Wednesday, November 15, 2017

ምልክትህ ፍቅር ነው

Read in PDF
     
ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ ከሰጠው በጣት የሚቆጠሩ ቀጥተኛ ትዕዛዛት መካከል ደቀ መዛሙርቱ ከሌላው ማህበረሰብ፣ የተለያዩ የእምነት ፍልስፍናዎችና ትምህርቶች አቀንቃኞች፣ የቤተ እምነት/ተቋማት ተከታዮች … የክርስቶስ ኢየሱስ (አማኞች/ክርስቲያን) ለመሆናቸው ተለይተው የሚታወቁበት መታወቂያ ምልክት በተመለከተ የሰጠው ግልጽና አጭር ትዕዛዝ አንዱ ነው። ይህ ጽሑፍ የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ፥ እንደ ወደድኋችሁ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ። ርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ፥ ደቀ መዛሙርቴ እንደ ሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ” እንዲል በሰጠው ቀጭኝ ትዕዛዝ ዙሪያ መጽሐፍ ቅዱስ መሰረት አድርጎ አጭር ትንታኔ ይሰጣል።
የጽሑፉ ዓላማ
v  ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሰጠው ቀጥተኛ ትዕዛዝ መሰረት በቅዱሳት መጻህፍት ግልጽ በሆነ ቋንቋ፣ አቀራረብና አገላለጽ የአማኞች ምልክት ፍቅርና ፍቅር ለመሆኑ፤ ዋሊያ ወደ ምንጭ ውሃ እንደሚናፍቅ- የእግዚአብሔር ቃል ለመማር፣ ለማወቅና ገንዘባቸው ለማድረግ ለሚጓጉ፣ ለሚናፍቁ፣ ቅን፣ ታጋሽ፣ ንጹህና በእግዚአብሔር ፊት የተሰበረ ልብ ላላቸው ወገኖች ለማስታወስና ለማስገንዘብ ተጻፈ።
v  ጽሑፉ ልበ ጠማሞችን፣ ዳህጸ ልሳን ፈላጊዎችን፣ ሐሜተኞችን፣ ጸብ አጫሪዎችን፣ ወሬ ለቃሚዎችን፣ ነገር አጣማሚዎችን፣ አሳዳችጆችና ወንጀል ቸርቻሪዎችን አይመለከትም። “እኔ እላችኋለሁ፥ ሰዎች ለሚናገሩት ስለ ከንቱ ነገር ሁሉ በፍርድ ቀን መልስ ይሰጡበታል” እንዲል (የማቴዎስ ወንጌል 12፥ 36) ።
የጽሑፉ ውስኑነት
v  ጽሑፍ ማዕከል አድርጎ በሚያትተው ርዕሰ ጉዳይ ላይ በዋናነት ቅዱሳት መጻህፍትን ያማከለ እንደ መሆኑ መጠን ከአራተኛ ክፍለ ዘመን በፊት ከክርስትና እምነትም ሆነ ከእምነቱ ተከታዮች ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት ያልነበረው 326 ዓ.ም አከባቢ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስመስቀል” የክርስትና ምልክት እንዲሆን ካስተላለፈው ፖለቲካዊ ውሳኔ ጋር ተያይዞ የክርስትና ምልክት ከሆነው መስቀል ጋር ተያይዞ ሊነሱ የሚችሉ ተዛማጅ ጥያቄዎችን አያካትትም።
v  ይህ መልዕክት እንደ ቅዳሴ የተባለውንና የተነገረውን ብቻ ሳያላምጥ ሰምቶ ከመሄድ ውጪ ጥያቄ እንዳይጠይቅ ተደርጎ ለተገነባ ግራና ቀኙን ለማያውቅ ምእመን ብቻ ሳይሆን “አገልግሎት” በሚል ፈሊጥ አገልግሎት ካባ ውስጥ ተወሽቆ መድረክ ላይ ወጥቶ እንቡር  የሚል ወንጀል ቸርቻሪ ስመ መነኩሴ፣ ሰባኪና ዘማሪንም ጭምር ይመለከታል።
መሪ ቃል
ልጆች ሆይ፥ ገና ጥቂት ጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ፤ ትፈልጉኛላችሁ፤ ለአይሁድም፦ እኔ ወደምሄድበት እናንተ ልትመጡ አይቻላችሁም እንዳልኋቸው፥ አሁን ለእናንተ ደግሞ እላችኋለሁ። እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ፥ እንደ ወደድኋችሁ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ። እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ፥ ደቀ መዛሙርቴ እንደ ሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉዮሐንስ ወንጌል 13 33-35
ትንታኔ
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሆነ ከመምህራቸው የሰሙትንና የተማሩትን የምሥራች ቃል ይዘው ዓለምን ያዳረሱ የወንጌል ባለ አደራዎች ደቀ መዛሙርቱ ሐዋርያት አገልግሎት ላይ ያለ የመስቀል ምልክትን የእምነታቸው ሁነኛ ምልክት አድርገው ሲንቀሳቀሱ፣ ሲያስተምሩም ሆነ ሲያመልኩ አንድም ቦታ አናገኛቸውም። የለም አልተፃፈም። ያልተፃፈው በመጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ሳይሆን እስከ አራተኛ ክፍለ ዘመን በነበሩ የክርስትና የታሪክ ጸሐፊዎች፣ አገልጋዮችና የቤተ ክርስትያን መሪዎች መዛግብትና የግል ማስታወሻ አንዳች የሚገኝ ነገር የለም።
ቅዱሳት መፃህፍት እንደሚመሰክሩልን እግዚአብሔር ለሰው ልጅ ያደረገው መልካም ነገር ሁሉ ከፍቅር የተነሳ መሆኑን ነው አስረግጠው የሚመሰክሩልን። አማኞችም እንዲሁ የእምነታችን ምልክት፣ አርማ ወይም ልዩ መለዮና መታወቂያ ፍቅር እንዲሆን ነው የታዘዝነው (ዮሐ 13 33) ። ወደድኩህ/ሽ፣ አበድኩልህ/ሽ፣ ከነፍኩልህ/ሽ … ብሎ ስለመሽኮርመም (“ኢሮስ”) ፤ እንደ አየር ጸባይ ከፍ ዝቅ ስለሚለው ተለዋዋጭ ፍጥረታዊ ስሜት አይደለም የምናገረው። 

ዓለም “ፍቅር! ፣ ፍቅር ያሸንፋል!፣ ፍቅር ነው ቋንቋ! …  እያለች ስለምትዘፍነው የውሸት ዘፈንም አይደለም። ዓለም የምትዘፍንለት “ፍቅር” ቢፋቅ ሞት ነውና። ኢየሱስ እየተናገረው ስላለ የፍቅር ዓይነት ዓለም ለሰው ልጆች ትሰጠው ዘንድ የማይቻላት ዓይነት ልዩ ሰማያዊ ፍቅር ነው። ይህ ፍቅር፥
ü  አዲስ ሰው በመሆን፤
ü  በቃሉ ኃይልና ሥልጣን በመለወጥ፤
ü  በክርስቶስ ኢየሱስ የሚገኝ ፀጋና በረከት እንዲሁም የሰማያዊው ጥሪ ተካፋይ በመሆን፤
ü  በኢየሱስ ክርስቶስ ስም በመታጠብ፣
ü  በመንፈሱም በመቀደስና ለእግዚአብሔር በመለየት የሚገኝ እግዚአብሔርን መምሰል ነው።  
ዓለም ይህን የእግዚአብሔር መንፈስ ሁለመናውን የተቆጣጠረው፣ ለጽድቅ የተሽነፈ፣ አድልዎ የማያውቀው፣ ሰውን በክርስቶስ መነጽር ብቻ የሚያይና ለሰው ዘር በሙሉ ፍቅሩን የማይነፍግ፣ በጓዳም ሆነ በአደባባይ በቃሉና በሥራው የተመሰከረለት …  ዓይነቱ ሰው ከቤቱ ሲወጣና ሲገባ፣ በከተማይቱ ጎዳናዎችና አደባባዮች ሲራመድ፣ በትምህርት ቤት፣ በሥራ ቦታ፣ በገበያ … ሲመላለስ ስታይ የኢየሱስ ደቀ መዝሙር/አማኝ መሆኑን ለይታ ታውቀዋለች። ዓለም የእግዚአብሔርን ሰው ለይታ ለማወቅ ጊዜም አይፈጅባትም። ምንም ዓይነት የሰው እጅ ያበጃጀው ልዩ ምልክትና አርማ በላዩ ላይ ሳያኖር፣ ሳይሸከምና ሳያነባብር በፊትዋ የሚመላለሰውንና የሚሻገረውን ሰው የኢየሱስ ደቀ መዝሙር ለመሆኑ አትስተውም። ኢየሱስ ህይወት ነውና።
ü  በሰው አገር ሳይቀር የምትታወቀው ሁከትና ብጥብጥ በመፍጠር ነው፤
ü  የምትታወቀው በጸብ ጫሪነት ነው፤
ü  የምትታወቀው ፍቅር አጥተህ እርስ በርስ ስትቧቀስ፣ ስትፋጅና ስትናቆር ነው፤
ü  የተገለጠ ማንነትህ እንደ ጅብ እርስ በርስ መናከስህን የማትተው መሆንህ ነው፤
ü  ዓለም ስለ አንተ የምታውቀው ዛሬም ከነ አሮጌ ማንነትህ የምትመላለስ የመሸብህ መሆንህን ነው፤
ü  በአውሮፓና በአሜሪካ ሳይቀር ፖሊስ ጣቢያ ስትመላለስና ፍርድ ቤት ስትካሰስ ነው የምትታወቀው። ለመሆኑ የትኛው እምነትህ/ሥራህ ነው ደቀ መዝሙር የሚያሰኝህ? ምንህ ነው ክርስቲያን? መስቀል ቤተ ክርስቲያን ጉልላት ላይ አውጥተህ መትከልህና አንገትህ ላይ ማንጠልጠልህ ይሆንን? ከዚህ በላይ የእግዚአብሔርን ስም በአደባባይ በአህዛብ ፊት ማሰደብ ምን አለ?
ክርስትያናዊ ህይወት ሌላ ተጨማሪ ምልክት/አርማ የማይሻው በቂ ምልክት ነው
ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች እንዲህ ሲል ጻፈላቸው “በሰዎችና በመላእክት ልሳን ብናገር ፍቅር ግን ከሌለኝ እንደሚጮኽ ናስ ወይም እንደሚንሽዋሽዋ ጸናጽል ሆኜአለሁ። ትንቢትም ቢኖረኝ ምሥጢርንም ሁሉና እውቀትን ሁሉ ባውቅ፥ ተራሮችንም እስካፈልስ ድረስ እምነት ሁሉ ቢኖረኝ ፍቅር ግን ከሌለኝ ከንቱ ነኝ። ድሆችንም ልመግብ ያለኝን ሁሉ ባካፍል፥ ሥጋዬንም ለእሳት መቃጠል አሳልፌ ብሰጥ ፍቅር ግን ከሌለኝ ምንም አይጠቅመኝም” እንዲል (2 ቆሮ. 13) የጌታ መሆንህ የሚታወቀው በፍቅርህ ነው።
ዮሐንስም “ፍቅር የሌለው እግዚአብሔርን አያውቅም፥ እግዚአብሔር ፍቅር ነውና” ሲል የምናገኘው (1 ዮሐንስ 4፥ 8) ። ጎበዝ! ሰው የእግዚአብሔር ፍቅር ከሌለው ዋጋ የለውም። የእግዚአብሔር ፍቅር የሌለው ሰው ደግሞ የሰው ፍቅር የለውም። ሊኖረውም አይችልም። የሰው ፍቅር ሳይኖረው እግዚአብሔርን እወዳለሁ የሚል ሰው ያለ/የተገኘ እንደሆነም ያ ሰው ሐሰተኛ፣ ሸማቂ፣ ግብዝ ሰው ብቻ ነው።
እግዚአብሔርን ማወቅም ሆነ በእግዚአብሔር ለመታወቅ የፍቅር ሰው መሆን አንድና ሁለት የለውም። ፍቅር ህይወት ነውና። ህይወት ደግሞ “ከምልክት” በላይ ኑሮ ነው። የፍቅር ህይወት/ኑሮ ራሱ ሌላ ተጨማሪ አርማ የማይሻው በቂ ምልክት ነውና። ጥያቄው፥ ፍቅር (ህይወት/ኑሮ ሳይኖርህ) ምልክት ተሸክመህ/አንጠልጥለህ ብትዞርና ብትመላለስ ምን ዋጋ አለው?  የእግዚአብሔር ፍቅር በህይወት/በኑሮ የሚገለጽ እንጂ በቃላት ጋጋታ በአጭር አገላለፅ/አባባል የሚተረጎም አልያም ሰው በእጁ በሚያበጃጀው ምልክት የሚገለጽ አይደለም።
ለዚህም ነው ብዬ አምናለሁ ሐዋሪያው ቅዱስ ጳውሎስ የጎደላቸው ነገር ሳይኖር፤ በመንፈሳዊ ስጦታዎች የተንበሸበሹ ዳሩ ግን ፍቅር ከማጣታቸው የተነሳ በማሃከላቸው እየሆነ ያለውን አስቀያሚ ድርጊትና ልምምዶች ሰምቶ በቆርንቶስ ለምትገኘው ቤተ ክርስትያን ለቆሮንቶስ ሰዎች በፃፈው መልዕክቱ የፍቅር ትርጉም በመስጠት ፈንታ የፍቅርን “ባህሪ”/ጸባይ አብጠርጥሮ፣ አስፍቶና ተንተን አድርጎ እንዲህ ሲል የፃፈላቸው “… ፍቅር ይታገሣል፥ ቸርነትንም ያደርጋል፤ ፍቅር አይቀናም፤ ፍቅር አይመካም፥ አይታበይም፤ ፍቅር ለዘወትር አይወድቅም፤ ትንቢት ቢሆን ግን ይሻራል፤ ልሳኖች ቢሆኑ ይቀራሉ፤ እውቀትም ቢሆን ይሻራል። እንዲህም ከሆነ፥ እምነት ተስፋ ፍቅር እነዚህ ሦስቱ ጸንተው ይኖራሉ፤ ከእነዚህም የሚበልጠው ፍቅር ነው።” እንዲል (2 ቆሮ. 13 13)
ወዳጄ! “አዎን አማኝ ነኝ!” ፣ “አዎን ክርስትያን ነኝ!” ፣ “አዎን የክርስቶስ ኢየሱስ ደቀ መዝሙር/ተከታይ ነኝ” ብለህ የምታምን/ኚ ከሆነ ቅዱሳት መጻህፍት ግልጽ በሆነ ቋንቋ እንደሚመሰክሩልህና እንደሚያስተምሩት ሌላ መታወቂያ ምልክት የለህም/ሽም። የክርስቶስ ኢየሱስ ደቀ መዝሙር፣ ተከታይ፣ አማኝ ወይም ክርስትያን ለመሆንህ ልዩ መታወቂያህ ፍቅር ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እያለ ያለው አማኖች በፍቅራቸው ተለይተው ይታወቃሉ ነው የሚለው ያለው።
ከእግዚአብሔር የተሻለ ሃሳብ የለህም!
ያለው- የሌለው፣ ነጭ- ጥቁር፣ የቅርብ- የሩቅ፣ ሃብታም- ድሃ፣ የተማረ- ያልተማረ … ሳትልና ሳትለይ ሰውን ሁሉ በክርስቶስ ኢየሱስ እኩል የሆነ ፍቅር የምትሰጥና የምታሳይ መሆንህን ስትመለከት ዓለም በዚህ ልዩና ድንቅ ማንነትህ የክርስቶስ መሆንህን ታውቃለች። እደግመዋለሁ፥ ዓለም የክርስቶስ ኢየሱስ ደቀ መዝሙር፣ ተከታይ፣ አማኝ ወይም ክርስቲያን መሆንህን ለይታ የምታውቀው በሌላ በምንም ሳይሆን ለሰውና ለእግዚአብሔር ባለህ ፍቅር ነው።
ሌላ ምልክት የለህም። የኢየሱስ ለመሆንህ ምልክትህ ፍቅር ነው። በነገራችን ላይ በብሉይ ኪዳን (ዘፀአት 20፥4 ና 5) ሆነ በአዲስ ኪዳን (1ኛ ቆሮ 10:14) ማንኛውም ዓይነት ምልክት (የሰው አእምሮ፣ እውቅትና ጥበብ ውጤት ወይም የእጅ ሥራን) በተመለከተ የመፅሐፍ ቅዱስ አስተምህሮ ግልፅ ነው። ሌሎች አርማና ምልክት አላቸው አይደል? ክርስትና/ቤተ ክርስቲያንስ ቢሆን/ብትሆን ልዩ ምልክት ቢኖረው/ቢኖራት ምን ችግር አለበት? በማለት መንታ መንገድ ላይ ቆመህ ታመነታ ይሆናል። ወዳጄ! ለእርስዎ ያለኝ ምላሽ አጭር ነው። የክርስቶስ ኢየሱስ ደቀ መዝሙር፣ ተከታይ፣ አማኝ/ክርስቲያን ለመሆንዎ ከፍቅር በተጨማሪ ወይም ሌላ የተሻለ ምልክት ቢያስፈልግ ኖሮ ኢየሱስ መላ ባላጣ ነበር።  ደግሞም ከእግዚአብሔር የተሻለ ሃሳብ የሎትም! በማለት እቅጭዋን ስነግሮት በታላቅ ትህትና ነው። “ምን አለበት?!” ብሎ ፍልስፍናም በእግዚአብሔር መንግሥት ቦታ የለውም። እስራኤልን ገደል የጨመረ ምን ቢሆን ነውና? እንዲህ ዓይነቱ የሻገተ አስተሳሰብና እምነት ነበር እስራኤልን ያንኮታኮተው (መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 8፥7) ይመልከቱ። ያየኸውን ሁሉ የራስህ የማድረግ ክፉ በሽታ።
ወጣም ወረደ፥ የአንድ እውነተኛ አማኝ መታወቂያ፤ የክርስቶስ ተከታይ/ደቀ መዝሙርም ሆነ የቅዱሳን ጉባኤ የሆነችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ብቸኛ መለዮ ወይም ምልክት ፍቅር ነው። ምልክትህ ፍቅር ነው! ቤተ ክርስቲያን ማለት ደግሞ የክርስቲያኖች ህብረት/ጉባኤ፣ የቅዱሳን ስብስብ/መገኛ ማለት እስከሆነ ድረስ የቤተ ክርስቲያን ምልክትም ቢሆን እንዲሁ የተለየ አይደለም። ምልክትዋ ፍቅር ነው። ከሌሎች ቤተ እምነቶችና ጉባኤዎች በፍቅርዋ ብቻ ተለይታ ትታወቃለች።
ኢየሱስም አለ የእኔ ተከታይ መሆንህን ዓለም ለይታ የምታውቅህ “በፍቅርህ ነው” እንዲል። ጳውሎስም አበክሮ የሚለምነው፥
v  ፍቅርን እንድናጸና፣ አጥብቀን እንድንይዝና እንድንለማመድ ነው፤ (2 ቆሮ 2፥ 8)
v  ግብዝነት በሌለው ፍቅር እንድንመላለስ ነው፤ (2 ቆሮ 6፥ 6)
v  ከምንም በላይ ፍቅርን እንድንከታተል ነው፤ (2 ቆሮ 14፥ 1)
v  ፍቅርን እንድንለብስ ነው። 
በሌላ አነጋገር፥
ü  ሁከተኛ፣ ነገረኛ፣ ጸበኛ፣ ብሎ ክርስትያን የለም፤
ü  ደበኛ፣ በእግዚአብሔር ስም በንጹሐን ህይወት ቁማር የሚጫወት አታላይና አጭበርባሪ፣ የጥልቁ መልዕክተኛ፣ አመንዝራ ብሎ አማኝ የለም፤
ü  ሐሜተኛ፣ አሽሙረኛ፣ ወሬ ለቃሚ ብሎ ደቀ መዝሙር የለም፤
ü  ቀናተኛ/ምቀኛ፣ ልበ ጠማማ፣ መሰሪ፣ ተንኮለኛ፣ የወንድሙን ውድቀት እንጅ መልካምነት የማይመኝ ሰረኛ ብሎ የክርስቶስ ኢየሱስ ተከታይ የለም፤
ü  በልሎች ውድቀትና ኪሳር እንጀራውን የሚጋግር ሌባ ብሎ የእግዚአብሔር መንግሥት ማህበርተኛ የለም።

የፍቅርና የሰላምም አምላክ ከእናንተ ጋር ይሁን


3 comments:

 1. በሌላ አነጋገር፥
  ü ሁከተኛ፣ ነገረኛ፣ ጸበኛ፣ ብሎ ክርስትያን የለም፤
  ü ደበኛ፣ በእግዚአብሔር ስም በንጹሐን ህይወት ቁማር የሚጫወት አታላይና አጭበርባሪ፣ የጥልቁ መልዕክተኛ፣ አመንዝራ ብሎ አማኝ የለም፤
  ü ሐሜተኛ፣ አሽሙረኛ፣ ወሬ ለቃሚ ብሎ ደቀ መዝሙር የለም፤
  ü ቀናተኛ/ምቀኛ፣ ልበ ጠማማ፣ መሰሪ፣ ተንኮለኛ፣ የወንድሙን ውድቀት እንጅ መልካምነት የማይመኝ ሰረኛ ብሎ የክርስቶስ ኢየሱስ ተከታይ የለም፤
  ü በልሎች ውድቀትና ኪሳር እንጀራውን የሚጋግር ሌባ ብሎ የእግዚአብሔር መንግሥት ማህበርተኛ የለም።

  ይህ አባባል በትክክል ማህበረ ቅዱሳን የሚባሉትን እኩያን ይገልፃቸዋል። አባ ሰላማዎች እንኳን ደህና መጣችሁ።

  ReplyDelete