Thursday, August 17, 2017

ኢትዮጵያ፥ እግዚአብሔር በደህና ጊዜ የሸጣት አገር“የሃይማኖት አገር!” የሚለው አባባል ኢትዮጵያ ውስጥ ጊዜው ያለፈበትና የተበላ ተረት ሆኖዋል። አጥር ተሳልሞ የሚመለስ፣ ዕሮብና ዓርብ ራሱን ጥሉላት ከሆኑ የምግብ ዓይነቶች ከልክሎ ሲያበቃ ምላሱ የሰው አጥንት ስታደቅ ጸሐይ የምትጠልቅበት፣ ዛሬ ቅድስት አርሴማ ናት ነገ አቡነ ሐራ ነው እያለ ሲኖዶስ የማያውቃቸውን ስሞች እየጠራና ቀናት እየቆጠረ አብያተ ክርስቲያናትን የሚያሳድድ፤ መቼ ይሄ ብቻ - እሁድ በመጣ ቁጥር በክራባት ታንቆ ሲዘምርና “ሲያመልክ” እንደ ቦይንግ 767 ክንፉን ዘርግቶ የሚዘል፣ በቀን አምስት ጊዜ እየታጠበ ሶላት ለማድረስ ወደ መስጅድ የሚመላለስ፣ ቁጥር በክትባት መልክ በቀበሌ የተሰጠ ይመስል ኢትዮጵያ ውስጥ ወደ ቤተ እምነቶች የሚመላለስ ሃይማኖተኛ ዜጋ ቁጥር ከመቼውም ጊዜ በላይ ጨምሯል።  
ኢትዮጵያ ውስጥ “ሃይማኖት አልባ” በተለምዶ “ከሃዲ” የሚባለውና በባህላችንም መሰረት በየትኛውም መልኩ ተቀባይነት የሌላው፣ በጋራ ተሰባስበው የሚወያዩበት “ማዕከል” ቀርቶ “ሃይማኖት አልባ/ከሃዲ” ግለሰብን (ሃይማኖት አልባ ግለሰብ የሞራል ኮምፓስ የለውም እያልኩ አይደለም። የ“ሃይማኖት አልባ” ዜጎች ቁጥር ማነስ  ቆጭቶኝም አይደለም) ወይም ሰውን በኩራዝም ቢሆን ፈልጎ ማግኘት ቀላል አይደለም። ቀለል ባለ አማርኛ - ኢትዮጵያ ውስጥ የአንድ ሺህ ሰው እጅ ለመጨበጥ አጋጣሚውን ያገኙ እንደሆነ ከጨበጡት እጅ ዘጠኝ መቶ ዘጠና ዘጠኙ ከራሱ በላይ በሆነ “ፈጣሪ አለ” ብሎ በመለኮታዊ ሃይል “የሚያምን” ህዝብ ነው። በአንጻሩ ምድሪቱ ከሙስና የተነሳ እየተናጠች ሳይ ደግሞ - “ኢትዮጵያ፥ እግዚአብሔር በደህና ጊዜ የሸጣት አገር” አስብሎኛል።

የጽሑፉ ዓላማ፥ የዚህ ጽሑፍ ዋና ዓላማ የህዝብና የአገርን ድካም/ውድቀት ማተት አይደለም። ይልቁንም ያዕቆብ “እምነት ያለ ሥራ የሞተ ነው” እንዲል (ያዕቆብ 2:26) እንደ አማኞች የቆምንበትን መንገድ ዘወትር እንመረምርና እንፈትሽ ዘንድ ግዴታችን ነውና በወንድማዊ መንፈስ የደከመችን ነፍስ ለማጽናት፣ የሳተችም ትመለስ ዘንድ ተጻፈ።
የዋና ርዕስ ትርጓሜ፥ በምድሪቱ የነገሰውና ጣራ የነካው አሳፋሪ የዜጎች ራስ ወዳድነትና ስግብግብነት ለማመላከት ታስቦ እንጅ ገዢና ሸያጭ፣ ለዋጭና ተለዋጭ ኖሮ አይደለም። አንባቢም በዚህ መንፈስ የመልዕክቱን ይዘት ይረዳና በቅን መንፈስ ያነብ ዘንድ እጋብዛለሁ።
ሐተታ
ኢትዮጵያ ውስጥ ሙስና ሙድ ነው። ሁሉም ነገር በጽድቅ ቀርቶ በአቋራጭ ሆናል። ከሰኞ እስከ ቅዳሜ ለጉድ ይዘረፋል እሁድ ጥዋት “ታቦት” የድርሻው ይቦጨቅለታል። ሰዉ ሙስና ለመስራት በጥዋት ተነስቶ ስለት የሚሳልባት አገር ሆናለች። “ስለቱ” ሲደርለት ደግሞ ሰላም አለው። እንደውም ጥላና ዕጣን ቀርቶ ጨዋታው በሚሊዮንና በዶላር ሆኗል። ሙሰኛው በስምምነቱ (በተሳለው መሰረት) ለተማጸነው ታቦት እስከበጠሰ ድረስም የጥፋተኝነት ስሜት፣ ሃዘኔታና ርህራሄ ብሎ ነገር የለም። አይሰማውም። ሰዉ በሰራው በደልና ጥፋት ሊጸጸት ቀርቶ  እንዲህ ያለ ነገር ሲሰማ በራሱ ከት ብሎ ነው የሚስቀው። ምን አለፋዎት፥ ፈሪሃ እግዚአብሔር ከምድሪቱ ጸሐይ እንዳየ ጤዛ ብን ብሎ ጠፍቷል።
“ፎቅ፣ መኪና፣ አይፎን 7 ፕላስ፣ ጋላክሲ 8፣ ፍላት ስክሪን ቴሌቪዝን፣ ሌዘር ሶፋ …” ሰዉ ልብ ላይ ነግሷል። በቁሳቁስ ፍቅር ልቡ ጠፍቶበታል። ከመቃብር ለማያልፍ ነገርም ነፍሱን ሽጧል። መጽሐፍ ቅዱስ “ምን አለበት .. ዘመኑ ያመጠው ነገር ነው … ግድ ይላል …” እያልን የጽድቅን መንገድ ትተን ከድጡ ወደ ማጡ እንድንከባለል አያስተምረንም። እንደውም መጽሐፍ ቅዱስ “ሰው ነፍሱን ሸጦ ዓለምን ቢያተርፍ ምን ዋጋ አለው” እንዲል እግዚአብሔር የሰውን ልጅ ሲፈጥረው አፈር ለሚበላው፣ ርካሽ ኮልኮሌ ነገር ተጠላልፎ እንዲወድቅ ሳይሆን ለከበረ ነገር እንዳጨው ነው የሚስያተምረን። 
የእግዚአብሔር ሰው ሆይ!
Ø ካላጭበረበርክና ካላታለልክ፤
Ø ካልሰረቅክና ካልመነተፍክ፤
Ø ድሃ ካልበደልክና ካላስለቀስክ፤
Ø ፍትህ ካላጠመምክ፤
Ø ሰነድ ካልደለዝክና ካልደመሰስክ፤
Ø ካላምታታህና ካላወናበድክ፤
Ø የህዝብ ሀብት፣ የመንግሥት ንብረት ገበያ እያወረድክ ካልቸበቸብክ፤
Ø የታካሚዎችህን ኩላሊት እያወጣህ ካልሸጥክ፤
Ø “ዓይኔን ግንባር ያድርገው” እያልክ የሰው እምነት ካልበላክና ካልሸመጠጥክ፤
Ø ከዚህም ከዛም ወሬ እያቀባበልክ፣ እየሸቃቀትክና እየለቃቀምክ አንዱን ከአንዱ እያላተምክ፣ እያናከስክ፣ ካልሾለክና ካላለፍክ ሰርተህ በጽድቅ የማያልፍልህ ከሆነ፤ ቀዳዳ በዝቶብህ ኑሮ አልሞላ ካለህ፤ ደስ ይበልህ። አይለፍልህ፣ አይምላልህም። ሳያልፍልህ ቢቀር ይሻላል ብዬ ስጽፍልህም በታላቅ ትህትናና ደስታ በተሞላበት ወንድማዊ ፍቅር ነው።
ደግሞም የዛሬ መቸገርህን ልትመልከት አይገባም። ነገ ሌላ ቀን ነውና። ኑሮ ቢሞላም ባይሞላም በምድር ክበብ ላይ የተቀመጠ፣ የሌለውን እንዳለው የሚጠራ፣ ዘመናት ቆጥሮ ሲመጣ የማይመሽበት፣ ችግርን እንዳለፈ ወንዝ የሚያስረሳ፣ ለታመነችው ነፍስ የታመነ፣ በጽድቅ ለምትመላለስ ነፍስ ብድራትን የሚሰጥ የያዕቆብ አምላክ እግዚአብሔር ዛሬም ህያው ነው። በጽድቅ ለቆመች ነፍስ እግዚአብሔር መልካም አምላክ ነው።
ምን ለመሆን? የትስ ለመድረስ ነው?
ወዳጄ! በሰዎች ዘንድ ሚዛን የሚደፋ፣ ጆሮ የሚሞላና በዓይን የሚታይ ነገር ባይኖርህም በሸለቆ ቢሆን በተራራ ከእግዚአብሔር ጋር መኖርን የሚመስል ነገር የለም። ስላምና ዕረፍት ከመቃብር በማያልፍ ቁሳቁስ ሳይሆን ፍጹም የሆነ ሀሴት ያለው በእግዚአብሔር ጥላ ሥር ነው። ምን የመሰለ አልጋ ገዝተህ ስታበቃ የሌሊት እንቅልፍ ርቆብህ ስትገለባበጥ የምታድረው ሰላምህን ያሳጣህ ፍለጋ ስለተሰማራህና ስለኮበለልክ ነው። ጠቢቡም “ብርን የሚወድድ ሰው ብርን አይጠግብም፤ ባለጠግነትንም የሚወድድ ትርፉን አይጠግብም” እንዲል (መክብብ 5:10) ።
አማኝ ቤት አይገንባ፣ መኪና አይኑረው፣ በድህነት አዘቅት ውስጥ ተዘፍቆ ይኑር … እያልኩ አይደለም። አላልኩም። ሰባራ መርፌ ብትሆንም በጽድቅ ያልተገኘ ማንኛውም ነገር ሁሉ ለእውነተኛ አማኝ፣ የልጅነት መንፈስ ለተቀበለች ነፍስ አልተሰጠም ነው መልዕክቴ። በድህነት አላምንም። የሰው ጠላትም የለኝም እንጅ ድህነት ለጠላቴም ቢሆን አልመኝለትም። ከእግዚአብሔር ያልሆነ፣ እግዚአብሔር የማያውቀው፣ በጽድቅ ያልተገኘ፣ የድካሜ ፍሬ ያልሆነ ሃብትና ንብረት አጠገቤ ሊደርስ፣ ቤቴም ሊገባ ቀርቶ በዚህ መንገድ ከተሰማራች ነፍስ ህብረት እንዲኖረኝ ራሴን አሳልፌ አልሰጥም።
ምን ለመሆን? የትስ ለመድረስ ነው? ለየትኛው ዘመን? ሺህ ዘመን አይኖር። ሺህ ዘመን አነሰኝ ወይም ሺህ ዘመን ቢኖኝ ኖሮ አደርገው ነበር ማለትም አይደለም። እልፍም ቢሆን አልውለውም። የራሴ ያልሆነ፣ ያልተሰጠኝ፣ የማይገባኝ፣ በስርቆት፣ በማጭበርበር፣ በውንብድና … የተገኘ ወርቅና ጨርቅ፤ ሀብትና ንብረት ራሴን ከምክብ ሰው አለኝ የሚለውና የሚመካበት ማንኛውም ነገር ቀርቶብኝ ሰላሜን ይዤ ከእግዚአብሔር ጋራ ኑሮ እመርጣለሁ።
“ጎመን በጤና” ነው ያለው ያገሬ ሰው። ስለ ወደፊቱ፣ ስለማላውቀው ዓለም አይደለም እየጻፍኩልህ ያለሁት። እግዚአብሔር በህይወቴ ያስተማረኝና በነፍሴ ስላለፈው ሰይፍ ነው ለምስክርነት የምጽፍለህ። ጎበዝ! ኑሮዬ ይበቃኛል ማለትን ካልተማርክ አደጋ ላይ ነህ። እንዴት? አማኝ ብሎ ስስታም፣ ሰገብጋባ፣ ያልዘራውን የሚያጭድ ወሮበላ የለምና። እንዲህ ያለች ነፍስም በእግዚአብሔር መንግሥት ዕድል ፈንታ የላትም። ጽድቅ የማትሰብክ፣ አመጻን የማትቃወማና የማታወግዝ ጉባኤም ከእግዚአብሔር አይደለችም። ጥበብ በጎዳና ላይ ትጮሃለች!
ቀለል ባለ አማርኛ። አንድ አማኝ በሙስና የተገኘ ሃብት ሊሰበስብ፤ የራሱ ያልሆነና ያልተሰጠውን በህገ ወጥ መንገድ ሊያግበሰብስ፣ አቋራጭ ፍለጋ ሊሰጥና ሊቀበል ቀርቶ ያየም እንደሆነ ይገልጠው/ትገልጠው ዘንድ ነው የእግዚአብሔር እስትንፋስ ያለበት ቅዱስ መጽሐፍ የሚያዘው። ምን ነው ቢሉ? ሙስና የጨለማ ልጆች ስራ ነውና። “የብርሃኑ ፍሬ በበጎነትና በጽድቅ በእውነትም ሁሉ ነውና ለጌታ ደስ የሚያሰኘውን እየመረመራችሁ፥ እንደ ብርሃን ልጆች ተመላለሱ፤ ፍሬም ከሌለው ከጨለማ ሥራ ጋር አትተባበሩ፥ ይልቁን ግለጡት እንጂ” እንዲል (ኤፌሶን 5፡9-11)።
ሙስና የጨለማ ልጆች ስራ/መገለጫ ነው
ሐዋርያት አንድ ጊዜ ፈፅመው አምነው የተቀበሉት ወንጌል እንደ ቋንጣ ቁልቁሊት ተንጠልጥለው፤ እንደ አሥር ሳንቲም ፌስታል እሳት የበላቸው፤ እንደ ቁራጭ ስጋ የአውሬ ራት የሆኑና ራሳቸውን ለሞት አሳልፈው የሰጡ የመላዕክት ዘር ስላላቸው አልያም ዝገት ከማይበላው ብረት የተሰሩ ልዩ ፍጥረት ስለነበሩ አይደለም። ይልቁን የክርስትና ህይወት ቁርጥ ያለ፣ ግልጽና የጠራ ምርጫ ላይ የተመሰረተ የህይወት ጉዞ መሆኑ ስለገባቸው እንጅ። ሰሚ ጆሮ ያለው ያድምጥ፥ ክርስትና ዜግነት አልያም የቡና ወይም የጊዮርጊስ የእግር ኳስ ክለብ ማሊያ አይደለም፤ ጊዜና ቦታ እያመሳከርን የምንለብሰውና የምናወልቀውም አይደለም። ክርስትና የተፈተነ የጽድቅ ህይወት ነው።
ጎበዝ! ክርስትና በመሆን እንጅ በመመሳሰል የሚኖር ህይወት አይደለም። በማመንና በአለማመን፤ በመሆንና በመስሰል መካከል ደግሞ ሌላ ምንም ነገር የለም። ከሆንክ ነህ - ካልሆንክ ደግሞ አይደለህም። ጥያቄው ግልጽ ነው። ህይወትህ ማንን ያንጸባርቃል? ህይወትህ ማንን ይመስክራል? ሰዎች አንተን ሲያዩ በአንተ ኑሮ ማንን ነው የሚያዩት? ጻድቁን እግዚአብሔር ወይስ የሐሰት አባት ተብሎ የተነገረለትን ነፍሰ ገዳዩን ዲያብሎስን? ጎረቤት፣ የስራ ባለ ደረባ፣ አብሮ አደግ (በአጠቃላይ በቅርብ የሚያውቅህ ሰው) ስለ አንተ የሚሰጠው ምስክርነት ምንድነው? ሰዎች ስለ አንተ እግዚአብሔርን ያመሰግናሉ ወይስ “እሱ ብሎ ደግሞ ክርስቲያን” ማለት ነው የሚቀናቸው? ጥጉ፥ በመመሳሰል በምንኖረው ኑሮ ራሳችንን እንጂ እግዚአብሔርን አይደለም የምናታልለው። ከሁለቱ አንዱን መምረጥ ደግሞ የእኔና የእርስዎ ድርሻ ነው። ይህ ምርጫ ተራ ምርጫ አይደለም። ይህ ምርጫ ይግባኝ የማይባልበት የህይወትና የሞት ምርጫ ነው።
ሰባ ነፍሳት በከንቱ ገድሎ ሲያበቃ በጥላ ተድብቆ እግዚአብሔርን ሸውዶ ከፍርድ ስላመለጠ ሽፍታ እየሰማህ በመላዕክት፣ በቅዱሳን፣ በጻድቃንና በሰማዕታት ስም እኔ ነኝ ያለ ድግስ ደግሰህ፣ አገር ምድሩን ጠርተህ፣ ታጥቀህ ስላበላህና ስላጠጣህ ከፍርድ አመልጣለሁ ብለህ የምታምን ከሆነም የተሸወድከው አንተ ነህ። አሊያም የሚሰራ፣ ሁለትም አፍ ካለው ሰይፍ ይልቅ የተሳለ፣ ነፍስንና መንፈስንም ጅማትንና ቅልጥምንም እስኪለይ ድረስ የሚወጋ ቃል - ደብተራ ጠላ ጠግቦ ከፃፈው ተረት ጋር ተቀላቅሎብሃል ማለት ነው። በአጭሩ፥ የውሃ ጠብታ ብረትን እንደሚያዝግ ሁሉ ሙስናም እንዲሁ ነፍስን የሚያገማ፣ ከእግዚአብሔር ህብረት የሚለይ፣ እግዚአብሔርም አጥብቆ የሚፀየፈው የጨለማ ልጆች ስራ/መገለጫ ነው።
ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል
14 August 2017
አውሮፓ

ኢ-ሜይል፥ yetdgnayalehe@gmail.com

4 comments:

  1. ቃለ ሕይወትያሰማልን እውነቱን ተናግሮ የመሸበት ማደር ርእሱ ግን አልተስማማኝም እግዚአብሔር ይተዋል እንጅ አይሸጥም

    ReplyDelete
  2. Egziabhern msadb yasktal!!!

    ReplyDelete