Tuesday, June 27, 2017

«ውግዘቱን እንቃወማለን!!!»«የተወገዘ ሲኖዶስ ማውገዝ አይችልም!!»
ከሃያ ዓመታት በፊት ለሁለት የተከፈለው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሲኖዶስ የመከፈሉ ዋነኛው ምክንያት የቀነኖ ጥሰት እንደ ነበር ሁላችን የምናውቀው የአደባባይ ምሥጢር ነው። 


በቤተክርስቲያኒቱ ጥብቅ ቀኖና መሰረት አንድ ፓትርያርክ በህይወት እያለ ሌላ ፓትርያርክ መሾም ፍጹም የተወገዘና በእግዚአብሔር ፊት እርም የሆነ ግብር እንደ ሆነ በግልጽ ተቀምጦ ሳለ ኢትዮጵያ ያለው ሲኖዶስ ግን ለእግዚአብሔርና የቀደሙ አባቶቻችን ላስቀመጡልን መንፈሳዊ ቀኖና ከመገዛት ይልቅ ለመንግስት ፖለቲካ በመንበርከክ በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር በአቶ ታምራት ላይኔ በተሰጠው ትዕዛዝ መሠረት ሲኖዶሱ አራተኛውን የኢትዮጵያ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስን ከአገር ተሰደው እንዲወጡ በማድረግ በእርሳቸው መንበር ላይ ሌላ ፓርያርክ አምስተኛ አድርጎ ሾሟል ይህ ፍጹም ሕገ ቤተክርስቲያንን እና ቀኖና ቤተክርስቲያንን የጣሰ አካሄድ አግባብ አለመሆኑን በብፁዓን አባቶችና በአገር ሽማግሌዎች ለሲኖዶሱ አባላት ቢገለጽላቸውም እግዚአብሔርን ባለመፍራትና ለሚመሩት መንጋ መከፋፈል ባለመጠንቀቅ በእምቢታቸው ስለ ጸኑ በስደት ላይ የሚገኘው ሕጋዊው ቅዱስ ሲኖዶስ በማይፈታ ጽኑ ማሰሪያ ኢትዮጵያ የሚገኘውን ሲኖዶስ አውግዞታል በዚህ ከባድ ውግዘት ታስሮ ያለ ሲኖዶስ ከታሰረበት ውግዘት ሳይፈታ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችን በተለያየ ጊዜ ማህበረ ቅዱሳን ቀምሮ በሚያመጣለት የሐሰት የክስ ዶሴ በመመራት ጠርቶ ሳይጠይቅና ምላሻቸውን ሳይሰማ አውግዣለው እያለ የሚያውጀው ውግዘት ፍጹም የማይሰራና ተራ የሆነ ኢቀኖናዊ ውግዘት በመሆኑ «ወፈ ገዝት» ከመባል የዘለለ ቁም ነገር የሌለው ከንቱ ወሬ ነው። ወፈ- ገዝት በረባው ባልረባው ጉዳይ ላይ አውግዣለው የሚል የሰነፍ ካህን ማስፈራሪያና በስልጣነ ክህነት የዋሕ ክርስቲያኖችን ማስደንገጫ መሳሪያ ነው፤ አንዲት ወፍ ከዛፍ ዛፍ ስትበር መስቀል፡ እያወጣ ባለሽበት ቁሚ ገዝቼሻለው የማለት ያህል ነው።
በዘንድሮው የግንቦት ስብሰባ መምህር አሰግድ ሳህሉን አውግዣላው ያለው ሲኖዶስ በመገናኛ ብዙሃን በፓትርያርኩ፡ ወኪልነት፡ ያስተላለፈው መግለጫ በአደባባይ ሲኖዶሱ እራሱን ያዋረደበት፣ አዕምሮ ባለው ሕዝብ ዘንድ ቀሎ የታየበትና ጳጳሳቱ በሕዝብ የህሊና ሚዛን መሳቂያ መሳለቂያ የሆኑበት ውሳኔ ነው። በቤተክርስቲያኒቱ ቀኖና መሰረት አንድ ሰው ሊወገዝ የሚችለው ትምህርተ ሥላሴን ክዶ ሲያስክድ ሲገኝ፣ የክርስቶስን የባህርይ አምላክነትና አዳኝነት ክዶ ሲያስክድ ሲገኝ በአጠቃላይ ከመጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮ ውጪ በሆነ መንገድ የቤተክርስቲያኒቱን ዶግማ ሆን ብሎ በዓላማ ሲያፋልስ ሲገኝ እንደ ሆነ የቀኖናዋ መጻሕፍት በግልጽ ያስቀምጣሉ። ውግዘት አንድን ሰው ከቤተ ክርስቲያን ሕብረት የሚለይ ከቅዱሳት ምሥጢራት መሳተፍን የሚከለክል የቤተ ክርስቲያኒቱ የመጨረሻ ውሳኔ በመሆኑ ከፍተኛ ጥንቃቄና ትዕግስትን የሚጠይቅ ነው። ውግዘት ሊተላለፍ የሚችለውም ግለሰቡ ተጠርቶ የእምነት ክህደት ቃሉን እንዲሰጥ ተጠይቆ፣ ተመክሮና ተዘክሮ በእምቢታው ጸንቶ የሚገኝ ከሆነ ብቻ ለቤተክርስቲያን ደኅንነት ሲባል ግለሰቡ ተወግዞ እንዲለይ ይደረጋል። ይህንን ደረጃ ሳይጠብቅ ሥልጣኑን መከታ አድርጎ አወግዛለሁ የሚል የትኛውም ሲኖዶስና ሊቀ ጳጳስ በቤተክርቲያን ቀኖና መሠረት እርሱ ራሱ የተወገዘ ይሁን ብሎ መጽሐፍ አስቀድሞ አውግዞታል «ኤጲስቆጶስ በማይገባ አያውግዝ ሰዎችን ሊያሳዝናቸውና ፈርተው እንዲገዙለት ፈልጎ በማይገባ ቢያወግዝ እርሱ ከእግዚአብሔር ዘንድ የታሰረ የተወገዘ ይሁን ካህናትም በእውነት ይቋቋሙት።» ፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 5184

ይህንን ቀኖናዊ አካሄድ ሳይከተልና መምህር አሰግድ ሳህሉን ጠርቶ ሳያነጋግር ሲኖዶሱ መምህሩን አውግዣለው ማለቱ ከሞራል ሕግ አንጻር ኢሰብአዊ ፣ ከቤተ ክርስቲያን ሕግ አንጻር ኢቀኖናዊ፣ ከአገሪቱ ሕግ አንጻር ኢፍትሐዊ የሆነ ወንጀል ነው የተፈጸመው።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በየጊዜው የአማንያኗ ቁጥር እየቀነሰና በሚልየን የሚቆጠሩ ተከታዮቿ ወደ ሌሎች ቤተ እምነቶች እየፈለሱ ባሉበት በዚህ አሳዛኝ ሰዓት እንደ መምህር አሰግድ ሳህሉ ያሉትን ጠንካራ እና በመንፈስ ቅዱስ ጸጋ ወንጌልን የሚያስተምሩ ልጆቿን በፍቅር መያዝ ሲገባት በውሃ ቀጠነ ምክንያት ልጆቿን እየገፋች ማስወጣቷ ከእውነተኛው ዳኛ ከእግዚአብሔር ቅጣትና ፍርድ ማምጣቱ የማይጠረጠር ነው። ቤተክርስቲያን በሩዋን ከፍታ የጠፋውን ታስገባለች እንጂ በሩዋን ከፍታ የገባውን አታስወጣም፤ ወንጌል ለቤተክርስቲያን ክብርና ውበቷ እንጂ ልጆቿን የምታሳድድበት የክስ ምክንያት አይደለም። ስለ መምህር አሰግድ ሳህሉ የወንጌል አገልግሎት ከሕዝቡ በላይ ማንም ምስክር ሊሆን አይችልም የሚያስተውልና ወንጌልን ጠንቅቆ የሚያነበው ሕዝብ የመምህሩ ትምህርት ፍጹም ትክክለኛና ከመጸሐፍ ቅዱስ ያልወጣ ንጹሕ ወንጌል እንደሆነ በግልጽ ይመሰክራል፤ በማህበረ ቅዱሳን የሐሰት የክስ ዶሴ የተጠመዘዘው ሲኖዶስ ግን እውነትን በሐሰት ገልብጦ የመምህሩ ትምህርት ኑፋቄ ነው በማለት ራሱን በአደባባይ ሲያዋርድ ተሰምቷል።

በሐሰት የተቀናበረው ክስና ውግዘትም እንኳን የመምህሩን ትምህርት በግልጽ በሚያውቀውና ነገሮችን በማስተዋል በሚከታተለው ሕዝብ ቀርቶ ለህሊናቸው በሚኖሩ የቤተክርስቲያኒቱ ሊቃውንት፣ ካህናትና፣ የነገረ መለኮት ምሁራን ዘንድ ተቀባይነት የሌለው የወረደ አዋጅ ነው። ቤተክርስቲያን እውነተኛ የወንጌል አገልጋይ ልጆቿን በየጊዜው «በሲኖዶስ» ተብዬው እያወገዘች እንድታሳድድ ከጀርባ ሆኖ ይህንን የክፋትና የተንኮል ሴራ የሚሰራው «ማህበረ ቅዱሳን» እያለ ራሱን የሚጠራው የአጋንንት ማህበር ነው። ይህን ማህበር ብዙዎች ክርስቲያኖች በየዋህነትና በቅንንነት እንደሚያዩት ለቤተ ክርስቲያን የሚቆረቆር ሳይሆን ቤተ ክርስቲያንን እያቆረቆዘና ህልውናዋን እየተፈታተነ ያለ ፀረ -ወንጌል ማህበር ነው። የዋሖችን አጥምዶ ለመያዝ በእስትራቴጂ እየተመራ ቤተክርስቲያን አሰራለው፣ ገዳማትን እደጉማለው፣ የአብነት ትምህርት ቤቶችን አስፋፋለው እያለ በሚልየን የሚቆጠር ገንዘብ በየዓመቱ ከቤተክርስቲያኒቱ አማኞች በአካፋ እየሰበሰበ በማንኪያ የጠብታ ያህል ለቤተክርስቲያን እየሰጠ እራሱን እንደ ቤተክርስቲያን አለኝታ በየሚዲያው እያስጮኽ ቢዝነስ የሚሰራ የንግድ ተቋም ነው።

ይህ የዋሐን ክርስቲያኖችን በተለያየ መንገድ እያጠመደ ደጋፊውና አባላቱ እያደረገ ሃያ ዓመታት በላይ ቤተክርስቲያን ላይ ተጣብቆ የኖረው ማህበር በሕዝብ ዘንድ ተወዳጅነትና ተቀባይነት የሚያገኙ የወንጌል አገልጋዮችና ዘማርያንን እንዲሁም ለማህበሩ የማይንበረከኩ ጠንካራ የቤተክርስቲያን ካህናትን በተለያየ ጊዜ ያለስማቸው ስም እየሰጠና በአመራር ተብዬዎቹ ሆን ተብሎ በሚዘጋጅ የሐሰት የክስ ዶሴ በማቀናበር በእጅ ጥምዘዛ በሚገዛቸው ጳጳሳት በኩል ሲያስወግዝና ሲያሳድድ ኖሯል እያደረገም ይገኛል። ማህበሩ ይህን የሚያደርግበት ዋነኛ ምክንያትም ሕዝብን ሞኖፖላይዝ አድርጎ በመያዝ የቤተክርስቲያን አውደ ምህረቶችንና የመምሪያ ተቅዋማትን በመቆጣጠር ከዘመናት በፊት ቀርጸው ለተነሱበት ድብቅ የፖለቲካ ፍጆታ ቤተክርስቲያኒቱን መጠቀሚያ ለማድረግ ነው።

ይህ የክፋት ማህበር በልዩ የአገልግሎት ጸጋቸው ሕዝብን ይይዛሉ ብሎ የሚሰጋቸውንና ለማህበሩ እኩይ ዓላም እጅ ያልሰጡትን አገልጋዮች የሚያሸማቅቅበትና የማህበሩ ግዞተኛ የሚያደርግበት ነውር ሲያጣባቸው የሐሰት የክስ ዶሴ በመክፈት መናፍቅ ነው፣ ተሃድሶ ነው፣ ጸረ ቅዱሳን ነው እያስባለ ሕዝብን በማደናገርና ለዚህ ዓላማ መጠቀሚያ እንዲሆኑ አስቀድሞ በሚያዘጋጃቸው ጳጳሳት በኩል አገልጋዮችን ያስወግዛል።

እነዚህ አውጋዥ ጳጳሳት አንዳንዶቹ በድብቅ በሰሩት ነውራቸውና ማህበሩ በያዘባቸው መረጃ መሰረት አሸማቆ የማህበሩ ተገዥ ያደረጋቸው ናቸው፤ ነውራቸውም ከመነኮሱ በኋላ ልጅ የወለዱ፣ ሁለት ሚስት በድብቅ ያስቀመጡ፣ የቤተክርስቲያንን ገንዘብ በመዝረፍ የግል ሕንጻና ሃብት ያከበቱ ሲሆን፤ ሌሎቹ አውጋዥ ጳጳሳት ደግሞ ከመጰጰሳቸው በፊት ማህበሩ አስቀድሞ ከየቦታው የመለመላቸው የማህበሩ ዓላማ አስፈጻሚ እንዲሆኑ በትግል ጵጵስና ያሰጣቸው ናቸው። እነዚህ ጳጳሳት ከየገጠሩና ከየገዳማቱ በቤተክርስቲያኒቱ ትምህርት እየደከሙ ሞያ የቀመሱትን መነኮሳት በተለያየ ስልት ማህበሩ በእጁ በማስገባት ወደፊት ጳጳስ እናስደርጎታለን ከማህበሩ ጋር አብረው ይስሩ በማለት በዘዴ ከያዛቸው በኋላ የማህበሩ ዓላማ አስፈጻሚ መሆናቸውን በደንብ አድርጎ ሰርቶ ሲጨረስ የጳጳሳት ምርጫ ሲቃረብ ያለ የሌለ መረጃ ለሲኖዶሱ ቀድሞ በሚጠቀምባቸው ጳጳሳት በኩል በማስቀረብ በድብቅ የመለመላቸው መነኮሳት ጵጵስና እንዲሾሙ ያስደርጋል፣ በዚህ ውለታ ተማምለውና ከማህበሩ ጋር ኪዳን ተሳስረው የሲኖዶስ አባላት የሚሆኑ ጳጳሳት በየዓመቱ የጥቅምትና የግንቦት ሲኖዶስ ስብሰባ በመጣ ቁጥር ማህበሩ ቀርጾና አስጠንቶ የሚሰጣቸውን አጀንዳና ክስ በሲኖዶስ ካልጸደቀ ሞተን እንገኛለን በማለት ቤተክርስቲያንን ለውረደትና ለመከራ እየዳረጓት ይገኛሉ።
 
 መምህር አሰግድ ሳህሉን ለሃያ ዓመታት ያህል ሲያሳድደውና ስሙን ሲያስጠፋው የኖረው ይህ የክፋት ማህበር የሚከስበት ነውር ስላላገኘበትና መምህሩን በሚከስባቸው ቦታዎች ሁሉ እፍረትና ውርደት እየተከናነበ ለዓመታት ስለተመለሰ ዛሬ ላይ መምህሩ በሚሰጠው ድንቅ የወንጌል አገልግሎት ብዙ ሕዝብ ስለሚከታተለውና በሃገር ውስጥም ሆነ በውጪው ዓለም ያሉ ክርስቲያኖች የመምህሩን ትምህርት በፍቅርና በናፍቆት ስለሚያዳምጡ ሕዝቡን ከመምህሩ ለመለየት ያለው ብቸኛ አማራጭ መምህሩን ማስወገዝ ይህንን በየሚዲያው ማናፈስ ስለሆነ ገና የሲኖዶሱ ስብሰባ ከመጀመሩ ማህበሩ «አሰግድ ሳህሉ ተወገዘ» ብሎ አስቀድሞ በየሚዲያው ማስጮኽ ጀመረ። መምህሩ ተጠርቶ በሊቃውንት ጉባዔም ሆነ በሲኖዶሱ ሳይጠየቅ ተወግዟል የሚል አዋጅ የነውር ባሪያው ባደረጋቸው ጳጳሳት በኩል በተጽእኖ መግለጫ እንዲሰጥ አደረገ።

የተወደዳችሁ ሕዝበ ክርስቲያን ሆይ!! እንዲህ ዓይነቱን ተንኮልና ሸፍጥ የተሞላበት አምባገነናዊ ውግዘት ፈጽሞ እንዳትቀበሉት። ከዚህ ፍትሐዊነትና መንፈሳዊነት ከጎደለው ሥልጣንን መከታ አድርጎ ከተላለፈ ውግዘት ጋር የሚስማማ ማንኛውም ክርስቲያን በወንጌል ላይ እንዳመጸና የዲያብሎስ ተባባሪ አድርጎ ራሱን እንደ ደመረ አስቀድሞ ይወቅ።

በቤተክርስቲያን የቀኖና መጻሕፍትም እንዲህ ዓይነቱን ከንቱ ውግዘት እንዳንቀበል እውነተኞቹ ጥንታውያን ቅዱሳን አባቶቻችን በግልጽ አስቀምጠዋል። «ኤጲስ ቆጶስ በማይገባ አያውግዝ ሰዎችን ሊያሳዝናቸውና ፈርተው እንዲገዙለት ፈልጎ በማይገባ ቢያወግዝ እርሱ ከእግዚአብሔር ዘንድ የታሰረ የተወገዘ ይሁን ካህናትም በእውነት ይቋቋሙት።» ፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 5184
 
ክርስቲያኖች ሆይ! ሁላችን እግዚአብሔር አስተዋይ ሕሊና እና ማገናዘብ የሚችል አዕምሮ የሰጠን ድንቅ ፍጥረቶች ነን የምናውቀውን እና የሰማነውን ንጹሕ የወንጌል አገልግሎት በሐሰት ውንጀላ «ኑፋቄ» ነው ብሎ የሚከስና ለከሰሰበትም ክስ ማሳረጃ ሳያቀርብ በግብታዊነት አውግዣለው የሚልን አባት እንደ አባትነቱ ብናከብረውም ከጀርባ ከተሴራው ሴራ አንጻር ግን ይህንን ከንቱ ውግዘት በፍጹም የማንቀበለው መሆናችንን በተግባር ማሳየት አለብን፣ የሚሰጡ የወንጌል አገልግሎቶችን በመካፈልና ከወንድማችን ከመምህር አሰግድ ሳህሉ ጎን በመቆም ለእውነትና ለክርስቶስ ወንጌል ያላችሁን ፍቅርና ጽናት ታሳዩ ዘንድ በተዋጀንበትና የቤዛነት ደኅንነት ባገኘንበት በክርስቶስ ደም እንጠይቃችኋለን።

መምህር  አሰግድ ሳህሉ ባንተ ላይ የደረሰው ይህ ፈተና የወንጌል ፍሬ ነውና በዚህ ደስ ይበልህ «ስለ ክርስቶስ ስም ብትነቀፉ የክብር መንፈስ የእግዚአብሔር መንፈስ በእናንተ ላይ ያርፋልና ብፁዓን ናችሁ።"1 ጴጥሮስ 4:14 ከቀድሞ ጀምሮ የነበሩ እውነተኛ የወንጌል አገልጋዮችና የክርስቶስ ታማኝ ባለሟሎች እውነትን በጥብዓት፣ የጸድቅን መንገድ ባልተሸቃቀጠ ወንጌል ገልጸው ሲያስተምሩ ይጠብቃቸው የነበረው የክብር ዙፋንና የንግሥና ዘውድ ሳይሆን ስደትና ሰይፍ ነው፤ ነገር ግን እነርሱ እየቀለጡ ለብዙዎች ብርሃን ሆነዋል፣ አልጫውን ዓለም በወንጌል ጨውነት አጣፍጠዋል፣ በነውር፣ በሟርትና በባቢሎን እርኩሰት የቆሸሸውን ብልሹ የሰዎች ሕይወት በክርስቶስ መዓዛ ውብ አድርገው ቀይረውታል፡፡ አንተም ስታደርግ የነበረው ይህንን የደጋግ አባቶችህን የእውነተኞቹን የወንጌል ገበሬዎች ተጋድሎ ነውና በጌታ ደስ ይበልህ ያገለገልከውና ያከበርከው ጌታ ለጠላት እጅ አሳልፎ የሚሰጥ ሳይሆን በጠላቶችህ ፊት ራስህን በዘይት የሚቀባ ንጉሥ ነው። ክርስቶስ በአንተ ላይ ያለውን መለኮታዊ ዓላማ የሰዎች ድካምና ከንቱ ውግዘት ፈጽሞ፣ ፈጽሞ፣ ፈጽሞ ሊያስቆመው አይችልም ፣ እግዚአብሔር ካንተ ጋር ነው፣ የዲያብሎስን ምሽግ እያፈራረስክ ነው፣ ጠላት ተጨንቋል፣ በብዙ ስቃይ ተቅበዝብዟል፣ ድሉ ግን ካንተ ጋር ነው በርታ ጌታ መንፈስ ቅዱስ በምንገድህ ሁሉ ካንተ ጋር ይሁን ሰባሪው ጌታ ሁሌም ከፊትህ ይቅደም።

ሳሙኤል ጥብቡ

6 comments:

 1. እውነቱ ይነገርJune 29, 2017 at 6:52 PM

  በአንድም ነገር እንኳ በተቃዋሚዎች አትደንግጡ!
  ይህም ለእነርሱ የጥፋት ለእናንተ ግን የመዳን ምልክት ነው፤ (ፊልጵ 1፡28)

  ስደትና መጠላት የወንጌል ባህሪ መሆኑ የገባው ባላደራ
  ለዚህ መወገዝ የሚሰጠው መልስ፡
  በስምህ መጠላት መታደል ነውና
  የአፌ ቃልና የልቤ ሃሳብ
  በፊትህ ያማረ ይሁን (መዝ 20፡14)
  በማለት ያሬዳዊ ዝማሬውን በከበሮና በጸናጽን
  ከጎንደሩ አቋቋም ጋር ያቀልጠዋል!!!

  ReplyDelete
 2. ምን ትሆኑ እንግዲህ? ባይገርማችሁ እኛም እናንተን አውግዘናል!!!
  ማነህ... ይልቅ ፈጠን ብለህ ተረኛውን አስገባልኝ!!!
  ጥይት ራሱ መቶ ራሱ ይጮሃል አሉ:: ዳይ! ዳይ!

  ReplyDelete
 3. Wow, what a distortion of Historical fact !!
  Whether you like it or not, the legitimate Synod of the Ethiopian Orthodox Tewahdo Church, who has never violated any of its doctrine , laws and guidelines is the one who is in its original seat in Addis Ababa. The group you want us to believe is the legitimate Synod, whose seat is in USA is never recognized by any oriental sister churches or any member church of the world council of churches.
  I think it would be a good idea for you to advise your friend Teacher to join the USA Synod.

  ReplyDelete
 4. kkkkkkkkkk ere benatih ataskegn. masferariya mehonu new? gena minun ayehina ante haratiqa menafik wede adarashih hidna chefir

  ReplyDelete
 5. አይ ሳሙኤል ጠባቡ አፍንጫ ሲመታ ዐይን ያለቅሳል

  ReplyDelete
 6. እንዲህ ነገር ከመብላት ሰርተህ ብላ፡ አባትክን ሰትሰድብ ህሊናህ ምን አለህ?

  ReplyDelete