Sunday, September 17, 2017

ቀሲስ ዘማሪ አሸናፊ ገብረ ማርያም ለጳጳሳቱ ይናገራል

ለጰጳሳት የተላከ ደብዳቤ ክፍል አንድ /ከቀሲስ ዘማሪ አሸናፊ /ማርያም/

ከፍ ያለ አክብሮት ለብጽዕናችሁ አቀርባለሁ፡፡ ወደዚህ ከፍ ያለ ጥሪ ስትመጡ ብዙ የህይወት ተጋደሎ አድርጋችሁ፣ በጠበበው ደጅ በትዕግስት ተራምዳችሁ ነውና መደመጥ ይገባችኋል፡፡ የደብዳቤዬ ዓላማ የእናንተ እረኝነት በትውልዱ ውስጥ ትርጉም ያለው ሆኖ እንዲቀጥል ያለኝኝ የልጅነት ናፍቆቴን ለማሳየት ነው፡፡ እናንተ የተቀደሰውን ህዝብ እንድትጠብቁ በእግዚአብሔር የተሾማችሁ እረኞች እንደመሆናችሁ ከፍ ያለ ክብር ይገባችኋል፡፡ በገዛ ደሙ የዋጃትን ቤተክርስቲያን ለመምራት የክርስቶስ እንደራሴ ናችሁ፡፡ ባለአደራ ናችሁ፡፡ የሐ፤ 2028 በሲመታችሁ ዕለት የምትገቡት ኪዳን እሳት ውስጥ ቀልጦ ለመጤስ እንደተዘገነ ቅዱስ እጣን ያደርጋችኋል፡፡ የሚቀጣጠል የመብራት መቅረዝ እጃችሁ ውስጥ አለ፡፡ ዘይቱን እየቀዳችሁ እስከ ሙሽራው መምጫ የምታበሩልን አምስቱ ልባሞች ናችሁ፡፡ በደብተራ ሙሴ ሃያ አራት ሰዓት ትበራ የነበረችውን ያችን መብራት አስቧት፡፡ መብራቷ ከጠፋች የእግዚአብሔር ክብር እንደ ጎደለ ማመልከቻ ነበረ፡፡ አፍኒንና ፊንሃስም መብራቱን በማጥፋታቸው ይወቀሱ ነበር ፡፡ 1 ሳሙ 33 

በእናንተ ልብ ውስጥ እረፍት የሚነሳ መብራት መቀጣጠል አለበት፡፡ ፍጥነታችሁ እንደ ቤተክህነት ሳይሆን መሬት ላይ እንዳለችው ዓለም መሆን አለበት፡፡ እንደ ቅዱስ ጳውሎስ ከአይሁድ ጋር እንደ አይሁድ ከአህዛብ ጋር እንደ አህዛብ ሆናችሁ መስራት አለባችሁ፡፡ አንዳንድ ሰዎች ጳጳሳት ይመገባሉ? ይተኛሉ? ይስቃሉ? ብለው በመገረም የሚጠይቁት በእነሱ ዓለም እንደምትገኙ ባለመረዳታቸው ነው፡፡ ጳጳስ ወንጌል አያስተምረም? ለመንጋው ሲል አይሞትም? ለኢየሱስ ክርስቶስ ደፍሮ አይመሰክርም? ብለው ነው መገረም ያለባቸው፡፡ እንደ ማንኛውም ህዝብ ቀለል ያለ ኑሮ የመኖር ነጻነታችሁን ጥሪያችሁ ወስዶባችኋል፡፡ በእጃችሁ ያለው መስቀል ስለክርስቶስ ሁሉን እንድትተውና ብዙ ዋጋ እንድትከፍሉ የኪዳን ምልክት ነው፡፡ 

Tuesday, September 12, 2017

ራያ ቢራ፥ ኢሳይያስ ስለ እናንተ በእውነት ትንቢት ተናገረ
D/n Mulugeta Weldegebrial
September 5, 2017
Europe
የጽሑፉ ዓላማ፥
ይህ ጽሑፍ በምንም ዓይነት መልኩ የራያ ቢራ ፋብሪካ ማስታወቂያ /ለመደገፍ ታስቦ የተዘጋጀ ጽሑፍ አይደለም። የጽሑፉ ዓላማበክርስትናእምነት ተከታዮች ህይወት ላይ የነገሰና የሰለጠነ ልቅ የሆነ፣ ሃይ ባይ ያጣ የግብዝነት ህይወትን ለማራገፍ ታስቦ የተዘጋጀ ጽሑፍ ነው።
የጽሑፉ ውስኑነት፥
ጽሑፉ በኢ-ሜይል አድራሻዬ ለተላከልኝ/ለቀረበልኝ ጥያቄ ታሳቢ አድርጎ የተዘጋጀ ሐተታ ነው። ከክስተቱ ተያይዘው ሊነሱ የሚችሉ በርካታ ጥያቄዎች ማለትም “የራያ ፋብሪካ ማስታወቂያ ትክክል ነው ትክክል አይደለም? ፤ ቢራ መጠጣት ኃጢአት ነው ኃጢአት አይደለም? ፤ በቢራ ጥርሙስ አንገት ላይ መስቀል ማንጠልጠልስ መስቀሉን ያረክሰዋል ወይስ መስቀሉ ቢራውን ይቀድሰዋል? ማስታወቂያው ከክርስትና ጋር በተለይ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ተቋማዊ ሰውነት የሚያገናኘው ነገር አለ - የለም? …”  እና ሌሎች ሊነሱ ስለሚችሉ ጥያቄዎች መልስ አይሰጥም። ጽሑፉ በይዘቱ መጽሐፍ ቅዱስን መሰረት በማድረግ ተከሰተ በተባለ ጉዳይና ጩኸቱን እያቀለጠው ባለው ትውልድ መካከል ያለው አንፃራዊ ግኑኝነት ላይ ብቻ የሚያጠነጥን ፅሑፍ ነው።
ጽሑፉ ይነስም ይብዛ ምንም ዓይነት የአልኮል መጠጥ (ጠላና ጠጅ ጨምሮ) የማይቀምሱትን፣ መጠጥ ባለፈበት የማያልፉትን፣ ሃይማኖታዊም ሆነ ባህላዊ በዓላት ሲያከብሩ በውሃ የሚያከብሩትን ወንዶችና ሴቶች የክርስትና እምነት ተከታዮችን/አማኞችን አይመለከትም። 

Saturday, September 9, 2017

በአዲስ ዓመት አዲስ ማንነት

“በአረጀ ልብስ አዲስ እራፊ የሚያኖር የለም፤ መጣፊያው ልብሱን ይቦጭቀዋልና፥ መቀደዱም የባሰ ይሆናል። በአረጀ አቁማዳ አዲስ የወይን ጠጅ የሚያኖር የለም፤ ቢደረግ ግን፥ አቁማዳው ይፈነዳል፥ የወይን ጠጁም ይፈሳል አቁማዳውም ይጠፋል፤ ነገር ግን አዲሱን የወይን ጠጅ በአዲስ አቁማዳ ያኖረዋል፥ ሁለቱም ይጠባበቃሉ።” (ማቴዎስ 9፡16-17)

ስንጀምር አዲስ ያልነውን ዓመት የጊዜ ዑደቱን ሲጨርስ አሮጌ እንለዋለን፡፡ ስንጀምረው አዲስ ብለን የጠራነውን 2009 ዓ.ም.ን አሮጌ እያልን መጥራት ከጀመርን ቀናት ተቆጥረዋል፡፡ አዲስ ለተባለው 2010 ዓ.ም. ዓ.ም. ስፍራውን ሊለቅም የሰዓታት ጊዜ ቀርተውታል፡፡ እግዚአብሔር ቢፈቅድና ብንኖር 2010 ዓ.ም. እንደዚሁ አሮጌ የምንልበት ጊዜ ይመጣል፡፡ አሁን ግን አዲስ ዓመት ነው፡፡ ይህ የዘመን አቆጣጠር ሂደት ይቀጥላል፡፡ እኛም አዲስና አሮጌ ማለታችን ይቀጥላል፡፡ ትልቁ ነገር እኛ ሳንለወጥና በክርስቶስ የአዲስ ሕይወት ባለቤቶች ሳንሆን በአሮጌው ማንነታችን አዲስ ዓመት ብንል በአሮጌው ማንነት ላለነው ትርጉም የሌለው መሆኑ ነው፣ እንደውም አሮጌነታችንን ያባብሰዋል፡፡