Tuesday, September 12, 2017

ራያ ቢራ፥ ኢሳይያስ ስለ እናንተ በእውነት ትንቢት ተናገረ
D/n Mulugeta Weldegebrial
September 5, 2017
Europe
የጽሑፉ ዓላማ፥
ይህ ጽሑፍ በምንም ዓይነት መልኩ የራያ ቢራ ፋብሪካ ማስታወቂያ /ለመደገፍ ታስቦ የተዘጋጀ ጽሑፍ አይደለም። የጽሑፉ ዓላማበክርስትናእምነት ተከታዮች ህይወት ላይ የነገሰና የሰለጠነ ልቅ የሆነ፣ ሃይ ባይ ያጣ የግብዝነት ህይወትን ለማራገፍ ታስቦ የተዘጋጀ ጽሑፍ ነው።
የጽሑፉ ውስኑነት፥
ጽሑፉ በኢ-ሜይል አድራሻዬ ለተላከልኝ/ለቀረበልኝ ጥያቄ ታሳቢ አድርጎ የተዘጋጀ ሐተታ ነው። ከክስተቱ ተያይዘው ሊነሱ የሚችሉ በርካታ ጥያቄዎች ማለትም “የራያ ፋብሪካ ማስታወቂያ ትክክል ነው ትክክል አይደለም? ፤ ቢራ መጠጣት ኃጢአት ነው ኃጢአት አይደለም? ፤ በቢራ ጥርሙስ አንገት ላይ መስቀል ማንጠልጠልስ መስቀሉን ያረክሰዋል ወይስ መስቀሉ ቢራውን ይቀድሰዋል? ማስታወቂያው ከክርስትና ጋር በተለይ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ተቋማዊ ሰውነት የሚያገናኘው ነገር አለ - የለም? …”  እና ሌሎች ሊነሱ ስለሚችሉ ጥያቄዎች መልስ አይሰጥም። ጽሑፉ በይዘቱ መጽሐፍ ቅዱስን መሰረት በማድረግ ተከሰተ በተባለ ጉዳይና ጩኸቱን እያቀለጠው ባለው ትውልድ መካከል ያለው አንፃራዊ ግኑኝነት ላይ ብቻ የሚያጠነጥን ፅሑፍ ነው።
ጽሑፉ ይነስም ይብዛ ምንም ዓይነት የአልኮል መጠጥ (ጠላና ጠጅ ጨምሮ) የማይቀምሱትን፣ መጠጥ ባለፈበት የማያልፉትን፣ ሃይማኖታዊም ሆነ ባህላዊ በዓላት ሲያከብሩ በውሃ የሚያከብሩትን ወንዶችና ሴቶች የክርስትና እምነት ተከታዮችን/አማኞችን አይመለከትም። 

መሪ ቃል፥
“በዚያን ጊዜ ጻፎችና ፈሪሳውያን ከኢየሩሳሌም ወደ ኢየሱስ ቀረቡና፦ ደቀ መዛሙርትህ ስለ ምን የሽማግሎችን ወግ ይተላለፋሉ? እንጀራ ሲበሉ እጃቸውን አይታጠቡምና አሉት። እርሱም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ እናንተስ ስለ ወጋችሁ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ስለ ምን ትተላለፋላችሁ? እግዚአብሔር፦ አባትህንና እናትህን አክብር፤ ደግሞ፦ አባቱን ወይም እናቱን የሰደበ ፈጽሞ ይሙት ብሎአልና፤ እናንተ ግን፦ አባቱን ወይም እናቱን፦ ከእኔ የምትጠቀምበት መባ ነው የሚል ሁሉ፥ አባቱን ወይም እናቱን አያከብርም ትላላችሁ፤ ስለ ወጋችሁም የእግዚአብሔርን ቃል ሻራችሁ። እናንተ ግብዞች፥ ኢሳይያስ ስለ እናንተ፦ ይህ ሕዝብ በከንፈሩ ያከብረኛል፥ ልቡ ግን ከእኔ በጣም የራቀ ነው፤ የሰውም ሥርዓት የሆነ ትምህርት እያስተማሩ በከንቱ ያመልኩኛል ብሎ በእውነት ትንቢት ተናገረ። ሕዝቡንም ጠርቶ፦ ስሙ አስተውሉም፤ ሰውን የሚያረክሰው ወደ አፍ የሚገባ አይደለም፥ ከአፍ የሚወጣው ግን ሰውን የሚያረክሰው ይህ ነው አላቸው። በዚያን ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ቀርበው፦ ፈሪሳውያን ይህን ቃል ሰምተው እንደ ተሰናከሉ አወቅህን? አሉት። እርሱ ግን መልሶ፦ የሰማዩ አባቴ ያልተከለው ተክል ሁሉ ይነቀላል። ተዉአቸው፤ ዕውሮችን የሚመሩ ዕውሮች ናቸው፤ ዕውርም ዕውርን ቢመራው ሁለቱም ወደ ጉድጓድ ይወድቃሉ አለ። ጴጥሮስም መልሶ፦ ምሳሌውን ተርጕምልን አለው። ኢየሱስም እንዲህ አለ፦ እናንተ ደግሞ እስካሁን የማታስተውሉ ናችሁን? ወደ አፍ የሚገባ ሁሉ ወደ ሆድ አልፎ ወደ እዳሪ እንዲጣል አትመለከቱምን? ከአፍ የሚወጣ ግን ከልብ ይወጣል፥ ሰውንም የሚያረክሰው ነው። ከልብ ክፉ አሳብ፥ መግደል፥ ምንዝርነት፥ ዝሙት፥ መስረቅ፥ በውሸት መመስከር፥ ስድብ ይወጣልና። ሰውን የሚያረክሰው ይህ ነው እንጂ፥ ባልታጠበ እጅ መብላትስ ሰውን አያረክሰውም” (የማቴዎስ ወንጌል 15 1-20)።
ሐተታ፥
በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች አደባባይ ላይ ሽንጣቸውን ገትረው ሲሞግቱ፣ ሲከራከሩ፣ መጻህፍት እያጣቀሱ ምላሳቸው ከትናጋቸው እስኪጣበቅ ድረስ ሲሰብኩ፣ በየምኩራቡና በየመንገዱ የጸሎት መፃህፍት ይዘው እግሮቻቸው እስኪዝሉና እስኪዝለፈለፉ ድረስ ተገትረው ሲጸልዩ በሩቅ ለሚያያቸው፣ ጠጋ ብሎ ላላጠናቸውና ለማያውቃቸው ሰው አጀብ የሚያስብሉ፤ በጎ ዓላማና ቅን አስተሳሰብ ያላቸው መስለው የሚታዩ፤ ዳሩ ግን ቃላቸውና ድርጊታቸው ፈጽሞ የማይገናኝ፤ በሃይማኖታዊ ግብዝነታቸው የሚታወቁ ጻፎችና ፈሪሳውያን አስመልክቶ ኢየሱስ የተናገረው ቃል ነበር።
ጻፎችና ፈሪሳውያን ከእግዚአብሔር ቃልና ትዕዛዝ ይልቅ “የሽማግሎች/የአባቶች ወግ” ለሚሉት ነገር የላቀ ስፍራ ሰጥተው “ለምን እጃቸውን ሳይታጠቡ ይበላሉ” ሲሉ (በነገራችን ላይ ለደቀ መዛሙርቱ ጤና ተጨንቀው እንዳይደለ አንባቢ ልብ ይል ዘንድ እጠይቃለሁ) የጌታን ደቀ መዛሙርት ሲከሱ፣ በእነርሱ ላይ ሲያጉረመርሙ፣ ከፍ ዝቅ ሲያደርጓቸው፣ ሲቆጡና አቧራ ሲያስነሱ እናገኛቸዋለን። ኢየሱስ ደግሞ ጻፎችና ፈሪሳውያን “የሽማግሎች/የአባቶች ወግ” የሚሉት ነገር የእግዚአብሔር ቃል ወይም የእግዚአብሔር ትዕዛዝ ማለት እንዳይደለ፣ ሥልጣን እንደሌላቸውና፤ ሰው ሰራሽ ስርዓት እንደሆኑ፤ የመጠበቅና የመፈጸም ግዴታ እንደሌለባቸው በሚገባቸው ቋንቋ ሲነግራቸው እንመለከታለን።
ኢየሱስ፥ ነገሩን ካነሳችሁት አይቀር እንደውም በዚህ አጋጣሚ ይውጣላችሁ፣ ቁርጡን ልንገራችሁ በማለትም ይዘውት የቀረቡትን አልባሌ ክስ እንዲህ ሲል ገልብጦ ያስነብባቸዋል። እናንተ እንደምትለፍፉት ሳይሆን “ሰው የሚረክሰው ባልታጠበ እጅ በመመገቡ ሳይሆን በልብ ንጽህና ጉድለት ነው” በማለት።
ኢየሱስ ተናግሮ አልጨረሰም። በሌላ ስፍራ “እናንተ ዕውሮች መሪዎች፥ ትንኝን የምታጠሩ ግመልንም የምትውጡ” ይላል (የማቴዎስ ወንጌል 23፥24)። የማያስጨንቀው የሚያስጨንቃቸው ጻፎችና ፈሪሳውያን መስማት የማይፈልጉትን ኢየሱስ እንዲህ ሲል ይናገራቸዋል “ከውስጥ ከሰው ልብ የሚወጣ ክፉ አሳብ፥ መግደል፥ ምንዝርነት፥ ዝሙት፥ መስረቅ፥ በውሸት መመስከር፥ ስድብ ይወጣል። ሰውን የሚያረክሰው ይህ ነው ሲል ሚስማሩን ያጠብቀዋል።
እውነት ነው! ካስሰበህ፣ ካስጨነቀህና ካልተቆጣህ አይቀር ሊያሳስብህና ሊያስቆጣህ የሚገባው ነፍስን የሚያነቅዝ የተዘፈቅክበት የሥጋ ሥራ ነው። ከነተረቱ "ባለቤቱ ያላከበረውን አሞሌ ባለዳ አይቀበለውም" - አንተ ያላከበርከውን ዓለም በአንተ ፈንታ ታከብርልህ ዘንድ መጠበቅህ በራሱ የወረደ መንፈሳዊ ማንነትህንና የገባህበትን አዘቅት ጥልቀት ነው የሚያሳየው።   
ሰይጣን ከዚህ በላይ ደስታ የለውም። ሰይጣን በማያስጨንቅ፣ በማያሳስብና ረብ/ዋጋ በሌለው ነገር ተጠምደህ ከድጡ ወደ ማጡ ስትንከባለል ከማየት የበለጠ ደስታ የለውም። ወገን! መቆጣትህ ባልከፋ ነበር ዳሩ ግን የሚያጮህህ የእግዚአብሔርን ኃይልና መፃህፍትን አለማወቅህ እንጂ ለእግዚአብሔር ማደርህ እንዳይደለ ስጽፍልህ በታላቅ ትህትና ነው።
እንደ ዜጋ ሃይማኖታዊም ሆነ ባህላዊ፣ ፖለቲካዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ አለመግባባትን ተከትሎ የሚፈጠረው ቅሬታ ተቃውሞህን አግባብ ባለው መንገድ ቅሬታህን የመግለጽና የማሰማት ህገ መንግሥታዊ መብትህ ነው። ይህን ህገ መንግሥታዊ መብትህን ተጠቅመህ ጉዳዩን ወደሚመለከተው አካል መውስድም ሆነ በሚመለከታቸው አካላት ፊት ቀርበህ አቤቱታህን ማሰማት ትችላለህ። ቤተ-ክርስቲያንም ብትሆን ይህን ህገ መንግሥታዊ መብትህን አልነፈገችህም አትነፍግህምም።
ቁምነገሩ፥ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሰረት በሌለው ስሜት ላይ የተመሰረተ ክስ ይዘህ በክርስትና ስምና ሽፋን የሚደረግ ማንኛውም ዓይነት ፍጥረታዊ ማጉረምረም በእግዚአብሔር ፊት ቦታ እንደሌለው፤ ድርጊቱም የጽድቅ ሥራ ሳይሆን እንደውም በራስ ላይ ፍርድን መጋበዝ እንደሆነ በቅዱሳት መጻሕፍት በግልጽ ከሰፈረው ቃል አብረን እናነባለን። መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናትም ሆነ ለማንበብ ጊዜ የሌለህ ዓይነት ሰው የሆንክ እንደሆነ ቢራና/መጠጥና መስቀል ምንና ምን ናቸው? የሚለውን ጥያቄህን ይዘህ ደጀ ሰላም ብቅ በማለት “የነፍስ” አባትህን ትጠይቅ ዘንድ አበረታታሃለሁ።  
ጥያቄ አለኝ፥
መስቀል የቢራ ጥርሙስ አንገት ላይ ተንጠለጠለ ብለህ የምትጮኸው፤ የምትቆጣው፤ አቧራ የምታስነሳውና ዘራፍ የምትለው ምክንያትህ ምንድ ነው? ቢራ ምን ስለሆነ ነው? ቢራ “የዲያብሎስ ሽንት ተረፈ ምርት ነው” ብለህ ስለምታምን ነው? ቢራርኩስ ነው/ሃጢአት ነውብለህ ስለምታምን ይሆን ወይ? የሚያስጮክህ ምንድነው? መስቀሉተዋረደ፣ ረከሰ” ነው? ወይስ ሌላ ምክንያት አለህ? የሚስጮህህ “መስቀል ረከሰ ብለህ ከሆነ” (ይህ የእኔ ግምት ነው) ለመሆኑ አንተን “የሚቀድስ” መስቀልን የሚያክል ነገር የሚያረክስ ምን አዲስ ነገር ቢፈጠር ነው? እንደው ግን፥
ü  የሚካኤል፣ የገብርኤል፣ የተክልዬ፣ የአቡዬ፣ የአንድዬ፣ የእምዬ፣ወርሃዊና ዓመታዊ ዝክር/ንግሥ የምታስበው ለጎረቤት የአልኮል መጠኑ የማይታወቅ ጠላ ጠምቀህ፣ ጠጅ ጥለህ፤ ሌዘር ጃኬትለባሾች (ለክብር እንግዶችህ) ደግሞ ቮድካና ስካች አይደለም ወይ የምታቀርበው?  
ü  ለቤተ ክርስትያን አገልጋዮች ያለህን ክብር የምትገልጸው (ግብረ ሰላም) የአልኮል መጠኑ አስር አስራ አምስት እጥፍ የሆነው ከቢራ ይልቅ የበረታ የመጠጥ ዓይነቶች በማቅረብ አይደለም ወይ?
ü  መነኩሴና ሊቀ ጳጳሳት ቤት ድረስ ለመጎብኘት ስትሄድየኔ ብጤሊሸርበው ቀርቶ ሰምቶት፣ አይቶትና አሽቶት የማያውቀው የመጠጥ ዓይነት ተሸክመህ አይደለም ወይ የምትሄደው?
ü  ሃይማኖታዊ ሆነ ባህላዊ በዓላት የምታከብረው በመጠጥ ታጅበህ አይደለም ወይ?
ü  ጾምህን የምትፈታው በመጠጥ አይደለምን?
ü  በዬ መሸታ ቤቱ ስትዘአልና ስትጨፍር የምታድረው መስቀል አንገትህ ላይ አንደ ተንጠለጠለ አይደለም ወይ?
ü  የደስታህ ቀን (ክርስትና፣ ሰርግ፣ ምርቃት …) የምታከብረው መጠጥ በሌለበት ነው?
ü  በተለይ የትላልቅ አብያተ ክርስቲያናት የገቢ ምንጭ መስቀል አንገትዋ ላይ አንጠልጥላ ስጋዋን ሸጣ ከምታገኘው ገቢ የምትሰጠው የምስኪን ገንዘብ አይደለም ወይ?  
ማናቸውም የአልኮል መጠጦች- ጠላ፣ ጠጅና አረቄ ጨምሮ መጠጥ ብሎ ነገር የማትቀምስና የማትጠጣ ከሆነ፤ ከዚህ ሁሉ ቅሌትና ምስቅልቅ የጸዳህ አማኝ እንደሆንክ በእውነቱ ነገር የራያ ቢራ ፋብሪካ ምርቱን ለማስተዋወቅ የሰራው በምስል የተደገፈ የማስታወቂያ ሥራ የእምነትህ “ምልክት” የሆነው መስቀል የማስታወቂያው አንዱ ክፍል ሆኖ ስታገኘው ነገሩ አሳዝኖህና አስቆጥቶህ ለምን?” በማለት ተፈጸመ የምትለው አሳፋሪ ድርጊት አድራጊው በማወቅም ሆነ ባለማወቅ በስህተትም ሆነ በድፍረት የዋለው ድርጊት ተቀባይነት የሌለው፣ አስነዋሪ ድርጊት መሆኑንና ድርጅቱ ሃላፊነትና ተጠያቂነት ተሰምቶት ስህተቱን ያስተካክልና ከስህተቱ ይታረም ዘንድ የመቃወም፣ ድምጽህን የማሰማት፣ አቤት የማለትና የመቆጣት መንፈስዊ መብት ይኖርሃል። ያን ጊዜ ብትቆጣ ያምርብሃል።
ሥልጣ ሆነ መብ የለህም!
ሐቁ፥ ሥልጣኑም ሆነ መብቱ የለህም። እግዚአብሔርም በጳውሎስ እጅ የሚያስገርም ተአምራት ያደርግ ነበር፤ ስለዚህም ከአካሉ ጨርቅ ወይም ልብስ ወደ ድውዮች ይወስዱ ነበር፥ ደዌያቸውም ይለቃቸው ነበር ክፉዎች መናፍስትም ይወጡ ነበር። አጋንንትንም እያወጡ ይዞሩ ከነበሩት አይሁድ አንዳንዶች፦ ጳውሎስ በሚሰብከው በኢየሱስ እናምላችኋለን እያሉ ክፉዎች መናፍስት ባሉባቸው ላይ የጌታን የኢየሱስን ስም ይጠሩባቸው ዘንድ ሞከሩ። የካህናትም አለቃ ለሆነ አስቄዋ ለሚሉት ለአንድ አይሁዳዊ ይህን ያደረጉ ሰባት ልጆች ነበሩት። ክፉው መንፈስ ግን መልሶ፦ ኢየሱስንስ አውቀዋለሁ ጳውሎስንም አውቀዋለሁ፤ እናንተሳ እነማን ናችሁ? አላቸው። ክፉው መንፈስም ያለበት ሰው ዘለለባቸው ቆስለውም ከዚያ ቤት ዕራቁታቸውን እስኪሸሹ ድረስ በረታባቸው አሸነፋቸውም” እንዲል (የሐዋርያት ሥራ 19፥ 11-16) ። ጥያቄው ቀላል ነው። መስቀል ቢራ ጠርሙስ አንገት ላይ ተንጥጠለ ብለህ የምትቆጣው አንተ ማን ነህ? ማን ነኝ አልክ?
ጣመኝ ድገመኝ እያልክ እንደ ውሃ ስታንቆረቁረው የምታድረው “አንተ” ሆነህ ሳለ ገልበጥ ብለህ ደግሞ “መስቀል ቢራ ጠርሙስ አንገት ላይ ታሰረ” ብለህ ዘራፍ ማለት ምን ማለት ነው? ምነውሳ አሿፊ በዛ ዘንድሮ? ጎበዝ! መጽሐፍ ቅዱስ “ከአንድ ምንጭ ጣፋጭ ውሃና መራራ አይመነጭም” (ያዕቆብ 311) እንዲል፣ የእስልምና፣ የቡድሃ፣ የባሃኢ … ቤተ እምነቶች እንደ ተቋም ማንኛውንም ዓይነት የአልኮል ይዘት ያለው መጠጥ በአንቀጸ ኃይማኖታቸው በግልጽና በጥብቅ የተከለከለና የተወገዘ ነው። ሐራም ነው (ተደብቆ የሚኮመኩም አንድስንኳ የለም አላልኩም) ።
የራያ ቢራ ፋብሪካ የእነዚህ ቤተ እምነቶች ምልክት የሆነው አርማ የቢራ ጠርሙስ አንገት ላይ አስሮ ለማስታወቂያ ሥራ ቢጠቀምበትና የእምነቱ ተከታዮችም በድርጊቱ ቢቆጡ ያምርባቸዋል። በህግም ተጠያቂ ነው። ትንግርት የሆነብኝ ነገር ቢኖር በአርባና በሰማኒያ ቀኑ የጠላን ጣዕም የሚያውቅ ዜጋ ምኔ ተነካ ነው የሚለው? ህንጻ ገንብታ ለመጠጥ ቤት የምታከራይ ቤተ እምነት? መሸታ ቤት ንስሃ የሚሰጡና የሚቀበሉ መነኮሳት የወረሯት ቤት? ልታፍር ይገባታል።  
ከፍ ዝቅ የሚያደርግህ ምንድ ነው? ቢራ “ርኩስ ነው” ብለህ የምታምን ከሆነም መጀመሪያ አንተ ራስህ “ርኩስ” ከሆነ ነገር መከልከልና መራቅ ይጠበቅበሃል። አይጠበቅብህም ወይ? “ቢራ ችግር አለው” ወይም “ቢራ ርኩስ ነው” ብለህ ብታምን ነው እንጂ “ቅዱስ ነው” ብለህ የምታምን ብትሆን ኖሮ አቧራ ባላስነሳህ ነበር። “ቢራ ምንም ችግር የለበትም” ብለህ የምታምን ከሆነ ደግሞ መጀመሪያውኑ ችግር ባልፈጠርክ እኔም ይህን ጽሑፍ ለማዘጋጀት ባልተገደድኩ ነበር። ጥያቄህ ምንድነው?
ራስህ አንፃራዊ በሆነ መንገድ ተዘፍቀህና እግዚአብሔር በማይወደው፣ ከአንድ መንፈሳዊ ሰው በማይጠበቅ ህይወት ውስጥ ተጠላልፈህ ስታበቃ በእግዚአብሔር ስም የምታሰማው ጭኸት ጥፋት በራስህ ላይ የመጥራት ያክል ነው። ጎበዝ! መንፈሳዊ መብትና ስልጣን ብቻ አይደለም የሌለህ የሞራል ብቃትም ሆነ ህጋዊ መሰረት ጭምር ነው።
ክርስትና ተቀላቅለው የሚሮጡት ሩጫ አይደለም። መጀመሪያ ራስህን ለይ፤ የጽድቅ ህይወት ይኑርህ፣ ከዚህ በኋላ ድምጽህን ብታሰማ ጩኸትህ ጉልበት ይኖረዋል። ለመሆኑ፥
Ø  ቢራም ሆነ ማናቸውም የአልኮል መጠጥ የምትጠጣው አንገትህን መስቀል አውልቀህ ነው ወይስ ያሰርከው ማተብ/መስቀል እንደ ተንጠለተለ ነው?
Ø  በኪዳን ያገባሃትን የልጆችህን እናት - ሚስትህን ትተህ የሰው ሚስት የምታማግጠውና የምታባልገው (ጣትህ ላይ ያጠለቅከውን ቀለበት ብታወልቀውም) የአንገትህ መስቀል አንደ ተንጠለጠለ አይደለም ወይ? ወይስ ሴቶቻችንማተብ ሳይበጠስ አንሶላ መጋፈፍ የለም!” ማለት ጀምረዋል?
Ø  የጣትህን ቀለበት ስታወልቅ ያንገትህ መስቀል ትዝ ብሎህ ያውቃል ወይ? ትዝ ብሎህ አያውቅም። ለምን? አንገትህ ላይ ያንጠለጠልከው መስቀል ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ባህል፣ ወግና ልማድ ሆኖብህ ያጠለቅከው እንጂ በወንጌል ንቃተ ህሊናህ አግኝተህ አይደለም። አንድም ሰው ፈርተህ የጣትህን ቀለበት ስታወልቅ የአንገትህ መስቀል እንደተንጠለጠለ ያሻህን የምትሆነው በከንፈርህ እንጅ በልብህ ለእግዚአብሔር ቦታ ስለሌለህ ነው። ታዲያ ዛሬ የራያ ቢራ ፋብሪካ ድርጊት አስቆጥቶህ ዘራፍ የምትለው ግብዝ በመሆንህ አይደለምን?
Ø  መስቀል አንገትህ ላይ አንጠልጥለህ ስትዋሽ፣ ስትሰርቅ፣ ወዳጅህ በሌልለበት ስታማ፣ ዝሙት ስትሰራና ስትፈጽም ያላፈርክ መስቀል ጠርሙስ አንገት ላይ ታሰረ ብለህ አረፋ የምትደፍቀው አንተ ማን ነህ?
Ø  በቀጥታም በተዘዋዋሪም፣ ባለማወቅም ሆነ በድፍረት በሰውና በእግዚአብሔር በደል፣ ወንጀል፣ ክፋት፣ አመጻ፣ ሴረኝነት ... የምትፈጽመው የአንገትህ መስቀል እንደ ተንጠለጠለ አይደለም ወይ? ካልሆነ መጀመሪያውኑ ግድ ባላለህም ነበር። የራያ ቢራ ፋብሪካ የቢራ ጠርሙስ አንገት ላይ መስቀል አስሮ አድቭርታይዝመንት ሰራ አልሰራ ትርጉም ባልሰጠህ ነበር።
Ø  ወዳጄ ሆይ! በነፍስህ ላይ የተከመረውን ጉድፍና ቆሻሻ ትተህ በሰዎች ፊት ሙገሳና ውዳሴ ለማግኘት ምን ነው ለታይታ በረታህ? ለምን ያልሆንከውን ሆነህ ለመታየት ትሞክራህ?
Ø  በንጹሐን ላይ መማለጃን ስትቀበል (ሙስና ስትሰራ) የአንገትህን መስቀል እያወለቅክ ነውን?
Ø  በእግዚአብሔር ቅባቶች (በቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች) ላይ አፍህን ስትከፍትና ምላስህን ስታላቅቅየእምነቴ መገለጫ” የምትለውን መስቀል ከአንገትህ አውልቀህ ነው ወይ?
Ø  እግዚአብሔር ያከበራቸውን በጽድቅና በቅድስና የሚመላለሱትን የእግዚአብሔር ባሪያዎች እንደ ሰፈር ውሻ ስታሳድድ እግዚአብሔርን ያልፈራህ ሰውዬ ምን ነው የማያሳስብ አሳስቦህ ተቅበዘበዝክ?
ያገሬ ሰው የገበያ ግርግር ለሌባ ያመቻልነው ያለው። ደግሞ “ለመጮህ!” ምን ችግር አለው?! ለጉድ ይጮህለታል። ምን ነው ቢሉ? ከኪስህ የምታወጣው ሳንቲም፤ የምትከፍለው የህይወት መስዋዕትነት የለማ። እንደውም አጋጣሚው ተገኝቶ ነው! በትርፍ ሰዓትህ ሶሻል ሚድያ ላይ ተደብቀህ አፈር የሚያንከባልሉ ቃላት እየተጠቀምክ ያዙኝ ልቀቁኝ ማለት ምን ችግር አለው።
እኔን አትጥላ፥
ጳውሎስ ለገላትያ ሰዎች በጻፈው መልዕክቱ “ሰውን ወይስ እግዚአብሔርን አሁን እሺ አሰኛለሁን? ሰውን ደስ ላሰኝ እፈልጋለሁን? አሁን ሰውን ደስ ባሰኝ የክርስቶስ ባሪያ ባልሆንሁም” ይላል (ገላትያ 1፥10)። ከመልዕክቱ ይዘት የተነሳ እኔን ልትጠላኝ፣ ልትረግመኝ፣ ልትሰድበኝ፣ ለክፉ ነገር በብርቱ ልትፈልገኝና ሞት ልትመኝልኝ አይገባም። በቅዱሳት መጻህፍት ከተጻፈ ውጭ አዲስ ነገር ፈጥሬ የጻፍኩት ጽሑፍ የለኝምና። እኔ መልዕክተኛ ነኝ። የመልዕክቱ ባለቤት እግዚአብሔር ነው። እውነት ነው እውነት በራሱ ያሳምማል። ሁሉም ሰው እውነትን መስማት፣ ማወቅና የራሱ ማድረግ ይፈልጋል/ይሻል ብሎ ማመንም ሆነ መጠበቅ የሰውን ተፈጥሮ በሚገባ አለማጤን ብቻ ሳይሆን የዋህነትም ነው። ምን ነው ቢሉ? ሥጋ መሆን የሚፈልገው ነገር አለውና። እውነት ደግሞ መራራ ናት። እውነትን አምኖ መቀበልም ሆነ የራስ ማድረግ ሥጋን መጎሰም፣ ሥርዓት/ዲስፕሊን ማስያዝ ይጠይቃል። ዋጋ ያስከፍላል።
ወዳጄ! በመልዕክቱ ላትስማማ ትችል ይሆናል። ይህ የእኔ ችግር አይሆንም። አይደለምም። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ቤርያ የሚለውን ላስታውስህ “በተሰሎንቄ ከሚኖሩት ይልቅ ልበ ሰፊዎች ነበሩና፦ ነገሩ እንደዚሁ ይሆንን? ብለው ዕለት ዕለት መጻሕፍትን እየመረመሩ ቃሉን በሙሉ ፈቃድ ተቀበሉ”  (የሐዋርያት ሥራ 17፥11) ይላል። ጽሑፎቼን ጨምሮ ማናቸውንም በክርስትና ስም (ስብከት ሊሆን ይችላል በጽሑፍ መልክ የተዘጋጀ ወይም መዝሙር ሊሆን ይችላል) በእግዚአብሔር ቃል እየመረመርክ ሐቁን ማወቅና ገንዘብህ ማድረግ አሁንም የአንተ ድርሻ ነው። ቀዳሚና ተከታይ የሌለው ብቸኛ ዳኛ የእግዚአብሔር እስትንፋስ ያለበት መጽሐፍ ቅዱስ ነውና። ትናንት በነቢያትና በሐዋርያት የሰራ ድንቅ የእግዚአብሔር መንፈስ ዛሬም ህያው ነው ብዬ አምናለሁ። መጽሐፍ ቅዱስም በተበተኑ አጥንቶች ነፍስ የሚዘራና የሚሰጥ ህያው የእግዚአብሔር ቃል ነው ብዬ አምናለሁ። የምሰብክከው/የማስተምረውም ይህን መጽሐፍ ነው።
በእርግጥ፥ የብዙሐኑን ስሜት ለመጠበቅ፣ ስምና ዝና እንዲሁም ተወዳጅነት ለማትረፍ ከሰው ጋር የማያገጭ/የማያጣላ ለብ ያለ እየመረጥኩ ብጽፍ “ደስ” ባለኝ ነበር። ማንም ሰው እንዲጠላኝም ሆነ በክፉ ዓይን እንዲያየኝ አልፈልግምና። ታዲያ በሰዎች ዘንድ ተወዳጅነት ለማትረፍ (ቲፎዞ/አጨብጫቢ ፍለጋ) አቅጄ እንደማልጽፍ ሁሉ ሰው እንዲጠላኝ ብዬ የምሰራው ስራ እንደሌለም አስምሬበት ማለፍ እወዳለሁ። ዳሩ ግን፥ በቅዱሳት መጻህፍት የተጻፈውን ሐቅ መግለጤ ስም የሚያሰጠኝና የሚያስጠቁረኝ ከሆነ ውጤቱን አሜን ብዬ በደስታ ከመቀበል ውጭ ምንም አማራጭ የለኝም። አይኖረኝምም። እግዚአብሔርንና በልጁ ደም የመሰረታትን ቤተ ክርስትያን በጽድቅና በእውነት ማገልገል ዕድል ፈንታዬ ነውና።
የእግዚአብሔር ሰላም ከእናንተ ጋር ይሁን 

4 comments:

 1. ምርጥ ምርጥ የምርጥ ምርጥ

  ReplyDelete
 2. ውድ ወንድሜ በጣም አሪፍ እይታ ነው፤ እኔንም በተለየ ሁኔታ እንድመለከት ነው ያረገኝ፡፡ በሰሞነኛ ስሜት እኔም እምቡር አምቡር ብዬ ስለነበር፡፡ ነገር ግን አንገታችን ላይ መስቀል አንጠልጥለን ስንት ነገር/ኃጢዓት/ እየሰራን መስቀሉ የቢራ አንገት ላይ ሆነ ብሎ መሟገት የሚያስችል የሞራልም የመንፈሳዊም ብቃት የለንም፡፡ መጽሐፍ ‹‹ ከጠላት መልካም አሳሳም የወዳጅ ንክሻ ይሻላል፡፡›› ይላል፡፡ እንዲህ እንዳንተ እውነቱን ግልጥ አድርጎ የሚነግረን አያጣን ይመስለኛል በኃጢዓት ተዘፍቀን የቀረነው፡፡ እግዚአብሔር ጸጋውን ያብዛልህ፡፡

  ReplyDelete
 3. we know who you are the first thing you are pro and you work day and night by wearing Ethiopian church name, and please expose your self and write what you want to write unless other wise it is sin.

  ReplyDelete
 4. ወንድሜ የጻፍከው የሰውን ጸባይ እንጅ የቤተክርስቲያንን አይደለም፡፡ መስቀል ደግሞ የቤተክረስቲያን እንጅ ደካማ የሆነ የሰው ልጅ መለያ አይደለም፡፡ ስለዚህ ……….እንደፈለጉ እንደደሚጠቀሙት የቢራ ፋብሪካም የቤተክርስቲያንን መለያ ወስዶ መጠቀም በፍጹም ተገቢ አይደለም፡፡ ለነገሩ ……..ልብ ይስጥህ፡፡

  ReplyDelete