት በመጽሐፍ ቅዱስ የለም፡፡ ስለዚህ ቤተክርስቲያን በክርስቶስ ደም የተዋጁ ሰዎች ስብስብ መሆኗን ማስተባበልና ስያሜውን ለሌላ አካል መስጠት ተገቢ አይደለም፡፡ ቤተክርስቲያንን ሌላ አካል አድርጎ ማሰብና ለቤተክርስቲያንም የሌላትንና በክርስቶስ ደም እንዲሁም በመንፈስ ቅዱስ የሚከናወነውን መቀደሳችንን የቤተክርስቲያን ተግባር አድርጎ ማቅረብ ትልቅ ኑፋቄ ነው፡፡
“እንደዚሁም ቤተ ክርስቲያን በማንኛውም ጻድቅ ወይም ቅዱስ መጠንም አትለካም ወይም አትወከልም፡፡ ቤተክርስቲያን ፍጹም ባለቤቷና መልኳ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው፡፡ ሌሎች የአካሏ አንድ ከፍል ብቻ ናቸው፡፡” (ገጽ 10)
ይህ እውነት የሚመስል ነገር ያለበት ቢመስልም ለቤተክርስቲያንና ከክርስቶስ ጋር ላላት ግንኙነት የተሰጠው ትርጉም መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት የሌለው ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ክርስቶስና ቤተ ክርስቲያን የተገለጹት በራስነትና በአካልነት ነው፡፡ ክርስቶስ የቤተ ክርስቲያን ራስ ነው ቤተ ክርስቲያን ደግሞ አካሉ ናት፡፡ ሁሉንም ከእግሩ በታች አስገዛለት ከሁሉ በላይም ራስ እንዲሆን ለቤተ ክርስቲያን ሰጠው። እርስዋም አካሉና ሁሉን በሁሉ የሚሞላ የእርሱ ሙላቱ ናት።” (ኤፌ 1፥22-23)፡፡ ሆኖም በክርስቶስና በቤተ ክርስቲያን መካከል ያለውን መያያዝ ብቻ ሳይሆን ያለውን ልዩነትም መዘንጋት የለብንም፡፡ ክርስቶስ ፍጹም ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ግን ፍጹም ልትሆን የተጠራች ናት፣ “እድፈት ወይም የፊት መጨማደድ ወይም እንዲህ ያለ ነገር ሳይሆንባት ቅድስትና ያለ ነውር ትሆን ዘንድ ክብርት የሆነችን ቤተ ክርስቲያን ለራሱ እንዲያቀርብ” ፈልጎ ራሱን የሰጠላት በክርስቶስ ደም የተዋጁ የሰዎች ስብስብ ናት፡፡ (ኤፌ. 5፥26-27)፡፡ ስለዚህ ቤተ ክርስቲያንን ከዚህ ውጪ ማሰብ ሌላ አካል አድርጎ ለማቅረብ ካልሆነ በቀር ምንም መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት የለውም፡፡ ይልቁንም “ሌሎች የአካሏ አንድ ከፍል ብቻ ናቸው፡፡” በማለት የቀረበው የማኅበረ ቅዱሳን እንግዳ ትምህርት ቤተ ክርስቲያንን ራስ ማድረግና እርስዋን በክርስቶስ ስፍራ ማስቀመጥ ነው የሚሆነው፡፡ ምንም ቢሆን ግን ቤተ ክርስቲያን አካል ብቻ ናት፤ እያንዳንዱ በክርስቶስ ያመነ ምእመንም የአካሉ ብልት ነው እንጂ ቤተ ክርስቲያን ራስ ተብላ የምትጠራበት አግባብ ከቶ የለም፡፡ ስለዚህ ማኅበረ ቅዱሳን ስልታዊ በሚመስል ግን በተሳሳተ መንገድ ቤተክርስቲያንን ሌላ አካል አድርጎ ነውና ያቀረበው ትምህርቱ ክርስቲያናዊ አይደለም፡፡
ሌላው ካህናትና ምእመናን ብሎ የሁሉም መጠሪያ የሆነውን ካህንነትን (አገልጋይነትን) ለተወሰኑ ሰዎች መስጠቱና ገሚሱን ካህናት ገሚሱን ምእመናን በማለት መከፋፈሉ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አይደለም፣ በክርስቶስ ያመኑ ሁሉ ካህናት ተብለዋልና፡፡
እናንተ ግን ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃኑ የጠራችሁን የእርሱን በጎነት እንድትናገሩ የተመረጠ ትውልድ፥ የንጉሥ ካህናት፥ ቅዱስ ሕዝብ፥ ለርስቱ የተለየ ወገን ናችሁ፤” (1ጴጥ. 2፥9)
“ለወደደን ከኃጢአታችንም በደሙ ላጠበን፥ መንግሥትም ለአምላኩና ለአባቱም ካህናት እንድንሆን ላደረገ፥ ለእርሱ ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ክብርና ኃይል ይሁን፤ አሜን።” (ራእ. 1፥5-6)
“መጽሐፉን ትወስድ ዘንድ ማኅተሞቹንም ትፈታ ዘንድ ይገባሃል፥ ታርደሃልና፥ በደምህም ለእግዚአብሔር ከነገድ ሁሉ ከቋንቋም ሁሉ ከወገንም ሁሉ ከሕዝብም ሁሉ ሰዎችን ዋጅተህ ለአምላካችን መንግሥትና ካህናት ይሆኑ ዘንድ አደረግሃቸው፥ በምድርም ላይ ይነግሣሉ እያሉ አዲስን ቅኔ ይዘምራሉ።” (ራእ. 5፥9-10)
“በፊተኛው ትንሣኤ ዕድል ያለው ብፁዕና ቅዱስ ነው፤ ሁለተኛው ሞት በእነርሱ ላይ ሥልጣን የለውም፥ ዳሩ ግን የእግዚአብሔርና የክርስቶስ ካህናት ይሆናሉ ከእርሱም ጋር ይህን ሺህ ዓመት ይነግሣሉ።” (ራእ. 20፥6)
ከእነርሱ መካከል ግን በዚህ ምድር ላይ ባለው አገልግሎት ቤተክርስቲያንን ለመመገብና ለመምራት የተሾሙ ካህናት ከሚለው ስያሜ ውጪ በሌሎች ስያሜዎች ነው የተጠሩት፡፡ ለምሳሌ ሐዋርያት፣ ነቢያት ወንጌል ሰባኪዎች፣ እረኞች፣ ጳጳሳት፣ ቀሳውስት፣ ኤጲስ ቆጶሳት፣ ዲያቆናት፣ ወዘተ.፡፡ ከዚህ ውጪ በመጓዝ በሊቀ ካህናት ክርስቶስ አማኞች ሁሉ ካህናት መደረጋቸውን ወደ ጎን ትቶ ካህናትና ምእመናን የሚለው አጠራር ልማዳዊ እንጂ አዲስ ኪዳናዊ አይደለም፡፡ በኦሪትም ቢሆን የሌዊ ነገድ ብቻ ሳይሆን እስራኤል በአጠቃላይ ካህናት ተብለው የነበረ መሆኑን እዚህ ላይ ማስታዋሱ ይጠቅማል፡፡ “…እናንተም የካህናት መንግሥት የተቀደሰም ሕዝብ ትሆኑልኛላችሁ። ለእስራኤል ልጆች የምትነግራቸው ቃል ይህ ነው።” (ዘፀ. 19፥6)፡፡ ከሞላ ጎደል እነዚህ ስሕተቶች ቢታረሙ ለቤተ ክርስቲያን የተሰጠው ፍቺ ትክክለኛ ይሆናል፡፡
ይልቁንም ቤተክርስቲያን በሚለው ዐቢይ ርእስ ሥር “ቤተክርስቲያን ማን ናት?” ተብሎ ተጠይቆ በመጀመሪያ የተሰጠው መልስ ፍጹም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነው፡፡ አንደኛው “ቤተ ክርስቲያን በክርስቶስ ራስነት አንድ አካል የሆኑ የምእመናን አንድነት ናት፡፡” ተብሏል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ “ቤተክርስቲያን የክርስቶስ አካል ናት፡፡” የሚል ነው (ገጽ 5)፡፡
ከዚህ በተጨማሪ “በእግዚአብሔር ያመኑ”፣ “በክርስቶስ ቤዛነት የዳኑ”፣ “በጥምቀት ዳግመኛ የተወለዱ” እና “በቅዱስ ሥጋውና በክቡር ደሙ የተዋጁ ‘አዲስ ሰዎች’ አንድነት ናት” በሚል በሥዕል ከተደገፉ ነጥቦች ጋር ቀርቧል፡፡ ከአራቱ የመጀመሪያዎቹ ሁለቱ ነጥቦች ትክክለኛ ሲሆኑ ቀሪዎቹ ሁለቱ ግን በውስጣቸው የተዛቡ ሐሳቦችን ይዘዋል፡፡ አንደኛው ከጥምቀት ጋር በተያያዘ የቀረበው ነው፡፡ በእርግጥ የጥምቀት ጉዳይ ብዙ ክርክር ያለበት መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ በክርስቶስ አዳኝነት ያመነ ሁሉ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ይጠመቃል፡፡ የሚጠመቀው ግን በእግዚአብሔር ቃልና በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት ባገኘው የልብ ለውጥ የሆነ ዳግም ልደት ከክርስቶስ ጋር መተባበሩን ለመመስከር እንጂ ከውሃው ለመወለድ አይደለም፡፡ ውሃው ዳግም መወለድን ማሳያ ትእምርት ነውና፡፡                 
“በቅዱስ ሥጋውና በክቡር ደሙ የተዋጁ ‘አዲስ ሰዎች’ አንድነት ናት” የሚለውም ስሕተት አለበት፡፡ እዚህ ላይ በቅዱስ ሥጋውና በክቡር ደሙ ሲባል በቅዱስ ቁርባን ለማለት ነው ወይ? እንዲህ ከሆነ ስሕተት ነው፤ እኛ የተዋጀነው በቀራንዮ መስቀል ላይ በፈሰሰው ክቡር የክርስቶስ ደም ነው እንጂ ለሞቱ መታሰቢያ እንዲሆን በምሴተ ሐሙስ በተሰጠው ኅብስትና ወይን አይደለም፡፡ “ከአባቶቻችሁ ከወረሳችሁት ከከንቱ ኑሮአችሁ በሚያልፍ ነገር በብር ወይም በወርቅ ሳይሆን፥ ነውርና እድፍ እንደ ሌለው እንደ በግ ደም በክቡር የክርስቶስ ደም እንደ ተዋጃችሁ ታውቃላችሁ።” (1ጴጥ. 1፥18-19)፡፡ መጽሔቱ ላይ ያለው ሥዕል የሚያሳየው ግን ቅዱስ ቁርባንን ነው፡፡ እንዲህ ከሆነም በሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ አንድ ጊዜ ለዘለዓለም በሰማያዊቱ መቅደስ ውስጥ የቀረበውን መሥዋዕት እርሱ ለሞቱ መታሰቢያና ለእኛ በረከት እንዲሆን የሰጠው ኅብስትና ወይን መተካት ነው የሚሆነው፡፡ ይህን ስናደርግ መሥዋዕት አቅራቢውን ሊቀካህናት ኢየሱስ ክርስቶስን በሌላ ምድራዊ “ካህን”፣ እርሱ ያቀረበውን ሕያውና ነውር የሌለበትን መሥዋዕት ለሞቱ መታሰቢያ እንዲሆን በሰጠው ሥጋ ወደሙ፣ እርሱ መሥዋዕቱን ያቀረበበትን ሰማያዊውንና በእግዚአብሔር የተተከለውን መቅደስ በምድራዊና በሰው እጅ በተሠራ መቅደስ መተካት ነው የሚሆነው ስለዚህ የተሳሳተ ገለጻ ነው፡፡
ሌላው “ቤተክርስቲያን የሰዎችና የመላእክት አንድነት ናት፡፡” በሚል የቀረበውን ሐሳብ እንመለከታለን፡፡ በዚህ ነጥብ ሥር የቀረቡት ጥቅሶች ዘፍጥረት 28፥12-13 እና ዕብ. 1፥14 ላይ ያለው ቃል ነው፡፡ የያዕቆብን መሰላል ማርያም ናት ሳይል የተሳሳተውን ትርጉም ማለፉ መልካም አድርጓል፡፡ ሆኖም መላእክትን ክርስቶስ በደሙ የዋጃት የቤተ ክርስቲያን ግማሽ አካላት አድርጎ ማቅረብ ስሕተት ነው፡፡ ክርስቶስ ደሙን ያፈሰሰላት ቤተ ክርስቲያን በክርስቶስ ያመኑ ሰዎች ጉባኤ ወይም ስብስብ ናት፡፡ በዚህ ስብስብ ውስጥ መላእክት አልተቆጠሩም፡፡ ሆኖም መላእክት ከላይ እንደ ተገለጸው መዳንን ይወርሱ ዘንድ ያላቸውን ሰዎች ለማገዝ ወይም ለመርዳት ከእግዚአብሔር የሚላኩ የሚላኩ መናፍስት ናቸው፡፡
ይቀጥላል

4 comments:

 1. ስንት ተከፈለህ? ሃራጥቃ አከርካሪው ተመታ እኮ አልሠማህም ምሥኪን

  ReplyDelete
 2. Man endetsafew sim yemateksut lemindin new be wongel mefrat ale ende

  ReplyDelete
 3. NOT TRUE..NOT TRUE.. Please go to the western and preach to them.

  ReplyDelete
 4. ስታሳዝኑ ከአውሮፓ አለቆቻችሁ የሚሰጣችሁ የዶላር እርጥባን እንዳይቀር ተግታችሁ ስም አጥፉ የእውነት አምላክ ፍርዱን ይስጣችሁ። እኛ ስራ ላይ ነን

  ReplyDelete